Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  እኔ የምለዉበተሃድሶው የተንቆረቆሩ ‹‹ሒሶች›› ማረፊያቸው የት ነው?

  በተሃድሶው የተንቆረቆሩ ‹‹ሒሶች›› ማረፊያቸው የት ነው?

  ቀን:

  (ክፍል አንድ)

  በልዑል ዘሩ

  ገዥው ፓርቲና መንግሥት (ብዙ ጊዜ በተደበላለቀ ስያሜ ይጠራሉ) ተሃድሶ ያውም ʻጥልቅʼ የሚባለውን ማድረግ ከጀመሩ ከራርመዋል፡፡ ምንም እንኳን ኢሕአዴግ ላለፉት ሦስት ጉባዔዎቹ (ከስድስት ዓመታት) ወዲህ ጀምሮ የመልካም አስተዳደር ችግርና ሙስና ‹‹የሥርዓቱ አደጋ ነው›› ሲል ቢቆይምና ስለቁርጠኝነቱ ደጋግሞ ቢያወሳም ሥጋቱ የከራረመ ነበር፡፡

  አንዳንድ ውስጥ አዋቂዎች ሥርዓቱ አሰፍስፎ የመጣውን ችግር እያወቀ ፈጥኖ ለማሻሻል ያልቻለባቸውን ምክንያቶች ያስቀምጣሉ፡፡ አንደኛው ከ2003 ዓ.ም. ወዲህ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መታቀዱና እንደ ባቡር፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብና የስኳር ፕሮጀክት ዓይነት ግዙፍ ፕሮጀክቶች መጀመራቸው ግንባሩ ውስጡን ከማጥራት ይልቅ ወደፊት ብቻ እንዲያይ ማድረጉ ነው፡፡ እዚህ ላይ መንግሥትም ሆነ ገዥው ፓርቲ ከአቅም በላይ የተለጠጡ ዕቅዶችን ይፋ ሳያደርጉ በፀደይ ሕዝባዊ አብዮት ሲመቱ ከነበሩት የሰሜን አፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ዕጣ ፈንታ አንፃርም ለማምለጥም ነበር ያሉ ነበሩ፡፡

  ሁለተኛው በሥርዓቱ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ መሞታቸው የፈጠረው ከውስጥ ይልቅ ወደ ውጭ የማየት ዝንባሌ ነው፡፡ እዚህ ላይ በአንድ በኩል የእሳቸው ሕልፈተ ሕይወት ሥርዓቱን ለብተና አገርንም ለአደጋ ያጋልጣል የሚል ሥጋት የነበራቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል በግንባሩ ውስጥ የኃይል ሚዛኑን በመቀየርና በማመጣጠን በብዙኃኑ ተቀባይነት ያለው መንግሥታዊ ሥርዓት እንደሚዋቀር ተስፋም የነበራቸው፣ በውስጥም በውጭም ቁጥራቸው ትንሽ አልነበረም፡፡

  እነዚህ ትልልቅ ክስተቶች የሥርዓቱን የተሃድሶ ጊዜ ከማራዘም ባሻገር አጉል መታበይና መዘናጋት ውስጥ የከተቱበት ሁኔታም ነበር፡፡ በተለይ በትልልቆቹ ዕቅዶችና በህዳሴው ግድብ፣ በመሀልም በአቶ መለስ ሕልፈት ወቅት የሕዝቡ ንቅናቄና ድጋፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍ እያለ መምጣቱ ታይቷል፡፡ በተለይ ገዥው ፓርቲ ሀብትና ጊዜ በብዛት እያባከነባቸው ባሉ ልዩ ልዩ በዓላትና ሥነ ሥርዓቶች ላይ የተለያዩ ደጋፊ አደረጃጀቶች (ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የነዋሪ ፎረሞችና ሊጎች) የሕዝቡን ፍላጎት ጋርደው አረበረቡ፡፡ ከወረዳ እስከ ክልሎች የሙሉ ጊዜ ሠራተኛ ሆነው በደመወዝ የተቀጠሩ የየብሔረሰቡ የባህል ቡድኖችና ኪነቶች ብሔረሰብ እየወከሉ በየመድረኩ አሸበሸቡ፣ ብዙ ተናገሩ….፡፡

  ከዚህ ሁሉ በላይ በድርጅቱም ሆነ በመንግሥት መዋቅሩ አድርባይነትና ኪራይ ሰብሳቢነት ተስፋፋ፡፡ በብሔረሰብ፣ በሃይማኖትና በጥቅም ዙሪያ መሰባሰብና አገራዊ እሴትን መግፋት ‹‹ትክክለኛ›› ተግባር መሰለ፡፡ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና አሳታፊነትን የመሳሰሉ የመልካም አስተዳደር እሴቶች የወረቀት ጌጥ ብቻ ሆነው ቀሩ፡፡ በኢሕአዴግ ስም መነገድ፣ መሞዳሞድና የግል ጥቅምን ማካበት መጠኑ ይለያይ እንጂ ዋነኛው የዘመኑ መገለጫ መሰለና አረፈው፡፡ በዚያው ልክ ሥርዓቱን ሊገዳደሩ የሚችሉ የዴሞክራሲ ተቋማትና የፖለቲካ ድርጅቶች ተሽመደመዱ፣ ተዳከሙ፡፡

  ሁለተኛው ተሃድሶ መደረግ ከነበረበት ቢያንስ ስድስትና ሰባት ዓመታት ባክነዋል ብያለሁ፡፡ በእነዚህ ጊዜዎች ውስጥ በአገሪቱ ሰላም ነበር፡፡ ልማትም (መንገዶች፣ የከተሞች የቤት ግንባታዎች፣ ባቡርና ኃይል ማመንጫዎችን ጨምሮ፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የጤና ተቋማት) ተስፋፍተዋል፡፡ በመንግሥት ተሠርቷል፡፡ በፍጥነትና በአቋራጭ የበለፀጉትን ጨምሮ ሕይወታቸው የተቀየረ ዜጎችም ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡ ስለዚህ አገሪቱና ሕዝቦቿ ‹‹አድገዋል›› የሚለው በምጣኔ ሀብት መመዘኛ ቢያወዛግብም የልማት መፋጠኑን መደበቅ ፈጽሞ አይቻልም፡፡

  በዚህ መልካም እውነታ ውስጥ ግን ሌላ መጥፎ እውነትም እየተብሰከሰከ ከፍ ያለ ቁጣ ቀስቅሷል፡፡ አንዱና ዋነኛው ፀረ ዴሞክራሲያዊነት በሥርዓቱም ሆነ በአገሪቱ ውስጥ ጥርስ እያወጣ መምጣቱ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መዳከም፣ የአማራጭ ሐሳቦች መንጠፍ፣ የመገናኛ ብዙኃን መድቀቅና መበተን፣ የመደራጀት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ከወረቀት አለማለፍ፣ ብዝኃነት በሞላበት አገር ገዥው ፓርቲ ‹‹መቶ በመቶ›› ምርጫ ማሸነፍ … የለየለት የፀረ ዴሞክራሲ ማሳያ ሆኑ፡፡ ይህም የዴሞክራሲን በር ወደ መዝጋት አቀረበው፡፡

  በሌላ በኩል በሥርዓቱ ውስጥ የነገሠው የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ሙስና (በዚህ ላይ አሉባልታው ተጨምሮበት) ሕዝቡን ክፉኛ አሳዘነው፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ነፍሰ በላው ተሰገሰገ፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ በተሾመ ኃላፊ ስምና በቡድን በተደራጀ ኃይል  አዛዥነት ሌብነት ተጧጧፈ፡፡ እንደ መሬት፣ ኮንስትራክሽን ዘርፍ፣ ኮንትሮባንድና የገንዘብ ዝውውርን በመሳሰሉ ከፍ ያለ የአገር ሀብት የያዙ መስኮች ተዋናዮቹ ጥቂቶች ጥገኞች ሆኑ፡፡ ተገልጋዩም ሕዝብ ከዚህ በመነሳት ሥርዓቱ ‹‹የእነ እገሌ ነው›› የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሶ እርሙን አወጣ፡፡ በእጅ መሄድ ብቻ የዜግነት መብትም መሰለ፡፡

  ከላይ ካነሳኋቸው ሁለት ሕገወጥነቶች ተነጥለው የማይታዩ የሕዝብ ቅሬታ ቆስቋሾች በከተሞች በመልሶ ማልማትና በሕገወጥ ግንባታ ስም ሰፋ ያለ መፈናቀል ታየ፡፡ በዚያው ልክ አዳዲስ በሚመስሉ ሠፈሮች በአብዛኛው በሥርዓቱ ውስጥ የተሰገሰጉ ጥገኞች ባለ ሕንፃና የትልልቅ ሆቴል ባለቤት ሆኑ፡፡ ሠርተውም ይሁን ተመቻችቶላቸው ሰፋ ያለ ሀብት በጥቂቶች እጅ የገባ መሰለ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በሌላ አመለካከት ወገን የሚጠረጠሩ ባለሀብቶች ተሰደዱ፣ ወይም እየከሰሙ መጡ…፡፡

  ጤነኛ ለማይመስለው የሀብት ክፍፍል ሌሎች ማሳያዎችን ለመጠቃቀስ ያህል በቢሊዮን ብሮች የሚያንቀሳቅሱ ከፍተኛ ኮንትራክተሮችና ብዙዎቹ የመስኩ ባለሀብቶች በአንዴ የከበሩ ዘመነኞች ሆኑ፡፡ በሶማሌ፣ በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉልና በሁመራ አካባቢ በሰፋፊ እርሻ ‹‹የተሰማሩ›› አብዛኞቹ ሥርዓቱ ውስጥ ለመሸጉ ሙሰኞች ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ለዘርፉ የተመደበውን ከፍተኛ ብድር ለከተማ ቤት፣ ለማሽነሪ ኪራይና ለንግድ ሥራ ያዋሉትም ትንሽ እንዳልሆኑ ታወቀ፡፡ ‹‹ሜካናይዝድ እርሻም›› የተወራለትን ያህል ሳይሆን ቀረ፡፡

  በአዲስ አበባና በዙሪያው ባሉ የኦሮሚያ ታዳጊ ከተሞች መሬት ተቸበቸበ፣ ተሸነሸነ፡፡ በዚህም ውስጥ በተለይ ካድሬዎችና የሥራ ኃላፊዎች በገፍ ሀብት አግበሰበሱ፡፡ ቢዘገይም ቡራዩ፣ ሰበታ፣ ለገጣፎና ሱሉልታን የመሳሰሉ ከተሞች ከንቲባዎችና የመሬት ላይ ኃላፊዎች ተጠያቂ ተደረጉ፡፡ ግን ከደረሰው ጥፋትና የሕዝብ ሀብት ንጥቂያ ጋር ፍፁም ሊጣጣም የማይችል ዕርምጃ ነበር፡፡

  በገቢዎችና ጉምሩክ መስክም ተመሳሳይ ነው፡፡ ዋነኛው ኮንትሮባንዲስት ከመንግሥት መዋቅር ውስጥ የወጣው ወይም የተሻረከው ሆነ፡፡ የቀረጥ ነፃ ውንብድናን ጨምሮ የታክስ ማጭበርበርና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ለጥቂቶች የተፈቀደ ‹‹ሕጋዊ ወንጀል›› መሰለ፡፡ በ2005 ዓ.ም. በሕገወጥ መንገድ የግንባታ ብረት አስገብተው በፀረ ሙስና ተከሰው የነበሩና ጉዳያቸው እስካሁን ለሕግ ያልቀረበ 112 የሚደርሱ ‹‹ጮሌዎች›› ውስጥ ብዙዎቹን የኮሚሽኑ ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› መጽሔትም አቅርቦዋቸው አይተናል፡፡

