በጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
ባለፉት በርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የአሠራርና የአስተዳደር ለውጥ ከተደረገባቸው ነገሮች ውስጥ፣ የግብር አከፋፈልና አሰባሰብ ለመሆኑ አከራካሪ አይመስለኝም፡፡ የአገሪቱ የኢኮኖም ዘርፍ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፍ እየተቀየረ ሲመጣ፣ የግብር አከፋፈልና አሰባሰብ ሕግጋቶችና ደንቦችም በሚታይና ጉልህ በሚባል መንገድ ተቀይረዋል። የግብር አከፋፈሉና አሰባሰቡ “ባህላዊ” ከመሆን አልፎ “ዘመናዊ” እየመሰለ ለመምጣቱ ሌት ተቀን የሚማረረውን የነጋዴ ማኅበረሰብ ማነጋገሩ ብቻ በቂ ነው።
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የግብር ሕጉ ላይ ትችት ለመሰንዘርና የገዥው ፓርቲ የግብር ፖሊሲ በአገሪቱ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ኑሮ ላይ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመጠቆም የታሰበ ባለመሆኑ፣ ወደፊት ጊዜና ዕድል ሲኖር ጸሐፊው እንደ አንድ የግብር ባለሙያ አስተያያቶቹን በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ይሰጣል። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የኢትዮጵያ ገቢዎችና የጉምሩክ ባለሥልጣን በየክፍለ ከተማው በከፈታቸው ጽሕፈት ቤቶቹ በግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ ላይ የሚፈጽመውን ማጉላላትና “በደል” በመጠቆም፣ የባለሥልጣኑ የሚመለከታቸው ሹማምንት አስፈላጊውን ማሻሻል እንዲያደርጉ፣ ታክስ ከፋዩንም ከመጉላላትና ከሙሰኞች እንዲታደጉት ለማሳሰብ ነው።
አግባብ ባልሆኑ አሠራሮችና ውጣ ውረዶች በየመንግሥት መሥርያ ቤቱ በነጋዴው ማኅበረሰብ ላይ ከፍተኛ መጉላላትና በደል እየደረስ ነው። ይህ በደል ሰሚ በማጣቱም ከዚህ በደልና መጉላላትም ለማምለጥ ብዙዎች ለሙስና እየተጋለጡ ለመሆናቸው ነጋሪ የሚያስፈልገው አይመስለኝም፡፡ ይህን በደል “ሞላሽ” አሠራር ግን ለማሻሻል ሙከራ እየተደረገ ለመሆኑ የሚታይ ምንም ነገር የለም፡፡ በተለይም በየክፍለ ከተማው ያሉ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች በጣም ጥቂት ከሚባሉ ሠራተኞች በስተቀር፣ አብዛኞቹ ባለጉዳይ ለማስተናገድም ሆነ መውጫ ቀዳዳው ጠፍቶት ለሚመጣ ግብር ከፋይ መፍትሔ ለመስጠት ብቃትም ሆነ ፍላጎት የሌላቸው ለመሆኑ በእነዚህ ጽሕፈት ቤቶች የሚጉላላው ባለጉዳይ ቋሚ ምስክር ነው፡፡
ለዚህ ጽሑፍ ምክንያት የሆነኝ በተለይ በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ነው፡፡ በርካታ የአገሬው ሰው የሚገምተው ቦሌ ክፍለ ከተማ በብዙ ሁኔታዎች ኢትዮጵያ ውስጥ “የተሻለ” የተባለ ክፍለ ከተማ ነው፡፡ ከዚህ የተሻለ ተብሎ ከሚታሰበው ክፍለ ከተማ ውስጥ በየመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያሉት አሠራሮች ፍፁም ግዴለሽነት የሚታይባቸው ብቃት ያላቸው ሠራተኞችና አስተዳዳሪዎች የሌሉበት መሆኑን ለተገነዘበ ሰው፣ በተለይም በዚህ ጽሕፈት ቤት በግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ ላይ የሚደርሰውን ግፍና መጉላላት ላጤነ ሰው በሌሎች ክፍላተ ከተሞች ችግሩ የባሰ መሆኑን በቀላሉ ይረዳል።
