Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቻምበሮችን በቅንነት የሚያገለግሉ ወንበር ይሰጣቸው

የአሜሪካው ምርጫ ተጠናቀቀ፡፡ ትራምፕ አሸናፊ ሆኑ፡፡ ለአሸናፊነት ቅድመ ግምት የተሰጣቸው ሒላሪ ክሊንተን ሳይሳካላቸው ቀረ፡፡ አሜሪካውያን ለትራምፕ ይሁንታ መስጠት አነጋጋሪ ቢሆንም፣ ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ ለወራት በተጋጋለ ስሜት አንዳንዴ አፈንጋጭ ሲካሄድ የነበረው ምርጫ ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ፈጥሮ እንዲቋጭ ምክንያት ሆኗል፡፡ የምርጫው ውጤት ከተገለጸ በኋላ ሒላሪ ክሊንተን ለአሸናፊው ተመራጭ ፕሬዚዳንት ትራምፕ እንኳን ደስ አለዎት ብለው ደወሉ፡፡ አሸናፊውና አነጋጋሪው የአሜሪካ ተመራጭ ሚስተር ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ሒላሪን ‹‹ልመረጥ እንጂ አስርሽ ነበር›› ባለው አንደበታቸው አሸናፊነታቸው እንደታወቀ ባደረጉት የመጀመርያ ንግግር ‹‹ሒላሪ ለአገርዋ ያገለገለች፣ ለእኛ የለፋች አገሯን ያገለገለች ብርቱ ሴት ናት›› በሚል የሙገሳ ቃላት ሒላሪን አንቆለጳጰሷቸው ባደረጉት የመጀመርያ ንግግር

እንዲህ ያለው የምርጫ ሒደት ማስቀናቱ አይቀርም፡፡ ይህ ከአገራችን ውጭ ትኩረታችንን የሳበው ጉዳይ በዚህ መልክ ተጠናቀቀ አሜሪካውያኑ ተፎካካሪዎች ምርጫው የመጨረሻ የምረጡኝ ዘመቻውን ባጋጋሉበት ወቅት እዚህ አገራችን ውስጥ ይካሄድ የነበረውን አንድ ድርጊት እየተከታተልን ነበር፡፡ የነትራምፕ አገራዊ እዚህ ደግሞ የማኅበር ሆነ እንጂ ነገሩ ያው ምርጫ ነው፡፡ እንደ አሜሪካው ምርጫ የዓለምን ትኩረት ባይስብም እንደ አንድዜጋ ብዙዎች ስንከታተለው የነበረው አገራዊ ምርጫ ጉዳይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምርጫ ትኩረቴን ስቦ ነበር፡፡

የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለመምራ የተካሄደው የምርጫ ሒደት እንደኔ ላሉ በተለየ የምንመለከተው፤ ምናልባትም ተመሳሳይ ሆኑ ተቋማትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ማኅበራት ሊተገብሩት የሚገባ ምሳሌ ሆኗል በሚል ነው፡፡ ፌዴሬሽኑን ለመምራትና ለመመረጥ የተኬደበት መንገድ ያልተለመደ ስለነበር መሳካት አለመሳካቱ አጠራጣሪ ቢሆንም ሻለቃ ኃይሌና ጓደኞቹ ተሳክቶላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በበጎ የምትነሳበት የሁላችንንም ስሜት በሐሴት የሚሞላው የአትሌቲክስ ወይም የአትሌቶቻችን የድል ዜናዎች ተቀዛቀዘ፤ ይህ መለወጥ ይኖርበታል ተብሎ እነ ሻለቃ ኃይሌ ያገባናል ለመፍትሔ የተደረገው ርብርብና ውጤቱም ቢሆን ያልተለመደ ነው፡፡ ለዚህ ነው ትኩረቴን ሳበ ያልኩት፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በተመሳሳይ በሚቋቋሙ ማኅበራት ያልተደፈረ የተባለ ዕቅድ ይዘው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ሥራውን በምናውቀው ሙያተኞች ሊመራ ይገባል ብለው ይዘው የተነሡት ዓላማ ተሳክቶላቸው ፌዴሬሽኑ በአትሌቲክሱ ትልቅ ስም ያላቸውን አትሌቶች ወደ አመራር አምጥቷል፡፡ እነ ኃይሌ ውጥናቸው ተሳክቶ ውጤት እየራቀው ነው የተባለውን የአትሌቲክስ ወደ ቀድሞው ቦታ ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ለማድረግ ልንመረጥ ይገባል ብለው የተጓዙበት መንገድ መሳካቱ መልካም ነው፡፡ የተነሱበትን ዓላማ በትክክል ማሳካታቸውን የምናውቀው ወደፊት ቢሆንም ከወዲሁ ማለት የሚችለው ይቅናችሁ ብቻ ነው ከልብ ከሆነ በራስተነሰሳሽነት መሥራት መልካም ነው፡፡

እንዲህ ያለውን አካሄድ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቶችን ለመምራት አቶ ክቡርገና ባልተለመደ መንገድ የምረጡኝ ዘመቻ አድርገው መመረጣቸውን እንዳስብም አድርጎኛል፡፡ እንዲያውም አቶ ክቡር ባልተለመደ አካሄድ ምረጡኝ ብለው ይህንን እሠራለሁ ብለው ሲመረጡ ‹‹ይቻላል›› የሚለውን መሪ ቃል ያጎሉት በኃይሌ ገብረ ሥላሴ ምሥል ነበር፡፡ አቶ ክቡር ከተመረጡ በኋላም ንግድ ምክር ቤቶቹን አሠራር በመለወጥ እስከዛሬ ስማቸውን የሚያስነሳ ሥራዎች ሠርተዋልም ይባላል፡፡ ለውጥ እንዳመጡም ይታመናል፡፡ በተግባርም እንደሚታየው እነዚህ ንግድ ምክር ቤቶች የእርሳቸው አሻራ ያረፈበትን የተለያዩ ሥራዎች እንዲሠሩ ነው፡፡ (በኋላ ንግድ ምክር ቤቶች ቢፈርሱ ይሻላል ቢሉም ማለት ነው፡፡) የኃይሌና የክቡር ገና ተመሳሳይ ታሪክ በውጤት እስከታጀበ ድረስ ልንለምደው ልንጠቀምበት የሚገባ ነው፡፡ አንዳንዴ እንዲህ ባለው መንገድ የተሻለ አገልግሎት የተሻለ ውጤት ሊመጣ ይችላል፡፡

የሁለቱን ግለሰቦች የአሁኑና የቅድመ ታሪክ እንዳስታውስ ያደረገኝ ሌላ ጉዳይ አሁንም የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ አቶ ክቡር ገናና ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በተለያየ ጊዜም ቢሆን ኃይሌ በቦርድ አባልነት አቶ ክቡር ፕሬዚዳንት የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቱን እንዲያገለግሉ ተመርጠው ነበር፡፡

አቶ ክቡር ከፕሬዚዳንትነት ከለቀቁ በኋላ ከሁለት ዓመት በፊት ንግድ ምክር ቤቶች ቢፈርሱ ይሻላል ማለታቸው፣ ኃይሌ ደግሞ የቦርድ አመራር ሆኖ ከተመረጠ በኋላ በንግድ ምክር ቤቱ ውስጥ የነበረው ያለመግባት በቦርድ አባልነት ሳይገፉበት ቀርቷል፡፡

አቶ ክቡር ንግድ ምክር ቤቶች ቢፈርሱ ይሻላል ያሉት የሚጠበቅባቸውን እየሠሩ ባለመሆኑ ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደምንሰማውም ንግድ ምክር ቤቶች ሽኩቻ መንደር መምሰላቸው ጥቂቶች ብቻ መሪ ለመሆን የሚፋከቱበት መሆኑ አቶ ክቡር የንግድ ምክር ቤቶችን አካሄድ እንዲኮንኑ፣ ኃይሌም ቢመረጥም ሳይሠራ እንዲለቅ እንዳደረጉት ይታመናል፡፡ ስለዚህ እንደ ንግድ ምክር ቤት ያሉ ተቋማት አሁን የሚያባቸውን ክፍተት ለመድፈን ከተፈለገ እንደ ኃይሌ ማኅበሩን ወደ ውጤት አመጣለሁ የሚል ነጋዴ ሲኖር ጭምር ነው፡፡

ጠንካራ ነጋዴ አመራሮች ደፍረው ከወጡ ለውጥ ይመጣል፡፡ በትክክል ነጋዴዎች መሆናቸው በሚታመኑ ቢመራ ጥሩ ነበር፡፡ ስለዚህ ፉክቻው ያለው እንዲያውም ንግድ ምክር ቤቶቹን እየመሩ ያሉት ወይም እንመራለን ብለው ከሚቀርቡት ጥቂት የማይባሉት ምሳሌ ሊሆን የሚችል ኩባንያዎችን በመምራት የተፈተኑ ያለመሆን ግን ችግሩን ጎድቷል፡፡

ቻምበሩን ለማገልገል ሳይሆን ቻምበሩን ለመገልገል የሚፈልጉ እየበዙ መምጣታቸው በትክክል የንግድ እውቀት ያላቸውና ትላልቅ ኩባንያዎችን የሚመሩ ሰዎች ገሸሽ ብለዋል፡፡ ጭራሽ ዛሬ የንግድ ምክር ቤቶች የምርጫ ሒደታቸው ጥያቄ አስነስቶ ምርጫቸው ይጣራ እስከማለት የተደረሰው ጠንካራ የንግድ መሪዎች ስለዚህ ንግዱ ኅብረተሰብ ምክር ቤቶች ጠንክረው እንዲወጡ በየጊዜው እየታየ ካለው ፉክቻ እንዲላቀቁ ከተፈለገ ጥሩ ነጋዴዎች ወይም ውጤታማ የሆኑና በምሳሌነት በምንጠቅሳቸው ነጋዴዎች በራስ ፍላጎት ጭምር መውጣት ይገባቸዋል፡፡  

የእነ ኃይሌ የምርጫ ሒደትና አነሳስም ብዙ ሊያስተምራቸው ይገባል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ማኅበራችን ነው የሚሉ አባላትም ማኅራቸው እንዲያድግ ምሳሌ ነጋዴዎችን ወደ አመራር እንዲመጡ የመገፋፋት ኃላፊነታቸውን ካልተወጡ መጠበቅ ዘበት ይሆናል፡፡ ስለዚህ የማኅበራት የአመራር ቦታዎች በዘርፉ በታወቁ ሰዎች እንዲመራ እነ የኃይሌን ዱካ መከ ተከተል ሳይሻል ይቀራል?  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት