Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትሁኔታዎች እንዳደረጉ አድርገው ይቅዘፉን ወይስ ልንቀዝፋቸው እንፈቅዳለን?

ሁኔታዎች እንዳደረጉ አድርገው ይቅዘፉን ወይስ ልንቀዝፋቸው እንፈቅዳለን?

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

የኢሕአዴግ የአዙረኝ አታዙረኝ “ፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት”

በጨዋታ ላይ “አዙረኝም አታዙረኝ” ማለት ይቻላል፡፡ በእውነተኛ ኑሮ ውስጥ ግን መደናበርን ኑሮ ካላደረጉት በቀር አንዱን መምረጥ ያሻል፡፡ ኢሕአዴግ ሙስናን/ኪራይ ሰብሳቢነትን እታገላለሁ የሚለው ራሱ የእነዚህ ሁሉ ወኪል ሆኖ፣ ለእነዚህ ችግሮች መቀጠልና ማደግ የሚስማማ ሁኔታ ታቅፎ ነው፡፡

ሰበቡ እኔ ከወረድኩ ኢትዮጵያ ትበታተናለች፣ ልማቱ ይሰናከላል፣ የዱሮው ሥርዓት ይመለሳል የሚልም ይሁን ሌላ የፈለገው፣ ኢሕአዴግ በእውነተኛ የሕዝብ ድምፅ ለመለካት እስካልተዘጋጀና የመንግሥት አውታራትን የራሱ ጋሻ ጃግሬ መከማቻ ማድረግ እስከቀጠለ ድረስ፣ ይህም ጉልበት ሆኖት ሕዝብን ከጉልበቱ በታች እስከተመለከተ (እንደ ፓርቲም እንደ መንግሥትም የወሰዳቸው ዕርምጃዎች ከእሱ ፍላጎት ውጪ ተጠያቂ የማይሆኑ እስከሆኑ) ድረስ፣ ሥልጣንን እንደ ርስት ያነቀ ኃይል ከመሆን አልወጣም ማለት ነው፡፡ ድጋፍን በጥቅማጥቅም የሚገዛና የሚያቆይ፣ የተቃወመውን ከጥቅም የሚያርቅ ከሆነም ሙሰኛ/ኪራይ ሰብሳቢ ሆነ ማለት ነው፡፡ ወገንተኝነቱ ጠባብ የሆነውን ክፍልፋይ ብሔርተኛነትን ርዕዮተ ዓለሙ እስካደረገና የፖለቲካ መደራጃው እስካደረገ ድረስም ራሱ የጥበትና የአድልኦ ጎሬ ሆነ ማለት ነው፡፡ ራሱ የችግሩ አካል ሆኖ፣ መንግሥታዊ ሥራው በሚስጥራዊነትና በመረጃ ድበቃ ከተዋጠ፣ የሕዝብ በነፃ መደራጀትና መንቀሳቀስ ቅዠት የሚለቅበት ከሆነ፣ ሁሉን ነገር የፓርቲና የመንግሥታዊ ቅርንጫፉ ቅጣይ በማድረግ የሚሠራ ከሆነ፣ አልፎም የመሠረታዊ ፍላጎት እጥረትን (በተለይም የመኖሪያና የኪራይ ቤት እጥረትንና የቤት ዋጋ ንረትን) ታቅፎ መኖር ከቀጠለ፣ ለአቋራጭ ጥቅም አባራሪነት (ለሙስና) ምቹ ዳስ ከመሆንም በላይ ውኃ አጠጪና ፍግ አቅራቢ ሆነ ማለት ነው፡፡

የችግሩ አካል ሆኖ፣ ችግሩ ሙቀትና ምግብ እንዲያገኝ ፈቅዶ፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስናን በቢሮክራሲያዊ ቁጥጥር፣ በፕሮፓጋንዳና በአዳራሽ ውስጥ ተሃድሶ፣ እንዲሁም ሰው በመቀያየር ለመግታት መሞከር “የአዙረኝ አታዙረኝ” መደናበር የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡ ሥርዓተ ኑሮ መሆን የቻለን ችግር በአዳራሽ ተሃድሶ (በስብከት፣ በሂስና በግለሂስ) ወይም በሹም ሽር እንዴት መግታት ይቻላል!? ራሱን ሥርዓቱን ከማደስ በቀር ምን መፍትሔ ሊኖር ይችላል!? ዴሞክራሲ በአግባቡ ተዘረጋግቶ ሥርዓቱ ራሱ እከሌ ከእከሌ ሳይል አጋላጭና ጠያቂ ካልሆነ፣ ሽፍንፍን አሠራሮች ካልተቀዳደዱ፣ ሕዝብ ለመብቱና ለጥቅሙ ተከራካሪ ሆኖ የመንግሥትና የመንግሥት ሹሞች መዘባነኛ የመሆንን ግንኙነት ካልበጣጠሰ፣ እንዳሻቸው ዋጋ እየቆለሉ ጥራትና መጠን እያጓደሉ የሚዘርፉትን የነጋዴ ሌቦችንም ሌላ አማራጭ እየፈለገና አልገዛችሁም እያለ ልክ ካላስገባ፣ እንዴት ግፈኛ ጥቅም አባራሪነት ዝርጥርጡ ይወጣል!? ማደጊያና መሾሚያ፣ በሥራ ገበታም ላይ መዝለቂያ የሥራ ፍሬያማነት ብቻ ካልሆነ፣ ግልጽ አሠራር ጨዋነትና መተራረም የሠራተኞች ኑሮ ካልተደረገ እንደምን የጥገኝነት አኗኗር ይራገፋል!?

