የመሠረተ ልማት ተቋማት እርስ በርስ ባለመናበባቸው እየደረሱ ያሉ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት የተቋቋመው የፌዴራል የተቀናጀ የመሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ በይፋ ሥራውን ጀመረ፡፡
በአዋጅ ቁጥር 875/2006 የተቋቋመው የመሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ፣ ራሱን በሰው ኃይልና በመዋቅሮች ሲያደራጅ ቆይቶ በዚህ ሳምንት በይፋ ሥራውን መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ኤጀንሲው የተቋቋመባቸው ዓላማዎች በአገሪቱ በስፋት እየተካሄዱ የሚገኙት የመንገድና የባቡር አውታሮች፣ የኤሌክትሪክና የቴሌኮም ዝርጋታዎች እርስ በርስ ተናበው እንዲገነቡ ማድረግ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የመሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ ዕድገት እያስመዘገበች ቢሆንም ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ያህል ጥቅም አላገኘችም፡፡
ለዚህም የሚሰጠው ምክንያት የመሠረተ ልማት ግንባታ እየተከናወነ ያለው ባልተናበበና ባልተቀናጀ ሁኔታ በመሆኑ ነው፡፡
‹‹በዚህ የተነሳ የፕሮጀክቶች መጓተት፣ የማኅበራዊ ችግሮች መከሰት፣ የሥራ ቦታ ደኅንነት ችግር ያልተፈለጉ ወጪዎች እያስከተሉ ነው፤›› በማለት መግለጫው አስታውቋል፡፡
የአብዛኞቹ ችግሮች መነሻቸው ደካማና ያልተቀናጀ ዕቅድና የክትትል ማነስ እንደሆነ መግለጫው ጠቁሞ፣ ይህ ዓይነት አሠራር ደግሞ ለፕሮጀክቶቹ መዘግየትና ለኪሳራ እየዳረገ ነው ብሏል፡፡
ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሆነው ይኼ የመሠረተ ልማት ኤጀንሲ በ13 ዳይሬክተሮችና በ14 ቡድኖች የተዋቀረ ነው፡፡
ይኼንን ተቋም ቀደም ሲል የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ በቀለ ንጉሤ እንዲመሩት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም መሾማቸው ይታወሳል፡፡