Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበሐሰተኛ ማስረጃ የምትታመስ አገር

በሐሰተኛ ማስረጃ የምትታመስ አገር

ቀን:

በቶፊቅ ተማም

በአሁኑ ወቅት በዓለማችን እየተዘወተረና ዓለም አቀፋዊ ይዘትን እየተላበሰ የመጣ ጉዳይ ቢኖር የሐሰተኛ መረጃ ጉዳይ ነው:: ይህም ጉዳይ ከአውሮፓ እስከ አፍሪካ፣ ከአፍሪካ እስከ እስያ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ አውስትራሊያ ይህ ጉዳይ በእጅጉ ተንሠራፍቶ እንደ አንድ አዋጭ ቢዝነስ ዘርፍ እየተዘወተረ የሚገኝ ሲሆን፣ አገሮቹም ይህን ተግባር ለመካላከል ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ለአብነት ይህልም በቅርብ ዓመታት ወደ ሥልጣን የመጡትና ቡልዶዘሩ በመባል የሚታወቁት የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ ሥልጣን በያዙ ሰሞን ያካሄዱት አንዱና ዋነኛ ተግባር የነበረው፣ በሐሰተኛ ማስረጃ የተቀጠሩና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ያገኙ የነበሩ ወደ አሥር ሺሕ ገደማ የሚሆኑ ሠራተኞችን ከሥራ ማሰናበት ነበር፡፡ እንዲሁም ስምና ያልተገባ ተግባር (Name and Shame) በሚል መርህ ስማቸውን በተለያዩ ቦታዎች በመለጠፍና በምትካቸው ትክክለኛ ማስረጃ ያለቸው ዜጎችን ሲተኩ፣ አገሪቱም በሐሰተኛ ማስረጃ በተቀጠሩ (Fraudulent Workers) ሳቢያ በዓመት ከ107 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለወርኃዊ ደመወዝ ታወጣ እንደነበር የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ በኢትዮጵያም በዚህ ረገድ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ወጪ መሆኑን በቀላሉ መገመት ይቻላል፡፡

ይህ ጉዳይ በአገራችን ካለፉት ጥቂት አሥርት ዓመታት ወዲህ በስፋት እየተስተዋለ ነው፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በአገሪቱ የትምህርት ጥራት ጉድለት ሳቢያ ብቁ ባለሙያ የማፍራት ውስንነት በሚታይበት በዚህ ወቅት፣ ከዚህ በባሰ  በሐሰተኛ ሰነድ የተለያዩ ሕገወጥ ድርጊቶች በተለያዩ የግልና የመንግሥት ተቋማት እየተፈጸመ ነው፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍና ለሚታየው የመልካም አስተዳደር ችግር መንስዔ ነው ብሎ በማሰብ፣ ዘግይቶም ቢሆን መንግሥት የማጉፉሊን ፈለግ ተከትቧል፡፡ ከወረዳ እስከ ፌዴራል ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ ለቅሬታ ምንጭ ምክንያቶች አንዱ ነው ብሎ ያመነበትን በሠራተኛ አቅም ማነስ ምክንያት ይከሰታል ያለውን የአገልግሎት ጥራት ማነስን ለመቅረፍ፣ በአገሪቱ ያሉ የመንግሥት ተቋማት የተቋሞቻቸውን ሠራተኞች የትምህርትና የሥራ ልምድ ማጣራት ጀምረዋል፡፡ በሐሰተኛ የትምህርት መረጃና የሥራ ልምድ መረጃ በማይገባቸው ቦታ ላይ ያሉ ሠራተኞች ራሳቸውን እንዲያጋልጡ እያደረገ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት በኦሮሚያ ክልል 6,700 ገደማ ሠራተኞች ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ፣ የሥራ ልምድ፣ የመንጃ ፈቃድና  የሙያ ብቃት ምዘና ከተለያዩ የግልና የመንግሥት ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ማቅረባቸውን በማመን ራሳቸውን ማጋለጣቸው ሲገለጽ፣ በ3,400 ሠራተኞች ላይ ጥቆማ መቅረቡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተገልጿል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ከተገኙ የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች አብዛኛዎቹ ሐሰተኛ ዲግሪ መሆናችው ሲታይ፣ በመንግሥት ተቋማት በክህሎት ማነስ ምክንያት ለሚከሰተው የመልካም አስተዳደር ችግር ማሳያ ነው፡፡ ሲቪል ሰርቪሱ በማይመጥኑት ሰዎች መያዙን ያመለክታል፡፡ እንደ ኦሮሚያ ክልል ሁሉ አማራ ክልልም በሐሰተኛ መረጃ ሲጠቀሙ የነበሩ ሠራተኞች ላይ የራሱን አስተዳደራዊ ዕርምጃ መውሰዱ ተሰምቷል፡፡ የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በአመራርነት የሚሠሩ አመራሮችን የትምህርት ማስረጃ በመመርመር፣ በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የያዛቸውን ሰዎች ከሥራ ማሰናበቱም ከዚህ ቀደም ተገልጿል፡፡  ከዚህ ጎን ለጎንም አሶሳ ዩኒቨርሲቲ  ወደ 20 የሚጠጉ የአስተዳደር ሠራተኞችን በሐሰተኛ መረጃ ምክንያት ከሥራ አግዷል፡፡

እንደ ኦሮሚያና አማራ ክልል ሁሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በሐሰተኛ ማስረጃ የተቀጠሩና የደረጃ ዕድገት ያገኙ ሠራተኞችን ለመለየት መዘጋጀቱንና እንቅስቃሴ መጀመሩን ሪፖርተር በኅዳር 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ዕትሙ አስነብቧል፡፡ ከ105 ሺሕ በላይ ሠራተኞች በተለያዩ በከተማው አስተዳደር ተቋማት እንደሚሠሩ የታወቀ ሲሆን፣ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሠራተኞች በሐሰተኛ የትምህርት፣ የሥራ ልምድ እንዲሁም የሙያ ብቃት ምዘና መረጃ እንደሚሠሩ ተገምቷል፡፡ ይህም በከተማ አስተዳደሩ በሰፊው የሚስተዋል ችግር መሆኑን ልብ ይላል፡፡ ያለ ዕውቀታቸው ኃላፊነት መያዛቸው በከተማው ለሚታዩ የመልካም አስተዳደር ጉድለት እንደ አንድ ምክንያትነት የተቀመጠ ሲሆን፣ የከተማ አስተዳደሩ በሐሰተኛ መረጃ የተቀጠሩ ሰዎች ራሳቸውን እንዲያጋልጡ ተጠይቀዋል፡፡ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞች በማህደራቸው ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እንዳስገቡ በማመን የይቅርታ ጊዜውን በመጠቀም ያመለከቱ መሆኑ ሲገለጽ፣ በርካታ ጥቆማዎች ግን ከኅብረተሰቡ እንደ ደረሰው ተገልጿል፡፡

በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በኦሮሚያ ክልል ብቻ ለጊዜው ከስድስት ሺሕ በላይ ሰዎች ሲገለገሉ መቆየታቸው ሲታወቅ፣ ጊዜውን ጠብቆ እንደሚፈነዳ ፈንጂ የሚታሰበው የሐሰተኛ መረጃ ጉዳይ በተቀሩት ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች፣ እንዲሁም በግልና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሊኖር የሚችለው የሐሰተኛ ሰነድ ተጠቃሚዎች ቁጥር በእጅጉ ሊያሻቅብ ይችላል፡፡ ይህም እንደ አገር የተጋረጠ ፈተና መሆኑን መገመት አያዳግትም፡፡ 

ከሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በመለስ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ስንመለከት፣ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን በስፋት ከሚካሄዱ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ጀርባ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ሰዎች አሉ፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩና ከሚገባቸው የኮንትራክተርነት ደረጃ በላይ በሕገወጥ መንገድ በሌላቸው የሙያ ብቃት ደረጃ የማይገባቸውን ደረጃ ይዘው በተገኙ የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ላይ ተገቢ ዕርምጃ መወሰዱ ከሁለት ዓመት በፊት የተገለጸ ሲሆን፣ እነዚህም በአገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለሚስተዋለው የጥራት ችግር ዋነኛ ተዋናዮች ናቸው፡፡ ከዚህ ባለፈም የሚያደርሱት አደጋ የመልካም አስተዳደር ችግር ከመሆን ባለፈ፣ የሕይወትና የንብረት ዋጋ ማስከፈሉ እንደማይቀር መገመት ያስችላል፡፡

 ከዚሁ ጎን ለጎን በአገሪቱ የሚገኙ ከመቶ በላይ ሥራ ተቋራጮች ከደረጃ አራት እስከ አሥር የሚገኙ በሐሰተኛ መረጃ የሥራ ተቋራጭነት ፈቃድ ያወጡ መሆናቸውን የደረሰበት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር፣ ተገቢውን ምክርና ሥልጠና ሰጥቶ ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲገቡ ማድረጉም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በሕገወጥ መረጃ ሲንቀሳቀሱ ነበሩ ያላቸውን 30 የሥራ ተቋራጮች ማገዱም በቅርቡ በመገናኛ ብዙኃን ተገልጿል፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው ለአብነት በኦሮሚያ ክልል ከተገኙ የሐሰተኛ ማስረጃዎች አንዱ ሐሰተኛ የመንጃ ፈቃድ ሲሆን፣ ይህም በአሁኑ ጊዜ በትራፊክ አደጋ ምክንያት ለሚደርሰው የሰው ሕይወትና የንብረት አደጋ የራሱን አሉታዊ  አስተዋፅኦ እያደረገ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ባደረገው ጥናት ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው አሽከርካሪዎች በሐሰተኛ መንጃ ፈቃድ ሲያሽከረክሩ መያዙን የገለጸ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ በአገሪቱ እየተከሰተ ያለው የሕይወት መጥፋት፣ የአካል መጉደልየንብረት ውድመት አደጋ ከመልካም አስተዳደር ችግርነትም በላይ መሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል፡፡

ሌላው ከሐሰተኛ መረጃ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የሐሰተኛ የሕክምና መረጃ ጉዳይ ነው፡፡ የሐሰተኛ የሕክምና መረጃ በመያዝ በጤና ተቋማት የተቀጠሩና የሥራ ፈቃድ ያወጡ ግለሶቦች መኖራቸው ሲታይ፣ ክብር የሆነው የሰው ሕይወት ላይ የተጋረጠ ፈተና መሆኑ መገንዘብ ያሻል፡፡ ከጤናው ባልተናነሰ ይህ የሐሰተኛ መረጃ ጉዳይ በአገሪቱ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አንስቶ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ የተዛመተ በመሆኑ፣ ትውልድን በአግባቡ ቀርፆ ለማውጣት የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፍ ነው፡፡ ይህም የአንድን አገር መፃኢ ዕድል በሚወስነው ትምህርት ላይ የተጋረጠ ፈተና መሆኑ፣ ጉዳዩ ከመልካም አስተዳደር ችግርነትም በላይ ገዝፎ እንዲታይ ያደርገዋል፡፡  

ዘርፈ ብዙ የሆነውን የሐሰተኛ መረጃ ጉዳይ እጅግ ውስብስብ ነው፡፡ በሐሰተኛ ሰነዶች ሚሊዮን ብሮችና በርካታ ንብረቶች ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መመዝበራቸውና ዜጎች ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን በተለያዩ ጊዜያት በመገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል፡፡ ይህም በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል ፡፡

ከአንድ ገበሬ ጎጆ በየጊዜው የሚወጣ ጪስ ከዕለት ወደ ዕለት ጎጆውን እንደሚያበላሸው ሁሉ፣ በአገራችን የሚታየው በሐሰተኛ መረጃ የመጠቀም አዝማሚያ ከዕለት ወደ ዕለት ጨምሮ ችግሩ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ የተንሰራፋ ነው፡፡ ይህን ችግር መቅረፍ ለነገ የማይባል ተግባር ነው፡፡ ይህንም ችግር ለመቅረፍ እንደ መፍትሔ ከሚወሰዱ ተግባሮች መካከል በኅብረተሰቡ ዘንድ ይህን ድርጊት የመዋጋት ሥራ በአግባቡ ማከናወን፣ የትምህርት ተቋማትን በዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ ማጠናከር፣ ቀጣሪ ተቋማት የሚቀጥሩዋቸው ባለሙያዎች ማንነት በአግባቡ መፈተሽ፣ ዘመናዊ የሐሰተኛ መረጃ መለያ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ እንዲሁም በየተቋማት የሠራተኞችን የትምህርት፣ የሥራ ልምድና ሌሎች መረጃዎችን ተመልሶ የሚያጣራ ቡድን (Background Screening) በማዋቀር መሥራት ተገቢ ይሆናል፡፡

በመጨረሻም ከላይ በአጭሩ እንደተገለጸው በየጊዜው በየተቋማቱ የሐሰተኛ መረጃ ችግርን ለመቅረፍ የተጠየቅ አሠራር ባለመዘርጋቱ ሳቢያ፣ ችግሩ እጅግ ተንሰራፍቶ ዛሬ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚወራለት አጀንዳ ሆኖ መገኘቱ ያልተዘራን ማጨድ እንደማይቻል ያገነዝበናል፡፡ በሐሰተኛ መረጃ ዙሪያ ያነሳሁትን አጭር ሐሳብ በአግባቡ ይገልጽልኛል ብዬ በማስበው በዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ግጥም ላብቃ፡፡

ተጠየቅ ከሌለ ሚዛኑ ካልደፋ፣

ለጊዜው ይሞከር ያሉት ነገር ይጥፋ፤

ስንቱ መጋረጃ ለፀሐይ ተብሎ እንደተሰቀለ፣

ፀሐይቱም ጠልቃ ተንጠልጥሎ ቀረ፤

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

                                                     

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...