ተሃድሶ ጠለቀኝ ያለና ብክነትን ለመግታት መመርያ ያወጣ መንግሥት 2010 ዓ.ም. መባቻ ላይ (የነሐሴና የጳጉሜ ቀናት ውስጥ) “የፍቅር ቀን”፣ “የሰላም ቀን”፣ ‹‹የአረጋውያን፣ የእናቶች፣ የሕፃናት፣ የኢትዮጵያ ቀን፣ ወዘተ›› የሚል ፕሮፓጋንዳዊ ቴአትር ለመሥራት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ሲያወጣ ምን ይባላል! ይህንን ለመሳሰለው ከንቱ ልፋት ውድ የሕዝብ ሀብት ከማባከን ያልዘለለው የኢሕአዴግ ውሽልሽል ፀረ ጥገኝነት/ፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ከግንዛቤ መደናበርም የመጣ ነው፡፡ አዲስ ራዕይ (የካቲት – መጋቢት 2009) “ከሥር መሠረታቸው ይነቀሉ ያልናቸው ጠባብነትና ትምክህተኝነት አሁን የት ደረሱ?” በሚል ርዕስ ያቀረበው ረዘም ያለ ጽሑፍ በኢሕአዴግ ትንታኔ ውስጥ ምን ያህል እውነታዊነትን የሳተ “አዙረኝ አታዙረኝ” እንዳለ ለማየት የሚያስችል ነው፡፡ “ይነቀሉ ያልናቸው ….” ብሎ የጀመረው ርዕሱ ራሱ ምኞታዊነትን ፈንጣቂ ነው፡፡

ጽሑፉ ጠባብነትንና ትምክህትን እናወግዛለን ግን ለምን በፓርቲያችን ውስጥ ተሠራጭተው ተገኙ ለሚል ጥያቄ መልስ ሲሰጥ፣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አመለካከትን በአግባቡ አለመያዝ (ከጥገኛ አመለካከት ጋር መዳቀል)፣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲዊ ሕይወትና ትግል መሟሟት፣ ግለኝነት እየተስፋፋ አድርባይነት እየጠነከረ ሙስናን እያስከተለ መምጣት መሆኑን ይናገርና በእነዚህ በሦስቱ ምክንያቶች የፖለቲካ ሥልጣንን በርስትነት ይዞ ወደ ጥገኛ ገዢ መደብ እየተሸጋገሩ መምጣት ተከተለ ይለናል (ገጽ 34 እስከ 35)፡፡ ሹማምንቱን በግለሰብነት ወስዶ ሥልጣንን በርስትነት ይዞ ወደ ጥገኛ ገዥ የመሸጋገር ችግር እንደታየባቸው ሲነግረን፣ ለዚህ እንዲበቁ የረዳቸው የፓርቲው ገዥነት በነፃና በፍትሐዊ ምርጫ ላይ ያልተንጠለጠለ መሆኑ እንደሆነ፣ ፓርቲው በምርጫ እንደማይንሸራተት ሆኖ ሥልጣንን በርስትነት በመያዙ ራሱም ወደ ጥገኛ ገዥነት ገና ዱሮ የተሸጋገረ መሆኑን አይነግረንም ወይም አልተረዳውም፡፡ ሦስት ተብለው የተጠቃቀሱልን “ምክንያቶች”ም ከችግሩ ገላ አልፈው የማይጠልቁ ናቸው፡፡ አመለካከት ለምን ተዳቀለ? “የአብዮታዊ” ሕይወትና ትግል ለምን ተሟሟተ? ግለኝነት ለምን ተስፋፋ? መጠየቅና መመለስ የነበረባቸው ጥያቄዎች ነበሩ፡፡

“ጠባብነት/ትምክህት ሊከስም የሚችለው አብዮታዊ ዴሞክራሲን ከእነዚህ አስተሳሰቦች የሚለየው ዋነኛ ጉዳይ ምን እንደሆነ በውል ለይቶ… ጠባብነትን/ትምክህትን አጋልጦና ተክቶ እንዲሰርፅና ተቀባይነት እንዲያገኝ ሲደርግ ብቻ ነው፤” ተብሎ ገጽ 39 ላይ የተቀመጠውን በቅጡ ስናስተውል፣ ኢሕአዴግ አባላቱንም ሆነ ሕዝብን ከጊዜ ጊዜ እየሰበሰበ በቃላት መወትወቱ ለምን ማባሪያ እንዳጣ ይገባናል፡፡ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የሚባል አፋዊ ርዕዮተ ዓለም ለአባላቱ ሰጥቶ የርዕዮተ ዓለሙን “ጥራት” በሀተታና በአዳራሸ ትክተካ ለመጠበቅ የመሞከር፣ ‹‹ጥበትንና ትምክህትን›› በስብከት እነቅላለሁ የማለት ቅዠትም እንደተጠናወተው እንገነዘባለን፡፡ በኢሕአዴግ አባላት ላይም ሆነ በሌሎች የኅብረተሰባችን አባላት ላይ የካድሬዎች ስብከት ከሚያስከትለው ውጤት ይበልጥ የኑሮ ስብከት የትና የት ኃያል እደሆነ፣ የፓርቲ አባላቱን ከመላሸቅና ከመንቀዝ የመጠበቅ ጉዳይም ከምንም ነገር በላይ የአኗኗር ለውጥን (በሕዝብ ድምፅ፣ በግልጽ አሠራር፣ በጋዜጠኛና በሕዝብ ንቁ ተመልካችነት ውስጥ መኖርን) የሚጠይቅ መሆኑ ገና የጉዞ ፈር ተደርጎ አልተያዘም፡፡ ወይም እዚያ ፈር ውስጥ መግባት እንደ ጦር ተፈርቷል፡፡

