Wednesday, February 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹በዩኒቨርሲቲዎች የተፈጠረው ችግር ለውጥ ቢታይበትም ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል ማለት አይቻልም››

‹‹በዩኒቨርሲቲዎች የተፈጠረው ችግር ለውጥ ቢታይበትም ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል ማለት አይቻልም››

ቀን:

ትምህርት ሚኒስቴር

ከኅዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አጋጥሞ በነበረው ችግር ለውጥ ቢታይም፣ ሙሉ በሙሉ እንዳልተቀረፈ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ዓርብ ታኅሳስ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ እንደተናገሩት፣ በዩኒቨርሲቲዎች በተፈጠረው ችግር ለውጥ ቢታይም ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል ማለት አይቻልም፡፡ በተፈጠረው ችግር ሳቢያ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደቱ መስተጓጎሉንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የመማር ማስተማሩ ሒደት ከመታወኩ በተጨማሪ፣ በአራት ተማሪዎች ላይ የሞት አደጋ ማጋጠሙን ተናግረዋል፡፡

በተፈጠረው ችግር ሳቢያ ሁኔታውን በመፍራት ተማሪዎች ከግቢ የመውጣትና ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸውን የማስወጣት ችግር ገጥሞ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ችግሩን ለማስቆም ሲባልም መንግሥት በፌዴራልና በክልል መሥሪያ ቤቶች ያሉ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሠማሩ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ ‹‹በተቋማቱ ከግቢ ጥበቃ ኃይል በላይ የሆነ ሁኔታ ስለገጠመና በግቢ ውስጥ ያሉ ተማሪዎችም ደኅንነት ስላልተሰማቸው፣ የግቢ ጥበቃ ኃይሉን በፌዴራል ፖሊስና በፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች የማጠናከር ሥራ ሠርተናል፤›› ብለዋል፡፡

በተፈጠረው ችግር ሥጋት ውስጥ የገቡ ተማሪዎች ግቢ ውስጥ አንቆይም የሚል ጥያቄ አንስተው እንደነበር የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ‹‹ይህንን የማረጋጋት ሥራ የሚከናወነው፣ በተቋማት ውስጥ ያጋጠመንን ዝርዝር ችግር የሚረዱና መፍትሔ የሚሰጡ ወደ ሃያ ተቋማት ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ትናንትናና ዛሬን ጨምሮ የተሠማሩ የፌዴራል መንግሥቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አሉ፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ‹‹በተቀሩት ተቋማት የሁኔታዎችን መቀየር ዓይተን እየተከታተልን ተጨማሪ የሰው ኃይል እናሠማራለን የሚል ዕቅድ ነው የያዝነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

በሚቀጥሉት ቀናት ሰፋ ያለ ውይይት ከተማሪዎች ጋር እንደሚደረግ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የትምህርት ተቋማቱን በየጊዜው እየተነሱ የሚያምሷቸው ጉዳዮች እንዴት መፈታት እንዳለባቸው ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

‹‹ተማሪዎችን አሁን ካሉበት ድባብ የማውጣት፣ ሰላማዊ የመማር ማስተማሩን ወደ ቦታው መመለስ፣ ተቋርጠው የነበሩ ትምህርቶችንና የባከኑ ጊዜያት እንዲካካሱ የማድረግና የዓመቱ የትምህርት ጊዜ ተቻችሎ በሚሄድበት ላይ ሰፊ ሥራ ይከናወናል፤›› ብለዋል፡፡

ሕይወታቸው እንዳለፈ የተጠቆሙት ተማሪዎች የት ዩኒቨርሲቲ ይማሩ እንደነበርና ከየት አካባቢ እንደመጡ እንዲገልጹ የተጠየቁት ሚኒስትር ዴኤታው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ቁጥሩና አካባቢው የት እንደሆነ ሳይሆን በኢትዮጵያ ላይ የደረሰ አደጋ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ቁጥሩ ብዙ ጠቃሚ እንዳልሆነ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ‹‹የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች አንድነት የሚያውክ፣ የሕዝቦችን ፍቅርና አብሮነትን መበጠስ የሚፈልግ ኃይል ባደረገው ጥረት የተከሰተ ችግር ነው፤›› ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎችም ሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር ችግሩን በመፍራት ከግቢ የወጡ ተማሪዎችን እንዲመለሱ ጥሪ እያቀረቡ ነው፡፡ በቀጣይ በተማሪዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ኃላፊነት ማን ነው የሚወስደው? የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ደኅንነታቸውን መጠበቅ ያለባቸው ራሳቸው ተማሪዎቹ ናቸው፡፡ ሌላ ተግባር ውስጥ የገባን ተማሪ ማጋለጥ አለባቸው፡፡ ለየትኛውም ኃይል መጠቀሚያ መሆን የለባቸውም፤›› ብለዋል፡፡

እየተከሰቱ ላሉ ችግሮች ዋነኛ ምክንያቶችና የችግሮች ምንጭ ምንድናቸው የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር ቀርቦ ሲመልሱ፣ ‹‹ምንጩ ጠላት ያዘጋጀው አጀንዳ ነው፡፡ ሌላ ነገር አይደለም፡፡ ጉዳዩ ፖለቲካዊ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከመውጫ ፈተናው ጋር በተያያዘ ፈተናውን ማለፍ የማይችሉ ተማሪዎች ዕጣ ፈንታ ምንድነው? አንዳንዶች ወደ ዩኒቨርሲቲ ስንገባ ስላልተነገረን ጉዳዩን ቀድመን አናውቀውምና አሁን ላይ ፈተና ውሰዱ ማለት የመብት ጥሰት ነው እያሉ ያነሳሉ፣ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው? የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በሰጡት ምላሽም፣ ‹‹የመውጫ ፈተና እግረ መንገድ የመጣ ጥያቄ ነው፡፡ የተነሳውም በጥቂት ተቋማት ነው፡፡ የሚሰጠውም መውጫ ላይ እንጂ መግቢያ ላይ አይደለም፡፡ የመብት ጥሰት ነው ከተባለም አይደለም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹በመጀመርያው ፈተና ያልተሳካለት ተማሪ ሁለት ተጨማሪ ዕድል ያገኛል፡፡ እስኪበቃ ድረስ መፈተን አለበት፡፡ ማብቃት የተቋማቱ፣ መብቃት ደግሞ የተማሪው ግዴታ ነው፡፡ በዚህ የመውጫ ፈተና ሁለት ጊዜ ተጨማሪ ዕድል አግኝቶ ያልበቃ ተማሪ መብቃት ይኖርበታል፡፡ ያልበቃው ተማሪ እንዲበቃ ይሆናል፡፡ በራሱም በተቋማቱም፤›› ብለዋል፡፡

ተማሪዎች ወደ ግቢ ሲመለሱ ዋስትናቸው ምንድነው የሚል ጥያቄም ከሪፖርተር ቀርቦላቸው የነበረ ሲሆን በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ዋስትናቸው ሕገ መንግሥቱ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በምሽት የተማሪዎች እንቅስቃሴ እንዳይኖር መደረጉን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ጉዳይ ስለሚያስገድድ ነው ብለዋል፡፡

ከዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ተማሪዎቹ አትውጡ እንደሚባሉ፣ ለዚህ ምክንያቱ ሲወጡ አደጋ ይደርስባቸዋል ተብሎ ስለሚታሰብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ኅዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የተፈጠረ ችግር ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተዛምቶ የአራት ተማሪዎች ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት ከመሆኑ ባሻገር፣ ዘጠኝ ያህል ዩኒርሲቲዎች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የማስተማር ሥራቸውን አቋርጠዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የካቲት አብዮት – ጥያቄዎችሽ ዛሬም እየወዘወዙን ነው!

በበቀለ ሹሜ አጭር መግቢያ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከ1960ዎች ወጣቶች ርዝራዦች አንዱ...

የሰሞኑ የ“መኖሪያ ቤቶች” የጨረታ ሽያጭ ምን ዓይነት ሕጋዊ መሠረት አለው?   

በዳዊት ዮሐንስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አየር ላይ ከሚንሸረሸሩ ዜናዎች...

ሁለቱ ወጎች፡ ከሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! እስከ በዓሉ ቤርሙዳ

በተክለ ጻድቅ በላቸው ሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! ከሁለት ሦስት ዓመት...

ለትግራይ ክልል ድርቅ ተፈናቃዮች አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ...