Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናህልምና ቅዠት አላስተኛ ሲሉስ?

ህልምና ቅዠት አላስተኛ ሲሉስ?

ቀን:

ሰላም! ሰላም! በቀደም ለረቡዕ አጥቢያ በግራ ጎኔ ተኝቼ ማን ወክሎኝ እንደሆነ አላውቅም፣ ማንን እንደወከልኩም እንጃ፣ በአንዴ ከደላላነት ወደ ፖለቲከኝነት ተመንድጌ ለምርጫ ስወዳደደር በህልሜ ሳይ ቀውጢ ጩኸት ሰማሁ። ‹‹ገና ሳልመረጥ ይኼ ሕዝብ የሚጮህብኝ ምን አድርጌው ነው?›› ስል ማንጠግቦሽ ‹‹ኧረ ውረድ!›› ስትል በሰመመን እሰማታለሁ። ‹‹ገና ሥልጣን ላይ ሳልወጣ ምን ብዬ ነው የምወርደው?›› ስላት ብርድ ልብሱን ገፈፈችኝ። የጥቅምት ስስ ንፋስ ላዬ ላይ ሽው ሲል ብድግ አልኩ። ለካ ጩኸቱ ከጎረቤት ነው። ህልምና ቅዠት መምታታቸው ሳያንስ በምርጫና በተመራጭነት ዕጣ ያለተፈጥሯችን ይጫወቱብን ጀመር ማለት ነው እያልኩ ሮጬ ወጣሁ። የማንጠግቦሽ ቡና አጣጭ በዕድሜ ከባሻዬ ቢበልጡ እንጂ የማያንሱት አዛውንት የሚለየን ግድግዳ ነው። ‹‹ምነው ምን ሆኑ?›› ብዬ ዘልዬ ቤታቸው ስገባ ቴሌቪዥኑ በርቷል። ሬዲዮው ይለፈልፋል። ልጆቻቸው አሜሪካ አገር ስለሚኖሩ ምናልባት ክፉ ወሬ ሰምተው ይሆን ብዬ ክው አልኩ።

‹‹ኧረ ይንገሩኝ፤›› ስላቸው፣ ወይኔ ልጆቼ! ወይኔ! ወይኔ! ገና ጎናቸውን ሳያደላድሉ እንደ ጥራጊ በእኚህ መጥረጊያ ሰውዬ ተጠርገው ሊመጡ?›› አሉ። ‹‹ማናቸው መጥረጊያው?›› ብዬ ወደ ማንጠግቦሽ ሳይ፣ ‹እንጃልህ!› ዓይነት ትከሻዋን ትሰብቃለች። ኋላ ቴሌቪዥኑ ከነገረኝ ብዬ ዓይኔን ስወረውር አቶ ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን እንዳሸነፉ ይዘግባል። ነገሩ ገባኝ። እኚህ አዛውንት ጎረቤቴ ልጆቻቸው አሜሪካ ከገቡ ወዲህ ትንሽ ጉራ ቢጤ ያስቸግራቸው ነበር። በተለይ ሠፈር ውስጥ ሥራ ፈተው የሚያዩዋቸውን ወጣቶች፣ ‹‹አትንቀሳቀሱም? ሥራ አትሠሩም? ዝቅ ብላችሁ እስኪ ሥሩ፤›› እያሉ ሲወርፉ እሰማለሁ። እናም እነዚህ ወጣቶች በጣም እየተናደዱባቸው ሲሄዱ አንድ ቀን መንገድ ላይ አቁመው፣ ‹‹እኚህ ሰውዬ ከተመረጡ እኮ አሜሪካዊ ያልሆነ በተለይ ከአፍሪካ የሄደ ሁሉ በነጋታው ተባራሪ ነው…›› ብለዋቸው ኑሮ እውነት መስሏቸው መንታ አነቡ። ‹ወይ ካለው ተፈጠር ወይ ካለው ተጠጋ› ተቀይሮ ወይ ተመረጥ ወይ ከተመረጠው ወግን ሆኖ የዘንድሮ ኑሮ እንቅልፍ አጣን እኮ እናንተ!

ኋላ ነገሩ ደህና አድርጎ ሲገባኝ እነዚያን ወጣቶች በልቤ እየረገምኩ፣ ‹‹ይበሉ እንደ እሱ አይደለም። የአሜሪካ ዲሞክራሲ እኮ እንደ አፍሪካ አይደለም። የጠቅል አሽከር ብሎ ነገር እዚያ የለም። በሰማይ ላይ ሁለት ፀሐይ እንደማይወጣ ሁሉ አንድ ሰው ከፊት መወከል ስላለበት እንጂ እሳቤውና ውሳኔው በምክክር ነው። ምናምን ምናምን…›› እያልኩ የማወቀውንም የማላውቀውንም ቀበጣጥሬ አረጋጋኋቸው። ማንጠግቦሽ፣ ‹‹ትናንትና ቡና ጠርቼዎ ምነው ቀሩ?›› ብላ በጎን ሐዘናቸውን ልትበርዝ ጣልቃ ትገባላች። በግራ በቀኝ አዋክበን እንባቸውን ካስቆምንላቸው በኋላ ለከሰዓት በኋላ ቡና ተቀጣጥረን እኔና ማንጠግቦሽ ተመልሰን አልጋችን ውስጥ ገባን። ‹‹አይገርምህም?›› ብላ ጀመረች። ‹‹ምኑ?›› አልኳት። ‹‹ባሻዬ የእድሩ ሊቀመንበር ሆነው በድጋሚ የተመረጡት ትናንትና ነው። ግን ማንም የሰማና ያወቀ የለም። እኚህ ሴትዮ እድሩ ላይ ያላቸው መተማመን ምን ያህል እንደሆነ ታውቃለህ። ባሻዬ እንዳይቀድሙኝ ብቻ አንጂ ስሞትማ ሠርግ አስመስለው እንደሚያስቀብሩኝ አልጠራጠርም ነው የሚሉት። ግን ይኼው ባሻዬ በትናንትናው የእድሩ ሊቀመንበርነት ምርጫ ለመሸነፍ ጫፍ ላይ ደርሰው በአንድ አብላጫ ድምፅ መመረጣቸውን ሊያውቁ ቀርቶ ለምርጫ መቅረባቸውንም አልሰሙም፤›› ስትለኝ እም ብዬ ዝም አልኩ። እንኳን ሌላው እኔ ራሴ ባሻዬ ለምርጫ መቅረባቸውን፣ ቀርበው መወዳደራቸውን ስላልሰማሁ አፍሬያለሁ። ይኼኔ ባሻዬ አሜሪካዊ ቢሆኑ ኖሮ ብዬ ሳስብ ለሊቀመንበርነት ቀርቶ ለመኖር በእግዜር መታሰባቸውን ሳስብ ቀኑ መሽቶ እንደሚነጋ ታየኝና መኖሬን ጠላሁት። እንኳንም ግን ሕይወት በሰው ልጅ አብላጫ ድምፅ የሚወሰንና የሚሻር አልሆነ አትሉም!

አረፋፍጄ ቁርሴን በልቼ ቡናዬን ጠጥቼ ከቤቴ ወጣሁ። እንደ ትናንት በእንጥልጥል የተውኩት ቢዝነስ ነበረኝና ወደዚያው መጓዝ ጀመርኩ። ነገሩ ሁለት ሺሕ ካሬ ሜትር የሚሸጥ ቦታ ነው። ሁለት መቶ ካሬው ላይ ኤልሼፕ ቤት ተሠርቶበታል። ትናንትናውኑ የሚገዛ ሰው ፈልጌ አግኝቼ ሻጩ ቆይ ነገ ይሁን ስላለ ለአዳር ተወሰነ። በበኩሌ ከንክኖኛል። ‹‹አሁኑኑ ገዢ ካገኘህ አምጣና ወደዚያ ገላግለኝ፤›› ሲለኝ እንዳልነበር ምን ሰምቶ ነው ነገ ኑ ያለው እያልኩ ሳወጣ ሳወርድ ስልኬ ጠራ። ገዢው ደንበኛዬ ነው። ‹‹ወደ አንተ እየመጣሁ ነው። ያው ዋጋው 14 ሚሊዮን ብር ነው። አይተኸው ደግሞ መደራደር ነው፤›› አልኩትና ስልኩ ተዘጋ። ወዲያው መልሶ ስልኬ ጮኸ። ሻጩ ደንበኛዬ ነው። ‹‹አቤት! አቤት!›› አልኩኝ ‹ጭራዬን› እየቆላሁ። ገና አፉን እንዳላሟሸ ያስታውቃል።