ጥገኞች በገበያ ተወዳድረው ከመሸጥ ይልቅ የመንግሥት ሥልጣንን በመያዝም ሆነ ከያዙት ጋር በመሻረክ ለመክበር ስላላቸው ፍላጎት ይነግረናል (ገጽ 32)፡፡ ግን ይህንን ፍላጎታቸውን ማረፊያ የመንፈግ ጉዳይ የመንግሥትን ከጥገኛ ግንኙነት መራቅንና የሽፍንፍን አሠራሮችን መበጣጠስ እንደሚሻ አያስተውልም፡፡ ጭራሽ፣ የራሱ በሚስጥርና በአፈና የተሞላና በክፍልፋይ ብሔረተኛነት የሚመራ አገዛዝ ዋናው የጥገኞች የዘረፋ ጉረኖ ሆኖ ሳለ “ሊበራል ዴሞክራሲ የጥገኞች መዝረፊያ” እያለ ያወራል (ገጽ 35)፡፡ ኢሕአዴግ ከየትኛውም ብሔር ብሔረሰብ የበቀለ ጥገኛ ኃይል የዘረፋ ጉጉቱን ይዞ በሕዝብ ድጋፍ ሥልጣን ሊጨብጥ የሚችለው “የወንዜ ጅብ ይብላኝ” የሚል መፈክርን ወደ ሕዝብ ካጋባ መሆኑን ሲያሳውቀን (ገጽ 33)፣ የትግራይ ጠባብነት የትግራይ ተወላጆችን ወገኖቼ እንደሚል ሁሉ የሌላውም ብሔር ጥበት እንደዚያው ስለማድረጉ ይነግረንና አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግን ሰዎችን ከብሔር ምንጫቸው ውጪ በፖለቲካ አቋማቸውና ተግባራቸው የሚፈርጅ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ አሥፍሯል፡፡ ይህን ሁሉ የሚቀባጥርልን ግን የብሔሬ ተወላጅ ሁሉ ወገኔ ለማለትና “የወንዜ ጅብ ይብላኝ” ለማለት በሚመቹ ብሔርተኛ አደረጃጀቶች (ከደኢሕዴን በስተቀር በትግራዊነት፣ በአማራነትና በኦሮሞነት ቅርፆች) ውስጥ ተኮልኩሎ ነው፡፡

ብሔርተኛ የፖለቲካ አደረጃጀት ለጎሰኛ አድልኦና ለዜጎች መብት ጥሰት ምቹ መሆኑ በየክልሉ ሁሉ የታየ ነው፡፡ የብሔርተኛ ፖለቲካዊ ቡድን ጥፋት ከቡድኑ አልፎ የብሔረሰቡ መወቀሻና መጠመጃ የሚሆነውም በአደረጃጀት ቅርፁ ምክንያት ነው፡፡ ይህ እውነት ስለመሆኑ የሕወሓት የሥልጣን አያያዝ ትግራዊነት ላይ ከመነሻ ጀምሮ ያሰከተለው አፍራሽ ውጤት 26 ዓመት ሙሉ ዓይን ላይ የተገሸረ ምስክር ሆኖ ቆይቷል፡፡ በቅርቡም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የተከሰተው ታጣቂዎችን ያሳተፈ ግጭት ሶማሌ ውስጥ ለኦሮሞነት፣ ኦሮሚያ ውስጥ ለሶማሌነት ጠንቅ ሊሆን እንደቻለ ታይቷል፡፡ ይህ ሁሉ ልምድ የብሔርተኛ ፖለቲካዊ አደረጃጀትን ትልቅ መዘዘኛነትን ከማስገንዘብ አልፎ መታወቂያ ላይ ብሔረሰባዊ ምንጭን ከማስሞላት እንድንርቅ የሚያስጠነቅቅ ነው፡፡ ነገር ግን ትምህርት ስለመወሰዱ የሚጠቁም ፖለቲካዊ ጥረት አይታይም የአዳራሽ ተሃድሶን ከጥረት ካልቆጠርነው በቀር፡፡

የአዳራሽ ተሃድሶን የፈያጅነት ልክ የዱሮ ልምድ ውስጥ ሳንገባ ትኩስ በትኩስ አይተነዋል፡፡ ባለብዙ መልክ ግጭት እያየን ያለነው የምናካሂዳቸው ጉባዔዎችና ኮንፈረንሶች ገና ሳይበርዱ ሆኗል፡፡ የአሁኑ ተሃድሷችን ከበፊቱ የጠለቀ ነው፣ ዴሞክራሲም እየጠለቀ ነው ቢባልም፣ አዲስ ራዕይም “የመታደስ ንቅናቄው ከድርጅት ወደ መንግሥት መዋቅሩ፣ ከዚያም ወደ ሕዝቡ እንዲወርድ ተደርጓል” ቢለንም (ገጽ 81)፣ በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱ የምናገኘው የሥራ ባህል ከቀድሞው አልተሻሻለም፣ መንግሥታዊ ሐኪም ቤቶች አካባቢ እንዲያውም የአሠራር መዝረክረክና ሰው አገጣባሪነት ባስ ያለ ይመስላል፡፡ ጥቅምት 2010 ዓ.ም. ውስጥ አረና ትግራይ መቀሌ ላይ ሠልፍ አደርጋለሁ ሲል የታየው መብረክረክና የማሰነካከል ሙከራ የዴሞክራሲያችን አጠላለቅ ከአዳራሽ ወሬ እንዳላለፈ የመሰከረ ነበር፡፡ ዕውናችን ጉዳችንን ይህንን ያህል እያሳየን፣ ኢሕአዴግ ራሱ በመዳንና በመጥፋት ምርጫ ውስጥ ስለመገኘቱ እየተናገረ (የተጠቀሰው ገጽ 70)፣ መፍትሔ በማይሆን ስብሰባና ሹምሽር ውስጥ መትረክረክ ለመታረም እምቢ ከማለት ወይም ሞትን ለመቀበል ባለመፍቀድ “ምንም ብትሞቺ እንዴት አደርሽ አንቺ!” እንዳለው ሰውዬ ከመሆን በምን ይለያል! “ጥገኞች… የበላይነታቸውን በሌሎች ብሔሮች ላይ በመጫን ለመበዝበዝ፣ ካልተሳካላቸው ደግሞ የራሳችን የሚሉትን ሕዝብ ከሌላው በመነጠል ለመበዝበዝ ነው የሚፈልጉት” (ገጽ 14) በማለት አንድ ዓይነት የፖለቲካ ባህርይ ሊያሳይ ለማይችል የምጥመጣ አኗኗር፣ አንድ ዓይነት የፖለቲካ ባህርይ ማሸከምንስ ምን እንበለው? እውቀት ወይስ እንዳመጣ ሽጥሸጣ?   

