የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአገሪቱ የሚገኙ የኢንቨስትመንት ተቋማት በሁከት ምክንያት ለሚወድሙ ንብረቶች የመድን ዋስትና ሽፋን እንዲሰጡ ለማድረግ፣ በኢንሹራንስ ፖሊሲ ላይ ማሻሻያ ሊያደርግ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ እንደገለጹት፣ ቀደም ባሉ ጊዜያት በሁከት ለሚወድሙ ንብረቶች የመድን ሽፋን አልነበረም፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት በእሳት አደጋ፣ በዝርፊያና በአመፅ ምክንያት ለሚወድሙና ለሚጠፉ ንብረቶች የመድን ሽፋን እንዲኖር ለማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ፖሊሲውን እንዲያሻሽል ይደረጋል ሲሉ አቶ ፍፁም ሐሙስ ኅዳር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች አስረድተዋል፡፡
በተለይ በዝርፊያ የሚጠፉና በአመፅ የሚወድሙ ንብረቶች ባለፉት ዓመታት የመድን ሽፋን ሳይኖራቸው ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ከ2008 ዓ.ም. መጀመርያ ጀምሮ በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የበርካታ ዜጎችና ኢንቨስተሮች ንብረት ላይ ውድመት ከተከሰተ በኋላ፣ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለመሰል አደጋዎች የመድን ሽፋን መስጠት እንዳለባቸው ታምኗል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ግን በደርግ ዘመን ለተመሳሳይ አደጋዎች በወቅቱ ብቸኛ የነበረው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሁለት ማዕቀፎች ነበሩት፡፡
የመጀመርያው በወቅቱ ዋነኛው የጦርነት ቀጣና በነበረው በኤርትራ ራስ ገዝ ውስጥ ተልዕኮ ተሰጥቶ የሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪ ሲቃጠል ካሳ ይከፈላል፡፡ የጠፋው ተሽከርካሪም እንዲተካ ይደረጋል፡፡ ሁለተኛው የመድን ሽፋን በሽፍታ ወይም በሽምቅ ውጊያ ለሚጠፋ ንብረት የሚከፈል ነው፡፡
ነገር ግን ኢሕአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ መሰል ጥፋቶች ባለመከሰታቸው በአገሪቱም አንፃራዊ ሰላም በመስፈኑ፣ የመድን ሽፋኑ ተፍቋል፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ይህንን ሽፋን ከማቆሙም በተጨማሪ በኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን የተቋቋሙትም 16 የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ይህንን የመድን ሽፋን አላካተቱም፡፡
በዚህ ምክንያት ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተቀሰቀሰው አመፅ ለወደሙ ፋብሪካዎች፣ የአበባና አትክልት እርሻዎች መንግሥት ካሳ ለመክፈል ተገዷል፡፡
መንግሥት በአሁኑ ወቅት ጉዳት ለደረሰባቸው ኢንቨስትመንቶች የአንድ ዓመት የግብር ዕፎይታ በመስጠት፣ ማሽኖች ከቀረጥ ነፃ ከውጭ እንዲገቡ በማድረግ፣ የተጎዱ ማሽኖችን በመተካት ላይ እንደሚገኝ አቶ ፍፁም አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ በሚደረገው የኢንሹራንስ ፖሊሲ ማስተካከያ ላይ አስተያየታቸውን ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