Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሰሞነኛው አየር

ሰሞነኛው አየር

ቀን:

ወቅቱ የአበባ፣ የመኸርና የነፋስ ነው፡፡ ቅዝቃዜና ነፋስ በሚቀላቅለው በዚህ ወቅት እንደየአካባቢው ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ዝናብ የሚያገኙ ሥፍራዎች አሉ፡፡ ደጋማ ወይም ውርጭ በሚበዛባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ደግሞ በቁር የሚመቱበት፣ በአበባና በፍሬ ደረጃ የሚገኙ ሰብሎችም ጥንቃቄ ካልተደረገ የሚቀጭጩበት ብሎም የሚበላሹበት ነው፡፡ ‹‹ውርጭ ሰብሉን መታው›› ሲባል በአብዛኛው የሚሰማውም በዚሁ ጊዜ ነው፡፡

በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ከጥቅምት እስከ ጥር ያሉት የበጋው አራት ወሮች ደረቅ የአየር ሁኔታ የሚኖርባቸው ናቸው፡፡ ጠዋት፣ ምሽትና ማለዳ ቅዝቃዜ ይኖራል፡፡ በብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክቶሬት ጊዜያዊ ዳይሬክተር ወይዘሮ ጫሊ ደበሌ እንደሚያስረዱት፣ በተለይ በደጋማ አካባቢዎች፣ ሰሜን ምሥራቅ፣ መካከለኛውና ደቡብ የአገሪቱ ደጋማ አካባቢዎች ላይ የማለዳው ቅዝቃዜ የሚያይልበት ወቅት ነው፡፡ ይሁንና በበጋ ወቅት በመደበኛነት ዝናብ የሚያገኙ እንደ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ደቡብ ኦሞ፣ ጋሞጎፋ፣ ወላይታና ሲዳማ ዝናብ ይኖራቸዋል፡፡

በዚህ ወቅት ዝናብ መጣል ሰብል ለደረሰባቸው አካባቢዎች አሉታዊ ቢሆንም፣ በበጋ ወቅት ዝናብ የሚያገኙት ጋሞጎፋ፣ ሰገን ሕዝቦች ወላይታና ጌድዮ ዞኖች፣ ከኦሮሚያ ደግሞ ባሌ፣ ጉጂና ቦረና ዞኖች በሶማሌ ደቡባዊ ቆላማ አካባቢዎች ወሳኝ ነው፡፡

የክረምቱ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት ትግራይ፣ አማራ፣ አፋር መካከለኛውና ምሥራቅ ኦሮሚያ፣ ሐረሪ አካባቢዎች በበጋ ጊዜ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ካልተፈጠረ በስተቀር ደረቃማና ፀሐያማ፣ ማለዳና ሌሊቱ ደግሞ ቅዝቃዜ የሚሆንበት ወቅት ነው፡፡

ከሳምንት በፊት በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ቅዝቃዜ የበዛበት እንደነበር ሲነገር ከርሟል፡፡ ይህንን አስመልክቶ ወይዘሮ ጫሊ እንደገለጹት፣ ባለፈው ሳምንት አብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ፣ ማለዳውና ጠዋቱ ቅዝቃዜ ያየለበት፣ ደጋማ አካባቢዎች ላይ የቀኑ የአየር ንብረት እስከ አምስት ዲግሪ ሴልሽየስ የወረደበት ነበር፡፡

ወቅቱ ክረምት ላይ የተዘራው እህል የሚሰበሰብበት ከመሆኑ አንፃር አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ እንደ ወይዘሮ ጫሊ፣ አርሶ አደሩ የደረሱ እህሎችን ቶሎ ቶሎ መሰብሰብ፣ ከታጨደ በኋላም በቅጡ መከመር አለበት፡፡

ካለው ውርጭና ከማለዳውና ከሌሊቱ ቅዝቃዜ ጋር በተያያዘም አበባና ፍሬ በመያዝ ላይ የሚገኙ ሰብሎች ላይ ጉዳት ይደርሳል፡፡ ስለሆነም አርሶ አደሩ በተለምዶ የሚጠቀመውን ዘዴ (ጭስ ማጨስ) ሲጠበቅበት፣ የግብርና ባለሙያዎች ደግሞ ምክር ሊሰጡ እንደሚገባ ጊዜያዊ ዳይሬክተሯ ያስረዳሉ፡፡

በብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ በየጊዜው የሚመጡ መረጃዎችን በመከታተል የሚደርሰውን ተፅዕኖ መቀነስ የሚቻል በመሆኑም ኅብረተሰቡ ይህንን እንዲከታተል፣ ለጤናው ሲልም በቅዝቃዜ ሰዓት ሙቀት የሚሰጥ ልብስ እንዲለብስ ይመክራሉ፡፡

የማለዳው ቅዝቃዜ ከማየሉና አየሩም ደረቃማና ነፋሻማ ከመሆኑ የተነሳ በሰብሎች ላይ ብቻ ሳይሆን በሰዎች ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ በተለይ በደጋማና መገለጫቸው ውርጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ፊትና ቆዳቸው ሲሰነጣጠቅ፣ ከንፈራቸው ሲደርቅና መልካቸው አመድ ሲመስል ይታያል፡፡ የእጅና እግር ጣቶቻቸው ሽብሽብ ማለትና የነበራቸውን ወዝ ማጣት እንዲሁም መጥቆር ይስተዋላል፡፡ ቅዝቃዜውና ነፋሱ በተለይ ቆዳቸውን በቅባት የማያለሰልሱ ሰዎችን ይበልጥ ይጎዳል፡፡ ይህ በአዲስ አበቤው ላይም ሰሞኑን የሚታይ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ እንደ ሳይነስ፣ አስምና ብሮንካይትስ የመሳሰሉ ከመተንፈሻ አካል ጋር የተያያዙ ችግሮች ከወቅቱ ጋር ተያይዞ ይባባሳሉ፡፡

በቴሌሜድ ሜዲካል ሰርቪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አማካሪ የሆኑት ዶ/ር አደፍርስ በየነ እንደሚሉት፣ ወቅቱ ነፋሻማ፣ ደረቅና ቅዝቃዜ ያለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ እንደ የአፍንጫ ወይም የአየር ቱቦዎች ላይ ያሉ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፣ የነበሩም ካሉ ይባባሳሉ፡፡

የላይኛው የመተንፈሻ አካል የሆነው አፍንጫና ከአፍንጫ አካባቢ ያሉ ሥፍራዎች ቀዝቃዛ አየር በሚመጣበት ጊዜ፣ ብርዱ በሚፈጥረው ጫና ይጎዳሉ፡፡ ለዚህ የተጋለጡ ሰዎች ዓይናቸውን ያሳክካቸዋል፣ ያስነጥሳቸዋል፣ ከአፍንጫ ፈሳሽ ይኖራቸዋል፡፡ ከአፍንጫ የሚወጣው ፈሳሽ ከቆየ ባክቴሪያ የሚሠራ ሲሆን፣ ይህም ሲከርም ኢንፌክሽን ያስከትላል፡፡ አፍንጫ መጠቅጠቅ ስለሚኖርም፣ ይህ እንዲቀንስ፣ የአለርጂ ተጋላጭነትን የሚቀንሱ መድኃኒቶች የሕክምና ባለሙያ በማማከር መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

ቀዝቃዛው የአየር ሁኔታ ሳይነስ ብቻ ሳይሆን አስምንም ያባብሳል፡፡ አየሩ ሲቀዘቅዝና ደረቅ ሲሆን፣ በተለይ አስም ያለባቸው ሰዎች የአየር ቧንቧቸው ስለሚጠብ ይቸገራሉ፡፡

ትኩሳት፣ ወይም ምንም ዓይነት ኢንፌክሽን ሳያሳዩ ለረዥም ጊዜ ሳል የሚተከልባቸው ሰዎችም ይኖራሉ፡፡ ሳሉ ከቅዝቃዜው ጋር ተያይዞ የመጣ ከሆነ፣ ቅዝቃዜው ሲለቅ ይተዋቸዋል፡፡

እንደ ዶ/ር አደፍርስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ በሚኖርበት ጊዜ ሰዎች ለውጡን መሠረት ያደረገ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ቅዝቃዜ ሲኖር በተለይ የመተንፈሻ አካል አለርጂ ያለባቸው ሰዎች፣ አፍንጫቸውን በመሃረብ ወይም በስካርፍ በመሸፈን ሙቀት ያለው አየር እንዲስቡ ማድረግ አለባቸው፡፡

በግብርናውም ዘርፍ ቢሆን፣ ካለው የአየር ንብረት ለውጥ ጋር አብሮ ለመኖር መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ወይዘሮ ጫሊ ይናገራሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...