ኢትዮጵያ እስካሁን ያለችው በዚህ ጨዋና ኩሩና አስተዋይ ሕዝብ ምክንያት እንጂ፣ በብቁ አመራር አለመሆኑ አሁን በትክክል ግልጽ እየሆነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጨዋና ኩሩ ሕዝብ በአስተዋይነቱና በአርቆ አሳቢነቱ ሳቢያ እርስ በርሱ ከመደጋገፍ በላይ፣ የሚወዳት አገሩ ክፉ እንዳይነካት ሲል በርካታ ችግሮችን ችሎ ኖሯል፣ እየኖረም ነው፡፡ ከአስመራሪው ድህነትና እንደ እሳት ከሚጋረፈው የኑሮ ውድነት ጋር እየታገለ፣ በየደረጃው ያሉ የአገር አስተዳዳሪዎችን በትዕግሥት ብዙ ጠብቋቸዋል፡፡ በስሙ ከሚነግዱበት ጀምሮ በአጉል ተስፋ እስከሚቀልዱበት ድረስ ከሚፈለገው በላይ ታግሷቸዋል፡፡ ይህ ትዕግሥቱ ግን ዘለዓለማዊ ባለመሆኑ በግልጽ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ ይህ ጨዋ ሕዝብ ውሸትን የሚፀየፍ፣ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን በፍፁም የማይቀበል፣ በአገሩ ህልውና የማይደራደር፣ ያለችውን ትንሽ ነገር ከወገኖቹ ጋር የሚካፈል፣ ህሊናውን የሚኮሰኩሱ ነገሮችን አጠገቡ የማያስደርስ፣ ችግሮች ሲያጋጥሙ እንደ ባህሉ በሽምግልና የሚፈታ፣ ለሰላም ትልቅ ቦታ የሚሰጥ፣ ወዘተ. ነው፡፡ ይህንን ሕዝብ በአግባቡ መምራት እያቃተ ግን አገር አደጋ ውስጥ ናት፡፡
ባለፉት 20 ዓመታት ተገኝቶ የነበረው አንፃራዊ ሰላም ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ጋር ተጣጥሞ ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ በየሥፍራው እያጋጠሙ ያሉ አሳዛኝ ድርጊቶች የዚህች ታሪካዊት አገር መገለጫ አይሆኑም ነበር፡፡ አገሪቱ ከእርስ በርስ ጦርነት ወጥታ በሕዝቦቿ ሙሉ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማቆም ሲገባ፣ በወረቀት ላይ ብቻ የሠፈረ ነገር ግን በተግባር መተርጎም ያልቻለ ዴሞክራሲ እየተሰበከ አገሪቱ የቅራኔ የስበት ማዕከል ሆናለች፡፡ ሌላው ቀርቶ በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻሉ ብቻ ልዩነቶች እየጦዙ አገሪቱን ጥላሸት የሚቀቡ ድርጊቶች ተፈጽመዋል፣ እየተፈጸሙም ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ባለመከበራቸው፣ ሰብዓዊ መብቶች በመጣሳቸውና በሕገ መንግሥቱ መሠረት መሥራት ባለመቻሉ ብቻ፣ አገሪቱን ከመቼውም ጊዜ በላይ ሥጋት ውስጥ የጣሉ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡ ያለፉት ሦስት ዓመታት ግጭቶች መብረድ አቅቷቸው አሁንም የዜጎች ሕይወት ይጠፋል፣ አካላቸው ይጎድላል፡፡ በዚህ ምክንያት በየቦታው ሰላም እየደፈረሰ አገሪቱ በየቀኑ ከድጡ ወደ ማጡ እየተንሸራተተች ነው፡፡ ይህ ጨዋ ሕዝብ የማይገባው መከራ ውስጥ እየገባ ነው፡፡
ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በየጊዜው ‹ጥልቅ ተሃድሶ› እያለ በሩን ዘግቶ በርካታ ስብሰባዎችና ግምገማዎችን ቢያደርግም፣ የአመራር ሽግሽግና ሹምሽር ቢፈጽምም፣ በየመግለጫዎቹ ለሕዝብ ቃል ቢገባም ጠብ የሚል ነገር ጠፍቷል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎም በውስጡ በተፈጠረ ሽኩቻ ተወጥሮ ነገ ምን እንደሚከሰት እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡ የሕዝብን መሠረታዊ ፍላጎት ተረድቶ ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አሁንም ማድበስበስ ውስጥ በመገባቱ፣ ከሕዝብ ጋር የሚያስማማ ምዕራፍ ሊጀመር አልቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በተለያዩ ሥፍራዎች ዘርፈ ብዙ በሆኑ ሰበቦች ግጭቶች እየተስፋፉ ነው፡፡ የሰው ሕይወት እየተቀጠፈ ነው፡፡ ሕዝብ ከዛሬ ነገ የተሻለ ነገር ሲጠብቅ የልጆቹን ሞት ይሰማል፡፡ ከተሃድሶና ከግምገማ በኋላ የተሻለ ነገር ይመጣል ሲባል ምንም ነገር ያልተፈጠረ ይመስል ዝም ይባላል፡፡ ጠንካራ ግምገማ በማድረግ የሕዝብን አንጀት የሚያርስ ውሳኔ ይተላለፋል ተብሎ የተነገረው ሁሉ የውኃ ሽታ ይሆናል፡፡ ሕዝብ ተስፋ በመቁረጥ ይብሰለሰላል፡፡ አገር በሚያስተዳድሩ ሰዎች ላይ ተስፋ ቆርጦ ያቄማል፡፡ እየሆነ ያለውም ይህ ነው፡፡
ይህንን የመሰለ ታጋሽ፣ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ በአግባቡ መምራት ባለመቻል ብቻ አገሪቱ ችግር ውስጥ እየገባች ነው፡፡ ለአገሩ ጥልቅ ፍቅር ያለውን ይህንን ኩሩ ሕዝብ በብሔር እየከፋፈሉ ለፍጅት የሚያዘጋጁ ኃይሎች የበላይነቱን እየያዙ ይመስላሉ፡፡ ለአገር ሁለንተናዊ ችግሮች ዘለቄታዊ መፍትሔ ለማስገኘት ጥረት ከማድረግ ይልቅ፣ ጊዜያዊና አቋራጭ መፍትሔ ላይ ርብርብ እየተደረገ ሕዝብን ግራ የማጋባት አጉል ልማድ በርትቷል፡፡ መንግሥት አገር መምራት ካልቻለ በሕጉና በሥርዓቱ መሠረት መደረግ ያለበትን ማድረግ ሲገባው፣ አገሪቱንና ሕዝቡን የማይወጡበት አረንቋ ውስጥ እየከተተ ነው፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት የተከሰቱ ግጭቶችን አብርዶ ዘላቂ ሰላም ማስፈን አለመቻል የችግሩን ፅኑነት ነው የሚያመለክተው፡፡ ማንነትን መሠረት ካደረጉ ጥያቄዎች ጀምሮ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማኅበራዊ ጉዳዮች የሚነሱ በርካታ ጥያቄዎችን ታቅፎ አገሪቱን አቅጣጫ አልባ መርከብ ማድረግ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችና በመዝናኛዎች በግለሰቦች ጠብ የሚጀመሩ ግጭቶች ወደ ብሔር እየተቀየሩ ሕይወት ይጠፋል፡፡ ለተቃውሞ የሚወጡ ወጣቶች መንገድ ሲዘጉ ግጭት ይፈጠርና ሕይወት በከንቱ ይቀጠፋል፡፡ ከአንዱ ሥፍራ ወደ ሌላው መንቀሳቀስ አስፈሪ እየሆነ ነው፡፡ ሕዝብ እየተሳቀቀ ነው፡፡ አገር በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እስከ መቼ ትቀጥላለች? መንግሥትስ በዚህ ሁኔታ አገር እየመራሁ ነው ለማለት ድፍረት ይኖረዋል? በጭራሽ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚለያዩት ይልቅ አንድ የሚያደርጉት እጅግ በጣም በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ከማንም በላይ ያውቃል፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ የአገሪቱ ግዛቶች ውስጥ ለዘመናት የጋራ እሴቶቹን አስከብሮ የኖረው ይህ ጨዋ ሕዝብ የሥነ ልቦና አንድነቱ ለማመን የሚያዳግት ነው፡፡ መስተጋብሩ በጣም የጠበቀ ከመሆኑ የተነሳ በንግግር ብቻ ሳይሆን በዓይን ጥቅሻም ይግባባል፡፡ ይህንን ጨዋ ሕዝብ መነጣጠል አይቻልም፡፡ የተለያዩ ወራሪዎችና ተስፋፊዎች አልተሳካላቸውም፡፡ ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያ ውስጥ በቆየባቸው አምስት ዓመታት ሞክሮ አልተሳካለትም፡፡ ይልቁንም ለዓለም የአርነት ግንባር ተዋጊዎች ትልቅ ልምድ የሆነ የሽምቅ ውጊያ በማድረግ፣ ፋሽስት ኢጣሊያን መቆሚያ መቀመጫ አሳጥቷል፡፡ ከዚያ ቀደም ሲል ደግሞ አንፀባራቂውንና የጥቁር ሕዝቦች መመኪያ የሆነውን ታላቁን የዓደዋ ጦርነት በድል አጠናቆ ተምሳሌትነቱን አሳይቷል፡፡ ይህንን አይበገሬና ጠንካራ ሕዝብ ይዞ ስንትና ስንት ተዓምር መሥራት እየተቻለ በአግባቡ መምራት ሲያቅት፣ የዘመኑን መሪዎች ብቃት ጥያቄ ውስጥ ይከታል፡፡ የዚህን ጨዋና ጀግና ሕዝብ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማስጠበቅ አቅቶ፣ ልጆቹን የብሔር ጦርነት ውስጥ የሚከት ተልካሻ ድርጊት ውስጥ መገኘት ያሳፍራል፡፡ ይህ ጨዋ ሕዝብ ይከበር፡፡ ይህች ታሪካዊት አገር በአግባቡ ትመራ፡፡
ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ነበረች፡፡ ወደፊትም መሆን ትችላለች፡፡ ይህን ራዕይ ዕውን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ የዚህን ጨዋና ኩሩ ሕዝብ ፍላጎት ያለማንገራገር በመፈጸም ብቻ ነው፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱን በምልዓት ለማስከበር የሚቻለው የሕግ የበላይነትን ከልብ በመቀበል ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የሠፈሩ መሠረታዊ መብቶችን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ፣ ሕዝብ በገዛ አገሩ ጉዳይ ባይተዋር ሳይሆን ወሳኝ መሆኑን ማመን፣ የብሔር ብቻ ሳይሆን የሐሳብ ብዝኃነትን ማስተናገድ፣ ሥልጣን የሚያዘው በነፃና በፍትሐዊ ምርጫ መሆኑን ከልብ መቀበልና ለተግባራዊነቱ መትጋት፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የፀጥታ ኃይሎች በሙሉ ለማንም ወገንተኛ ሳይሆኑ ታማኝነታቸው ለአገር ብቻ መሆኑን ማረጋገጥ፣ የዳኝነት ነፃነትን በተግባር ማሳየት፣ የሀብትና የሥልጣን ፍትሐዊ ክፍፍል እንዲኖር ማድረግ፣ ሕገወጥነትን ማጥፋት፣ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ፀር የሆኑ አፍራሽ አመለካከቶች የሚገሩባቸው የውይይት መድረኮችን በስፋት መፍጠር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት የሚደራጁበትና የሚሠሩበት ለሁሉም እኩል የሆነ ምኅዳር መፍጠር፣ ዛሬ ገዥ የሆነ ነገ ተቃዋሚ የሚሆንበት አጋጣሚ መኖሩን መተማመን፣ ወዘተ. አገርን ከአዘቅት ለማውጣት ጠቃሚ ነው፡፡ የበሳል አመራር ውጤትም የሚለካው በዚህ ብቻ ነው፡፡ የአመራር ብቃት አለመኖር አንዱ ማሳያው ካለፉት ሦስት ዓመታት ችግሮች ውስጥ መውጣት አለመቻሉ እንደሆነ መተማመን ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን መከራው ለአገር ነው፡፡ ለዚህም ነው አገሪቱ እስካሁን ያለችው በሕዝብ እንጂ በብቁ አመራር አይደለም የሚባለው!