  ከእነዚህ ትልልቅ ዘረፋዎች በላይ አነስተኛ ሙስናው ዜጎችን እያማረረ ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ቢስፋፋም መብራት ለማግኘት ‹‹ጉቦ›› ተፈለገ፡፡ የመጠጥ ውኃ፣ ቴሌኮምና የውስጥ ለውስጥ መንገዱም ያው ሆነ፡፡ ፖሊስ፣ ትራፊክ ፖሊስ፣ ፍርድ ቤት የሚሰማው ድምፅ ቀስ በቀስ ርትዕና ፍትህን እየተወ ‹‹የነጋዴ ባህሪ መሰለ››፡፡ የጤና፣ የባህልና ቱሪዝም፣ የንግድ ቢሮዎች ከብቃት ማረጋገጫ፣ ፈቃድ ከመስጠትና ከማደስ ጋር መሞዳሞድን ለመዱ፡፡ ደንብ ማስከበር እንኳን በጥቅም የሚደለል መዋቅር ሆነ፡፡ ሕዝብ የሚገለገል ሳይሆን አገልጋይ እየሆነ የመጣበት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ አንሰራራ፡፡

  ይህ ችግር መጠኑና ዓይነቱ ይለያይ እንጂ በሁሉም አካባቢዎች እንደተንሰራፋ መንግሥት አውቋል፡፡ ገዥው ፓርቲም በጉባዔ ጭምር ደጋግሞ እያነሳ ተማምሏል፡፡ ግን ፈጣንና ሥር ነቀል ለውጥ አልመጣም፡፡ እንዲያውም መንግሥታዊ ማናለብኝነት እያቆጠቆጠ መጣ፡፡ ኃፍረትና ሕዝብ ማዳመጥም ተረሳ፡፡

  ለአብነት ያህል በመልካም አስተዳደር ዕጦትና በሥራ አጥነት የተንገሸገሸውን ወጣት ብሶቱን አዳምጦ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ፣ በጋራ ማስተር ፕላን ስም ከቦታው የሚፈነቀልበት ሥጋት ተደቀነ፡፡ እዚህ ላይ ፕላኑ ምንም ያህል አገራዊ ፋይዳ ቢኖረውም ሕዝቡ ከገባበት ሥጋትና ውዥንብር ሳይወጣ ለመተግበር መመኮሩ ‹‹የመንግሥታዊ ማናለብኝነት›› ውጤት ነው፡፡ በዚህ ላይ በአገርም ውስጥ ሆነ በውጭ ያለው ተቃዋሚ ኃይል የተደረገውንም ያልተደረገውንም እየጨማመረ ሕዝቡን ‹‹መሬትህ ተዘረፈ›› ሲል ቀስቅሶታል፡፡ ያኔ ከተማ፣ ገጠር ሳይል ለጥቅሙና ለመብቱ ተነሳ (በነገራችን ላይ በቀዳሚው የሕዝብ እምቢተኝነት አብዛኛው ሕዝብ ተሳትፏል ማለት ይቻላል)፡፡

  በአማራ ክልልም ሕዝቡ ‹‹የተገፋ›› እንዲመስለው የሚያደርጉ ብርቱ ዘመቻዎች በራሱ በገዥው ፓርቲና በመንግሥት እንዝላልነት (አውቆ የተኛ አካሄድ) ተፈጸመ፡፡ ለአብነት በሰሜን ጎንደር የተነሱ የማንነት ጥያቄዎች፣ የክልልና የወረዳ የወሰን ጉዳዮች ሲድበሰበሱ ከርመው የቀውሱ ዋነኛ ክብሪት ሆኑ፡፡ በሚያሳፍር ደረጃ በአፍሪካ ትልቅ የሚባሉ ተራራና ኪነ ሕንፃ ለሕዝብ በተበተኑ ሰነዶች የሚገኙበት ቦታ እየተቀየረ ተሠራጩ፡፡ ብሔርና ክልል የአሁኒቷ ኢትዮጵያ ዋነኛ መገለጫ በሆኑበት ጊዜ የልማት ሥርጭቱ ለኢፍትሐዊነት ማጣቀሻ ሆነ፡፡

