Monday, October 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊበትምህርት ተደራሽነትና ፍትሃዊነት ላይ ክፍተቶች እንዳሉ ተገለጸ

  በትምህርት ተደራሽነትና ፍትሃዊነት ላይ ክፍተቶች እንዳሉ ተገለጸ

  ቀን:

  ባለፉት 25 ዓመታት በትምህርት ጥራት፣ ፍትሃዊነትና ተደራሽነት ዙሪያ የተከናወኑ ሥራዎች ውጤት ቢያስገኙም፣ አሁንም በርካታ ክፍተቶች ይታዩባቸዋል፡፡ እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት ሁሉን አቀፍ የሆነና በቅንጅት የተደገፈ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የትምህርት ሚኒስቴር አመራሮች አስታውቀዋል፡፡

  በሰመራ ከኅዳር 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄደውን አገር አቀፍ የትምህርትና ሥልጠና ጉባዔ አስመልክተው አመራሮቹ ጥቅምት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ጥላዬ ጌጤ እንደገለጹት፣ የሁለተኛ ደረጃ መምህራን አቅርቦት ችግርን ለመፍታት የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው አሥር ሺሕ ሰዎች የሥልጠና ላይ ደመወዝ 2008 ብር እየተከፈላቸው፣ በተመረጡ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በመምህርነት ሙያ በመሠለጥን ላይ ናቸው፡፡

  የትምህርት ተደራሽነት አድጓል ቢባልም፣ በአንዳንድ ክልሎች ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡ፣ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ተሳታፊ ያልሆኑ አካል ጉዳተኞች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡

  አቶ ንጉሤ ገብሬ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ‹‹የቴክኒክ፣ ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት የተቋቋሙት በ334 ወረዳዎች ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የምንረዳው ነገር ቢኖር ተደራሽነቱ ገና እንደሆነ ወይም ተጨማሪ የተደራሽነት ሥራ እንደሚጠብቀን ነው፤›› ብለዋል፡፡

  በሥልጠናው ላይ የሚታየውን የጥራት ችግር ለመቅረፍ የኢንዱስትሪ የትብብር ሥልጠና ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው፤ በአገሪቱ አሁን ያሉት ኢንዱስትሪዎች ግን በዚህ ዙሪያ አቅማቸውን እንዳልገነቡ፤ በዚህም የተነሳ በአፓረንትሺፕ ለሥልጠና የሚመጣው ሠልጣኝ ማሽኖቻቸውን እንዳይነካባቸው የመፈለግ አዝማሚያ እንደሚታይባቸው አስታውቀዋል፡፡

  ባለፈው ዓመት ግንቦት ላይ የተከለሰውና በዚህ ዙሪያ ላይ ትኩረት ያደረገው አዋጅ የመንግሥትና የግል ተቋማት የሆኑ ኢንዱስትሪዎች፣ ለሥልጣና የሚመጡላቸውን ሠልጣኝ ተማሪዎች በሚገባ እንዲያሠለጥኑ ግዴታ እንደጣለባቸው ተናግረዋል፡፡

  ዶ/ር ካባ ኡርጌሳ የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ‹‹ባለፈው ዓመት ወደተለያዩ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ከገቡት ተማሪዎች መካከል 35 ከመቶ ያህሉ ሴቶች መሆናቸውንና ይህንን ውጤት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጨረሻ ላይ ወደ 45 በመቶ ለማድረስ መታለሙን ገልጸዋል፡፡

  ባለፈው ዓመት የሴት መምህራንን ቁጥር ወደ 20 በመቶ፣ በአመራር ሰጭነት ወደ 16 በመቶ ከፍ ለማድረስ ታቅዶ፣ በመምህርነት 12 በመቶ፤ በአመራር ሰጭነት ደግሞ ሁለት በመቶ ላይ ተገትቷል፡፡ ይህም ቢሆን በምክትል ፕሬዚዳንት ደረጃ የደረሱ ሴት ምሁራን 15 በመቶ ደርሰዋል፡፡ እነዚህም በክረምቱ ወራትና በቅርቡም የተሾሙ ናቸው፡፡

  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የመማር ማስተማር፣ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የማኅበረሰብ አገልግሎት ተልዕዎቻቸውን በብቃት እንዲወጡ ማድረግ ትኩረት የተሰጠው ተግባር ሲሆን፣ በዚህም መሠረት በተያዘው የትምህርት ዘመን በድምሩ 3024 የዩኒቨርሲት መምህራን በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ መደረጉን ታውቋል፡፡

  የትምህርትና የቴክኖሎጂ ልማት ሠራዊት ግንባታ ለትምህርትና ሥልጠና ጥራት፣ ለሠላምና ለልማታችን›› በሚል መሪ ቃል ለ26ኛ ጊዜ በሚካሄደው አገር አቀፍ ጉባዔ፣ ያለፈው በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም፣ የትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሠራዊት ግንባታ ሒደት ያለበት ደረጃ፣ የልማታዊ መልካም አስተዳደር ፓኬጅና ዓመታዊ በጀት አፈጻጸም ይገመገማል፡፡

  ጉባኤው ለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በታቀደውና የ2008 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ በመወያየት የጋራ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img