የቦሌው የጉምሩክ ባለሥልጣን ቢሮ በተንጣለለ ፎቅ በአምስቱም ወለሎች (ፎቆች) ቢሮ አለው፡፡ በእነዚህ ቢሮዎችም በርካታ ሠራተኞች አሉ፡፡ ሆኖም ግብር ለመክፈል የሚመጣውን፣ የንግድ ፈቃድ ለመመለስ የሚመጣውንም ሆነ ከግብር ክፍያ ጋር በተያያዘ በጽሕፈት ቤቱ የሚመጡ ሰዎችን የሚያስተናግዱት ከሦስት ሰዎች አይበልጡም፡፡ “ንግድ ፈቃዴን ለመመለስ ሲያመላልሱኝ ስምንት ወር ፈጀብኝ፣ ሁለት ዓመት ፈጀብኝ. . .” ወዘተ. የሚሉ አቤቱተኞች መስማትና “እኔ ምን ላድርግህ? እና ምን ላድርግሽ? የራስህ/የራስሽ ጉዳይ. . .” የሚሉ የቢሮ ሠራተኞች መስማት በጣም የተለመደ መሆኑን በርካታ ብሶተኞች ለዚህ ጸሐፊ ገልጸዋል። ብዙዎች ከክፍለ ከተማው ከዕዳ ነፃ መሆናቸውን ማረጋገጫ (Clearance) ለማግኘት የፈጀባቸውን ጊዜና በዚህም የተነሳ በስሜታቸው፣ በሥራቸውና በገንዘባቸው ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በምሬት ሲናገሩ መስማት ልብ ይሰብራል። በአንድ ወቅት በዚሁ ባለሥልጣን ቢሮ በሠልፍ ለመስተናገድ የሚጠብቁ ወደ 300 የሚሆኑ ሰዎች ያስተናግድ የነበረው አንድ ሰው ብቻ ነበር፡፡ “እንደውልላቸኋለን ከ15 ቀናት በኋላ ኑ. . .” ወዘተ. እየተባሉ፣ የተባሉት ሳይደረግላቸው የቀሩና መልስ ለማግኘት ጊዜና ጫማ የጨረሱ ግብር ከፋዮች ቁጥር በመቶዎች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡
በእነዚህ ግብር ከፋዮች ላይ የሚደርሰው ግፍና መጉላላት ተመልካች ያጣ መሆኑ፣ አገሪቱ በመልካም አስተዳድር ዕጦት ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳለች ናሙና የሆነ ችግሩ ምን ያህል ጥልቅና ሰፊ እንደሆነም በግልጽ ያሳያል፡፡ ለአዲስና ለ‹‹ዘመናዊ›› የግብር አከፋፈል ሥልት አገራችን ገና አዲስ ነች ተብሎ ቢታመንም እንኳን፣ በዚህ ዘርፍ ልምድ ካላቸው ከበርካታ አገሮች ትምህርት መውሰድና ችግሮችን መቅረፍ ግብር ከፋዩንም በሚገባ ማስተናገድ የሚቻልበትን አሠራርና መመርያ መዘርጋት አስቸጋሪ አይደለም፡፡ ፈረንጆቹ እንደሚሉት ጎማውን እንደገና መፍጠር አያስፈልግም፡፡ ጎማው የተፈጠረ በመሆኑ ኃላፊነት ካለበት ክፍል የሚጠበቀው ጎማውን በተሻለ ሁኔታ ለማሽከርከር ልምድ መውሰድ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ግን ግድ የሚሰጠው አስተዳደር ወይም የባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ያስፈልጋል። የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እየሆነ የመጣው የንግዱ ኅብረተሰብ በተጉላላና በደል በደረሰበት ቁጥር ተጨማሪ ሥራ የመፍጠር፣ መዋዕለ ንዋዩን በአገሩ ላይ የማፍሰስና የንግድ ተቋሙን የማስፋፍት ፍላጎት እየደበዘዘ ይመጣል፡፡ የአዳዲስ ነጋዴዎችንም ፍላጎት ይሰብራል።
በቦሌ ክፍለ ከተማ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መግቢያ በር ላይ በየወለሉ ባሉ ቢሮዎች ምን ዓይነት አግልጋሎት እንደሚሰጥ የተዘረዘረ ቢሆንም፣ የአብዛኞቹ “ቡድኖች ሥራ” የምርመራና የማጣራት እንጂ በቀጥታ የግብር ከፋዩን ጉዳይ በማስተናገድ መፍትሔ ለመፈለግ የተዘጋጁ አይመስሉም፡፡ ግብር ከፋዩ በተቀላጠፈ ሁኔታ ካልተስተናገደ በመሥሪያ ቤቱም ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ እንደሚመጣ (አሁንም እንደመጣ) በሠራተኞቹም ሆነ በአስተዳዳሪዎቹ ከግምት ውስጥ የገባ አይመስልም፡፡ ይህ ጸሐፊ እንዳስተዋለው የጉምሩክ ሠራተኞች (አስተዳዳሪዎቹን ጨምሮ) የድሮ ባላባት፣ ግብር ከፋዩ ደግሞ ጭሰኛ የመሰለበት ግንኙነት ነው ያላቸው። የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ግብር ከፋዩ ደመወዝ ከፋያቸውና አስተዳዳሪያቸው መሆኑን የሚያውቁም አይመስሉም፡፡ ለነገሩ ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ በበርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚታይ ችግር ነው፡፡ ግብር ከፋዩ ደመወዝ ከፍሎ በሚያስተዳድራቸው የመንግሥት ሠራተኞች ምንም ሥልጣንም ሆነ መብት የለውም። ጉዳይ ለማስፈጸም ሁሌም መለመንና መለማማጥ ግፋ ካለም ጉቦ መክፍል አለበት። ስንት ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ አባወራዎችና እማወራዎች ስንት ንግድ ተቋም የሚመሩ ዜጎች ብቃት በሌላቸውና ግዴለሽ በሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች ሲዋከቡ፣ ሲመነጫጨቁና ሲዋረዱ ማየት እጅግ ያሳዝናል።
ገዥው ፓርቲ በተደጋጋሚ መልካም አስተዳደር እንደሌለና ሙስና እንደተንሰራፋ “በተሃድሶ” ነገሮችን እንድሚያስተካክልና እንደሚለውጥ ሲምልና ሲገዘት ብንሰማም፣ በተግባር ግን የምናየው ነገር ተገቢና አስፈላጊ ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎችን ዝም ለማሰኘት የጉልበት ዕርምጃ መውሰድ ነው። በየመንግሥት መሥሪያ ቤት በዜጎች ላይ የሚደርሰው መጉላላት፣ በደልና ግፍ ለማንም ሚስጥር አይደለም፡፡ እርማት ለመውሰድ ግን ግድ የሰጠው ክፍል እንደሌለ ነው ልንመሰክር የምንችለው። ዜጎች ደም እንባ የሚያለቅሱበት የቦሌው ክፍለ ከተማ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ብቻ እንዳልሆነ መናገር አያሻም፡፡ ለቀባሪው ማርዳት ነው የሚሆነው፡፡ በበርካታ መሥሪያ ቤቶች ብቃት የሌላቸው ሰዎች በዘመድና በፖለቲካ ታማኝነት ብቻ ተሹመው ሕዝብን እንድሚያጉላሉ፣ በጉቦ የዜጎችን ኪስ እንደሚያራቁቱ ለማንም ባለሥልጣን መንገር የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ ይህ አፍንጫቸው ሥር እየተደረገ ያለና አንዳንዴም በሽርክና ተጠቃሚ የሆኑበት ነው። ታዲያ አንድን ክፍለ ከተማ ያውም እንደ ቦሌ ዓይነት ክፍለ ከተማን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ማስተካከል ያልቻለ ኃይል፣ የአገሪቱን የተወሳሰበ ችግር በብቃት እንዴት ሊፈታ ይችላል?
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