  እነዚህና ሌሎች ጥቃቅን የሚመስሉ ክፍተቶች ሕዝብና መንግሥት እንዲቃቃሩ አደረጉ፡፡ ምንም እንኳን ይህንን ክፍተት ተጠቅመው አክራሪ የዳያስፖራ ፖለቲከኞችና ማኅበራዊ ድረ ገጾች ሕዝባዊ እምቢተኝነቱን ለማባባስ ቢሠሩም፣ የቀውሱ መነሻም መድረሻም የመንግሥት የተሃድሶና የለውጥ መንቀርፈፍና ቁርጠኝነት ማጣት ነው ለማለት ይቻላል፡፡

  ከላይ በስፋት የተንደረደርኩባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ልቦለዶች አይደሉም፡፡ ወይም በግል እምነት የተቀጣጠሉ የሥርዓቱ ጉድለቶች እንዳልሆኑም ለማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡ ይልቁንም ራሱ ገዥው ፓርቲና መንግሥት ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ ያስፈልገናል፣ ተሃድሶውን ወቅቱን ጠብቀን በእንጭጩ ባለማረማችን በሕዝብ ግፊት ተገደን የገባንበት ሆኗል፤›› ካሉ በኋላ በተለያዩ መድረኮች የተነገሩ ናቸው፡፡ ብዙዎቹም በትልልቁ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጭምር ተቀባይነት አግኝተው ‹‹እውን እስካሁን የት ነበርን?!›› እስከማለት አድርሰዋል፡፡

  ከሥርዓቱ ሰዎች ውጪም በአንድ ወቅት በኃላፊነት ላይ በነበሩ ሰዎች፣ ሚዛናዊ በሆኑ ታዛቢዎችና በምሁራን በቃልም በጽሑፍም የተነሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ሥርዓቱን ከድተው ወይም ተነጥለው የሄዱ የ‹‹ቀድሞ›› ባለሥልጣናትም ቢሆኑም ምንም እንኳን ለራሳቸው ወቅታዊ የፖለቲካ ትርፍ ሲሉ የሚለጥጡት ጉዳይ ቢኖርም፣ ችግሮቹን በተጨማሪ ማስረጃዎች እያደመቁ የሕዝቡን መከፋት አባብሰውታል፡፡

  ይህ ሁሉ በመሆኑ መንግሥት ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ላይ ነኝ እንኳን ቢል ያልረገበው የሕዝብ ቁጣ (በኋላ የጥፋት አካሄድ መላበሱ ባይቀርም) ተቀስቅሶ ብዙ ጥፋት ደረሰ፡፡ በግርድፍ መረጃ በ11 ወራት ብቻ ከ1,500 በላይ ዜጎችና የፀጥታ ኃይሎች ሕይወት አለፈ፡፡ በኦሮሚያ (ሰበታ፣ አምቦ፣ አርሲ ነገሌ፣ ሻሸመኔ፣ ባቱ፣ ነቀምት፣ ምሥራቅ ሐረርጌ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ…) በሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ በባህር ዳርና በምዕራብ ጎጃም ወረዳዎች፤ በደቡብ ክልል ኮንሶና ዲላ አካባቢ በሺዎች የሚቆጠሩ የግለሰብ ቤቶችና ድርጅቶች ወደሙ፡፡ የመንግሥት መዋቅሮችና ግምታቸው በቢሊዮን ብር የሚሰላ ኢንቨስትመንቶችና ኩባንያዎችም እንዳይሆኑ ሆኑ፡፡

  ይኼ ጥፋት መንግሥትን በአገር አቀፍ ደረጃ እስከ ስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (State of Emergency) ለማውጣት አስገደደ፡፡ ሕገ መንግሥቱን የተካ ‹‹ወታደራዊ›› የሚመስል የመንግሥት አስተዳደር በመዘርጋት ጥፋትና ሞቱ ቢቆምም፣ አሁንም ግን በአገሪቱ ላይ አሉታዊ ገጽታ እንዳረበበ ነው፡፡ በተለይ በሕዝቡ ውስጥ የፀጥታ ኃይሎች አዋጁን ለጥጠው እንዳይጠቀሙ፣ የዜጎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም የሚታይ ሥጋት አለ፡፡ በፖለቲከኞች በኩልም የመሰብሰብ፣ በሕጋዊ መንገድ የቅስቀሳ ሥራ መሥራትና የሐሳብ ነፃነት መገደብ እንደ ጉዳት ይነሳል፡፡ ከሁሉ በላይ ምንም እንኳ ሰሞኑን ማሻሻያ ተደርጎ ዕገዳ ቢነሳም፣ ዲፕሎማቶችና ቱሪስቶች ከዋና ከተማዋ 40 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውጪ መሄድ እንደማይችሉ ተደርጎ መነገሩ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ ነበር፡፡

  ይህ ነባራዊ ሀቅ ባለበት ሁኔታ አሁንም ገዥው ፓርቲና መንግሥት የ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ጉዳያቸውን የዘነጉት አይመስልም፡፡ በቅርቡ እንዳየነው ለማሻሻያና ለለውጥ ዕርምጃው አንድ ጅምር ሊባል የሚችል ሹም ሽር ተካሂዷል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልልና በፌዴራል መንግሥት ደረጃ በተካሄደ የካቢኔ አባላት ሹመት አዳዲስና በፖለቲካው ውስጥ ያልሰለቹ ፊቶች ታይተዋል፡፡ ምሁራን በርከት ብለው መሾማቸውም በሕዝቡ ውስጥ የተደበላለቀ ስሜትን ፈጥሯል፡፡ በቀጣዮቹ ቀናትም አማራ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች እንዲሁም ታዳጊዎቹ ቆላማ ክልሎችም የሚያደርጉት ሹም ሽር እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡

  አሁን በሕዝቡ እየተነሳ ያለው ‹‹ተጠየቅ›› ግን አንዱ ይህ ሹም ሽር እስከ ታችኛው የመንግሥት እርከን ታስቦበት ይወርዳል ወይ? የሚለው ነው፡፡ በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን በመሰሉ በአድርባይነትና በሙስና የተለወሱ ብሎም ሕዝብ ያማረሩ መዋቅሮች እንዴት ሊታደሱ ይችላሉ? የሚል ጉጉት አለ፡፡ በሌላ በኩል እስካሁን በተካሄዱ ግምገማዎች፣ ለሕዝብ ጭምር ይፋ በተደረጉ የብልሹ አስተዳደሮች መፈጠር ማሳያ ጥናቶች የተነሱ ኃጢያቶችና የተንቆረቆሩ ‹‹ሒሶች›› ማረፊያቸው የት ነው? ባለቤታቸውስ እነማን ናቸው? እንዴት ተጠየቁ? ምን ዕርምጃና እርምትስ ተወሰደ? … የሚል ብርቱ ጥያቄም ይነሳል፡፡

  በቀጣዩ ክፍል ሁለት ምልከታዬ በተለይ ኢሕአዴግን በመሠረቱት አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ውስጥ ከተነሱ ሒሶች አንፃር ተሃድሶውን ራሱ ለመገምገም እሞክራለሁ፡፡ ሊወሰዱ የሚችሉትን ዕርምጃዎች ለማመልከትም ይሞከራል፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡  

           

           

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...