Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናአቶ መላኩ ፈንታና አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ የእርስ በርስ የመከላከያ ምስክረነታቸውን...

አቶ መላኩ ፈንታና አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ የእርስ በርስ የመከላከያ ምስክረነታቸውን ሰጡ

ቀን:

‹‹የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቢኖሩ አንከሰስም ነበር››

አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ

በከፍተኛ የሙስና ተግባር ወንጀል ተከሰው ላለፉት አራት ዓመታት በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ የእርስ በርስ የመከላከያ ምስክርነታቸውን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አሰሙ፡፡

- Advertisement -

አቶ መላኩ ፈንታ፣ አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስና የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ከተማ ከበደ የእርስ በርስ መከላከያ ምስክርነታቸውን ያሰሙት፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በወንጀል መዝገብ ቁጥር 141352 ባቀረበው ክስ ላይ ፍርድ ቤት እንዲከላከሉ ብይን ከሰጠ በኋላ ነው፡፡

ዓቃቤ ሕግ መሥርቶት የነበረው ክስ በ2001 ዓ.ም. በተካሄደው አራጣ አበዳሪዎችን ለሕግ የማቅረብ ተግባር በጥቆማ ከቀረቡት ዘጠኝ አራጣ አበዳሪዎች ውስጥ፣ አቶ ከተማ ከበደም አራጣ አበዳሪ መሆናቸውን የሚያስረዱ ማስረጃዎች ቀርበው እያለ፣ ከአቶ መላኩና አቶ ገብረ ዋህድ ጋር ባላቸው ሥውር የጥቅም ግንኙነት ምክንያት፣ በሌሎቹ ላይ ምርመራ ተጣርቶ በሕግ እንዲጠየቁ ሲደረጉ እሳቸው እንዳይጠየቁ መደረጋቸውን በሚመለከት ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱም የዓቃቤ ሕግን ምስክሮች ሰምቶ እንዲከላከሉ ትዕዛዝ በመስጠቱ፣ እነርሱም አንዱ በአንዱ ላይ የመከላከያ ምስክር ሆነው በመቅረብ ለፍርድ ቤት የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመጀመርያ የተከሳሽነት የምስክርነት ቃል በራሳቸው ላይ የሰጡት አቶ መላኩ ፈንታ ናቸው፡፡ አቶ መላኩ በሰጡት የተከሳሽነት የምስክር ቃል ክስ የተመሠረተባቸው መንግሥት በሰጠው አቅጣጫ መሠረት በተደረገው ጥናት አሥር አራጣ አበዳሪዎች እንዲከሰሱ ማስረጃ ለባለሥልጠኑ ከደረሰው በኋላ ዘጠኙ በሕግ እንዲጠየቁ ሲደረግ፣ አቶ ከተማ ግን ሥውር የጥቅም ግንኙነት ስላላቸው እንዳይከሰሱ ስላለማድረጋቸው ነው፡፡

ይህንንም ሲያስረዱ ከፍተኛ ነጋዴዎች ሆነው ወይም ከፍተኛ ገቢ እያላቸው በአግባቡ ታክስ የማይከፍሉና አሳንሰው የሚከፍሉ እንዳሉ በሚደርስ ጥቆማ መሠረት 1,000 በሚሆኑ ድርጀቶች ላይ ጥናት ተደርጓል፡፡ በተደረገው ጥናት ከዘጠኝ እስከ አሥር በሚሆኑ ድርጅቶች ላይ እጅግ በጣም ከፍተኛ ገንዘብ መገኘቱንና ይህም አራጣ በማበደር የተገኘ መሆኑን የሚያሳይ ፍንጭ መገኘቱን አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ እሳቸው የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙበትና በተቋሙም አዲስ ሪፎርም እየተደረገ ስለነበር ሁኔታውን በደንብ ካጤኑ በኋላ፣ ወደ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጽሕፈት ቤት መሄዳቸውን አስረድተዋል፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ሦስት ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ የመጀመርያው እዚህ ቦታ ላይ ሥራ ከተባሉ ከረባታቸውን አስረውና ፕሮቶኮል ጠብቀው በየሪሰፕሽኑ መገኘት፣ ሁለተኛ ከሚገኘው ገቢ የድርሻቸውን መውሰድ፣ በሦስተኛ ደረጃ የእሳቸውን እገዛ ካገኙና ማንም ጣልቃ ሳይገባባቸው በተቋሙ ሠርተው ለውጥ ማምጣት መሆኑን እንዳስረዷቸው ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም ሦስተኛውን ሐሳብ በመደገፍ እንደሚያግዟቸው ቃል በመግባት ወደ ሥራው እንዲያተኩሩ መመርያ እንደሰጧቸውና ሥራቸውን መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ከፍተኛ ገንዘብ እንዳላቸው በጥናት የተረጋገጠባቸውን አቶ ገብረ ኪዳን በየነ፣ አቶ አየለ ደበላ፣ አቶ አያሌው ተሰማ፣ አቶ ከበደ ተሠራ፣ አቶ ሌንጫ ዘገዬና ሌሎችን በሚመለከት ገንዘቡ ከየት እንደተገኘ እንዲጣራ ማድረጋቸውን አቶ መላኩ አስረድተዋል፡፡ ገንዘቡ በከፍተኛ ወለድ ከ20 እስከ 33 በመቶ በማስከፈል የተገኘ መሆኑን ሲያረጋግጡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት ማድረጋቸውንም አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ተቋማቸው በአራጣ አበዳሪዎች ላይ ክስ የመመሥረት ሥልጣን ስለሌለው፣ ከሕግ ክፍል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እሸቱ ወልደ ሰማያት ጋር መመካከራቸውን ጠቁመዋል፡፡

አቶ እሸቱ ተጠርጣሪዎቹን ወደ ሕግ የማቅረብ ሥልጣን የፍትሕ ሚኒስቴር መሆኑን ገልጸው በውክልና ግን የእነሱ ተቋም መክሰስ እንደሚችል በማስረዳታቸው፣ አቶ መላኩም መስማማታቸውንና ውክልናውን አቶ እሸቱ በራሳቸው ስም ወስደው ክሱ መመሥረቱን ገልጸዋል፡፡ ተከሳሾቹም ከ20 ዓመታት በላይ ተፈርዶባቸውና በሕገወጥ መንገድ ያፈሩት ንብረት እንዲወረስ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ ከበደ ከተማን በሚመለከት አቶ መላኩ እንደገለጹት፣ እንኳን ሊመሳጠሩ ትውውቅ አልነበራቸውም፡፡ በአራጣም ይሁን በሌላ መንገድ ስለሳቸው የቀረበ ማስረጃ አልነበረም፡፡ በወቅቱ በመገናኛ ብዙኃን በተደረገ ጥሪ (ጥቆማ ማድረግን በሚመለከት) በአቶ ከተማ ላይ የመጣ ምንም ዓይነት ጥቆማ እንዳልነበር አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን የአቶ ከበደ ተሠራ ቤት ሲፈተሽ ለጌታነህ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ብድር የሰጡበት ሰነድ መገኘቱንና ለእሳቸውም ቀርቦላቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የብድር ውሉ አቶ ከተማ ለልጃቸው ትዕግሥት ከተማ ወኪል ሆነው ለጌታነህ ድርጅት ባለቤት አቶ ዮሐንስ ጌታነህ ብድር የሰጡበት ሰነድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ብድሩ አራጣ የሚያስብለውን ገፋፍቶ ማበደር፣ መያዣ ይዞ ማበደርና ከባንክ ወለድ በላይ አስከፍሎ ማበደር የሚለውን መሥፈርት የማያሟላና አራጣ ሊባል የማይችል በመሆኑ እንዳላስከሰሳቸው አስረድተዋል፡፡

ያም ሆኖ ግን ያለውን ሁኔታ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሲያስረዷቸው፣ ተጨማሪ ጥናትና ክትትል እንዲደረግበት ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት እንዲልኩት በሰጡት ትዕዛዝ መሠረት በአቶ ገብረ ዋህድ አማካይነት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ምስክርነት እስከሰጡበት ጊዜ ድረስ ለማንም ተናግረው እንደማያውቁ ገልጸዋል፡፡

አቶ መለስም በወቀቱ ፓርላማ ላይ ተጠይቀው አራጣ አበዳሪዎችን በሕግ መጠየቅ ተገቢ መሆኑን መናገራቸውን ለፍርድ ቤቱ አስታውሰዋል፡፡ እሳቸው በሚያኙት ጥቅም ለእናታቸው ቤት እንደሠሩ ተደርጎ በዓቃቤ ሕግ ክስ እንደተመሠረተባቸው ጠቁመው፣ ‹‹እንኳን ቤት ልሠራላት በአግባቡም አልቀበርኳትም፤›› ብለዋል፡፡

ከእሳቸው ጋር ታስረው የተደበደቡና ንብረታቸው የታገደባቸው ሰዎች በእሳቸው ላይ ወጥተው ከመሰከሩ እንደሚፈቱና ንብረታቸውም እንደሚለቀቅላቸው ተነግሯቸው መመስከራቸውን ስም በመግለጽ ተናግረው፣ ተዓማኒነት የሌለው ምስክርነት እንደሆነ ሲቃወሙ ፍርድ ቤቱ በብይን እንደሚመዝነው አስታውቆ የተሰሙ ቢሆንም፣ እነሱ በሰጡት ምስክርነት ግን ብይን እንደተሰጠባቸው አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡

አንደኛው ምስክር አቶ ከተማን ያስተዋወቋቸው በ2001 ዓ.ም. ባህር ዳር የአልማ የመጀመርያ ስብሰባ ላይ እንደሆነ መመስከራቸውን አቶ መላኩ አስታውሰው፣ የአልማ ስብሰባ የተደረገው ግን አዲስ አበባ ከተማ በ2002 ዓ.ም. ሒልተን ሆቴል መሆኑን በመግለጽ የዓቃቤ ሕግ ምስክርነት መለያየትን ገልጸዋል፡፡

አቶ መላኩ አቶ ከተማን የተዋወቋቸው በሁለተኛው የአልማ ቴሌቶን ባህር ዳር ላይ ሲካሄድ መሆኑን ገልጸው፣ ከዚያ ውጪ የትም ቦት አይተዋቸውና አግኝተዋቸው እንደማያውቁ፣ ነገር ግን ማረሚያ ቤት በእስር ላይ የሚገኙና ከመሰከሩ ከእስር እንደሚፈቱ የተነገራቸው ምስክር፣ መላኩና ከተማ ከበደ በ2001 ዓ.ም. እሳቸው ከመታሰራቸው በፊት አቶ ከተማ ቤት በተደረገ ግብዣ ላይ ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር መገኘታቸውን መመስከራቸውን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ግለሰቡ በአራጣ ወንጀል በ2001 ዓ.ም. እስር ላይ እንደነበሩ በማስረዳት ጊዜው እንደማይገናኝ ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ ከአቶ ከተማ ከበደ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው፣ እሳቸውን በሚመለከት በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ትዕዛዝ ጉዳያቸው በደኅንነት በኩል ክትትል ይደረግባቸው እንደነበርና ከ1997 ዓ.ም. በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ አቶ ከተማ ሕጉን ጠብቀው ታክስና ግብር የሚከፍሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

አሁንም ከባስለሰሪሪሪበለሥልጣንም ሆነ ከጓደኛ ጋር ተጋብዘውም ሆነ ጋብዘው እንደማያውቁ፣ በዚህም የሚታወቁ መሆናቸውን፣ ነገር ግን አቶ ተፈራ ዋልዋ ቤት ብቻ መሄዳቸውን በማስረዳትና የሚናገሩት ሁሉ በማስረጃና በምስክር የሚረጋገጥ መሆኑን በዝርዝር በመግለጽ የተከሳሽነት የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ አቶ ገብረ ዋህድም ከአቶ ከተማ ከበደ ጋር ያላቸው ግንኙነት ከአቶ መላኩ ጋር በሚቀራረብ ሁኔታ የተከሳሽነታቸውን ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡

ከአቶ ከተማ ጋር እግዚአብሔር በሚያውቀው የተዋወቁት ከታሰሩ በኋላ መሆኑን አቶ ገብረ ዋህድ አስረድተዋል፡፡ አቶ ከተማ የተከሳሽነት ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው፣ ሁለቱ ተከሳሾች ካሉት ውጪ የሚናገሩት እንደሌላቸው ተናግረው ወደ መከላከያ ምስክርነት ተገብቷል፡፡

አቶ መላኩ ፈንታ የመከላከያ ጭብጥ ከሰጡ በኋላ አቶ ገብረ ዋህድንና አቶ ከተማን በመከላከያ ምስክርነት አቅርበዋቸዋል፡፡

አቶ ገብረ ዋህድ በሰጡት ምስክርነት ቃል፣ ‹‹ከሚከፍሉት ግብር ጋር ተመጣጣኝ ያልሆነ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ የተወሰኑ ሰዎች የገንዘብ ምንጭ እንዲጣራ ተደርጎ አራጣ መሆኑ በማስረጃ የተረጋገጠባቸውን ዘጠኝ ሰዎችና አንድ ድርጅት አገኘን፡፡ በታክስ ስወራና በአራጣ ወንጀል አጣምረን ክስ እንድናቀርብ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አመራር ተሰጠን፡፡ ነገር ግን የአራጣ ወንጀልን የማጣራትና ክስ የማቅረብ ሥልጣን ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በሕግ ስላልተሰጠው ሥልጣን ካለው የፍትሕ ሚኒስቴር (አሁን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ) በተሰጠን የውክልና ሥልጣን በግለሰቦቹ ላይ ክስ አቅርበናል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በተሰጠ አመራርና አቅጣጫ ክስ እንዲቀርብባቸው ከተወሰነባቸው ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ አቶ ከተማ ከበደ እንዳልነበሩ አቶ ገብረ ዋህድ አስረድተው፣ በእሳቸው ላይ ምርመራ ለማጣራትና ክስ ለማቅረብ ፍትሕ ሚኒስቴር የውክልና ሥልጣን እንዲሰጥ እንዳልተጠየቀ፣ እንዲሁም አቶ ከተማ ላይ በአራጣ ወንጀል ክስ እንዲቀርብባቸው አመራር እንዳልተሰጠ መስክረዋል፡፡

ከጊዜ በኋላ ግን አቶ ባህሩ አብርሃ የተባሉ ግለሰብ በታክስ ማጭበርበር የቀረበባቸውን ክስ በገንዘብ ተደራድሮ አዘግቶታል በሚል ጥቆማ፣ በሥነ ምግባር ጉድለት ከመደበኛ የወንጀል ዓቃቤ ሕግነት ሥራ እንዲነሱ የተወሰነባቸው የዓቃቤ ሕግ ምስክር የብድር ውል፣ መተማመኛ ሰነድና ዋስትና ይዘው እሳቸው ቢሮ መጥተው ‹‹አቶ ከተማ አራጣ አበዳሪ መሆናቸውን የሚያስረዳ ማስረጃ አግኝተናል፤›› ብለው ሰነዶቹን ሰጥተዋቸው መሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ሰነዶቹን ሲመለከቷቸው አንድ የብድር ሰነድና ሌሎችም ከዚሁ ሰነድ ጋር የተያያዙ፣ ወለድ ያልተጻፈበት፣ አበዳሪ ትዕግሥት ከተማ መሆኗን የሚናገርና በብድሩ ውል ምክያት ክስ ቀርቦ እስከ ሰበር ችሎት የብድሩ ውል ተቀባይነት አግኝቶ ዕዳው እንዲከፈል የተወሰነ መሆኑን የሚያስረዳ እንደበር ገልጸዋል፡፡ በመንግሥት በተሰጠው አቅጣጫ በተደጋግሚ አራጣ በማበደር የተሰማሩና የሙያ ሥራቸው ባደረጉ አበዳሪዎች ላይ ብቻ ክስ እንዲቀርብ የተሰጠውን አመራር የማያሟላ ስለሆነ፣ ሌሎች ማስረጃዎች እንዲፈለጉ ተወያይተውና ተስማምተው መለያየታቸውን መስክረዋል፡፡

ከቀድሞው ጠቀላይ ሚኒስትር ጋር በነበራቸው ስብሰባ አጀንዳ ተይዞ እንደተወያዩበት፣ ምስክሮቹ የሰጧቸውን ሰነዶች ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት እንዲላክ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ እንደተሰጠ ጠቁመዋል፡፡ ሰነዶቹን ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኃላፊዎች ጋር በስልክ ተነጋግረው በፖስታ አሽገው መላካቸውንም አስረድተዋል፡፡ በዓቃቤ ሕግ ምስክርነት የቀረቡት ዓቃቢያነ ሕጉ በአቶ ከተማ ላይ ተጨማሪ ማስረጃ እንዲፈለግ በተደረሰበት አቋም ላይ ተስማምተው በሰላም ከመለያየታቸው በስተቀር፣ በጊዜው በመካከላቸው አለመግባባት አልተፈጠረም፡፡ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አመራር ማስረጃዎቹ ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ከተላለፉ በኋላ አቶ ከተማ ላይ የተገኘ ማስረጃ ባለመኖሩ፣ እንዲሁም በሚዲያ በተደረገ ጥሪ አቶ ከተማ ከታክስ ስወራ ጋር በተያያዘም ሆነ አራጣ አበዳሪ መሆናቸውን የሚያሳይ መረጃ ለመሥሪያ ቤቱ ስላልቀረበ ክስ ሊቀርብባቸው አልቻለም፡፡ ‹‹ክስ የቀረበብን ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሕልፈት በኋላ ስለሆነ፣ እሳቸው በሕይወት ቢኖሩ ክስ ሊቀርብብን እንደማይችል በእርግጠኝነት አምናለሁ፤›› በማለት የምስክርነት ቃላቸውን አጠናቀዋል፡፡

አቶ ከተማ ከበደ ከአንደኛው ተከሳሽ ከአቶ መላኩ ፈንታ ጋር በአልማ የዕርዳታ ጥሪ ባህር ዳር በስብሰባ ላይ ተገናኝተው ከመጨባበጣቸው በስተቀር፣ ከዚያ በፊት አቶ መላኩን አግኝተዋቸው እንደማያውቁ፣ አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስን በዚህ ጉዳይ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በእስር ቤት በአካል ያዩዋቸውና ከዚያ በኋላ የሚያውቋቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሟች አቶ ዮሐንስ ጌታነህ ከ30 ዓመታት በፊት የሚያውቋቸው የቅርብ ጓደኛቸው እንደነበሩና የልብ ጓደኛሞች ስለነበሩ፣ በቤተሰብ ግንኙነታቸው የብድሩን ሰነድ ራሱ አዘጋጅቶና የራሳቸውን ባለቤትና ወንድም እንዲያውቁት አስፈርመው ‹‹ሰውና እንጨት ተሰባሪ ነው›› በማለት እንደሰጧቸው ተናግረዋል፡፡ አበዳሪ የ38 ዓመት ዕድሜ ያላት ልጃቸው ትዕግሥት ከተማ መሆኗንም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ስለአበዳሪዋ ትዕግሥት ከተማና ስለገንዘቡ መስቀለኛ ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም፣ በተከሳሾቹ ጠበቆች ተቃውሞ ስለቀረበበት ፍርድ ቤቱ የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን ሠርታችኋል ተብሎ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ፣ ከተሰጠው ትዕዛዝ ጋር ግንኙነት የሌለውና በምስክርነት የቀረቡት ተከሳሽ ራሳቸውን እንዲወነጅሉ የሚገፋፋ ጥያቄ መቅረብ የለበትም ብሎ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቶ ምስክርነቱ አብቅቷል፡፡

አቶ መላኩ ፈንታ ለአቶ ገብረ ዋህድና አቶ ከተማ ከበደ የመከላከያ ምስክር ሆነው ሲቀርቡ እንደገለጹት፣ በታክስና በግብር ሥርዓቱ በጥናት ላይ የተመሠረተ የሪፎርም ሥራ ለመሥራት አቋም ተይዞ እሳቸውና የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ ሱፍያን አህመድ፣ በወር አንድ ጊዜ መደበኛ ወይም እንደ አስፈላጊነቱ ከዚህ ባነሰ ጊዜ ውስጥ፣ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በአቶ መለስ ዜናዊ ሰብሳቢነት ሪፖርትና ጥናት እያቀረቡ አቅጣጫ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ በጥናት የተረጋገጠባቸው ከፍተኛ ገንዘብ እያንቀሳቀሱ አነስተኛ ግብር የሚከፍሉ ወይም በግብር ከፋይነት የማይታወቁ ዘጠኝ ሰዎች የገንዘብ ምንጭ እንዲታወቅ ክትትል እንዲደረግ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መመርያ መሰጠቱንም ጠቁመዋል፡፡ የገንዘቡ ምንጭ የተደጋገመ የአራጣ ብድር መሆኑን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች ስለተገኙ፣ የሕግ ማስከበር ዕርምጃ እንዲወሰድ አቋም ተይዞ ዘጠኙ ሰዎች ላይ ብቻ በታክስ ማጭበርበርና አራጣ ማበደር ወንጀል ክስ ለማቅረብ ከፍትሕ ሚኒስቴር በተሰጠ ውክልና ክስ እንደቀረበባቸው ገልጸዋል፡፡ በዚህ በዝርዝሩ ውስጥ አቶ ከተማ እንዳልነበሩም መናገራቸውን አስረድተዋል፡፡ በተደጋጋሚ አራጣ በማበደር ክስ የቀረበባቸው ሰዎች የተደረሰባቸው ከሚያንቀሳቅሱት ከፍተኛ ገንዘብ ጋር የማይመጣጠን ታክስና ግብር መክፈላቸው ከተረጋገጠ በኋላ፣ የሚያንቀሳቅሱት ገንዘብ ምንጩን ለማወቅ በተከናወነ የኢንተለጀንሲ ሥራ መሆኑንም አክለዋል፡፡ የአቶ ከተማ ድርጅት ኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከፍተኛ ግብር ከፋይ መሆኑንና በተደረገው የታክስ ምርመራ በሲስተሙ ውስጥ ታክሱን በአግባቡ የሚከፍልና ከታክስ ጋር የተያያዘ ሕገወጥ ድርጊት ባለመገኘቱ ክስ ለማቅረብ የሚያስችል መረጃና ሪፖርት እንዳልተገኘ አስረድተዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት በታክስ ሪፎርም ትግበራ አቶ ከተማን የሚያመለክት አጀንዳ እንዳልነበር፣ ለውይይትም እንዳልቀረበ፣ መንግሥት የሰጠውን ትምህርት ባልተቀበሉና ከሚያንቀሳቅሱት ከፍተኛ ገንዘብ ጋር ተመጣጣኝ ያልሆነ አነስተኛ ግብር ከፋዮችንና በተደጋጋሚ አራጣ አበዳሪዎችን ብቻ ለይቶ ለሕግ ማቅረብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአገሪቱ ታዋቂ በሆኑ ሁለት ግለሰቦች በዓለም አቀፍ የሩጫ ውድድር ለተገኘ ውጤት በሽልማት የተሰጠን የከተማ ቦታ በአንድ ቀን ጧትና ከሰዓት በኋላ በተጻፉ ሁለት የሽያጭ ውሎች፣ የሽያጭ ዋጋውን ከፍና ዝቅ በማድረግ በአነስተኛ ዋጋ የመንግሥት ክፍያ ፈጽመው ጉዳት ማድረሳቸው ከተረጋገጠ በኋላ፣ የግለሰቦቹን ታዋቂነትና በኢንቨስትመንት የነበራቸው ተሳትፎ ግምት ውስጥ ገብቶ ኅብረተሰቡ ግብር መክፈል እንዳለበት ተከታታይ ትምህርት በሚዲያ እንዲሰጡ ተደርጎ ክስ ሳይቀርብባቸው እንዲታለፉ አመራር እንደተሰጠበት አስረድተዋል፡፡ አቶ መላኩ እንደተናገሩት ክስ እንዳይቀርብባቸው የተደረጉ ሁለት ሰዎች ማንነትን መግለጽ ለአገር ካበረከቱት አስተዋጽኦና የገጽታ ግንባታ ጋር የማይጣጣም በመሆኑ፣ በምርመራ ላይ እያሉ በሰጡት የተከሳሽነት ቃል ስማቸውን እንዳልገለጹና አሁንም ለፍርድ ቤቱም ባስመዘገቡት ጭብጥ ላይ ተመሳሳይ አቋም መያዛቸውን ቢያስረዱም፣ አቶ ገብረ ዋህድ ስማቸውን እንዲገልጹ በመጠየቃቸው ምላሽ እንዲሰጡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም አቶ መላኩ እንደናገሩት ሻጭ አቶ ሚሊዮን ወልዴ የተባለ በ5000 ሜትር ሩጫ የኦሎምፒክ አሸናፊ የነበረ፣ ገዥ በአራጣ ወንጀል ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት ሕይወታቸው ያለፈው አቶ አየለ ደበላ መሆናቸውንና ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ደግሞ ሁለቱ የሽያጭ ዋጋ በተለያዩባቸው በአንድ ቀን በተጻፉ የአንድ ንብረት ሽያጭ ውሎች ላይ ምስክር ሆነው መፈረማቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ ከተማ ከበደን በሚመለከት አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ በዓቃቤ ሕግ ምስክርነት ለቀረቡት በጊዜው የገቢዎችና ጉምሩክ ዓቃቢያነ ሕጎች ያቀረቡላቸውን ሰነዶች በሚመለከት፣ በመንግሥት በተያዘው አቅጣጫ ክስ ለማቅረብ በቂ ባለመሆናቸው ተጨማሪ ማስረጃ እንዲፈለግ አመራር የተሰጠ መሆኑን ለአቶ ገብረ ዋህድ እንደገለጹላቸው ተናግረዋል፡፡ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ‹‹አቶ ገብረ ዋህድ በኬኬ ላይ ክስ ላለማቅረብ በአምስት ሚሊዮን ብር እየተደራደረ ነው፤›› ብለው ጠይቀዋቸው የቀረበው ማስረጃ ክስ ለማቅረብ በቂ ስላልሆነ ሌሎች ማስረጃዎች እንዲፈለጉ አመራር የተሰጠበት መሆኑን ለአቶ ገብረ ዋህድ እንዳስረዱዋቸውና ለባለሥልጣኑ ምላሽ መስጠታቸውን አቶ መላኩ አስረድተዋል፡፡ በገቢዎችና ጉምሩክ አሠራር ላይ የተለያዩ ባለሥልጣናት በተለያዩ ጊዜያት ጣልቃ በመግባት ተፅዕኖ ስለሚፈጥሩ፣ ስለአቶ ከተማ በከፍተኛ ባለሥልጣን የተነገረው ለጥርጣሬ ምክንያት እንዳይሆን፣ ባለሥልጣኑ አቶ ገብረ ዋህድ ከኬኬ ጋር በገንዘብ ድርድር ላይ እንዳሉ የነገሩዋቸውን፣ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በስብሰባ ላይ እንዳስረዷቸው ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የክትትል ሥራ እንደሚያስፈልገው ተረድተው ተገኙ የተባሉት ሰነዶች ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት እንዲላክ እንዳስረዱዋቸው፣ በዚህም መሠረት የጠቅላይ ሚኒስትሩን አቋም ለአቶ ገብረ ዋህድ ማስረዳታቸውንና በሌላ ጊዜም አቶ ገብረ ዋህድን ጠይቀው ሰነዶቹ ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት የተላኩ መሆናቸውን እንደገለጹላቸው ተናግረዋል፡፡ በሚመሩት መሥሪያ ቤትና በእርሳቸው ሥልጣን የሚፈለግባቸውን ተግባር ማከናወናቸውንም አስረድተዋል፡፡

ከተከሳሽ ጠበቃ በተነሳ ድጋሚ ጥያቄ፣ ‹‹አቶ ገብረ ዋህድ በኬኬ ላይ ክስ እንዳይቀርብ ለማድረግ በአምስት ሚሊዮን ብር እየተደራደሩ ነው፤›› በማለት የተናገሩትን ባለሥልጣን በስም እንዲገልጹ ጥያቄ ቀርቦላቸው፣ አቶ በረከት ስምኦን እንደሆኑና የመረጃው ምንጭ የዓቃቤ ሕግ ምስክር መሆናቸውን በማስረዳት፣ ይህንንም በምርመራ ላይ እያሉ በሰጡት የተከሳሽነት ቃል ላይ መግለጻቸውን መስክረዋል፡፡ የዓቃቤ ሕግ መስቀለኛ ጥያቅ ለማጠናቀቅ ፍርድ ቤቱ በአዳሪ ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ አብቅቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...