ዑራጓይ ለምታስተናግደው የ2018 ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ፣ ኢትዮጵያ በማጣሪያው ስትሳተፍ ቆይታለች፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ከሁለት ሳምንት በፊት የናይጄሪያ አቻውን በአዲስ አበባ ስታዲየም አስተናግዶ ነጥብ ተጋርቶ በአቻ ውጤት መለያየቱ ይታወሳል፡፡
ቡድኑ የመልስ ጨዋታውን ለማከናወን ወደ ናይጄሪያ ያመራው ባለፈው ሐሙስ ታኅሣሥ 5 ቀን 2010 ዓ.ም. መሆኑም ይታወቃል፡፡ ይሁንና ታዳጊዎቹ እንደ አንድ ብሔራዊ ቡድን የፌዴሬሽኑን ትኩረት እንዳላገኙ የቡድኑ አባላት ወደ ናይጄሪያ ከማቅናታቸው አስቀድሞ ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ ሌላው ቀርቶ የቡድኑን አጠቃላይ የዝግጅት ሒደትና የጉዞ ቅድመ ሁኔታ በሚመለከት፣ በፌዴሬሽኑ ይመለከታቸዋል የሚባሉ ክፍሎች ተገቢውን መረጃ መስጠት የሚያስችል አቅም እንዳልነበራቸው ታይቷል፡፡ ይህም በምርጫው ምክንያት ተቋሙን በኃላፊነት የሚመራ አካል ባለመኖሩ ምክንያት የተፈጠረ ክፍተት ስለመሆኑ የሚናገሩ አሉ፡፡
በእንስቷ አሠልጣኝ ሰላም ዘርዐይ ሲዘጋጅ የቆየው የሴቶች ብሔራዊ ቡድን፣ ከሜዳው ውጪ በናይጄሪያ በሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን በዝግጅት ወቅት የነበረውን የፌዴሬሽኑን ክትትል ትኩረት ማነስ ምክንያት ማድረግ እንደማይፈልጉ፣ ከቡድኑ አባላት አንዳንዶቹ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በኅትመት ምክንያት ውጤቱን መግለጽ ባንችልም፣ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቅዳሜ ታኅሣሥ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ተከናውኗል፡፡