Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቱሪዝም ዘርፍ የዚህ ዓመት የገቢ ዕቅድ በተከሰተው ሁከት ሰበብ መከለሱ ታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

– በኢንተርኔት መዘጋት ቱሪስቶች ተማረዋል

– በተቃውሞ ጦስ ብሔራዊ ፓርኮች ተጎድተዋል

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ ከቱሪዝም ዘርፍ ለማግኘት ያቀደውን ገቢም ሆነ ይመጣሉ ብሎ የሚገምታቸው የቱሪስቶች ቁጥር በተከሰተው ሁከት ምክንያት እንዲከለስ መደረጉን አስታወቀ፡፡ የተደረገው ክለሳ ግን ያን ያህል ቅናሽ እንደሌለው ታውቋል፡፡

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የነበረውን አፈጻጸም በማስመልከት በሰጡት መግለጫ ወቅት በሪፖርተር ተጠይቀው ሲያብራሩ፣ በበጀት ዓመቱ ታቅዶ የነበረው የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር 1.25 ሚሊዮን እንደሚደርስ ነበር ብለዋል፡፡ ሆኖም ይህ ቁጥር ወደ አንድ ሚሊዮን ዝቅ እንዲል መደረጉንና ይገኛል የተባለው የገቢ መጠንም ወደ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ዝቅ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ ይህ የገቢ መጠን ከአምናው የ3.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያነሰ ሆኗል፡፡

ከሐምሌ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በነበሩት ሦስት ወራት ውስጥ የቱሪዝም ዘርፉ ያስመዘገበው ገቢና የጎብኚዎች ቁጥር ምን ይመስል እንደነበር ሲያብራሩም ከ872.5 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገቢ መመዝገቡን፣ ከ233 ሺሕ በላይ ጎብኚዎችም መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህ የዘርፉ አፈጻጸም ግን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ከነበረው አኳያ ሲታይ መጠነኛ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ እንደ አቶ ገዛኸኝ ማብራሪያ፣ የ0.84 በመቶ ወይም ሰባት ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ሲመዘገብ የቱሪስቶች ቁጥርም በ1,979 ቀንሷል፡፡

ይህ ቢባልም ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአገሪቱ የተከሰተው ሁከትና ያስከተለው ደም መፋሰስ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ጫና ማሳደሩ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ አስጎብኚ ድርጅቶችና የሆቴል ባለንብረቶችም ስለጉዳቱ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ የክረምቱ ወራት ለቱሪዝም ዘርፍ ዝቅተኛ ፍሰት የሚታይበት በመሆኑ የጉዳቱ መጠን ያን ያህል አለመታየቱም ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ ከቢሾፍቱ የኢሬቻ ክብረ በዓል ግጭት ጀምሮ ያለው ሁኔታ ዘርፉን ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ መጣሉን፣ ከዚህም በላይ መንግሥት የደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ዘርፉን የበለጠ ተፅዕኖ ውስጥ መክተቱ በይፋ ተነግሯል፡፡

እንደ አስጎብኚዎች ከሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከሚያካትታቸው ክልከላዎች መካከል ዲፕሎማቶች ለአዋጁ አስፈጻሚ ኮማንድ ፖስት ሳያሳውቁ ከ40 ኪሎ ሜትር በላይ እንዳይጓዙ የሚለው ትልቁን ድርሻ በመያዝ፣ በርካታ የታያዙ የጉብኝት ቀጠሮዎች እንዲሰረዙ ሰበብ ሆኗል በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ መንግሥት ይህንን ክልከላ በቅርቡ ማንሳቱ ይታወቃል፡፡ በጠቅላላው በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ስለደረሰው ጉዳት በሁለተኛው ሩብ ዓመት ተካቶ መረጃው እንደሚቀርብ በመግለጽ፣ አቶ ገዛኸኝ የጉዳቱን መጠንና የተሰረዙ ጉብኝቶችን ብዛት ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ዝርዝሩ ገና እየተጠናቀረ ነው ብለዋል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል የተባለው ሌላኛው ክልከላ የኢንተርኔት መዘጋት ነው፡፡ መንግሥት በመላ አገሪቱ የጣለው ክልከላ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት የግጭት ቅስቀሳዎች ተስፋፍተዋል በሚል ምክንያት ቢሆንም፣ በርካታ ቱሪስቶች ግን በዚህ ምክንያት ቅሬታ እንዳደረባቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡ ለዚህ ምላሽ የሰጡት አቶ ገዛኸኝ፣ ምንም እንኳ የኢንተርኔት ግንኙነት ቢቋረጥም ሆቴሎችና የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች እንዲጠቀሙ መፈቀዱን ገልጸዋል፡፡ ይህም ሆኖ በርካታ ቱሪስቶች መማረራቸው ከአስጎብኚዎች ሲነገር ቆይቷል፡፡

በግጭቱ ወቅት በብሔራዊ ፓርኮች፣ በሎጆችና በሪዞርት ሆቴሎች ላይ ጉዳት መድረሱም ታውቋል፡፡ የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንዳብራሩት ከሆነ፣ አብያታና ሻላ ብሔራዊ ፓርኮች እንዲሁም በዙሪያቸው የሚገኙ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወድመዋል፡፡ በባሌ ብሔራዊ ፓርክ አካባቢም ተመሳሳይ ጉዳት መድረሱን አቶ ገዛኸኝ ጠቁመዋል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ጉባዔ ላይ፣ በአገሪቱ ከሚገኙ ፓርኮች መካከል እንደ አዋሽ፣ ነጭ ሣር፣ ባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ሙሉ ለሙሉ ለመጥፋት መቃረባቸውን አስጠንቀቀው እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች