Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጨረታ ማውጣት ሳያስፈልግ ማዳበሪያ በድርድር መግዛት የሚያስችል መመርያ ፀደቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ለ15 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዢ 600 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተይዟል

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ለምርት ዘመኑ የሚያስፈልገውን 15 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ፣ ጨረታ ማውጣት ሳያስፈልግ በቀጥታ ከአምራቾች ጋር በመደራደር ግዥ መፈጸም የሚያስችል መመርያ አፀደቀ፡፡

ማዳበሪያን ጨምሮ የግብርና ምርትና ግብዓቶችን የመገበያየት ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ግብርና ንግድ ኮርፖሬሽን፣ ከ2008/2009 ምርት ዘመን ከዓለም አቀፍ ማዳበሪያ አምራች ኩባንያዎች ጋር ተደራድሮ የሸመተው 13 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ቅናሽ ዋጋ እንደተገኘበት ይታወሳል፡፡

በወቅቱ በተደረገው ማሻሻያ በተለይ ከትራንስፖርትና ከኤልሲ አከፋፈት የተገኘውን ሳይጨምር፣ ከማዳበሪያ ግዥ ብቻ 2.6 ቢሊዮን ብር ሊወጣ ይችል የነበረ ገንዘብ መዳኑ ተገልጿል፡፡

ከዚህ መሠረታዊ ጭብጥ በመነሳት የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ከተያዘው ምርት ዘመን ጀምሮ ጨረታ ማውጣትና የንግድ ኩባንያዎችንና ኤጀንቶችን ማሳተፍ ሳያስፈልግ፣ ከግዙፍ ማዳበሪያ አምራቾች ጋር በመደራደር አገሪቱ የምትፈልገውን ያህል ማዳበሪያ መግዛት የሚያስችል መመርያ አፅድቋል፡፡

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ ኢያሱ አብርሃ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለፈው ዓመት የተገኘውን ውጤት በዚህ ዓመትም ለመድገም መመርያው ፀድቋል፡፡ ‹‹ባለፈው ዓመት ሊወጣ የነበረ 2.6 ቢሊዮን ብር ማዳን ተችሏል፡፡ ይህም በመሆኑ ለአርሶ አደሩ በሚቀርብ አንድ ኩንታል ማዳበሪያ ላይ የ350 ብር ቅናሽ ተደርጓል፤›› ሲሉ መመርያውን አፅድቆ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈለገበትን ምክንያት ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ምርት ዘመን ለተገዛው 13 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ 400 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል፡፡ በዚህ ዓመት ለሚገዛው 15 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ደግሞ 600 ሚሊዮን ዶላር እንደተመደበ ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓመት የመስኖ እርሻ እየተስፋፋ በመሆኑ የማዳበሪያ ፍላጎት መጨመሩን አስረድተዋል፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ማጠናቀቂያ በሆነው 2012 ዓ.ም. የአገሪቱ የማዳበሪያ ፍላጎት 2,062,106 ሜትሪክ ቶን ይደርሳል ተብሎ ዕቅድ ተይዟል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ማዳበሪያ አምራቾች ከአሥር ባይበልጡም፣ የኢትዮጵያ ግብርና ንግድ ኮርፖሬሽን በሚያወጣው ጨረታ በርካታ የንግድ ድርጅቶችና ኤጀንቶች ተሳታፊ እየሆኑ በአጠቃላይ ከ20 ተጫራቾች የሚበልጡበት ጊዜ ነበር፡፡

ነጋዴዎች በሚያሸንፉበት ወቅት የራሳቸውን ትርፍ የሚይዙ በመሆኑ መንግሥት ከፍተኛ ወጪ ሲያወጣ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ሚኒስትሩ እንዳብራሩት ከአምራቾች ጋር በሚደረገው ድርድር የማዳበሪያ ጥራት፣ ዋጋና አገር ውስጥ የሚገባበት ጊዜ ሁሉ ታሳቢ ይደረጋል፡፡ በዚህም አርሶ አደሩ ተጠቃሚ ይሆናል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች