Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፋይናንስ ተቋማት ለሕንፃ ግንባታ አግላይ የጨረታ መሥፈርቶችን በማውጣት እየተወቀሱ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ ‹‹ሰማይ ጠቀስ›› የሚባሉ ሕንፃዎችን የሚገነቡ የፋይናንስ ተቋማት ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል፡፡ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት መናኸሪያ መንደር እንደሚሆን በሚታመነው ‹‹ሠንጋተራ›› አካባቢ አሥር ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ቦታ ተረክበው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃዎችን የገነቡና ለማስገንባት በዝግጅት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡

እንደ ወጋገን ባንክ፣ ዳሸን ባንክ፣ ሕብረት ኢንሹራንስ ያሉ ተቋማት የሕንፃ ግንባታቸውን ወደ ማጠናቀቁ ተቃርበዋል፡፡ ከ30 ወለል በላይ ያላቸው እነዚህ የፋይናንስ ተቋማት ሕንፃዎች የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን የበለጠ በማንቀሳቀስ ለዘርፉ ዕድገትም ዓይነተኛ ሚና ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡ ከዚህም ባሻገር አዲስ አበባን የበርካታ ረዣዥም ሕንፃዎች ባለቤት ያደርጓታል ተብሎም ይታመናል፡፡

እስካሁን ባለው መረጃ የሕንፃዎቹን ግንባታ እንዲያከናውኑላቸው ሥራውን ለኮንትራክተሮች ከሰጡት መካከል ሕብረት ባንክ፣ ንብ ባንክ፣ ዘመን ባንክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ወጋገን ባንክ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ናይልና ኦሮሚያ ኢንሹራንስም የዋና መሥሪያ ቤቶቻቸውን ሕንፃ ለኮንትራክተሮች ሰጥተዋል፡፡

እያንዳንዱ ግንባታ የብራካታ ቢሊዮን ገንዘብ ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን፣ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማትም የራሳቸውን ሕንፃ ለመገንባት ቦታ ተረክበው፣ ዲዛይን አሠርተው ተቋራጭ ወደ መምረጡ እየገቡ ነው፡፡ ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ለዋና መሥሪያ ቤቱ ሕንፃ ግንባታ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል አካባቢ በሊዝ በተረከበው ቦታ ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ አኑሯል፡፡

በቅርቡም ንብ ኢንሹራንስ ባለ 30 ወለል የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ለመገንባት ጨረታ አውጥቷል፡፡ ንብ ኢንሹራንስ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት እንዳደረጉት ሁሉ የሚያወጣው ጨረታ የአገር ውስጥና የውጭ ኮንትራክተሮች የሚሳተፉበት ነው፡፡ ነገር ግን እስካሁን ዋና መሥሪያ ቤቶቻቸውን ለማስገንባት ከኮንትራክተሮች ጋር ውል የፈጸሙት አምስቱ ባንኮች በሙሉ (ሕብረት፣ ንብ፣ ዘመን፣ ወጋገንና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) የግንባታ ሥራውን የሰጡት ለቻይና ኮንትራክተሮች ነው፡፡

በጥቅሉ ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ የደረሰው የአምስቱ ባንኮች ሕንፃ ግንባታ ሥራን የወሰዱት የቻይና ኮንትራክተሮች ሲሆኑ፣ አንድ የቻይና ኮንትራክተር  የሕብረትና የንብ ባንክ ሕንፃዎችን ለመገንባት ዕድሉን አግኝቷል፡፡ የፋይናንስ ተቋማቱን ግንባታዎች የቻይና ኮንትራክተሮች ልቀው በጨረታ አሸናፊ በመሆን ቢወስዱም በሁሉም ጨረታዎች ላይ የአገር በቀል ኮንትራክተሮች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡ ነገር ግን አንዳቸውም ማሸነፍ እንዳልቻሉ ተጠቅሷል፡፡ ላለማሸነፋቸው ምክንያቱ የአቅማቸው ደካማነት ብቻ ሳይሆን፣ የቻይና ኮንትራክተሮች እንዲያሸንፉ ሆን ተብሎ የተመቻቸ ሁኔታ ስለተፈጠረላቸው ነው የሚል ቅሬታም ይሰነዘራል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በርካቶቹ የፋይናንስ ተቋማት የአገር ውስጥ ተቋራጮችን ላያሳትፉ ይችላሉ የሚል ሥጋት እየተስተጋባ ነው፡፡ ከፋይናንስ ተቋማቱ መካከል ሕንፃ ለማስገንባት የሚያወጧቸው ጨረታዎች ከጅምሩ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን የሚያገሉ እየሆኑ መምጣታቸው፣ ሥራው ለውጭ በተለይም ለቻይና ተቋራጮች በብቸኝነት እየሰጠ ነው የሚለውን ወቀሳ እያባባሰው ነው፡፡

በተለይ በቅርቡ ጨረታ ያወጣው ንብ ኢንሹራንስ፣ ለተጫራቾች ያወጣው መጫረቻ ሰነድ፣ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን ከጨረታ ውጭ የሚያደርግና የአገሪቱን የግዥ መመርያም የተጻረረ ነው በማለት፣ ተሳታፊዎች ሒደቱን እየኮነኑ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች በፋይናንስ ሕንፃ ግንባታ ጨረታዎች ላይ የሚታየው ክፍተት አሳሳቢ ነው ያሉ ኮንትራክተሮች በማኅበራቸው በኩል  መምከር እንደጀመሩም ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

ከአንድ ወር በፊት በንብ ባንክ ሕንፃ ግንባታ ጨረታ ሒደት ላይ ቅሬታ ያነሱ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ጉዳይ በእንጥልጥል ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ንብ ኢንሹራንስ ኩባንያም ከጅምሩ በጨረታ መሳተፍ የማያስችል፣ ገዳቢ መሥፈርት ማውጣቱን የሚገልጹ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ሁኔታው እንዳሳሰባቸው ይናገራሉ፡፡

የጨረታ ሰነዱ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን አግልሏል የሚሉ ኮንትራክተሮች እንደሚገልጹት፣ በጨረታ ሠነዱ ውስጥ የተቀመጡ አስገዳጅ መሥፈርቶችን በዋቢነት ይጠቅሳሉ፡፡

የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን ከጅምሩ ለተሳትፎ አይጋብዝም፣ አግላይ ነው ተብሎ በተቋራጮች የሚወቀሰውና በንብ ኢንሹራንስ የጨረታ ሰነድ ውስጥ ከተጠቀሰው ውስጥ አንዱ የሚከተለው አንቀጽ ነው፡፡ ‹‹አመልካች እያንዳንዳቸው ቢያንስ ከአምስት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ሁለት ሕንፃዎች በኮንትራክተርነት ገንብቶ በአምስት ዓመት ውስጥ ያጠናቀቀ መሆን ይኖርበታል፡፡ የተገነቡት ሕንፃዎች አሁን ሊገነባ ከታሰበው ጋር ተመሳሳይ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ በፊት የተገነቡት ሕንፃዎች አዲስ ከሚገነባው አኳያ ከመጠን፣ ከውስብስብነት እንዲሁም ከአሠራር ወይም ከቴክኖሎጂ አኳያ (ዝቅተኛው የወለል ስፋት 20 ሺሕ ካሬ ሜትር፣ ዝቅተኛው የወለል ብዛት G + 20፣ የጥልቅ ቁፋሮ እንዲሁም የዲዛይን፣ የገጠማና የአልሙኒየም መዋቅር ወዘተ.) የሚያከናውኗቸው ሥራዎች ተመሳሳይ መሆን ይጠበቅባቸዋል፤›› የሚለው ተቀምጧል፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት ባለፉት አምስት ዓመታት ይህንን ያህል ሕንፃ የገነባ የአገር ውስጥ ኮንትራክተር የለም፡፡ ይህ መሆኑ ከታወቀም አስገዳጅ መሥፈርት ሆኖ በሰነዱ ውስጥ መካተት አልነበረበትም በማለት ተቋራጮቹ ይሞግታሉ፡፡

ያነጋገርቸው ኮንትራክተሮች እንደሚገልጹት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በአገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን በውጭም ኮንትራክተር ቢሆን ከ20 ወለል በላይ ሕንጻ ኢትዮጵያ ውስጥ አልተገነባም፡፡ ብቸኛው በዚህ ወለል ብዛት የተገነባ ሕንፃ የአፍሪካ ኅብረት ብቻ መሆኑ እየታወቀ፣ በኢንሹራንስ ኩባንያው ጨረታ ሰነድ ውስጥ ግን በአምስት ዓመት ውስጥ ከ20 ወለል በላይ ያላቸው ሁለት ሕንፃዎችን መገንባት የሚለው አስገዳጅ አንቀጽ መቀመጡ፣ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን ለማግለል ስለታሰበ ነው የሚል ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡

እንደ ኮንትራክተሮቹ አስተያየት፣ የጨረታ ሰነዱ የአገሪቱን የግዥ መመርያ የተጻረረ ጭምር ነው፡፡ ተሻሽሎ በወጣው የግዥ መመርያ ለሕንፃ ግንባታ ሥራ በዓለም አቀፍ ጨረታ የሚወዳደር የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጭ የሚጠየቀው ዝቅተኛ መሥፈርት ሊሠራ ከታሰበው የሕንፃ ሥራ በአንድ ደረጃ ዝቅ ያለ መሆን አለበት ይላል፡፡ ለምሳሌ በአነስተኛ ሕንፃ ሥራ ልምድ ያለው የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጭ ለመካከለኛ ሕንፃ ግንባታ ሥራ ተቀባይነት ይኖረዋል በማለት መመሪያው አስፍሯል፡፡

ለሕንፃ ግንባታ ሥራ የሚወዳደረው የውጭ አገር ሥራ ተቋራጭ ከሆነም፣ ሊሠራ ከታሰበው የሕንፃ ደረጃ ጋር እኩል ወይም የበለጠ የሕንፃ ሥራ ልምድ ሊኖረው እንደሚገባና ከ15 እስከ 45 ፎቆች መሥራት እንደሚችል መመሪያው ቢደነገግም፣ በአንዳንድ የፋይናንስ ተቋማት ጨረታ ሰነድ ላይ ግን ከዚህ ውጭ እየተሠራ ነው በማለት ተቋራጮች ቅሬታ ያሰማሉ፡፡

የሕንፃ ግንባታዎችን ለቻይና ተቋራጮች ለመስጠት በብርቱ የሚፈለገው፣ የተሻለ ይሠራሉ፣ በፍጥነት ይጨርሳሉ ተብሎ ቢሆንም አንዳንዴ ግን ከዚህ ውጭ የሚደረጉ አላስፈላጊ ስምምነቶች እንዳሉም እየተነገረ ነው፡፡

ከአንዳንድ የፋይናንስ ተቋማት የተገኘው መረጃ የሚያስረዳው፣ ሕንፃዎቹን ልምድ ባላቸው ተቋማት ለማስገንባት የጨረታ ሰነዱን መስፈርቶች ጠበቅ ለማድረግ ሲባል የተደረገ እንጂ የአገር ውስጥ ተቋራጮችን ለማግለል እንዳልሆነ ነው፡፡ 

አንዳንድ አገር በቀል ተቋራጭዎች ግን እንዲህ ባለው አንቀጽ ጨረታውን ከመገደብ መሥፈርቱን ዝቅ በማድረግ የተሻለ አማራጭ መፍጠር ይቻል ነበር ይላሉ፡፡ ቻይናዎቹ የተሻለ ይሠራሉ የሚለውን የማይቀበሉትደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለዋና መሥሪያ ቤቶቻቸው ሕንፃዎች መካከል ሕብረትና ናይል ኢንሹራንስ ብቻ የሕንፃ ግንባታ ሥራዎችን ለአገር ውስጥ ተቋራጮች መስጠታነውንም በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡

በተለይ ሕብረት ኢንሹራንስ በቸርችል ጎዳና፣ ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ እያስገነባ ያለው ሕንጻ፣ ዛምራ በተባለው የአገር ውስጥ ኮንትራክተር አማካይነት ሲሆን የሕንፃ ግንባታውም በተያዘለት የጊዜ ገደብ መሠረት እየተካሔደ መሆኑም በመከራከሪያነት ተነስቷል፡፡ የናይል ኢንሹራንስ ሕንጻንም የሚገነባው አገር በቀል ተቋራጭ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች እነዚህን ሕንፃዎች ለመገንባት ብቃት እንዳላቸው እየታወቀ ለቻይኖች መስጠቱ፣ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን እንደሚጎዳ ተነግሯል፡፡

በከፍተኛ የጨረታ ዋጋ ለቻይና ኮንትራክተሮች ከሚሰጡ ፕሮጀክቶች መካከል በርካቶቹ እንደገና በሰብ ኮንትራት ለአገር ውስጥ ተቋራጮች የሚሰጡ መሆናቸው፣ ቻይኖቹ በከፍተኛ ዋጋ ያሸነፉትን ከፊል ሥራ ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች ማስተላለፋቸው የአገር ውስጦቹ ብቃት የላቸውም የሚለውን አባባል ውድቅ ያደርጋል ይላሉ፡፡    

ስለዚህም ተቋራጮች የፋይናንስ ተቋማት የጨረታ ሠነዶቻቸው የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን የማያገልና የግዥ መመርያውን የማይጻረር ይሁን የሚል አቋም ይዘዋል፡፡ የፋይናንስ ተቋማቱ ገንዘብም የሕዝብ እስከሆነ ድረስ ‹‹በተሻለ ለማሠራት›› በሚል ሰበብ ለሕዝብ ገንዘብ ብክነት መንገድ እየከፈተ እንደሚገን አሳስበዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች