የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ወደ ግሉ ዘርፍ ካዛወራቸው ድርጅቶች ማግኘት የነበረበት ሦስት ቢሊዮን ብር ውዝፍ ዕዳ ሊከፈል ባለመቻሉ፣ 20 ኩባንያዎችን ወደ ሕግ መውሰዱን አስታወቀ፡፡ ባለዕዳ ከሆኑ ኩባንያዎች መካከል የሼክ መሐመድ አል አሙዲ ኩባንያዎች የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት በተጨማሪ፣ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ከባለዕዳ ኩባንያዎቹ ጋር ምክክር አድርጎ ነበር፡፡ በወቅቱ ባለዕዳዎቹ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የገበያ ክፍተት፣ እንዲሁም የምርታማነት ችግር መኖሩን በመግለጽ የመክፈያ ጊዜ እንዲከለስላቸው አፅንኦት ሰጥተው ጠይቀው ነበር፡፡
ሚኒስቴሩ ይህንን አቤቱታ በመቀበል በተከለሰ የመክፈያ ጊዜ እንዲከፍሉ ተስማምቶ ነር፡፡ በዚህ መሠረት በተለይ የሼክ መሐመድ አል አሙዲ ድርጅቶች የሆኑት ሆራይዘን አዲስ ጎማ፣ ቡና ማዘጋጃና ማከማቻ፣ የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ በበቃ ኮፊ ስቴት ኩባንያዎች ያለባቸውን ሁለት ቢሊዮን ብር ዕዳ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ እንዲከፍሉ መግባባት ላይ ተደርሶም ነበር፡፡
ነገር ግን ሁለቱ ኩባንያዎች ማለትም ሆራይዘን አዲስ ጎማ 198.7 ሚሊዮን ብር፣ የቡና ማከማቻና ማዘጋጃ 174.6 ሚሊዮን ብር የከፈሉ ቢሆንም፣ ሌሎቹ ድርጅቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ባለመክፈላቸው ጉዳያቸው ወደ ሕግ መወሰዱ ተገልጿል፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወንዳፍራሽ አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ድርጅቶቹ ዕዳቸውን እንዲከፍሉ ባለፈው ዓመት ምክክር ተደርጎ መክፈል ጀምረው ነበር፡፡ ነገር ግን እንደገና አቋርጠዋል፡፡
‹‹ለልማት የሚውል ገንዘብ ነው፡፡ ለእነሱም ቅጣትና ወለድ ይጨምርባቸዋል፤›› ሲሉ አቶ ወንዳፍራሽ ገልጸው፣ ‹‹አሁንም ግን ከሕጉ ጎን ለጎን ኩባንያዎቹ እንዲከፍሉ ውይይት ይካሄዳል፤›› ሲሉ አቶ ወንዳፍራሽ አብራርተዋል፡፡ በዚህ መሠረት ዕዳቸውን የሚከፍሉ ድርጅቶች ክሳቸው የሚቋረጥ ሲሆን፣ መክፈል ያልቻሉ ድርጅቶች ግን ተወርሰው በሐራጅ ይሸጣሉ ተብሏል፡፡
አቶ ወንዳፍራሽ እንደሚሉት በኩባንያዎቹ ላይ በተናጠል ክስ ተመሥርቷል፡፡ ነገር ግን በእያንዳንዱ ክስ ላይ በዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