Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድ ዓውደ ርዕዮች ከአቅም በላይ የሚጭኑት ዋጋ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዓመት በፊት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በተዘጋጀ የንግድ ዓውደ ርዕይ የማዕከሉ አዳራሾች በተለያዩ በአገር ውስጥና በውጭ ነጋዴዎች እንዲሁም በደንበኞች ተሞልዋል፡፡ በደንበኞች ከተከበቡ ድንኳኖች መካከል ባህላዊ የቆዳና የሰውነት ክብደት መቀነሻ መድኃኒቶች በአንዱ እየተሸጠ ነው፡፡ መድኃኒቶቹን ቀምሞ የሚዘጋጀው ሶሪያዊ ግለሰብ ሲሆን፣ ማድያት ማጥፊያ፣ ቦርጭ ማጥፊያ፣ የተለያዩ የቆዳ መድኃኒቶች እንዲሁም በእርግዝና ወቅት በቆዳ ላይ የሚወጡ ሸንተረሮች ማጥፊያ ቅባቶችን ይሸጣል፡፡ ሰዎችም ተሻምተው ይገዙታል፡፡ ቋንቋ ችግር እንዳይሆንበትና ገበያው እንዳይስተጓጎልበትም ዓረብኛ ቋንቋ አቀላጥፈው የሚናገሩ በዓረብ አገር የኖሩ አሻሻጮችን ቀጥሯል፡፡

የቀመማቸው መድኃቶች ተሸጠው ሲያልቁም፣ ሰዎች እንዳያዩት በመጨነቅ ዘወር በማለት ሌላውን በጥንቃቄ ያዘጋጃል፡፡ ሁኔታው ግን ጥርጣሬ የሚያጭር ዓይነት ነበር፡፡ መድኃኒቶቹን ከምንና ከምን እንደሚያዘጋጃቸው አይናገርም፡፡ ነገሮችን የሚያከናውነውም ተደብቆ በምስጢር ነው፡፡

 ይህንን የተመለከቱት ቋንቋ የሚያስተረጉሙለት ሴቶች ብቻም ሳይሆኑ ከጐኑ የሚሸጡ ነጋዴዎችም ናቸው፡፡ ዝም ብለው ግን አላለፉትም፡፡ ‹‹አንዳች ነገር ቢኖር ነው እንጂ፤›› በማለት ከጥርጣሬና ከሥጋታቸው ባሻገር ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ሠራተኞች ወዲያውኑ ከቦታው ይደርሳሉ፡፡ ባደረጉት ፍተሻም መድኃኒቶቹን ለማዘጋጀት እንደ ግብዓት ሲጠቀምባቸው የነበሩ፣ ጊዜያቸው ያለፈባቸው የተለያዩ ቅባቶችና ኮስሞቲክሶች ተያዙ፡፡

እንዲህ ያሉ ያልተለመዱ ሕገ ወጥ የንግድ ትዕይቶች መስተናገድ በጀመሩበት ማዕከል ውስጥ የሚሰናዱ ሁለት ዋና ዋና የባዛር ዝግጅቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው እንደዚህ በዓልን መሠረት አድርገው የሚዘጋጁ የባዛርና የፌስቲቫል መልክ ያላቸው፣ ማኅበረሰቡ በብዛት የሚታደምባቸው፣ በበዓል ዋዜማ ሰሞን የሚመጡት ናቸው፡፡ ሌሎቹ የተለያዩ ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ዘርፎችን መሠረት አድርገው የሚዘጋጁ ዓውደ ርዕዮች ናቸው፡፡ ለዓብነትም ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን፣ ግብርናን፣ ቱሪዝምን፣ ኮንስትራክሽንና የመሳሰሉትን ለማስተናገድ የሚዘጋጁ ናቸው፡፡

በብዛት በዚህ ዝግጅት የሚሳተፉት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንደ መሆናቸው ለማበረታት ሲባል የሚጠየቁት የገንዘብ መጠንም ከሌሎቹ አንፃር ዝቅተኛ ነው፡፡ ጨረታ ሳይወጣ ቀድሞ የመጣ፣ ቀድሞ ይስተናገዳል በሚለው መርህ ከ400 እስከ 500,000 ብር ድረስ ለማዕከሉ ከፍለው አዳራሾችን እንዲጠቀሙ ይደረጋል፡፡

 በበዓል ዋዜማ ወቅት የሚዘጋጁት ግን ካላቸው የተሳታፊ ብዛት አንፃር በተለየ ሁኔታ የሚታዩ ናቸው፡፡ በቀን እስከ 25,000 የሚደርሱ ሰዎች ይጐበኟቸዋል፡፡ በተለይም በመዝጊያ ቀናት ወቅት የጐብኚዎቹ ቁጥር በቀን እስከ 50 ሺሕ ይደርሳል፡፡ ኩባንያዎቹ በማዕከሉ የሚስተናገዱትም በጨረታ አማካይነት ነው፡፡ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙትም የእነዚህ ኩባንያዎች ዓውደ ርዕዮች ናቸው፡፡ 68 በመቶ የሚሆነው የማዕከሉ ገቢ የሚመነጨውም ከእነዚህ ዝግጅቶች ነው፡፡

ብዛት ያላቸው የአገር ውስጥና የውጭ አገር ነጋዴዎችም ይሳተፉባቸዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ፕሮገራሞችን ከሚያዘጋጁ ድርጅቶች መካከል ሐበሻ ዊክሊ አንዱ ነው፡፡ የድርጅቱ ኃላፊ አቶ አዶኒክ ወርቁ እንደሚሉት፣ የተሳታፊ ድርጅቶች ምዝገባ በሚደረግበት ወቅት ከጤናና ከደኅንነት አኳያ ሊኖሩ ከሚችሉ ሥጋቶች ነፃ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ሕጋዊ ፈቃድ እንዲያቀርቡ ይጠየቃሉ፡፡ ሕገወጥ ነገር ሲፈጽሙ ከተገኙም እንደሚጠየቁበት ይነገራቸዋል ብለዋል፡፡ ‹‹ሕገ ወጥ ድርጊት የፈጸመ ነጋዴ ኃላፊነቱን እንዲወስድ ይደረጋል፣›› በማለት አልፎ አልፎ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ ምርቶች ሲሸጡ የተያዙ ነጋዴዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

ዓውደ ርዕዮቹ ሸቀጦች ‹‹በተመጣጣኝ ዋጋ›› በአንድ ቦታ ተሰባስበው ስለሚያገኙም ጎብኚዎች ጠቀም ያለ ገንዘብ ይዘው በመሄድ ይሸምታሉ፡፡ የአካባቢው ድባብም እንደ ዓውደ ርዕዮቹ ዓይነት ድምቀት ይኖረዋል፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ምግቦችን የሚያቀርቡ ሬስቶራንቶችም ታዳሚ ናቸው፡፡ ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ጀምሮ የሚቀርበው የሙዚቃ ድግስም ጎብኚዎችን ይስባል፡፡

ይሁንና ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች የሚያቀርቡ፣ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ዋጋ ጭነውና ጨምረው በመሸጥ ጎብኚዎችን የሚበዘብዙ ያጋጥማሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ የመጣው የመግቢያ ዋጋም ብዙዎችን እያማረረ ይገኛል፡፡ ይህም ጎብኚዎችን ብቻም  ሳይሆን ነጋዴዎቹንም እየተፈታተነ ነው፡፡

የሼባ ሌዘር የግብይት ባለሙያ አቶ ስለሺ ተሰማ እንደሚሉት፣ ድርጅቱ በዓውደ ርዕይ የሚሳተፈው ምርቱን ከመሸጥ ባሻገር ለማስተዋወቅ ነው፡፡ ለዓመታት ያለማቋረጥ ሲሳተፍ ቆይቷል፡፡ የኩባንያውን ምርቶች በስፋት ለማስተዋወቅ በማለት ምርቶቹ የሚሸጡበት ዋጋ እስከ አሥር በመቶ ቀንሰው ይሸጣሉ፡፡ ይሁንና ከጊዜ ወደ ጊዜ የቦታ ኪራይ ዋጋ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ፣ በዓውደ ርዕይ መሳተፍ ከጥቅሙ ጉዳቱ አመዝኗል ይላሉ፡፡ ‹‹ለዘጠኝ ካሬ ሜትር ቦታ ከ30 እስከ 50 ሺሕ ብር ድረስ ይጠይቃሉ፡፡ ደንበኞች በብዛት በሚገኙባቸው ቦታዎች የሚጠየቀው ዋጋ በጣም ውድ እየሆነ ነው፤›› በማለት አቶ ስለሺ አዝማሚያውን ተችተዋል፡፡

በርካቶች እንደ ሼባ ሌዘር ያሉ ኩባንያዎችና ሌሎች ነጋዴዎች፣ ለቦታው እንዲከፍሉ የሚጠየቁት ዋጋ ቢወደድም፣ ከተለመዱበት ቦታ ላለመታጣት ሲሉ የተጠየቁትን ይከፍላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ለቦታው ያወጡትን ገንዘብ በምርቶቻቸው ላይ ጨምረው ይሸጣሉ፡፡ ደንበኛን ያባርራል በማለት ምርታቸውን በገበያ ዋጋ መሸጡን የሚመርጡም አሉ፡፡ በዚህ ብዙም ሳይቆዩ በዋጋው ተማረው ቦታቸውን ለሌላ የሚለቁም ብዙዎች ናቸው፡፡

ተመሳሳይ ዕጣ ከገጠማቸው መካከልም ሼባ ሌዘር ይመደባል፡፡ ለዓመታት ይጠቀሙበት የነበረው 160 ካሬ ሜትር ቦታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዋጋው ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ መጥቷል፡፡ ባለፈው ዓመት በፋሲካ በዓል የንግድ ዓውደ ርዕይ ላይ ለቦታው የከፈሉት 270,000 ብር ነበር፡፡ ለአዲስ ዓመት ባዛር ግን ዋጋው በእጥፍ አድጎ 450,000 ብር እንዲከፍሉ ተጠይቀዋል፡፡

እስከ 300,000 ብር ድረስ ለመክፈል ቢደራደሩም ከ400,000 ብር አይቀንስም በመባላቸው ቦታውን ሌላ ተከራይ ለቀዋል፡፡ ‹‹ከ30 እስከ 45 በመቶ ከሽያጭ የሚገኘውን ገቢ ለኪራዩ ነው የምናውለው፤›› ሲሉ የዋጋው ጉዳይ አንድ ሊባል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ሌሎች ድርጅቶችም በተመሳሳይ ከዋጋ ጋር በተያያዘ ቦታቸውን እየለቀቁ ይገኛሉ፡፡ ሙሉ ልብስ፣ ሸሚዝ፣ ቲሸርት የመሳሰሉትን አልባሳት ከቱርክ የሚያስመጣው አናቶሊያ የተባለው ድርጅት ባለፈው ዓመት ለገና በተዘጋጀው ዓውደ ርዕይ ላይ ተሳታፊ ነበር፡፡ በወቅቱ 9 ካሬ ሜትር ቦታ በ36,000 ብር ነበር የተከራየው፡፡ ከሚጠየቀው ዋጋ አኳያ ዳግመኛ የመሳተፍ ሐሳብ እንደሌላቸው የድርጅቱ ኃላፊ ወ/ሪት ሕይወት መኰንን ተናግራለች፡፡

ዓውደ ርዕዩ በክልል ከተሞች የሚዘጋጅ ከሆነ ግን ዋጋው እስከ ሦስት እጥፍ ይቀንሳል፡፡ ‹‹ከወራት በፊት በቢሾፍቱ በተዘጋጀው ዓውደ ርዕይ ላይ ተሳትፈን ነበር፡፡ ለ15 ቀናት በቆየው ፕሮግራም ላይ 9 ካሬ ሜትር ቦታ ነበር የያዝነው፡፡ የከፈልነውም 12,000 ብር ብቻ ነበር፤›› ብላለች ሕይወት፡፡

ዋጋው ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ የመጣው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሲሆን፣ አዘጋጁንም ሆነ ነጋዴውን እያከሰረ እንደሚገኝ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ አቶ አዶኒክ እንደሚሉት፣ ከዚህ በፊት ባዛር የሚዘጋጀው በድርድር ነበር፡፡ ዋጋውም ቢበዛ እስከ ሦስት ሚሊዮን ብር ገደማ ነበር፡፡ በ2007 ዓ.ም. ግን በአንድ ጊዜ ስድስት ሚሊዮን ብር እንደገባ አቶ አዶኒክ አስታውሰዋል፡፡ ይህ ዋጋ በወቅቱ ጉድ ተብሎለትም ነበር፡፡ ይባስ ብሎ በ2008 ዓ.ም. ወደ አሥር ሚሊዮን ብር አሻቅቧል፡፡

‹‹ጨረታ ከተጀመረ በኋላ ነው ዋጋው በጣም የጨመረው፡፡ አንድ ተጫራች ስንት እንደሚሰጥ አይታወቅም፡፡ በግምት ነው የምንፎካከረው፡፡ ላለመቀደም እርስ በርስ  የመፈራራት ነገር አለ፡፡ ለዚህም አንዱ ከፍተኛ የመሰለውን ዋጋ ሰቅሎ ይጠራል፤›› የሚሉት አቶ አዶኒክ፣ ሁኔታው ነጋዴዎችንም ሆነ አዘጋጆችን እያከሰረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት ነጋዴዎች ለቦታ ኪራይ ይከፍሉ የነበረው 20,000 ብር አይደርስም ነበር፡፡ አሁን ግን እስከ 50,000 ብር እንዲከፍሉ እየተገደዱ ነው፡፡ ‹‹ለሙዚቃና ለመዝናኛ ብቻ እስከ አራት ሚሊዮን ብር ይወጣል፤›› በማለት ሁኔታው እየተባባሰ እንደሚገኝ አቶ አዶኒክ አብራርተዋል፡፡ ይህ መሆኑም በርካቶች በምርቶቻቸው ላይ ያለአግባብ ዋጋ እየጨመሩ እንዲሸጡ አድርጓቸዋል፡፡ እንደዚህም ሆኖ ጫናውን መቋቋም ያቃታቸው ነጋዴዎች ቦታቸውን እየለቀቁ ነው፡፡   

በአገሪቱ የመጀመሪያው የንግድ ዓውደ ርዕይ የተካሄደው በ1950ዎቹ ውስጥ ነበር፡፡ በ1970ዎቹ የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ከተቋቋመ በኃላ በቋሚነት የንግድ ዓውደ ርዕይ መካሄድ ተጀመረ፡፡ በ23 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ማዕከሉ የሚያገኘው ዓመታዊ ገቢ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ይገኛል፡፡

ከ11 ዓመታት በፊት የነበረው የማዕከሉ ዓመታዊ ገቢ 4.1 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን 60 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በወቅቱ የነበረው የአዘጋጆች ቁጥርም ቢሆን ከአሥር አይበልጥም ነበር፡፡ አሁን ግን ከ250 በላይ ሆነዋል፡፡ በዓመት በአማካይ 45 ኤግዚቢሽንና የንግድ ትርዒቶች ይካሄዱበታል፡፡ በዓመት ለማዘጋጀት የታሰቡ የንግድ ዓውደ ርዕዮችም ቦታ በቅድሚያ ይይዛሉ፡፡ የ2009 ዓ.ም. ፕሮግራምም 95 በመቶ ቀድሞ ተይዟል፡፡ የገና ዋዜማን ለማዘጋጀትም 23 ሚሊዮን ብር ተከፍሏል፡፡

አቶ ታምራት አድማሱ የአዲስ አበባ የኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ በዓልን መሠረት አድርገው በሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ላይ ከባህር ማዶም ከአገር ውስጥ የማይገባ ቁሳቁስ የለም፡፡ ሰዎችም የሚፈልጉትንና ሌላ ቦታ ያጡትን የሚያገኙበት ነው፡፡ ነጋዴዎችም በዓመት ከሚሸጡት በበለጠ በእነዚህ ቀናት ይሸጣሉ፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች በተመለከተ ሲናገሩም፣ ‹‹ደንበኞች ስለሚገዟቸው ዕቃዎች ደረጃና ዋጋ ያውቃሉ፡፡ ማዕከሉም ምርቶች መሸጥ ያለባቸው ከሰዎች አቅምና ከገበያ ሁኔታ አንፃር እንዲሆን ይመከራል፡፡ ብዙዎች ለሁለት ዓመት ለሦስት ዓመት አከማችተው ያስቀመጡትን በአንድ ጊዜ ሸጠው የሚመለሱበት ሁኔታ አለ፡፡ የቦታ ኪራይ ውድ ቢሆንም፣ ከብዛት ማትረፍ ስለሚችሉ ዋጋ ማስወደድ አይመከርም፡፡  የማይሆን ዋጋ ጨምረው ለመሸጥ ከሚሞክሩት ነጋዴዎች ባለመግዛት ደንበኞች ገበያውን መቆጣጠር ይችላሉ፤›› በማለት አማራጩን አብራርተዋል፡፡

የመግቢያ ዋጋም ቢሆን በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም ሦስት ብር የነበረው መግቢያ ዋጋ አሁን 30ና ከዚያም በላይ ሆኗል፡፡ ለዚህም አቶ ታምራት የተለያዩ ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹እኛ የጨረታ መነሻ ዋጋ እንኳ የለንም፡፡ ነገር ግን የጨረታ ዋጋ በየጊዜው እየተሰቀለ መጥቷል፡፡ ይህም ለመግቢያ ዋጋ መጨመር አንዱ ምክንያት ነው፡፡ በሌላ በኩል የተለያዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ይዘጋጃሉ፡፡ ትልቅ የሙዚቃ ድግስም ያዘጋጃሉ፡፡ አዘጋጆቹ ለዚህ ብቻ  በአማካይ ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ ያወጣሉ፡፡ አልበዛም ማለት አይደለም፡፡ እኛንም ያስደነገጠናል፡፡ ነገር ግን ነፃ ገበያ ነው፡፡ እኛ መቆጣጠር አንችልም፤›› ይላሉ፡፡

በጨረታ ዋጋ መናር ላይ ዓውደ ርዕይ አዘጋጅ ኩባንያዎች ንትርክ ውስጥ ሲገቡም ለመታዘብ ተችሏል፡፡ በአንድ ወቅት ማዕከሉ የሰረዘውን የጨረታ አሸናፊ ኩባንያ መልሶ እንዲያሳትፍ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መታዘዙም የሚታወስ ነው፡፡ ይሁንና ኩባንያዎች እርስ በርስ የተጋነነ ዋጋ በማቅረብ እየተካሰሱ መምጣታቸው እንደማያስገርም ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ በነፃ ገበያ ሰበብ ልጓም አልባ የዋጋ ግሽበት በዓውደ ርዕዮች አካባቢ መታየቱ ከበዛ ወደ ሌሎች እንዳይዛመትም የሚሰጉ አዘጋጆች አልታጡም፡፡  

የዋጋውን ያህል ባይሆንም ለሽያጭ የሚቀርቡ ምርቶች እንደ ባህላዊ መድኃኒቱ ሁሉ ከደረጃ በታችና አደገኛ የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ ማዕከሉ ይህንን የቁጥጥር ሥራ የሚሠሩ፣ ከጤና ቢሮና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ ከደኅንነትና ከጤና ጋር የሚያያዙ ችግሮች በማስመልከት በፀጥታና ደኅንነት ላይ የሚሠራ ክፍል አለው፡፡ ነጋዴዎች ከመግባታቸው በፊት ጎብኚዎች ላይ ችግር ቢፈጥሩ ተጠያቂ ስለሚሆኑ ከባድ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማብራሪያ ይሰጣቸዋል፡፡ የሚፈራረሙት ውልም አላቸው፡፡ በተጨማሪም አዘጋጆችም ኃላፊነት አለባቸው ተብሏል፡፡

በየወረዳውና ክፍለ ከተማው የሚገኙ የንግድ ቢሮ ሠራተኞችም ወደ ማዕከሉ እየሄዱ የሚያካሂዷቸው የቁጥጥር ሥራዎች እንዳሉ አቶ ታምራት ተናግረዋል፡፡ ‹‹የሚፈለገውን ያህል ሄዷል ወይ ቢባል ገና ይቀረዋል፡፡ ነገር ግን ሥርዓቱ አለ፤›› በማለት አልፎ አልፎ ያልሆነ ምርት የሚያቀርቡ ድርጅቶች እንደሚያጋጥሙ፣ ሕግ ፊት በማቅረብም ተገቢው ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው፣ ሕዝቡም ተመሳሳይ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ቀድሞ ሪፖርት በማድረግ ራሱን እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

     

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች