Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየደኅንነት ዕቅዶች መፈጸም ባለመቻላቸው የአገሪቱ ቀውስ ወደ አሳሳቢ ደረጃ እየደረሰ ነው ተባለ

የደኅንነት ዕቅዶች መፈጸም ባለመቻላቸው የአገሪቱ ቀውስ ወደ አሳሳቢ ደረጃ እየደረሰ ነው ተባለ

ቀን:

  • የኦሮሚያ ክልል መከላከያንና ፌዴራል መንግሥትን ወቅሷል
  • የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ በዝግ እንደቀጠለ ነው

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት የአገሪቱ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት ከአንድ ወር በፊት ያስቀመጠውን የአንድ ዓመት ዕቅድ መንግሥት ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻሉ፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስና ግጭቶች አሳሳቢ ደረጃ እየደረሱ ነው ተባለ፡፡

በኅዳር ወር 2010 ዓ.ም. መጀመርያ ላይ የተሰበሰበው ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት የአገሪቱን ግጭቶችና የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት ኢሕአዴግ ካስቀመጠው ፖለቲካዊ መፍትሔ በተጓዳኝ፣ በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች የፀጥታ አካላት ጥምረት የተቀናጀ የፀጥታና ደኅንነት ዕቅድ ወጥቶ ነበር፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ መፍትሔው ባለመቅደሙ የብሔራዊ ምክር ቤቱ ያፀደቀው የደኅንነት ዕቅድ ሙሉ ለሙሉ በተቀናጀ አኳኋን ወደ ትግበራ መግባት አለመቻሉን፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ ከፍተኛ የኢሕአዴግ አመራር ገልጸዋል፡፡

በዚህም የተነሳ በአገሪቱ ብሔር ተኮር ግጭቶች እየተዛመቱ ወደ አሳሳቢነት በመቀየር ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት አባላት ማለትም የሁሉም ክልሎች ፕሬዚዳንቶችና የፍትሕና ፀጥታ አካላት፣ የፌዴራል መንግሥት የደኅንነትና መረጃ አገልግሎት፣ እንዲሁም የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ጄኔራል መኰንኖች በተገኙበት መካሄዱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በወቅቱ መግለጫ ሰጥተው የነበሩት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በመገምገም አገሪቱ ካለችበት የፀጥታ ቀውስ እንድትወጣ የአንድ ዓመት ዝርዝር ዕቅድ መቀመጡን ተናግረው ነበር፡፡

በዕቅዱ ከተካተቱት መካከል በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል ተቀስቅሶ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉትን ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ማድረግ፣ ተፈናቃዮቹን በአስቸኳይ ማቋቋም፣ በሁለቱ ክልሎች መካከል ተቀስቅሶ በነበረው የዜጎችን ሕይወት የቀጠፈ ግጭት ላይ በተሳተፉ የፀጥታ አካላትና የፖለቲካ አመራሮች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ ዋናዎቹ እንደነበሩ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

የደኅንነት ምክር ቤቱ ይኼንን ዕቅድ ያስቀምጥ እንጂ የአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስና ግጭቶች መባባስና ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ እንዲሁም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተቃውሞዎች ባለፉት ሁለት ሳምንታት እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሰኞ ታኅሳስ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ሜታ ወረዳ ጨለንቆ አካባቢ በመከላከያ ሠራዊትና በአካባቢው ነዋሪዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት 15 ነዋሪዎች መገደላቸውን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በማግሥቱ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ጣታቸውን ቀስረው ሐዘናቸውን በይፋ በክልሉ ቴሌቪዥን ገልጸዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ ድጋፍ አለመጠየቁን የተናገሩት አቶ ለማ፣ ሠራዊቱን ማን እንዳዘዘ እንደማያውቁ ነገር ግን የተፈጸመው ጅምላ ግድያ መሆኑንና የክልሉ መንግሥት ሁሉንም መርምሮ ለሕግ እንደሚያቀርብ አስታውቀዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ አካላት ከሕዝቡ ጎን እንዲቆሙና ደኅንነቱን እንዲያረጋግጥም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ይኼንን ተከትሎ ማክሰኞ ታኅሳስ 3 ቀን 2010 ጠዋት በጨለንቆ ተፈጸመ የተባለውን ግድያ ለማውገዝ የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ተቃውሞ የወጡ መሆናቸውን የገለጹት የሪፖርተር ምንጮች፣ ተቃውሞውን ለመበተን በአካባቢው የተገኘው የመከላከያ ሠራዊት ከኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ጋር መወዛገባቸውን ገልጸዋል፡፡ ተቃውሞው በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ ማድረግ እንጂ በኃይል መበተን አይገባም በማለት ከኦሮሚያ ፖሊስ አባላት በመነሳቱ የተፈጠረው አለመግባባት፣ በሁለት ወታደሮች መካከል መሣሪያ መማዘዝ መፈጠሩን ምንጮች ይናገራሉ፡፡

በሁለቱም ወገኖች የሞቱና የቆሰሉ መኖራቸው ቢናፈስም ሪፖርተር ከክልሉ ፖሊስም ሆነ ከፌዴራል መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር ለማጣራት ያደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ ማረጋገጥ አልቻለም፡፡ በሁለቱ የፀጥታ አካላት የተፈጠረው ግጭት ወዲያውኑ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተቀሰቀሱ ብሔር ተኮር ግጭቶች የተማሪዎች ሕይወት ማለፉን፣ የመማር ማስተማር ሒደቱ መደናቀፉንና ወላጆች ልጆቻቸውን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እያወጡ መሆኑን መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በእነዚህ ግጭቶች መስፋፋት ውስጥ የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ፖለቲካዊ መፍትሔ ላይ ለመድረስ በሩን ዘግቶ ስብሰባ ተቀምጧል፡፡

ሰኞ ታኅሳሰ 2 ቀን የተጀመረው ይኼ ስብሰባ ሳምንቱን የቀጠለ ቢሆንም፣ የውይይቱ አጀንዳዎችም ሆነ እስካሁን ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች አልተገለጹም፡፡ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ስብሰባው መቀጠሉን ዓርብ ታኅሳስ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ማምሻውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ይህንን ስብሰባ በተመለከተም ዝርዝር መረጃ እንደማይሰጡ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...