Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ተሟገትየመንግሥት የሹመት ራሱ በጥልቅ ታድሷል?

  የመንግሥት የሹመት ራሱ በጥልቅ ታድሷል?

  ቀን:

  በገነት ዓለሙ

  የ2008 ዓ.ም. መሰናበቻ ዋነኛው የአገር ፖለቲካ አጀንዳ በኢሕአዴግ ‹‹በጥልቀት መታደስ›› ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የኢሕአዴግ ምክር ቤት ከነሐሴ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ባደረጓቸው ስብሰባዎች የሰጧቸው መግለጫዎች ይኼንን የ‹‹በጥልቅት መታደስ›› ውሳኔ የሚገልጹ ነበሩ፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ሌሎች የድርጅቱ ነባር አባላት አከታትለው የሰጡዋቸው ማብራያዎችም ይኼንኑ ‹‹በጥልቀት የመታደስ›› አስፈላጊነት የሚያብራሩ ነበሩ፡፡

  በእነዚህ ውሳኔዎች ማብራሪያዎች መሠረት ፓርላማው እስከሚሰበሰብና ከተሰበሰበም በኋላ ሲለሚወሰዱት የከፍተኛ አመራር የሹመት ቦታዎች ምደባ፣ ልዩ ትኩረት የሚሹ የቁልፍ ተቋማት ሹመት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የመቆጣጠር አቅም ስለማሳደግ፣ በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ከሚወዳደሩ ዕጩዎች መካከል አብላጫ ድምፅ ያገኘ ዕጩ አሸናፊ የሚሆንበትን የምርጫ ሥርዓት ለማሻሻል በ‹‹ጥልቀት የመታደሱ›› የዕቅዱ አካል እንደሆኑ ተነግሮናል፡፡

  አገራችን ውስጥ ምሬት ከፍ እያለ ንብረት እስከማጥፋት የተቆጣና ኢሕአዴግን ውረድልኝ እስከማለት የደፈረ ተቃውሞ ማስገምገም የጀመረው ከኅዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ቢሆንም፣ ለኢሕአዴግ ‹‹በጥልቀት መታደስ›› ዋናው መነሻ ይኼው ተቃውሞ ቢሆንም፣ መስከረም መጨረሻ ላይ የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሕግና ዕርምጃ ግን ማንም የጠበቀና የጠረጠረ አልነበረም፡፡ ፓርላማው ጭምር ያፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሕጉ በፀናበት፣ መንግሥትም የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣን ባገኘበት ወቅት ‹‹በጥልቀት የመታደስ›› አካል ናቸው ከተባሉት መካከል እንደገና ይፈተሻል የተባለውን የፌዴራል መንግሥት የከፍተኛ አመራር የሹመት ቦታዎች ምደባን አይተናል፡፡

  በዚያው በራሱ ‹‹በጥልቀት መታደስ›› ማዕቀፍ ውስጥ የካቢኔው የሹመት ቦታዎች ምደባ እንደገና ይፈተሻል የተባለበት ምክንያት ከሌሎች መካከልና ለምሳሌ ‹‹ሚኒስትርነት መታደስ አይደለም፡፡ በይገባኛል የሚገኝ ቦታ አይደለም፡፡ ሚኒስትርነት የሥራ ቦታ ነው፡፡ ከየትም ይምጣ (ከድርጅትም ከድርጅትም ውጪ ይምጣ) የሚሠራ ብቃት ያለው ሰው›› የሚይዘው ቦታ ነው ስለተባለ ነው፡፡

  ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም ባሉበት የቀጠሉትና አዲስ የተሾሙት ሹማምንት ሚኒስትሮች፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት ናቸው፡፡ መስተዳድር፣ ካቢኔ የሚባለውም ይኸው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ከፍተኛ አስፈጻሚና አስተዳደራዊ የሥልጣን አካልም እሱው ነው፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላትን ከሁለት ምክር ቤቶች አባላት ወይም ለሥራው ብቃት ካላቸው ሌሎች ግለሰብ መካከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዕጩነት አቅርቦ ሹመታቸውን ያስፀድቃል፤›› የሚለው ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ ሁለቱም ምክር ቤቶች የሚባሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ናቸው፡፡ ብቃት ያላቸውን ሚኒስትሮች በፓርቲውም፣ በሁለቱም ምክር ቤቶች ውስጥም ለማፈላለግ ከምክር ቤቶቻችን ከፓርቲው ውጪም ብቁ ሚኒስትሮችና ባለሙያዎችን ለመመልመል እስከ 2008 ዓ.ም. ክረምት ‹‹ጥልቅ መታደስ›› መጠበቅ ባላስፈለገ ነበር፡፡

  በዚህ ላይ ሚኒስትሮች አስፈጻሚዎች ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱን ማክበር ብቻ በጥልቀት መታደሱን በግድ ካስከተለው አደጋ ያድን ነበር፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የመንግሥቱን የሕግ አስፈጻሚ አካል የሚያደራጀውና የሚመራው በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘው ድርጅት (ወይም ያገኙት ጣምራ ድርጅቶች) መሆኑ የታወቀ ነው፡፡  የፌዴራልም ሆኖ የክልል መንግሥታት ሥራ አስፈጻሚዎች የሕዝብን የመታመን ክብር ተጎናጽፈው፣ ከበሬታንና ተሰሚነትን አግኝተው የኢኮኖሚና የዴሞክራሲ መርሐ ግብሮችን ለማሳካት እንዲችሉ፣ ለሕዝብ ጥቆማ ጭምር ቦታ በሰጠ አሠራር በሕዝብ ዘንድ የታመነባቸውን ከተቃዋሚም ከፓርቲ ፖለቲካ ውጪ ከሆኑትም ውስጥ የሚያካትት የምልመላና የሹመት እንቅስቃሴ እናያለን ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፡፡ ማክሰኞ ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በቀጥታ የተላለፈው ጉዳይ የቀረበበት የፓርላማ ውሎ ግን ይኼንን ገና አረጋግጦ አልመለሰልንም፡፡

  ‹‹በጥልቀት ከመታደስ›› አኳያም ሆኖ ‹‹በዕጩነት አቅርቦ ሹመታቸውን ያስፀድቃል›› ከሚለው ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 74(2) ተራ የአሿሿም ሥነ ሥርዓት አንፃር የዕጩ ተሿሚዎች የፖለቲካ ማንነት እንኳን ለእኛ ለፓርላማውም አልተገለጸም፡፡ ከዚህ በፊት በተለመደው አሠራር በዕጩ ተሿሚዎች አጭር የሕይወት ታሪክ ውስጥ ከትምህርት ደረጃ ጋር የቅርብ የነበረው ‹‹የፖለቲካ አመራር›› ታሪክ በዚህ ሹመት ውስጥ ፈጽሞ አልተነሳም፡፡ በዚህ ምክንያት ኢሕአዴግ ብቃትና የሚሠራ ሰው ፍለጋ ከራሱ ከድርጅቱ፣ ከአጋር ድርጀቶች እንዲያም ሲል ከፓርቲ ፖለቲካ ውጪ ያደረገውን ጥረትና ልፋት እንኳን አላሳየንም፡፡

  የተሿሚዎቹን የራሳቸውን ልብ የሚያሻቅል ሌላም ጉዳይ በአሿሿም አሠራሩ ውስጥ ነበር፡፡ ሰላሳ አባላት ካሉት ካቢኔው ውስጥ ባሉበት እንዲቀጥሉ የተደረጉት ዘጠኝ ብቻ ናቸው፡፡ የዝቅጠት አደጋ አጋጥሞኛል፣ መንግሥትና ፓርቲያችን የመንግሥት ሥልጣንን ሕዝብን ለመጥቀም ሳይሆን የግል ጥቅምን ለማሳደድ የሚያስችል ቅኝት መመልከት ጀምረናል ብሎ ለጥልቅ መታደስ የተነሳ፣ በዚህም መሠረት የሹመት ቦታዎችን ምደባ እንደገና የፈተሸ መንግሥት፣ ከቦታው ያነሳቸውንና በሌላ የተካቸውን ሁሉ ላልተገባ የጅምላ ሐሜት ዳርጓቸዋል፡፡፡ ይኼ ደግሞ ለአዲስ ተሿሚዎችም የማይመች የነግ በእኔን ጥርጣሬ ከአሁኑ የሚዘራ አሠራር ነው፡፡ አሠራሩ በአጠቃላይና በገዛ ራሱ ምክንያት ትክክል አይደለም፡፡

  ሕግና ደንብ እንዳመቸ የሚጣሉና የሚነሱበትን የገዢዎችን ተግባር በፅናት መዋጋት ያስፈልጋል፣ ማንም ሰውና ባለሥልጣን የሚፈጽመው ሕገወጥነትና አጥፊነት ከሥልጣን ሊወርድ ብቻ ሳይሆን ሥልጣን ላይ እያለም መጠየቅ መቻል አለብን የምንለው ሳይጠየቁ መኖር ከተቻለ ችግሩ ተደጋግሞ ላለመፈጸሙ ዋስትና ስለሚጠፋ፣ ችግሩ እንዳይከሰት ጠባቂው፣ ሲከሰትም አጋላጩና ተፈራጁ እንዳይኖር ስለሚያደርግ ነው፡፡ ከሥልጣን የተወገዱትን ወይም የተነሱትን የቀድሞ ባለሥልጣናት አሸኛኘትም ይኼንን ጎዶሏችንን የሚያጠናክር ለሌላም ብዙ አደጋዎች የሚያጋልጥ ነው፡፡

  በጥልቀት የመታደስ የኢሕአዴግ እንቅስቃሴ ሌላው የዘመቻ ግንባር የተወካዮች ምክር ቤትን የቁጥጥር ብቃት ማሳደግ ነው ሲባል ሰምተናል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በፌዴራልም በክልልም መንግሥታት ከፍተኛውና የሁሉም የበላይ የሥልጣን አካል ምክር ቤቶች መሆናቸውን ይደነግጋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 74(2) ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላትን ከሁለት ምክር ቤት አባላት ወይም ለሥራቸው ብቃት ካላቸው ከሌሎች ግለሰቦች መካከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዕጩነት አቅርቦ ሹመታቸውን ያፀድቃል ሲልም፣ የምክር ቤቱን የበላይነትና ሥልጣን በዚህ ዘርፍ ዘርዝሮ መደንገጉ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ዕጩ ማቅረብ ነው፡፡ ዕጩ የማቅረብ ሥልጣኑም ሌሎች ዝርዝር ግዴታዎችን ይጥልበታል፡፡ ምክር ቤቱ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ፣ ሕዝብ እያየው እየሰማው የሕዝብንም ልብ የሚረታ ውሳኔ መስጠት ይችል ዘንድ፣ ሁሉንም እውነቶችና መረጃዎች ሁሉ ማወቅ አለበት፡፡ ከዚህ ሁሉ አኳያ ኢሕአዴግ ራሱ በሚለው ‹‹በጥልቅ የመታደስ›› ጎዳና ላይ መረማመዱን እያሳየን ነው ለማለት እንቸገራለን፡፡ በዚህ ዓይነት አሠራር ደንገጥ አለማለትም ‹‹በጥልቀት መታደሱ›› በግንባር ቀደምትነት የሚያቀነቅነውን የምክር ቤቱን የተቆጣጣሪነት ሥልጣን ማጠናከር የሚለውን ዓላማ ይስታል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሕገ መንግሥቱን የፓርላማ ሥልጣን ይጥሳል፡፡

  በእዚህም ሆነ በሌላ ማንኛውም ጉዳይ የመንግሥት ከሽፍንፍን አሠራር መውጣት ከማንም በላይ የሚጠቅመው መንግሥትን ነው፡፡ በመተቻቸትም ሆነ በመዘረጣጠጥ ጭንቅ ተጠምዶ ሁሉንም ነገር (በአቶ መለስ ሞት ጊዜ እንዳየነው ሐዘንንም ጭምር) ሚስጥራዊ ከማድረግና በድርጅታዊ መንገድ ከማቀናበር፣ እንዲሁም የተቃውሞ፣ የክስና የውንጀላ ንፋስ ከማሳደድ አዙሪት የመላቀቁ ዕድል ይከፍትለታል፡፡ መንግሥት ሁሉንም እውነትና እውነቱን ሁሉ ሊነግረን የሚገባው ስለሚጠቅመው ብቻ ሳይሆን ግዴታውም ስለሆነ ነው፡፡ በሹም ሽሩም ጉዳይ ምክንያቱን መግለጽና ለሕዝብ ማብራሪያ መስጠት የሥራ አስፈጻሚነት ግዴታው ነው፡፡ የተወካዮችም ምክር ቤት መስተዳድሩን አቁሞ ገትሮና አጥብቆ መጠየቅ ኃላፊነቱ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ጠያቂነትና ተጠያቂነት እስከሌለ ድረስ ደግሞ ሥልጣን ላይ ማንም ተቀመጠ ማን ለብቃት መለኪያ፣ ለጉዳት መከላከያ፣ ለዝርፊያ መግቻ አይገኝለትም፡፡

  የኢሕአዴግ ‹‹በጥልቅ የመታደስ›› እንቅስቃሴ ግቡን እንዲመታ የምንነጋገርበት፣ የከፍተኛ ባለሥልጣናት የአሿሿም ሥርዓትና አሠራር ወግ እንዲኖረው ለማድረግ ሕገ መንግሥቱን ከማክበር በላይ የሚጠየቅ ሌላ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ግዳጅ የለውም፡፡

  ለምሳሌ ከ547 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል ከዚህ በፊት እንደነበረው ለመድኃኒት ያህል እንኳን አንድም የግልም ሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆነ እንደራሴ የለም፡፡ 502 እንደራሴዎች የኢሕአዴግ ድርጅቶች አባላት ናቸው፡፡ የተቀሩት 45 አባላት ደግሞ የኢሕአዴግ አጋር ፓርቲዎች አባላት ናቸው፡፡ እንዲህ ያለ የምርጫ ድል ከጊዜ ወዲህ ኢሕአዴግን ራሱን ጭምር ሌላው ቢቀር ማሳሰቡ አልቀረም፡፡ ከዚህም የተነሳ በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች መካከል አብላጫ ድምፅ ያገኘ ተወዳዳሪ አሸናፊ የሚሆንበት በሕገ መንግሥት አንቀጽ 54/2/ የተደነገገውን የምርጫ ሥርዓት አሻሽላለሁ እስከማለት የደፈረ ሥራም ‹‹በጥልቀት መታደሱ›› ውስጥ መካተቱን ሰምተናል፡፡ በነሐሴ ወር ውስጥ በቴሌቪዥን መግለጫ የሰጡት የኢሕአዴግ ነባር አባላት እንዳሉት እውነትም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዝብ ተወካዮች መሆን አለበት፡፡ በአንድ ፓርቲ ብቻ መያዝ አይገባውም ከተባለ ከምርጫ ሥርዓት ማሻሻል በላይ፣ ከእሱም የበለጠ ምናልባትም ከዚህ ይልቅ አሁንም ሕገ መንግሥቱን ማክበር የመሰለ ዛሬም ያልተወጣነው ግዳጅ አለብን፡፡ በምርጫ ሥርዓቱ ማሳሰብ ሕመምን መደበቅ ነው፡፡

  የምክር ቤቱ አባላት ዛሬ ሁሉም የኢሕአዴግና የአጋሮቹ የፓርቲ አባላት ቢሆኑም፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54/4/ መሠረት የመላው ሕዝብ ተወካዮች ናቸው፡፡ ተገዢነታቸውም ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝቡና ለህሊናቸው ብቻ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን የማክበር ጉዳይ ከተረጋገጠ፣ የምክር ቤት አባላት ተገዥነት ለህሊናቸው መሆኑ ካልተነጠቀ መንግሥት የመሠረተው ፓርቲ አስቀድሞ በወሰደው ውሳኔ መታሰር አይኖርባቸውም፡፡ አሁን ባለው የምክር ቤቱ አባላት ፍጥርጥርና ቅንብርም ቢሆን የቀረበውን ሹመት ለማፅደቅም ሆነ ላለማፅደቅ፣ ለመመርመርም ሆነ ለማንጠርጠር የሚከለከል ነገር የለም፡፡ የሚከለከለውና የከለከለው የፓርቲውን ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ በላይ ያደረገ፣ በህሊናቸው ዳኝነት የመመራት የሕዝብ ተወካዮችን ሕገ መንግሥታዊ መብትና ነፃነትን በፓርቲው የዕዝ ቁጥጥር ሥር ያስገባ አላግባብ የነገሠ አሠራር ነው፡፡ ኢሕአዴግ ይኼንን ኢሕገ መንግሥታዊነት መታገል አለበት፡፡ ኢዴሞክራሲያዊነትም እንዲሁ፡፡ በቅርቡ ሬድዮ ፋና ባዘጋጀው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውይይት ወቅት ኢሕአዴግ ለውጭ እንጂ በውስጡ ዴሞክራሲያዊ ነው፣ እንዲህ መሆንም ይችላል ሲባል ሰምተናል፡፡ ኢሕአዴግም ‹የውስጥ አልጋ የውጭ ቀጋ› ብሎ ባህርይ የለም ወሳኙ ውስጠ ፓርቲ ተፈጥሮዬ ነው ብሎ ዴሞክራሲያዊነቱን ተከራክሯል፡፡

  እውነቱ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ የኢሕአዴግ የድርጅቱና የአባል ድርጅቶቹ አቋም ፖሊሲና አቅጣጫ አድራጊ ፈጣሪ የድርጅቱ አመራር ነው፡፡ በአመራሩ ውስጥም ቢሆን የተሻለ ሐሳብና የተሻለ ችሎታን በውይይትና በክርክር የማንጠር ወይም በድምፅ የመለየት እስትንፋስ እንዳለው አይተን አናውቅም፡፡ ሁሉም ነገር አስቀድሞ የሚያልቅ እንጂ ውጤቱ ምን ይሆን? ማን የበለጠ ድምፅ ያገኝ ይሆን? የሚባል ጨዋታ እንኳን አለኝ ብሎ አያውቅም፡፡ ‹‹በጥልቀት መታደስ›› እንቅስቃሴው መሠረት እንደገና የተፈተሸው ‹‹ዝርዝር ዕቅድ፣ ዝርዝር አሠራር፣ ዝርዝር ፈጻሚ አካላት የተሰየመለት፣ የጊዜ ሰሌዳ የወጣለት›› የተባለው የከፍተኛ አመራር የሹመት ቦታዎች ምደባ ጉዳይ ከዚህ የኢሕአዴግ አድራጊ ፈጣሪነት ውጪ አልተከናወነም፡፡

  እስካሁን እንደምናውቀውና እንደለመድነው የከፍተኛ ባለሥልጣናት የሹመት ቦታዎች ምደባ፣ ድርሻ ድርሻን ባከፋፈለው የኢሕአዴግ ቀመር መሠረት የሚፈጸም ነው፡፡ የእስካሁኑ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የነበው ልምድ እንደሚያሳየው የፌዴሬሽን ምክር ቤት መሪነት፣ ጠቅላይ ሚኒስትርነት፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባነት፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትነትና ምክትል ፕሬዚዳንትነት የየትኛው አባል ድርጅት ሰው ምድብ ሆኖ እንደቆየ ብዙ ሰው የሚያውቀውና የሚለየው ነው፡፡ ምድቡ ላይ ቀደም ሲልም ሆኖ አሁን በዚህ ሹመት ውስጥ የታየው ዓይነት ለውጥ የተደረገውም የአመራር ቀመሩን መለወጥ ስላስፈለገ እንጂ፣ የምክር ቤቱን ወንበሮች የተቆጣጠሩት ኢሕአዴጎች ከብዙ አማካሪዎች ውስጥ የተሻለ ማነው ብለው የየግል ምርጫ አድርገው አለመሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

  አባላቱ በምክር ቤቱም ይሁን በፓርቲው ውስጥ እንዲመርጡና እንዲደግፉ ለቀረበላቸው ሐሳብ እጅ ከማውጣት የተሻለ ሚና የላቸውም፡፡ ከአመራሩ በኩል የቀረበውን ሐሳብ እቃወማለሁ፣ ከእሱ የተለየ ሐሳብ አለኝ የሚል ተከራካሪ ኢሕአዴግ ውስጥ ማግኘት ተዓምር መጠበቅ ነው፡፡ ከሞላ ጎደል ሁሉም አመራሩን ከማድነቅና ቢበዛ የማብራሪያ ጥያቄ ከመጠየቅ የማያልፉ ለፓርቲው ውሳኔ የመገዛት ግዴታ ያለባቸው ናቸው፡፡

  በፓርቲውና በምክር ቤቱ አባላት መካከል ያለውን ግንኙነት አጋንነኸዋል ብሎ የሚጠረጥር ካለ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 በምዕራፍ 26 ከአንቀጽ 202 እስከ 210 ድረስ ስለፓርቲ ተጠሪዎች የተደነገገውን (በ1999 ዓ.ም. የምክር ቤት ደንብ ጭምር የነበረ) እንዲመለከቱልኝ እጋብዛለሁ፡፡ እዚህ ሕግ ውስጥ የሕዝብ ወካዮች ወይም እንደራሴዎች የሚታወቁት ‹‹ፓርቲውን በመወከል›› ነው፡፡ ‹‹ፓርቲውን በመወከል በምክር ቤቱ የተለያዩ ኮሚቴዎች ውስጥ የሚሳተፉ›› ናቸው፡፡ ‹‹ፓርቲውን በመወከል በምክር ቤቱ ስብሰባ ሐሳብ የሚያቀርቡ የፓርቲ አባላት ስም ዝርዝር ለምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ያስተላልፋል›› ማለት የመንግሥት ተጠሪ (የገዢው ፓርቲ ተጠሪ) ሥልጣን ነው፡፡    

  እስካሁን የተነጋገርንባቸውን የከፍተኛ አመራር የሹመት ቦታዎች ምደባ ጉዳይ መልሰን በጥያቄ መልክ ብናዋቅረው፣ የመስተዳድሩ ወይም የካቢኔው አባላት ሹመት የሕዝብ ከበሬታና ተሰሚነት አግኝተው የኢኮኖሚና የዴሞክራሲ መርሐ ግብሮችን ለማሳካት የሚችሉ፣ ለሕዝብ ጥቆማና ተሳትፎ ቦታ የሰጠ፣ ከተቃዋሚም፣ ከፓርቲ ፖለቲካ ውጪም በሕዝብ ዘንድ የታመነባቸውን ባለሙያዎች ያካተተ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ማቅረብና መመለስ ግድ ያደርግብናል፡፡ ለሕዝብ ጥቆማና ተሳትፎ ቦታ የሰጠ የመሆኑ ጉዳይ ከሁሉም በፊት ውድቅ የሚደረግ ነው፡፡ የዚህ ምክንያት በመንግሥትም ሆነ በፓርቲው በኩል ይኼንን አድርገናል አልተባልንም፡፡ አድርገናል ቢሉንም ይኼንን የሚያሳምን ሥርዓት የለንም፡፡ አሠራሩን ሲሞክሩትም አላየንም፡፡ ሌላው ቢቀር በርካታዎቹ ተሿሚዎች የመጡባቸው የትምህርት ተቋማት ለዚህ ተሳትፎና ጥቆማ የታደሉ አይደሉም፡፡ የዚህ ምክንያት ዩኒቨርሲቲዎች የአካዳሚ ነፃነታቸውን ማስከበር ያልቻሉ ገዢዎች በሚፈቅዱትና በሚወዱት ያልተገደበ ነፃ እንቅስቃሴ የማይካሄድባቸው ልፍስፍስ ተቋማት በመሆናቸው ነው፡፡ የአዳዲሶቹ ሹማምንት ምንጭ ከገዢው ፓርቲ ውጪም ስለመሆኑ ከተቃዋሚዎች፣ ከፓርቲ ፖለቲካ ውጪም ስለማካተቱም በጭራሽ አልተነገረንም፡፡

  የሚያሳዝነው በአገራችን የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ ከሞላ ጎደል በሁሉም ዘንድ የተከበሩትና የታፈሩትን፣ የዓለም የጤና ድርጅት የመሰለ ታላቅ ተቋም በዋና ዳይሬክተርነት ለመምራት የሚወዳደሩትን የቀድሞውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጭምር ያለምንም ማብራሪያ መግለጫ መሰናበታቸውን ማየታችንና ለሐሜት ያጋለጠ አሠራር ጭምር መመስከሪያችን ነው፡፡ በጥቅምት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ሰኞ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ በተሰማው የሬድዮ ፋና ዜና መሠረት አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ አዲሱን ሥራቸውን መጀመራቸውን፣ አዲሱን  ሚኒስትር ከተቀበሏቸው መካከልም የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም አንዱ መሆናቸው ተነግሮናል፡፡

  በዚህ ልክና መልክ ነባር ባለሥልጣናትን መሸኘትና ማንሳት፣ በነበሩበት ሥልጣን ላይ ያልቀጠሉትን የቀድሞ ሹማምንት፣ ‹‹በጥልቀት መታደሱ›› ቋንቋ ‹‹ኢሕአዴግነትን የሥልጣን መቆናጠጫ የጥቅም መሣሪያ አድርጎ›› የሚያይ ብሎ ከጠራቸው ስሞች መካከል መፈረጅ ማለት አይደለም ወይ? ይኼንን ጥያቄ ከነትርጉምና አንድምታው ኢሕአዴግ ‹‹እሱን ለእኔ ተውት›› ይለን ይሆናል፡፡ ካሰናበትኳቸው፣ ከሥልጣን ካነሳኋቸው የገዛ ራሴ ሰዎች ጋር በድርጅታችን ባህልና ሕግ መሠረት እንተዋወቃለን ሊለን ይችላል፡፡ ችግራችንም ይኼው ነው፡፡ የኢሕአዴግም ችግር ይኼው ነው፡፡ የፓርቲውን ሕግ ከሕገ መንግሥቱ በላይ የማድረግ ችግር ነው፡፡

  የአገራችን ሥር የሰደደና ከኅዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የገነፈለው ችግር የሥር ምክንያት የመንግሥት ሥልጣንና ኢሕአዴግነትን የግል ጥቅም መሣሪያ ማድረግ ነው ብሎ በጥልቀት የመታደሱ እንቅስቃሴው አካል አድርጎ፣ ‹‹ሚንስትርነት በይገባኛል የሚያዝ ቦታ አይደለም›› በማለት ነባሮችን ያራገፈ መንግሥት፣ ለአዲስ ተሿሚዎችም ለሕዝብም ትምህርት ሊሆን ይችል የነበረውን ግልጽነትን ነፍጎናል፡፡ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት፣ ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጎድል ተጠያቂ ይሆናል የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ተፈጻሚነት ወደጎን አልፎታል፡፡ ለዚህ ሁሉና ለእንዲዚህ ዓይነቱ ‹ዝምታ›› ወይም ሚስጥራዊ አሠራር ማብራሪያና ምክንያት ተደርጎ የሚቀርብልን፣ በተለይም በአቶ መለስ ዜናዊ መታመም ጊዜ እንደሆንነውና እንደተነገረን የድርጅቱ የአሠራር ባህል ነው፡፡

  መታመማቸው የተደበቀው፣ መታመማቸውን ከሦስተኛ ሰው የተሰማው፣ መታመማቸውም ከተሰማ በኋላ ከዚህ በላይ ማወቅ አያስፈልግም የተባለውና ከዚያም ወዲህ ሞታቸው ሲነገር ገዥውንም ተቃዋሚውንም ያስገረመው የኢትዮጵያ ሕዝብ የበለጠ ግልጽነትን የሚጠይቀው ‹‹በውለታ መመለስ›› ደንብ አይደለም፡፡ ፓርቲው የሚኮራበትን ነባር ባህል የሚገረስስ፣ በመንግሥት ላይ የአሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት የሚያውጅ፣ የሕዝብን የማወቅ መብት የሚያቋቁም ሕገ መንግሥት ስላለ ነው፡፡ የእዚህ ፋይዳ ደግሞ ድርብ ድርብርብ ነው፡፡ መንግሥትን ከሐሜት ነፃ ያወጣዋል፡፡ መንግሥት የሚሾመው ለሕገ መንግሥቱ የሚገዛ ሳይሆን የጀርባ ትዕዛዝ የሚቀበል፣ ምሪት ሲስት ‹‹ዋ›› የሚባል፣ አልረባ ካለም ታምሜያለሁ ወይም ታሟል አስብሎ ዘወር እስከማድረግ አሻንጉሊት የሚሆን ሰው ነው ከሚለው ሕዝብ ውስጥ በሹክሹክታ ከገለማ ሐሜት ያድነዋል፡፡ እንዲህ ያለውን ሐሜት ከሕዝብ ስሜት ማራገፍ የሚቻለው፣ ተመሳሳይና ሌሎችም መሰል አስተሳሰቦች ኅብረተሰቡ ውስጥ መርዝ የማበጀት አቅማቸውን ማክሸፍ የሚቻለው የአሿሿም ሥርዓቶችን በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ መሠረት ስናከናውንና አብሮም ችግሩ እንዳይከሰት፣ ጠባቂ ሲከሰትም የሚያጋልጥ ሥርዓት ስንገነባ ነው፡፡

  የመንግሥትን የአሿሿም ትግልና ጥረት ታጥቦ ጭቃ የሚያደርገው ሌላው የአገር ችግር በሲቪል ሰርቪሱና በፖለቲካ ተሿሚዎች መካከል ልዩነት ያቋቋመ ሥርዓት አለመገንባታችን ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ለሁለት ዓመታት ያህል ከቆየ የምርጫ ዘመቻ በኋላ ባለፈው ማክሰኞ የተጠናቀቀው የአሜሪካ ምርጫ ነው፡፡ የአሜሪካ የዴሞክራቲክ ፓርቲና የሪፐብሊካን ፓርቲ ከአውታረ መንግሥቱ (ስቴት) ጋር ልዩ ትስስር በማበጀትና ባለማበጀት ምክንያት (ሥልጣን ማንም ያዘ ማን) ተጎጂና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ምክንያትና ሁኔታ የለም፡፡ ሁለቱም በሕግና በምርጫ ወጪና ወራጅ በመሆን ረገድ አይበላለጡም፡፡ በኢትዮጵያ ገዥውን ፓርቲ በዚህ ዓይነት መመዘኛ ከተቃዋሚዎቹ ጋር እኩል አድርጎ ማስቀመጥ በጭራሽ አይቻልም፡፡

  አሜሪካ ከዚህ በፊት በነበሩት ምርጫዎች የሆነውን አይተናል፡፡ ኦባማን ከሶሻሊዝም፣ ከአክራሪነትና ከጥቁር ዘረኝነት ጋር ለማያያዝ ተሞክሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አሜሪካ አልተወለደም፣ ስለዚህም ለሥልጣን አይበቃም ተብሎ ነበር፡፡ ኦባማ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ያኔ ያልሆነ ስም ሲሰጡት የነበሩት ሰዎች እንጠቃለን ብለው አልፈሩም፡፡ ሥልጣን ላይ እያለ ለምርጫ ሲወዳደርም እጅግ በጣም ውድ የሆነውን የግል ኢንሹራንስ መጠቀም የማይችለውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚሸፍን መንግሥታዊ የሕክምና ዋስትና ይኑር የሚል ኦባማ ኬር የሚባል (የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የትርፍ ጥቅም የሚነካ) የጤና ዋስትና በማምጣቱ የተነሳበት ተቃውሞ፣ ፍርኃት የሌለበት ከሒትለርና ከስታሊን ጋር እስከማመሳሰል የተስፈነጠረ ነበር፡፡ በሒላሪ ክሊንተንና በዶናልድ ትራምፕ መካከል የተካሄደውና ለኦባማም የተረፈው ክስ፣ ስድብና ማዋረድ በአገር ‹‹ክህደት ወንጀል›› ሁሉ የተሰየመ ነበር፡፡ ከሩሲያ ‹‹ጠላትነት›› ጋር እስኪጠላለፍ ድረስ የከፋውና የተካረረው፣ ብዙ ያዘራረጠውና ብዙ ጭቃ ያወጣው የምርጫ ዘመቻና ምርጫው ተጠናቆ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ ኑሮ ያለፍርኃት ቀጠለ፡፡

  በእኛ አገር የዚህ ዓይነት የከረረ ቅዋሜ ውስጥ ቀርቶ እውነት እውነቱን፣ ልክ ልኩን እናገራለሁ የሚል ቢኖር በመንግሥት እጠቃለሁ በሚል ፍርኃት ሲሳደድ መክረሙ የማይቀር ነው፡፡ ሌላውም ሰው ይሰጋል፣ ይሰጋለታል፡፡ ከገዥው ፓርቲ ጋር ለተጣመደም ሆነ በተቃራኒ ለቆመ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ወይም አዳራሽ ለመከራየት መፍራትና እምቢ ማለት የመጣው ከዚሁ ነው፡፡ ገዥውን ፓርቲ የሚያስቀይም ነገር ባደርግ በሆነ መንገድ ችግር ሊደርስብኝ ይችላል የሚል ፍርኃት የመጣው መንግሥታዊ የፀጥታ ኃይሉ ለየትኛውም ቡድን ታማኝ አለመሆኑ ወይም መሆን እንደሌለበት ሰው ስላላወቀ አይደለም፡፡ ለፓርቲ ጽሕፈት ቤት የሚሆን የኪራይ ቤት ቅድሚያ ይሰጠኝ፣ ወይም ለፓርቲ ጽሕፈት ቤት መሥሪያ የከተማ ቦታ ከሊዝ ውጪ ይሰጠኝ ብሎ ለመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲም ሆነ ለከተማው አስተዳደር ማመልከት ኢትዮጵያ ውስጥ ታላቅ ስላቅ ማስመዝገብ የሚሆነው ሕገ መንግሥቱ ስለማይፈቅድ አይደለም፡፡ ይኼንን መብት (አሁን መብት መሆኑ ቀርቶ ልዩ ዕድል ልዩ ፀጋ የሚሆነውን ልዩ ጥቅም) አግኝተው መንግሥት ቤት ገብተው፣ ቤት ሠርተው የሚኖሩና የሚሠሩ ፓርቲዎች እንዳሉ ቢታወቅም ጉዳዩ ግን የማይወራ የማይነሳ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

  ቅድም ስለአሜሪካ ስናወራ የአሜሪካ ሁለቱም ፓርቲዎች ከአውታረ መንግሥቱ ጋር ልዩ ትስስር በማበጀትና ባለማበጀት ምክንያት ተጎጂና ተጠቃሚ አለመሆናቸውን፣ ሁለቱም በሕግና በምርጫ ወጪና ወራጅ በመሆን ረገድ አይበላለጡም ብለናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የችግር ምንጭ አንድ ቡድን እጅ የገባ መንግሥት (ገቨርንመንት) ከመሆን በላይ ዓምደ መንግሥት (ስቴት) ይሆናል፡፡ ገዥው ፓርቲ ዕቅድና ፖሊሲውን በንቃት የሚያስፈጽም የሰው ኃይል ለማብዛት ያደረገው ትግል የመንግሥቱን መዋቅርና አውታራት ሁሉ በአባላትና በካድሬዎች እንዲጥለቀለቅ አድርጎታል፡፡ የመንግሥታዊ አካላት ለኢሕአዴግ ማጋደልም በግልጽ የሚታይና ከዚህ የመነጨ ነው፡፡

  ከብዙ ፓርቲዎች ወስጥ ሕዝብ የበለጠ ድምፅ የሰጠው ፓርቲ ሥልጣን ላይ እየወጣ በሚያስተዳድርበት የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ፣ የመንግሥት ሠራተኛው ሥራውን ለመሥራት በየምርጫው ዘመን በሚያሸንፈው ፓርቲ ፖለቲካ መጠመቅ አይኖርበትም አያስፈልገውም፡፡ የፓርቲ ፖሊሲና ስትራቴጂ ተፈራራቂ ነው፡፡ መንግሥታዊ የሕዝብ አገልጋይነት ዘላቂ ሥራ ነው፡፡ የአሸነፈው ፓርቲ ፖሊሲና ስትራቴጂ ከአጠቃላይ የሕዝብ አገልጋይነት ተግባር ውስጥ ገብቶ የተወሰነ አሻራ ሊያሳርፍ ይችላል እንጂ፣ የተገላቢጦሽ የመንግሥት ሠራተኛውና ተግባሩ የአሸናፊው ፓርቲ ተቀፅላ መሆን የለባቸውም፡፡ ሹማምንትና የሰው ኃይል ምደባዎች እነዚህን ሁሉ ከቁጥር ካላስገቡ የመንግሥት የገዛ ራሱን ፖሊሲ የማስፈጸም ብቃቱ ጭምር አደጋ ያጋጥመዋል፡፡

  መንግሥት ኢሕአዴግነትን የሥልጣንና የጥቅም መሣሪያ አድርጎ የሚያይን ሰው ልሽቀትና ሙስናን በቁርጥ መዋጋት ከፈለገ ግምገማው፣ ብጠራው፣ ሹም ሽሩ፣ የአሠራር ለውጥና ሥልጠናው ሁሉ ተንጋግቶ ጨዋነት የተሞላባት ሥራ ለምን ሥር መስደድ አልተቻለም? ታታሪነት፣ የግል ተነሳሽነት፣ የሥራ ፍቅርና ተገልጋይ አክባሪነት አልፍለቀለቅ ያለ ምን ጎድሎንና ምን ሆነን ነው? ምዕራብ ዴሞክራሲ ውስጥ የሚታየው የመንግሥት ሠራተኛ ይቅርና የግል ነጋዴ አግባብ ያልሆነ ድርጊት ቢፈጽም ለኃላፊ አሳውቆ መብትን የማስከበር የተገልጋይ ልበ ሙሉነትና ሽታውም የሌለው ለምንድነው? ብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ ግልጽነትን ግዴታው አድርጎ ማየት አለበት፡፡ ሕዝብ በሥልጣን መባለግን እንዲታገል የሚደረገው የአንደበት ጉትጎታ ልጓም ከማላላት፣ ምኅዳሩን ከማስፋት ጋር አለመገናኘቱም ሌላው ትልቁ ችግር ነው፡፡ ሐሳብን በመግለጽ፣ በመሰብሰብና በመቃወም መብቶች ረገድ ያለው እፍንፍን ያለ ሁኔታ፣ በጋዜጦችና በተቃዋሚዎች ላይ ያለው በወጥመድ የተሞላ አያያዝ፣ በየመንደር የሚያጋጥመው፣ በወሬም የሚናፈሰው፣ አደባባይ ላይና በሚዲያም ጭምር የምናየው ላለው መንግሥት በመታመንና ማን አህሎን የሚሉ ግለሰቦች የሚሳዩት የማናለብኝ ንግግርና ድርጊት ሁሉ ንቁ ተሳትፎን ከማደፋፈር ይልቅ አደብ መግዛትን የሚያስጠነቅቅ ነው፡፡ የአላንዳች ፍርኃትና በኃላፊነት ሕገወጥ ተግባራትንና የሙስና ሥራዎችን የማጋለጥና የመታገል ተግባር የመገኛና ዘዴዎች ወግና ባህል ካልሆነ፣ መንግሥትም ከየትም ይምጣ ከየት ጥፋቶችን ለማረምና አጥፊዎችን ለመጠየቅ የማያወላውል ካልሆነ፣ በቀላሉ መከሰት የሚችሉት ሕገወጥነትና ሙስና የአገር ብሔራዊ ስፖርት ይሆናሉ፡፡ የዚህ መድኃኒቱ በኢኮኖሚ፣ በማኅበረዊና በፖለቲካ ሕይወታችን ውስጥ ባለው ድቅድቅ ጨለማ ላይ የጋዜጠኛና የሕዝብ ዓይን እንዲበራበት ማድረግ ነው፡፡ እስከ ቁንጮ ሹም ድረስ ያለ የሥራና የእርስ በርስ ግንኙነት ማኅበራዊ ቤታችንን ጣሪያና ግድግዳ መስታወታማ አድርጎ ለመገንባት መቁረጥ ነው፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

   

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...