ደህና አረፈድክ ሳይለኝ፣ ‹‹ቦታው በዛሬው ገበያ መሠረት ከ14 ወደ 16 ሚሊዮን ብር ተሻግሯል፤›› አይለኝ መሰላችሁ? ‹‹እንዴ ትናንትና እኮ 14 ነው ብዬ ተናግሬያለሁ። ደግሞ አሁን ቦታውን ለማየት ወደ እርስዎ እየመጣን ነው…›› ስለው፣ ‹‹የለም! የለም! አንተ ዘመናዊ ደላላ አይደለህም እንዴ? ምንድነው በሚዲያ ዜና የዕለቱን የቢዝነስ ሁኔታ መከታተል እኮ አለብህ። ትናንት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሌላ ሰው ነበር። አሁን ግን ዶናልድ ትራምፕ ተመርጠዋል። የእሳቸው መመረጥ ታላቅ ታናሽ ሳይል የዓለምን ቢዝነስና ኢኮኖሚ ሲያናጋ የእኔና የአንተን የማይነካው ለምንድነው?›› ብሎኝ አረፈው። ግራ ገብቶኝ ባለሁበት ቆሜ ቀረሁ። ጊዜ ሳላጠፋ ለገዢው ደንበኛዬ ደውዬ የተባልኩትን ስነግረው ሳይበሳጭ፣ ‹‹ልክ ልደውልልህ ስል ቀደምከኝ። ትራምፕ ስለተመረጠ ለእኔ መቀነስ አለበት ብዬ እደራደረዋለሁ ብዬ ልነግርህ ልደውል ስል ነው የቀደምከኝ። ለማንኛውም ልምጣና እንደራደራለን…›› ብሎ ስልኩን ዘጋው። ወይ ሰበብ ፈላጊና ሰበቡ!

  እናላችሁ እንዲህ ከቦንቦሊኖ እስከ መሬትና ቤት ዋጋ በዶናልድ ትራምፕ ሚዛን ከፍ ዝቅ ሲጫወት እኔ ልቤ ጠፋ። ደንበኞቼን አገናኝቼ እኔ ላጥ አልኩ። ደላላ የመሆን ጥቅሙ በዚህ በዚህ ጊዜ ነው። ባጋደለው ቢመዝን በተቀዳው ቢጎድል ዋናው ማገናኘቱ ነው። ደግሞ ዘንድሮ የጠፋው አገኛኝ ነው። ይኼን እያሰብኩ ባሻዬ ትዝ አሉኝ። ሥራው አስጠልቶኛል። ታዲያ ለምን አንደኛዬን ወደ ሠፈር ሄጄ ባሻዬን እንኳን ደስ አለዎት አልልም ብዬ ሳስብ ስልኬ ጠራ። የደወለችው የልጅነት ወዳጄ ነበረች። አጫውቻችሁ አላውቅም እንጂ ከዚህች ወዳጄ ጋር የተጣላነው በምርጫ ነው። እንዴት እኔ እያለሁ፣ እኔን በቅድሚያ እያወክ ማንጠግቦሽን ለትዳር መረጥክ?›› ብላ አኩርፋኝ ነበር። ደስ ደስ ሲላት እንዲህ ትደውላለች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እንኳን አደረሰህ እንኳን አሻገረህ ብላ መደወሉን እርግፍ አድርጋ ትታው ነበር።

ምን ተገኘ ዛሬ ብዬ ስልኩን ሳነሳው ቁና ቁና ትተነፍሳለች። በቅጡ ሰላም አልተባልኩም። ‹‹ምነው ምን ሆነሻል?›› ስላት ‹‹ኧረ ተወኝ ተቃጥያለሁ፤›› ብላ ጀመረች። ቤት ለቤት ስለምንተዋወቅ የእናቷ ጤና አሳስቦኝ እማማ ሰላም አይደሉም?›› ስላት እሷ ምን ትሆናለች? የትራምፕ መመረጥ አናዶኝ ነው እንጂ፤ አትለኝ መሰላችሁ? እስኪ አሁን በእኔ ቦታ ብትሆኑ ምንድነው የምትሏት? ቆይ እኔ የትራምፕ ልዩ አማካሪ ነኝ ወይስ የጥላቻ ዘመቻ አስተባባሪ ነኝ። ብቻ ስለሰው ልጅ እያደር ዘረኛ መሆን፣ መጥበብ፣ እኔ እኔ ማለት፣ ወዘተ ኑሮዋን እያመረረው እንደመጣ አውርታ፣ ጤናህን ግን ደህና ነህ? ሳትል ማንጠግቦሽን ሳታነሳ ስልኩን ዘጋችው። ይኼን ያህል የእውነት የሰው ልጅ ሐሳብና ምርጫ የሚያብሰለስለን ከሆነ ታዲያ ቆይ ለምንድነው የቅርብ የቅርቡ ላይ እንቅልፍ እንቅልፍ የሚለን? እውነቴን እኮ ነው!

በሉ እንሰነባበት። ነገር ዓለሙ አስጠልቶኝ በቃ እየናወዝኩ ቤት ስደርስ ጠዋት በጩኸት የቀሰቀሱኝ አዛውንቷ ጎረቤቴ አቦላቸውን ፉት እያሉ በፈገግታ ተቀበሉኝ። በግድ ፈገግ አልኩ። በፈገግታቸው ውስጥ ደግሞ ሌላ የዶናልድ ትራምፕ ምዕራፍ ሲታየኝ፣ ‹‹ዕቃ ረሳሁ…›› ብዬ ወደ ባሻዬ ቤት ሄድኩ። ስገባ ተንደርድሬ ሄጄ ሳምኳቸውና፣ ‹‹እንኳን ደስ አለዎት፤›› አልኳቸው። ‹‹ምን ደስታ አለው ይኼ አንበርብር? ባስተባበርኩት፣ ባሰባሰብኩት፣ ባነሳሳሁት እድር ለምርጫ መቅረቤ በራሱ ሞት አይደለም እንዴ? ከዚህ የበለጠ ምን ውርደት አለ?›› ብለው በኩርፊያ ገላመጡኝ። ወይ ጣጣ አልኩ በልቤ። ወይ አፍሪካም ብያለሁ። ባሻዬ እንዲያ ቀልባቸው ተገፎ አላናግረኝ ሲሉ፣ ‹‹እስኪ መክሰስ ነገር ቀምሼ ልምጣ፤›› ብዬ ተነስቼ ወጣሁ።

ስወጣ ከልጃቸው ጋር በር ላይ ተገጣጠምንና ተያይዘን ገና ሳይመሽ ወደ ግሮሰሪያችን አመራን። ስንገባ ሰው ብቻ ነው። ሆታ፣ ተረብ፣ ስላቅ፣ ቁም ነገር ቀዝቅዞ ቢሰነብትም ድንሰበር የተሻገረ የሞቀ ወሬ ስለተገኘ ታዳሚው በነፃነት ያሻውን ያወራል። አንዱ፣ ‹‹አሜሪካ ለዘለዓለም ትኑር፤›› ብሎ ፅዋውን ሲያነሳ፣ ‹‹እሱን ተወው፣ ባይሆን ዴሞክራሲያቸው ለዘለዓለም ይኑር በል፤›› ብሎ ሌላው ያርመዋል። ‹‹ግን የአብላጫ ድምፅ ጉዳትን አያችሁት አይደል? አይመለስ አይከለስ። አንዴ ከተቆጠረ በኋላ  አበቃ፤›› ይላል ሌላው። ‹‹እሱን ሂድና ለምርጫ ቦርድ ንገረው። ይልቅ አሁን ለትራምፕ ቺርስ…›› ሲል ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ብርጭቆአቸውን አንስተው ‹ቺርስ› አሉት። ‹‹ዓለምን አየሃት። ለአሸናፊ እንጂ ለተሸናፊ እኮ ቦታ የላትም፤›› የሚለኝ የባሻዬ ልጅ ነው። ‹‹ከፋም ለማም በምርጫ መሆኑ ትልቅ ነገር ነው፤›› ብዬ ዝም አልኩ። አንዳንዴ እኮ ህልምና ቅዠትም ያምታታሉ፡፡ አላስተኛ እያሉ፡፡ አይደል እንዴ? መልካም ሰንበት!      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...