Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  በሕግ አምላክሕጉን መሙላት ያልቻሉት የማሟያ ምርጫዎች

  ሕጉን መሙላት ያልቻሉት የማሟያ ምርጫዎች

  ቀን:

  በውብሸት ሙላት

  በተለያዩ እርከን ላይ የሚገኙ የሕዝብ ምክር ቤቶች አባላታቸው በሚጓደሉባቸው ጊዜያት የማሟያ ምርጫ እንዲደረግ ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለውን የፌዴራሉን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በምሳሌነት ብንወስድ እንኳን ቢያንስ ሁለት አባላቱ እንደሞቱ ይታወቃል፡፡ አንዱ ከአዲስ አበባ፣ ሌላዋ ደግሞ ከአማራ ክልል የተወከሉ፡፡ ይሁን እንጂ በአሠራሩ ላይ የሁለት ድምፅ መጉደል ልዩነት እንደማያመጣበት በመገመትም ይሁን በሌላ ምክንያት የማሟያ ምርጫ አልተደረገም፡፡ የተወከሉበት የምርጫ ወረዳ የሚኖረው ሕዝብም በተለየ ሁኔታ የሚጠይቀው የሚወከልበትና እንደራሴ የሚያስፈልግበት ምክንያት እንደሌለ  ከግምት ባለማስገባትም ሊሆን ይችላል የማሟያ ምርጫው ያልተደረገው፡፡

  የውክልና ዴሞክራሲ ሥራ ላይ በሚውልባቸው ማናቸውም ተቋማት ዘንድ የተወከለው ሰው በተለያዩ ምክንያቶች በወኪልነቱ ላይቀጥል ይችላል፡፡ በወኪልነቱ ካልቀጠለ ተወካዩ የሕዝብ እንደራሴነቱ ይቀራል ማለት ነው፡፡ በእንደራሴነት የሚሠራባቸው በርካታ ተቋማት አሉ፡፡ ከቀበሌ ምክር ቤቶች እስከ ፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሉት ውስጥ እንደራሴዎች ይወከላሉ፡፡ የእነዚህ ምክር ቤቶች አባላት የሆኑ እንደራሴዎችም በተደራቢነት የሹመት ቦታዎችን ሊይዙ ይችላሉ፡፡

  እንደራሴ የሚሆነውን ሰው ለመምረጥ ምርጫ ይደረጋል፡፡ በምርጫ ውጤቱ አሸናፊ የሆነው እንደራሴ ይሆናል፡፡ አንድ እንደራሴ በተለያዩ ምክንያቶች ውክልናው በሚቀርበት፣ ወይም ደግሞ በሌላ መንግሥታዊ መዋቅርና የሥልጣን እርከን ለማገልገል ሲባል ቀድሞ ከነበረበት ምክር ቤት ወደ ሌላ ምክር ቤት መዛወር ሊጠበቅበት ይችላል፡፡ እንዲዛወር የሚፈልገው ራሱ ተመራጩ ወይም ፓርቲው ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥ የሕዝብ ፍላጎትም ሊኖር ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ የእንደራሴነት ቦታው ክፍት ይሆናል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ክፍተት ሲፈጠር በማሟያ ምርጫ ይደረጋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረትም የድጋሚ ምርጫ የሕግ ማዕቀፍን ከአተገባበሩ አንፃር ፍተሻ ማድረግ ነው፡፡  

  በኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 መሠረት፣ ምርጫ ለአምስት ዓቢይ ተግባራት ሊደረግ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው፣ የፌዴራልና የክልል የሕዝብ ተወካዮችን ለመምረጥ በየአምስት ዓመቱ የሚደረገውና ‘ጠቅላላ ምርጫ’ (general elections) በመባል የሚታወቀው ነው፡፡

  ሁለተኛው ደግሞ፣ የቀበሌ፣ የወረዳና እንደሁኔታው የዞን ምክር ቤቶች ላይ የሚገኙ አባላትን ለመምረጥ የሚደረጉ ሕጉ ላይ እንደተገለጸው ‘የአካባቢ ምርጫ’ (local elections) በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ እነዚህም ቢሆኑ በየአምስት ዓመቱ ነገር ግን የጠቅላላ ምርጫው በሚደረግብት ሳይሆን በሌላ ጊዜ የሚደረጉ ናቸው፡፡

  ሦስተኛው ደግሞ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተጓደሉ የምክር ቤት አባላትን ለመተካት ወይንም ቀድሞ ሕዝቡ የመረጠውን ወኪል ካወረደው በኋላ በምትኩ የሚመረጥበት ሥርዓት ሲሆን ‘የማሟያ ምርጫ’ (by-elections) ለማከናወን ምርጫ ይደረጋል፡፡

  አራተኛው፣ የምርጫ ቦርድ በተለያዩ ምክንያቶች አንድ የምርጫ ጣቢያ ላይ ችግር ሲከሰት ወይም ተወዳዳሪዎች እኩል ድምፅ በሚያገኙበት ጊዜ ለመለየት ሲባል የሚደረግ ሲሆን ስሙም  ‘የድጋሚ ምርጫ’ (reelection) ይባላል፡፡

  የመጨረሻው በተለያዩ ጉዳዮችና ምክንያቶች የሕዝብን ፍላጎት ለመለካት እንዲሁም የሕዝብን ውሳኔ ለማወቅ ሲባል የሚደረግ ምርጫ ነው፡፡ ይህም ‘ሕዝበ ውሳኔ’ (referendum) በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ግን ሦስተኛው ነው፡፡

  የማሟያ ምርጫ

  በአመኔታጦት ምክንያት ከተነሳ፣ በሥነ ምግባር ጉድለት ከምክር ቤት ከተባረረ፣ በወንጀል ተከስሶ የምክር ቤት ወንበሩን ካጣ፣ በሞት ወይም በሌሎች ምክንያቶች ምክር ቤቶች አባላታቸው ሲጓደሉ የማሟያ ምርጫ ይደረጋል፡፡

  በአገራችን በአመኔታጦት እንዲወርዱ የተደረጉ ወኪሎች ስለመኖራቸው በሰፊው የሚታወቀው በ1993ቱ የሕወሓት ክፍፍል ጊዜ የአንጃው ወገን የሆኑቱ የእነስየ አብርሃ ቡድንን ነው፡፡ የማሟያ ምርጫ በሌሎች ጊዜያትም ተከናውኗል፡፡ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የአዲስ አበባ ምክር ቤትን ስላልተረከበ የማሟያ ምርጫ ተደርጓል፡፡

  በአመኔታጦት ካልሆነ በስተቀር በሌሎች ምክንያቶች ስለሚደረጉ የማሟያ ምርጫዎች ዘርዘር ያለ ሕግ የለም፡፡ በአመኔታ ዕጦት ምክንያት አንድ ወኪል ከወንበሩ በመነሳቱ ለሚኖረው የማሟያ ምርጫ ዕጩዎች እንዴት ሊቀርቡ እንደሚችሉ እንይ፡፡ በመጀመሪያ በየትኛውም አገር፣ ኢትዮጵያንም ጨምሮ የወረደው ወኪል በራሱ ጊዜ አልወዳደርም እስካላለ ድረስ የመወዳደር መብት አለው፡፡ ሌሎች ተወዳዳሪዎችን ግን የይውረድልኝ ጥሪ ያቀረቡት አካላት ዕጩ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ማለትም በዜጎች አነሳሽነት ከሆነ የግል ተወዳዳሪ፣ በፓርቲ አነሳሽነት ከሆነ ደግሞ ፓርቲው ያቀርባል፡፡

  በኢትዮጵያ ሕግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥነ ምግባር ጉድለት ምክንያት አንድን ተወካይ ካባረረ ለዚህ ለጎደለው ወንበር የሚደረገው የማሟያ ምርጫ ላይ ይኼው በሥነ ምግባር የተባረረው ሰው መልሶ እንዲወዳር ሕጉ መብት ይሰጣል፡፡

  ይሁን እንጂ የማሟያ ምርጫ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከናወን ስለሚችል እስኪ ትንሽ አፍታተን እንመለከተው፡፡ የብዙ ነገሩ ማጠንጠኛ ብሔርን መሠረት ያደረገ ፌዴራላዊ አወቃቀር ከመሠረትን ሩብ ምዕት ዓመት ሞላን የሽግግር ዘመኑ ሲጨመር፡፡ ፌዴራላዊ አወቃቀር፣ ራስ ገዝነታቸውን መጠበቅ የሚፈልጉ ክፍሎች በጋራ በማዕከላዊው መንግሥት መሳተፍ በሚያስችል መልኩ አገርን የማቋቋምና የማስተዳደር ጥበብን የሚከተል አሠራር ነው፡፡ ማዕከላዊውን መንግሥት የሚዋቀረው ደግሞ በፌዴሬሽኑ መሥራቾች ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሁኔታ እንደ ሌሎች ፌዴራላዊ አገሮች መሥራቾቹ ክልሎች ሳይሆኑ፣ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው፡፡ ይኼ ራስን በራስ ማስተዳደር በምርጫ ሕጉ መግቢያ ላይ በመርህነትም በግብነትም የተቀመጠ ነው፡፡

  ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በፌዴራላዊ አስተደዳር ሥርዓት ራሳቸውን በራሳቸው ከማስተዳደራቸው ባለፈ የጋራ በሆነው፣ በኅብረት በመሠረቱት ፌዴሬሽን ውስጥም የመሳተፍ መብት አላቸው፡፡ የጋራ የሆኑትን ተቋማት በጋራ ይመራሉ፣ በጋራ ያስተዳድራሉ፡፡ በመሆኑም በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39(3) መሠረት እነዚህ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በፌዴራሉ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የመወከልና የመሳተፍ መብት አላቸው፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ካሉት ተቋማት ውስጥ የፌዴሬሽን፣ የሕዝብ ተወካዮችና የሚኒስትሮች ምክር ቤቶች፣ የዳኝነት ተቋሙ እንዲሁም ሌሎችም  ይገኙበታል፡፡ 

   ከላይ ከተገለጹት ተቋማት ውስጥ በሁለቱ ምክር ቤቶች የሚወከሉ አባላት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በምርጫ የሚፈጸሙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ምክር ቤቶች ወይም ከውጭ የሚመረጡ ሰዎች ደግሞ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊሾሙ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ሚኒስትሮችንም ይሁኑ ሌሎች ተሿሚዎች፣ ውክልናቸው በቀጥታ በሕዝቡ ባይሆንም ውክልና ግን አላቸው፡፡

  ከላይ እንደተገለጸው የዴሞክራሲ ሥርዓት፣ አንድም በቀጥታ ካልሆነም በውክልና ይተገበራል፡፡ ከተወሰኑ ጉዳዮችና ዝቅተኛ የሕዝብ ቁጥር ባላቸው የአስተዳደርርከኖች በስተቀር፣ አገሮች የውክልና ዴሞክራሲን ይጠቀማሉ፡፡ ስለሆነም ሕዝቡ እንደራሴውን ከመረጠ በኋላ ውክልናውን የተቀበለው ሰው የመረጠውን ሕዝቡ በመወከል የተለያዩ ተግባራትን እንደ ሕዝቡ በመሆን ይፈጽማል፡፡ እነዚህን ተግባራት የሚፈጽሙት እንደራሴዎች ቦታቸውን ሲለቁ የማሟያ ምርጫ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

  የማሟያ ምርጫ ምክንያቶችና አመራረጡ

  የማሟያ ምርጫ የሚደረገው በተለያዩ ዕርከኖች የሚገኙ ምክር ቤቶች በተጓደሉባቸው አባላት ምትክ ሌላ ለመምረጥ ከፈለጉ ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ ለመጓደሉ ምክንያት የሚሆነው ደግሞ ሞት፣ ከምክር ቤቱ ሲሰናበት፣ መራጩ አመኔታ ሲያጣበትና ሲያወርደው፣ በፍርድ ቤት ውሳኔ ሲታገድ ወዘተ. ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ምክንያቶች የምርጫ አዋጁ አንቀጽ 30 ላይ መረዳት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ የማሟያ ምርጫ የሚደረገው የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ሊያልቅ ከስድስት ወራት ያላነሰ ከቀረው ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ካነሰ እንደ ሕጉ የማሟያ ምርጫ አይፈቀድም፡፡

  ምክር ቤቱ የማሟያ ምርጫ እንዲደረግ ምርጫ ቦርድን በጠየቀ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ምርጫው መከናወን አለበት፡፡ እንግዲህ የማሟያ ምርጫ ብዙ የሚደረገው አንድ እንደራሴን ከአንድ የምርጫ ወረዳ ለመምረጥ ስለሚሆን በተለይ በኢትዮጵያ እንደ ጠቅላላ፣ የአካባቢ፣ የሕዝበ ውሳኔና የድጋሚ ምርጫ ሰፊ የምርጫ ቅስቀሳ አይኖርም፡፡ አገራዊ አጀንዳ ላይሆን ይችላል፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይሁኑ ግለሰቦች ላይወዳደሩ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ማሟያ ምርጫ ሲደረግ የሕዝብ ትኩረት ማነሱ አይቀርም፡፡ ይኼ የማሟያ ምርጫ ሲደረግ ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው የምክር ቤት አባላት ሞተው እንኳን መተካት ሳያስፈልግ ወንበራቸው ክፍት ሆኖ መቀጠሉን ሳንረሳ ነው፡፡

  የማሟያ ምርጫ ማከናወንን ግድ የሚሉ ሁኔታዎች ግን አሉ፡፡ አንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆነ ሰው  የአንድ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዲሆን ክልሉን የሚያስተዳድረው ፓርቲ ቢፈልግ ይህ ሰው ከፌዴራሉ በመለቀቅ የክልሉ ምክር ቤት አባል መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቀድሞ ከነበረበት ምክር ቤት በራስ ፈቃድ አባልነቱን ማቋረጥ አለበት፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደርበት የምርጫ ጣቢያ ላይ ያለውን ተመራጭ ከወረደ በኋላ እዚያ ቦታ ላይ ተወዳድሮ ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡ እነዚህን ሁለትደቶች ካለፈ በኋላ ነው የክልል ምክር ቤት አባል መሆን የሚችለው፡፡

  በአገራችን የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል ለመሆንም ይሁን ለክልል የቢሮ ኃላፊ ለመሆን እንደሌሎች የፓርላማ ሥርዓትን እንደሚከተሉ አገሮች የሕግ ግዴታ የለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትርና የክልል ርዕሰ መስተዳድር ለመሆን ግን እንደቅደም ተከተላቸው የፌዴራልና የክልል ምክር ቤት አባል መሆን ግድ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን በሚመለከት ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 73(1) ላይ ተደንግጓል፡፡ የክልሎቹ ሕግጋተ መንግሥታትም በተመሳሳይ መልኩ ይኼንኑ አሠራር በመከተል ተደንግጓል፡፡ ስለሆነም አንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበረ ወይም ባይሆንም እንኳን የክልል ምክር ቤት አባል እስካልሆነ ድረስ በርዕሰ መስተዳድርነት ክልል ሊመራ አይችልም ማለት ነው፡፡ ይህ አሠራር ለወረዳም፣ ልዩ ዞንም ቀበሌም ይሠራል፡፡

  እዚህ ላይ ከላይ ከተገለጸው አሠራር የሚያፈነግጥ ልማድን ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡ አንዳንድ ክልሎች የወረዳ አስተዳዳሪ ሆኖ የተመረጠው ሰው በመካከል ከሥልጣኑ ከተነሳና ከወረዳው ምክር ቤት አስተዳዳሪ የሚሆን ሰው ሳይኖር ከቀረ ወይም ሌላ ሰው መሾም ሲፈለግ ተጠባባቂ አስተዳዳሪ በማለት ይሾማሉ፡፡ ይህ ሰው የምክር ቤት አባል ያልሆነ ነገር ግን በክልል ርዕሰ መስተዳድር የተሾመ ነው፡፡ መርሁና የክልሎቹ ሕግጋተ መንግሥታት ከደነገጉት ባፈነገጠ መልኩ የሚደረግ አሠራር መሆኑ ነው፡፡

  ከላይ እንደተገለጸው የፌዴራል የሕዝብ ተወካይ የነበረ ሰው የክልል ርዕሰ መስተዳድር ለመሆን ቀድሞ የነበረበትን በመተው የክልሉ ምክር ቤት አባል መሆን ይጠበቅበታል ብለናል፡፡ እንደው ነገሩ የይስሙላ ካልሆነ በስተቀር መታለፍ ያለባቸው የሕግ መሰናክሎች ብዙ ናቸው፡፡ በቅድሚያ ርዕሰ መስተዳድር የሚሆነው ሰው በማሟያ ምርጫ የሚወዳደርበት ወረዳ ላይ ያለው ተወካይ መውረድ አለበት፡፡ ምናልባት ቀድሞ የነበረው ርዕሰ መስተዳድርና እንደ አዲስ የሚሾመው ሰው ተመሳሳይ የምርጫ ወረዳ የሚገኙ ከሆነ የቀድሞውን በማውረድ እንደገና እዚያው ቦታ ላይ የማሟያ ምርጫ ማድረግ ነው፡፡

  ሁለቱ አንድ የምርጫ ወረዳ ላይ የማይገኙ ከሆነ ግን አዲስ ለሚሾመው ሲባል የእዚያን አካባቢ ተወካይ ማውረድ ግድ ይላል ማለት ነው፡፡ ቀጥሎ የማሟያ ምርጫ ማድረግ፡፡ ይኼ ለሚሾመው ሰው ሲባል፣ አሠራሩን ሕጋዊ መሠረት ለመስጠት በማሰብ ብቻ ካልሆነ በስተቀር አስቸጋሪ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ዴሞክራሲ በሰፈነበት፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ በሚደረግበት አገር ቢሆን ይኼን ማሳካት አዳጋች ነው፡፡ አዳጋች የሚያደርገው የመራጩ ሕዝብ ሁኔታም ነው፡፡

  ለአዲሱ ተመራጭ ሲባል ቀድሞ የነበሩትን ማውረድ ላይፈልግ፣ አዲሱን ላይመርጥ ስለሚችል ነው፡፡ ከእዚህ አንፃር የክልል ምክር ቤት አባል ያልሆነን ሰው በፓርቲ ውሳኔ አስቀድሞ የክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዲሆን መወሰን ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም፡፡ የፓርቲውን ውሳኔ ሕጋዊ ለማድረግ ሲባል የሕዝብን ፍላጎት መጠምዘዝ ሊያስከትል ስለሚችል እንዲሁም ውሳኔው ቀድሞ ማለፍ የሚጠበቅበትደቶች ስላሉ፡፡ 

  የክልል ርዕሰ መስተዳድርነት የክልል ምክር ቤት አባልነትን ታሳቢ ካደረገ ዞሮ ዞሮ አባል የሚሆነው በምርጫ ሕጉ መሠረት ስለሚሆን የምርጫ መርሆችንና ግቦችን ማክበር በሕግ ከሚተዳድርና ሕገ መንግሥታዊነትን ማስፈን ከሚፈልግ የፖለቲካ ሥርዓት የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ እስኪ የምርጫ ሕጉ ታሳቢ ያደረጋቸውን እንመልከት፡፡

  በቅድሚያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ያላቸው በመሆኑ በጠቅላላ ምርጫ የወሰኑትን በራሳቸው ጊዜ እስኪሽሩት (አመኔታ በማጣት) ድረስ የፓርቲ ሰዎች እንዳሻቸው መወሰን የለባቸውም፡፡ ቀጥሎ ማንኛውም ምርጫ ዓለም አቀፍ መርሆዎችን ተከትሎ መከናወን ስላለበት የምርጫ ቅስቀሳ፣ ውድድር ወዘተ እንዲኖር ማድረግን ታሳቢ ማድረግ አለበት፡፡ ለምሳሌ ከሰሞኑ በአገረ አሜሪካ በአላባማ ግዛት አንድ የሴኔት አባልን ለመምረጥ የነበረውን ዘመቻ ልብ ይሏል፡፡ አንድ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግሥታዊነትንና ለሕዝብ ታማኝ መሆንን ሁልጊዜም ማክበርን ይጠይቃል ማለት ነው፡፡

  ሦስተኛው የምርጫ መርህና ግብ ደግሞ ማንኛውም ምርጫ ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት ብቻ ሳይሆን ዓላማቸውንም ለሕዝቡ የሚያስተዋውቁበት መድረክ ቀድሞ መዘጋጀት አለበት፡፡ እዚህ በጣም ጥቂት የሚባሉ ናቸው፡፡ በምርጫ አዋጁ መግቢያ ላይም የተቀመጡ ናቸው፡፡ የሚተገበሩትም ለአንደኛው ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ዓይነት ምርጫዎች ነው፡፡ የሚፈጸሙበት ወሰን እስካልተደነገገ ድረስ ለአምስቱም ዓይነት ምርጫዎች ይሠራሉ ማለት ነው፡፡

  ይህ ከሆነ ከፍ ሲል ሕገ መንግሥታዊነት ዝቅ ሲል ደግሞ የሕግ የበላይነት ለማስረጽም በእነዚህ ጥላ ሥር እየኖሩ መሆንን ለማስመስከርም ሕጉ በሚጠይቀው ልክም ፍላጎትም መሥራት ነው፡፡ ሕጉን ወደ ሰው ፍላጎት ከመጎተት ይልቅ ሰዎች  በሕጉ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ አስቀድመው እንደሚሠሩ ማሰብን ልማድ ማድረግ ነው፡፡

  በንጉሠ ነገሥት፣ በፕሬዚዳንት ወይም በጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን በማቋቋም የተለያዩ ጠቅላይ ግዛቶችን በማቋቋም ለእነሱም አስተዳዳሪ በመሾም እንዲህ ዓይነቱ አሠራር በመጓዝ መንግሥታዊ ተግባራትን ማከናወን ከጀመርን፣ እንደ አገር መቶ ዓመት አልፎናል፡፡ ቀጣይነት ያለው የታወቀ አሠራርን አለመከተል፣ መርሆችን አለማዳበር፣ ከሕግ ይልቅ ለፖለቲካዊ ውሳኔ ቅድሚያ መስጠት ግን፣ መሻገር ያልቻልናቸው ችግሮች ናቸው ማለት እንችላለን፡፡ ከዚህ አንፃር የጎደሉ አባላትን ባለማስመረጥ እንዲሁም ማሟያ ምርጫዎች ሲደረጉም የምርጫ ሕጉ በሚጠይቀው ልክ አለመሥራት፣ የማሟያ ምርጫን ቢያንስ ሥነ ሥርዓቱንና ሒደቱን በማክበር ረገድ እንኳን አሁንም እንደተጓደለ ነው፡፡

  አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...