ከብዙ በጥቂቱ እየቆነጠርን የተቸነው የኢሕአዴግ አዲስ ራዕይ ከቶ የማይጠበቅ ነገርም ይናገራል፡፡ ‹‹… [ጥገኞች] የሕዝቡን የዴሞክራሲ መብቶች በተሟላ ሁኔታ ካረጋገጡ ሕዝቡ በእነዚህ መብቶች በመጠቀም በሒደት ከሥልጣን ያፈናቅላቸዋል፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የዴሞክራሲ ሥርዓት ተግባራዊ ከሆነ፣ የመንግሥት ሥልጣን በርስትነት ይዘው የሕዝብ ንብረት በቀጣይነት እየዘረፉ ሊከብሩ አይችሉም፡፡ ሕዝቡ በምርጫም ሆነ በአመፅ የህልውናቸው መሠረት ከሆነው የመንግሥት ሥልጣን ያስወግዳቸዋል፡፡›› (የተጠቀሰው ገጽ 33 ሰረዝ የተጨመረ፡፡)

ይህን የመሰለውን ልቅም ያለ እውነት ማን በማን ላይ ተናገረው እንበል?! ድንገተኛ ቅዠት ነው ወይስ በኢሕአዴግ ውስጥ ፈራ ተባ የሚል የቅዋሜ እንቅስቃሴ ነው ይህንን ያስባለ?

ኢሕአዴጎች ወዴት እየሄዱ ነው? ወዴትስ ሊያደርሱን ነው?

እስካሁን ከተባለው ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ላለው አልቅቶች ለተራቡበት የኑሮ ሁኔታ ኢሕአዴግ የድርሻውን እንዳወጣ፣ ኢሕአዴግ የሠራቸው ጥፋቶችና ስህተቶች ከአመለካከት ብልሽትና ከሕግ በላይ ከመሆን የመጡ መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡ አንዳንዶች ይህንን ችግር ከአቶ ከመለስ ዜናዊ ሞት ጋር ያያይዙታል፡፡ የአመለካከት ብልሽቱም ሕገወጥነቱም ግን ቀደም የነበረና የአቶ መለስ ዜናዊም እጅ የነበረበት ነበር፡፡ የአቶ መለስ ሞት ያጎደለው ነገር ቢኖር ሁሉንም ለጥ ሰጥ አድርጎ መዳፉ ውስጥ ያስገባና ትንሹንም ትልቁንም የፖለቲካ ቅያስ የሚያወጣ ሰውን ነው፡፡ እሱ ሲያልፍ የእሱን ቅያሶች ሙጥኝ ማለት፣ ከዚያ በዘለለ በጥራዝ ነጠቅነትና በመሰለ መሙላት፣ የተሸፋፈነ የሥልጣንና የአንጃ ፍላጎትም መስለክለክ ተጀማምሮ ዛሬ ያለንበት ደረጃ ላይ ያደረሰን ይመስላል፡፡

በፌዴራልም ሆነ በክልሎች ደረጃ የሚታየው በአግባቡ የማስተዳደር ጉድለት፣ በተለይ በሶማሌ ክልልና በኦሮሚያ ክልል መሀል ንቁሪያና ግጭት ሲያዳግም መታየቱ፣ አለመረጋጋትና ፍጥጫን የመሰለ አዝማሚያ መከሰቱ (በተለይ ሶማሌ ክልል ውስጥ በተጠያቂነት የሚጠረጠሩን ተከታትሎ የመያዝ ፍላጎት ስለመጉደሉ የፌደራል መንግሥት የመሸፋፈን ልማዱን ጥሶ መግለጡ)፣ በፌዴራል መንግሥትና ክልሎችን በሚገዙ ቡድኖች መካከል የሕዝቦች ደኅንነትን በተመለከተ ኃላፊነት ላይ እንኳ ተደጋግፎ መሥራትን ያወላከፈ የፖለቲካ መቋሰልና መናናቅ ስለመኖሩ እንድንጠረጥር ያደረገ ነው፡፡ የተወሰነች የፖለቲካ ችግር ለመመከት ሲባል ክልላዊ መንግሥትን በብሔርተኝት ለመዋጥ የተመቸ የልዩ ታጣቂ ኃይል ባለቤት ማድረግ ምን ያህል ወደ እብሪት ሊወስድ እንደሚችል እንደታየ ሁሉ፣ አሁንም ነገሮች በጥንቃቄ ካልተያዙ ወደ ሌላ ሌላ ዓይነት መባረቅ ሊቀየሩ የመቻላቸው ዕድል ክፍት ነው፡፡

ውስጥ ውስጡን የሚወራውን የሹክሹክታ መአት ትተን፣ ልናስተውለው በምንችለው ደረጃ በኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ውስጥ መፈነካከር መድረሱ አንድና ሁለት የለውም፡፡ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የተራዘመ ስብሰባ ያወጣው ግምገማዊ መግለጫም የጥርጥሬና የመጠቃቃት ግንኙነት ውስጣቸው እንደነበር ነግሮናል፡፡ ከዚህ እውነታ ተነስቼ በደፈናው ኢሕአዴግ ከማለት ይልቅ ኢሕአዴጎች እያሉ ማውራትን መርጫለሁ፡፡ እናስ ኢሕዴጎች ምን እያሰባችሁልን ነው? ተመናቅራችሁ በየክልላዊ ጎጇችሁ ውስጥ ጋደም ብላችሁ የየቡድን ቁሰላችሁን እየላሳችሁ ኢሳያስ “ነደፈው” የሚባልለት የመቶ ዓመት ራስ ምታት በሩብ ምዕት ዓመት ውስጥ ተሟልቶ፣ ኢትዮጵያ ስትፈናዳ ኢሳያስ ለማየት እንዲበቃ እየተጋችሁ ነው? ወይስ ቅዠቶቻችሁንና ስህተቶቻችሁን አራግፋችሁ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች አለኝታ የመሆን ሐሳብ አላችሁ? ለመሆኑ በሥልጣን ላይ እንደ መሆናችሁና በሩብ ምዕት ዓመት ወስጥ ለደረሰው የፖለቲካ ብልሽት ዋና ባለድርሻዎች እንደ መሆናችሁ፣ እንደዚያም ሆኖ አገሪቱን በልማትና በኢኮኖሚ ወደፊት ማራመድ ስለቻላችሁና በአንፃራዊነት የልምምድና የድርጅት አቅም ብልጫ እናንተ ዘንድ ስላለ፣ አገሪቱንና ሕዝቦቿን ወደ ሥርዓት አልባነትና ወደ ፍጅት ከመግባት በማትረፍ ረገድ እናንተ ላይ የወደቀው ኃላፊነት ከተቀዋሚዎቻችሁ በላይ መሆኑ ይታወቃችኋል? በዚሁ አጋጣሚ የአገሪቱ የጦርና የፀጥታ ኃይሎች ከየትኛውም ፖለቲካዊ ቡድን ወገናዊነትና መከፋፈል ርቀው መቆየት መቻላቸው የመበታተንንና የመጠፋፋት አደጋን ለማምለጥም ሆነ ለኢሕአዴጎች መቃናት እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን እየጠቆምኩ፣ ለኢሕአዴጎችም ለሌሎች ወገኖቼም ጥቂት ነጥቦችን ላጋራ፡፡ 

የአንድ አገር ሕዝብ/ሕዝቦች በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ጉዟቸው ውስጥ ተራማጅ ፓርቲ ሊዋጣላቸው መቻሉ፣ ግስጋሴያቸው አስተማማኝ የለውጥ አቅም ማፍራቱን የሚጠቁም ነው፡፡ ተራማጅነት ግን ተራማጅ ነኝ ብሎ የማለት ወይም ሌላ የስም ጉትቻ ፈጥሮ ከሌላው የምለይ “አብዮታዊ ዴሞክራት”፣ ምንትሴ ነኝ እያሉ የመለፈፍ ነገር አደለም፡፡ የደረቀ ርዕዮተ ዓለም ተሸክሞ እሱን እያንጓጉ ጆሮ ማሰልቸት፣ መንግሥታዊ አውታራትንና ኅብረተሰብን ሁሉ በዚያ ለመጠረዝ መሞከርም ከግነዛ ጋር እንጂ ከተራማጅነት ጋር አንዳችም ተዛምዶ የለውም፡፡ “ትምክህተኞች፣ ጠባቦች፣ ጥገኞች፣ ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ የሁሉም ብሔሮች ደመኛ ጠላቶች…” እያሉ ነጋ ጠባ በመጮህና በጠላት ድርደራ ተፀናዋቾችን ማበራከት፣ ኅብረተሰቡንም በወዳጅና በጠላት ረድፈኝነት ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ተራማጅነት ሳይሆን ኢተራማጅነት ነው፡፡ የሕዝብ ድጋፍም ሆነ የሠራተኞችና የወጣቶች ነፃ ተነሳሽነትና ተረባራቢነት የሚታፈስበትን መንገድ ትቶ በቅዋሜና በብሶት መከበብ፣ በዚያም ውስጥ ሆኖ በይድረስ ይድረስ ሥራ ውስጥ መርመጥመጥ፣ ከሥር ጀምሮ በጥራት ችግሮች የተዋጠው ትምህርት በሁሉም ተዋንያን ርብርብ የሚነቀነቅበትን ፖለቲካዊ ለውጥ ሳያመጡ፣ በምዘና ለማቃናት መሞከር በድፍን ቅልነት ለግርግር ሰበብ መስጠት እንጂ ተራማጅነት አይሆንም፡፡ በአገር ልጆች መካከል ያለ መሽካከርንና መናቆርን ማቃለል ችግር በሆነበትና መደበኛ ሥራን ተረጋግቶ ማካሄድ ባልተቻለበት የተሽመደመደ ሁኔታ ውስጥ ተሁኖ፣ የጎረቤት ስደተኞችን ከመጠለያ ውጪ ከኅብረተሰብ ጋር ቀላቅሎ ስለማኖር ማውራት፣ እንኳን ከተራማጅነት ሊቆጠር ይቅርና በጤና መሆንንም ሊያስጠረጥር የሚችል ነው፡፡

ተራማጅነት ሕዝቦች ከድህነት በወጣና መሻሻሉን በሚቀጥል ኑሮ ውስጥ እንዲገቡ፣  ከመናጨት ይልቅ በፍቅርና በሰላም ውስጥ መተዳደር እንዲችሉ መዋደቅና ለዚህም የሚስፈልገውን እውነታዊ ንድፍና አመራር ማመንጨት ነው፡፡ በዚህ ጥቅል እሳቤ ውስጥ ብዙ ነገሮች ታዝለዋል፡፡ ሕዝቦች በመብቶችና በውዴታ ውስጥ እንዲኖሩ መታገል ለዴሞክራሲ ከመዋደቅ ውጪ ፈጽሞ ሊታሰብ አይችልም፡፡ የሕዝቦች በፍቅርና በሰላም የመኖር ጉዳይም በብዙ ነገር የተሳሰረ ህልውናን ማጤንንና አጢኖም መተቃቀፍን ይሻል፡፡ ይህ ውዴታና የህልውና ግዴታ የተግባቡበት ሒደት በተግባር መሬት ከያዘ፣ ያለጥርጥር አግላይ ከሆኑት ብሔርተኛ የፖለቲካ አደረጃጀቶች መውጣታችን፣ እናም በኅብረ ብሔራዊ ትቅቅፍና በእኩል ዜግነት መስተጋብር ውስጥ መግባታችን የማይቀር ነው፡፡ ብሔራዊ ክልሎች በሚባሉ አካባቢዎች ውስጥ ያሉ ዋነኛ ማኅበረሰቦችን ከውጥንቅጥ ንዑሳኖቻቸው ለይቶና አብልጦ ባለቤትና ባለ ብልጫ መብት ማድረግ (ሌላው ቀርቶ ንዑሳኑን የገዢ ፓርቲ ስብስብ ውስጥ መካተት የማይመለከታቸው ማድረግ) በመብቶች ውስጥ ማኖር ሳይሆን፣ በአድልኦና በመንጓለል ውስጥ ማኖር ነው፡፡ አንጓላይነትና ተንጓላይነት ፈጽሞ ለፍቅርና ለሰላም አይበጅም፡፡ ሶማሌ ክልል ውስጥ ኦሮሞና ሌሎች ንዑሳን፣ ኦሮሞ ውስጥ ሶማሌና ሌሎች ንዑሳን ተንጓለው መኗኗር እንደሚያስቸግር የደረስንበት ፖለቲካዊ ቀውስ እየነገረን ነው፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ዛሬ የተካሄዱ የመብት ትግሎች የለፉትም በእኩል መብቶች ውስጥ መኖርን ለመቀደጀት እንጂ፣ በተበላለጠ መብትና ዜግነት ውስጥ መኖርን በሌላ መልክ ለማስፈን አልነበረም፡፡

የሕዝቦች በውዴታ ውስጥ የመኖር ጉዳይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሥልጣን ቆይታ በፍትሐዊ ነፃ ምርጫ ከጊዜ ጊዜ መለካትን፣ የሕዝቦችን ዕጦትና ፍላጎት ማዳመጥን ይሻል፡፡ ሥልጣን ላይ ያለ ፓርቲን ሕዝብ መፍራትና ልቡን መሸሸግ ካመጣ፣ በሥልጣን ላይ ያለ ፓርቲም በአፈናና በማጭበርበር ማደር ከጀመረ፣ ተራማጅነትም በሕዝብ ውዴታ ውስጥ መኖርም ተሰልበዋል ማለት ነው፡፡ መብቶች ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆኑ ኢኮኖሚያዊ ፈርጅም አላቸው፡፡ እኩልነትና መተሳሰብም እንዲሁ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ አላቸው፡፡ እነዚህን ገጽታዎችን አቻችሎ ወደፊት ለመራመድ አለመቻል ቀውስ ያስከትላል፡፡

ሁሉን አካባቢ ያካተተ የኢኮኖሚ ልማት ለማምጣት የሚደረገው ትግል ብቻውን ብዙ ፈተና ያለበት ነው፡፡ ትምህርትንና ሥልጠናን የፈጠራ ምንጭ እንዲሆን አድርጎ ማልማት፣ ከፈጠራዎችና ከጥበቦች ውስጥ ለአገር የሚበጀቱን ለይቶ ማስፋፋት፣ ሥራ ፈጠራንና ከፍታን ማነቃቃትና እንዲሠረጫጩ ማገዝ ዞሮ ዞሮ የካፒታሊዝም ግንባታን የመመገብ ሥራዎች ናቸው፡፡ ካፒታሊዝም ደግሞ ይሉኝታ የለሽ ትርፍ አሳዳጅነትና ሀብት አግበስባሽነት ያለበት ነው፡፡ የካፒታሊዝም አምላኪ መሆን በማኅበራዊ ቅራኔዎችና ተዛነፎች ለመጠመድ እንደሚያጋልጥ ሁሉ፣ ካፒታዝምን በአቋራጭ ለመሸወድ መሞከርም ለውድቀት የሚዳርግ ምኞታዊነት ነው፡፡ የካፒታሊዝምን ጥፋትና ልማት አውቆ የሚቻለውን ያህል ለማለዘብና (ከማኅበራዊ ፍትሐዊነት ጋር) ለማግባባት መሥራት ከሕዝብ ድጋፍ ጋር ወደፊት ለመራመድ ያስችላል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓቱን በቅጡ የማወቅ ጉዳይ ግን ከመጻሕፍት ባለፈ፣ አሁን ባለው ዓለም አቀፋዊ መስተጋብሩ የሚሠራባቸውን ንዋይ የመምጠጫ፣ ተወዳዳሪዎችን የማገጃ/አዳክሞ የመጣያ ወይም የመሰልቀጫ ልዩ ልዩ ይፋዊና ሥውር ስልቶች በደንብ ተረድቶ ለመሹለክለክ፣ በሥርዓቱ ውስጥ በተግባር የኖሩ አማካሪዎችን መያዝንም ይጠይቃል፡፡

ካፒታሊዝምን በቅጡ ከማወቅ ጋርም የኢትዮጵያ የብዙ ብሔረሰቦች አገርነት ምን ዓይነት አካሄድና አቀነባበር እንደሚሻ መረዳትም አስፈላጊ ነው፡፡ ወደ ኋላ የቀረውን፣ የዘገየውንና በብልጠት የተቀደመውን ሳይዙ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ልቆ መታየት ወይም ተፎካካሪ የለሽ ሯጭ መሆን፣ ተገለልኩ፣ ተበለጥኩ፣ ተዘረፍኩ ባይነትን ይፈጥራል፡፡ ይህን መሰሉን ሮሮ “ካቅም ማነስ የመጣ የጥበት ችግር/ከውድድር ውጪ ሀብት የመሻት ጥገኛ አመለካከት” በሚል ትችት መርታት አይቻልም፡፡ በግል ባለሀብትነት ረድፍ ውስጥ ከየአካባቢው ነባር ነዋሪዎች ልቆ የወጣ የንግድ ባለይዞታነትም ሆነ አዲስ ኢንቨስትመንት አሉታዊ አቀባበል እንዳይገጥመው በባለቤትነት ድርሻ ሌሎችን ማሳተፍ፣ በአካባቢው ልማት ውስጥም መልካም ስም ማበጀት ይበጀዋል፡፡ ከዚህ አኳያ የአንድ ወይም የሌላ ክልል የ”ኢንዶውመንት” ሀብት የሚባሉ ኩባንያዎችን እንዳሻ እንዲሠሩ ማድረግ ምን ያህል ጠንቀኝነት እንዳለው ማስተዋል አይከብድም፡፡ “የፀረ ሰላሞች ዘረኝነት ያስከተለው ደመኝነት” የሚሉ ፋይዳቢስ ሰበበኝነትን ትተን ተዘረፍን ባይነትን በሚያስወግድ አኳኋን ኅብረ ብሔራዊ ይዞታ ውስጥ የሚገቡበትን መፍትሔ እስካላመጣን ድረስ፣ እንዲህ ዓይነት ንብረቶች በተለይ ሲሳይ የደራላቸው መናቆሪያና የጥቃት ዒላማ መሆናቸው አይቀርም፡፡ ከዚህም አልፎ በአክሲዮን ድርሻ ሰፊ አሳታፊነት አማካይነት የአገራችን ካፒታሊዝም ብሔረ ብዙ ሕዝባዊ ገጽታ እንዲኖረው የማድረግ አማራጭም ሊታይም የሚገባ ይመስለኛል፡፡ በፌዴራል ደረጃ ያሉ የልማት ተቋማት የመላ ሕዝቦች እንጂ አዲስ አበባ የተቀመጠ ገዥ ኃይል ይዞታ አለመሆናቸውን በቅጡ ከማሳወቅ ባለፈም፣ የራሳችን ባይነትን ለማጠናከር የአካባቢ መንግሥታትና ብሔረ ብዙ አሻራ እንዲያርፍባቸው የማድረግን አዋጪነት (ወደፊት በፌዴራል ይዞታነት ከመቀጠል አለመቀጠላቸው ጋር አገናዝቦ) መመርመርም ሳይጠቅም አይቀርም፡፡

በተለመዱ ውስን አማራጮች ውስጥ የሚሽከረከረው የጥቃቅንና አነስተኛ ሥራዎች ልማትም፣ ድህነትን በሰፊው ሊነቀንቅ ወደሚችል የሥራ ፈጠራ አብዮት መቀየር መቻሉ በዛሬው የኑሮ ክብደት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የባህል ደረጃችንን ሊያበለፅጉ የሚችሉና ብዙ ወጪ በማይጠይቅ ሥልጠና እንጀራ መብሊያ ሊሆኑ የሚችሉ የትርዒት፣ የአገልግሎት፣ የዕደ ጥበብና የመረታ ሥራዎች በአገሪቱ ኤምባሲዎችና ውጭ ባሉ የአገር ልጆች አማካይነት እየተቀዱ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ማድረግ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት ዋጋን በማቅለል ሰዎች ከኢንተርኔት ጎተራ ሊገኙ  የሚችሉ የሥራ ዓይነቶችን መኮረጅ እንዲያጧጡፉ በር መክፈት፣ ከዚህ ሁሉ ጋር በቅርቡ የበረኪናና የፈሳሽ ሳሙና አሠራርን በተመለከተ ያስተዋልነው ዓይነት የአሠልጣኝነትና የሥልጠና እንቅስቃሴዎች መፍላት፣ ለተወሰነ ጊዜ ቦግ ብሎ እስከ አዟሪ ድረስ የወረደ የሥራ ዕድል ፈጥሮ የነበረውን የኅትመት ሚዲያ ከዴሞክራሲ ግንባታ ጋር እንደገና ነፍስ እንዲዘራ ማድረግ፣ የተወሰነች ጥበብን ነክሶ እዚያችው ላይ የደረቀውን የቀርከሃ ዕደ ጥበብ ከሐበሻ እስከ ፈረንጅ የሚማርኩ፣ ከቀላል ዋጋ እስከ ውድ ዋጋ ድረስ የሚያወጡ ቁሳቁሶችን የሚያፈራ ትባት እንዲያገኝ መነቅነቅ፣ የከተማ አካባቢ ወንዞችን ከብክለት ጠብቆ ወደ ማራኪ የመዝናኛና የአትክልት ልማት ሥፍራዎች የመቀየርን ተግባር ማንቀሳቀስ፣ እነዚህን የመሳሰሉት ሁሉ የአነስተኛ ሥራዎች አብዮት መጀማመሪያ መሆን ይችላሉ፡፡

አንድ ለውጥ ከማድረግ በፊት ለውጡ የሚስከትላቸውን ተያያዥ ውጤቶችንም በቅጡ መመርመርና ጉዳቶች ቢኖሩ የማቻቻያ ብልኃትን ማዘጋጅት ይገባል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት በፊት የደመወዝ ጭማሪና ቀጥሎም የግብር ምጣኔ ለውጦች ተካሂደው ነበር፡፡ አሁን በ2010 ዓ.ም. የተደረገው የብር ምንዛሪን በ15 ከመቶ የማቅለል ዕርምጃም (አስቀድሞ የታሰበበት ከነበረ) ቀዳሚዎቹ የደመወዝና የግብር ጭማሪዎች፣ ግብይይት ላይ ካስከተሉት ተፅዕኖ ጋር እንዲቻቻል ሆኖ ሊመጣ ይችል ነበር፡፡

ለመሆኑ ላይ ላዩን እንደሚባለው የብር ዋጋን የማቅለል ምክንያታችን ወጪ ንግድን ለማሳደግ ተብሎ ነው? ወጪ ንግድ ያላደገው አገር ውስጥ ያለው ገበያ አትራፊነት እያማለለ አስቸግሮ ነው? ወይስ የእኛ ንግድ ገና ያላደገና በጥራት ተወዳዳሪ መሆን ችግር ሆኖበት? የተጣራ መረጃ የማግኘት ችግሩ እንዳለ ሆኖ የመልሱ አዝማሚያ ወዴት እንደሚያጋድል መገመት ቢቻልም፣ በጥቅሉ አዙሪቱን በማሳየት ላይ ልወሰን፡፡ የአገሪቱ ወጪ ንግድ ዛሬም ጥሬ ምርት በመላክ ላይ ያጋደለ መሆኑ አለ የማይባል እውነት ነው፡፡ ከማጋደለም አልፎ የሕዝብን የጥራጥሬና የሰብል ፍጆታን የሚሻማና ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን የሚተካ የአምራችነት ዕድገትን የሚጫን ገጽታ አለው፡፡ የእህልና ጥራጥሬ መወደድና የአገር ውስጥ የዘይት አምራችነት ተዳቅቆ ከውጭ በሚገቡ ውጤቶች መዋጡ የዚህ ገጽታ መገለጫ ነው፡፡ ጥሬ ዕቃ ላይ የተንጠለጠለ ወጪ ንግድን በኢንዱስትሪያዊ ውጤቶች የመተካቱ ጥረት ገና አዲስ ተውተርታሪ ነው፡፡ እንደ አዲስነቱም በጥራትና በደረጃ ፅኑ አስተማማኝነት የመቀዳጀት ፈተናውም ገና መጀመሩ ነው፡፡ የተፈበረኩ ውጤቶችን የመላኩ ስኬት ከውጭ በገቡ ሥራ ከፋቾች ላይ የተንጠለጠለ ከሆነም (የአገር ልጆች ከውጭዎቹ ቀስመውም ሆነ በሽርክና ውስጣዊ መሠረት ካላስያዙት) በፖለቲካ ግርግርም ሆነ በሌላ ምክንያት ባይተዋሮቹ ውልቅ ሲሉ፣ ባዶ የኢንዱስትሪ መንደር ታቅፎ የመቅረት አደጋ አብሮት ይቆያል፡፡  

መንግሥት የሚመራው ግንባታዊ ልማት (የኢንዱስትሪ መንደር መጠለያዎች ግንባታን ጨምሮ) አዲስ እሴት ገና የማያፈልቅ ከመሆኑም በላይ፣ በየጊዜው የሚንተረከክ በዚያው ልክ የሚሻው የውጭ ምንዛሪ የሚሰፋ ነው፡፡ በዚህ የግንባታ ልማት ውስጥ ያለው የውጭ ምንዛሪ አጠፋፍ ከውጭ በሚገዙ ግብዓቶችና መሣሪያዎች ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ የውጭ ሥራ ተቋራጭና ባለሙያ የመኮናተርም ወጪ ያለበት ነው፡፡

በሌላ ፈርጅ በአገሪቱ የሚታየው የውጭ ሸቀጥ ልማደኝነት የተስፋፋበት የከተሜ አኗኗር ከምግብ ሸቀጥ እስከ ቅንጦት ድረስ ቁሳቁስ ከማጋበስ አልፎ ቆሌ እስከ መቅዳት የሚሄድ ነው፡፡ የአምራች ኢንዱስትሪያችን ጨቅላነት፣ የመንግሥታዊው ግንባታ መስፋፋትና በፈረንጅ ያየሁት አይቅረኝ ያለ የውጭ ሸቀጥ ልማደኝነት በአንድ ላይ አገሪቱን በበረታ የውጭ ምንዛሪ ጥማት ውስጥ ከተዋልታል፡፡ አገሪቱ ወደ ውጭ ሸጣ ከምታተርፈው በላይ ከውጭ ገዥ የሆነችበት ሚዛን የሳተ አኗኗራችን ከበፊቱ ብሷል፡፡ እናም ለገቢ ዕቃ የሚወጣ ገንዘብንና የብድር ወለድን የመሸፈን ኃላፊነት በንግድና በሐዋላ ከተገኘ የውጭ ምንዛሪ አልፎ የብድርና የዕርዳታ ተስፈኛ ያደርጋል፡፡ (ገንዘብ እየዘረፉ ወደ ውጭ የሚያሸሹ ሌቦችና ወጣቶችን በማሰደድ ግፈኛ ንግድ የውጨ ምንዛሪን የሚመጥጡ ሰዎችም የዝባት ችግሩን በማባባስ ሚና እንዳላቸው አይረሳ፡፡)

በዚህ አንካሳነት ውስጥ ሆነን ብዙ ጥሬ ምርት ሸጠን ብዙ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የምናደርገውን መፍጨርጨር የሚመታ የዋጋ መውደቅ በዓለም ገበያ ቢመጣና ላኪዎች ወደ ውጭ መላክን ትርጉም አጥተውበት ችላ ቢሉ፣ ወይም ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ የተሻለ አዋጭ ሆኖ ቢያገኙት፣ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎታችን በውድም በግድም ላኪዎችን ተጭነን ለውዳቂ የውጭ ገበያ ዋጋ ተሸናፊ እስከመሆን ድረስ ያጥመለምለናል፡፡

የውጭ ገበያ ወደቀም አልወደቀ የብድርና የዕርዳታ ቀዳዳ የጠበበት ሁኔታ ሲመጣ ደግሞ ሌላ ራስ ምታት ይከተላል፡፡ መንግሥት የፖለቲካ ድጋፉን አሙቆ ከአገር ተወላጆች የሚላክ የውጭ ምንዛሪን በማሳደግ ችግሩን ካላቃለለ፣ ወይም የልማት ፕሮጅቶቹን ለማጠፍና ለማስታገስ ካልፈቀደና የምንዛሪ እጥረቱን ከአጠቃላይ የገቢ ዕቃዎች ድርሻ ላይ በመቀነስ ካጣጣ፣ የገቢ ዕቃዎችን ንግድ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ንፋስ ያምሰዋል፡፡ ገና በመጋዘን ዕቃዎች እያሉ እጥረት “ደርሶ” ዋጋዎች መናር ይጀምራሉ፡፡ እጥረቱ ሲሰነብት ዋናውን መገበያያ ዶላርን ምሳሌ እናድርግና አንድ ዶላር በጥቁር ገበያ የሚመነዘርበት ብር ባንኮች ከሚመነዝሩበት መጠን ጉልህ ልዩነት ያሳያል፡፡ ያን ጊዜ ከውጭ በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ ለዘመድ ወዳጅ ይልክ የነበረው ያችን ትርፍ ፍለጋ ወደ ሥውር መንገዶች ይዞርና ወደ መንግሥት የሚደርሰው የውጭ ምንዛሪ የበለጠ ያንሳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በጥቁር ገበያ በብዙ ብር መመንዘር የቻለ ዶላር ከበፊቱ የበለጠ የመግዛት አቅም አግኝቷልና በኮንትሮባንድ ከበፊቱ የበዛ ጥራጥሬ፣ ቡና፣ ከብትና ወርቅ ገዝቶ ይወስዳል፡፡ ይህ እንደገና የአገሪቱን የወጪ ንግድ አቅርቦትንና የውስጥ ገበያ አቅርቦት ያከሳል፡፡ የሁለቱ ውጤት ደግሞ እንደገና የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የዋጋ መወደድ፣ እንደገና የጥቁር ገበያ የዶላር መመናዘሪያ ከባንኮቹ ይበልጥ መራቅ፣ በአጠቃላይ ከአንዱ ወደ ሌላው የሚተላለፍ የችግር እሽክርክሪት ውስጥ መግባት ነው፡፡

በአገር ውስጥ ገበያ ላይ የተከሰተ የውጭ ሸቀጥ ጉድለትን በኮንትሮባንድ በማስገባትና የአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃን በኮንትሮባንድ በማስወጣት ላይ የተጠመደ ንግድን ለማሸነፍ (የባንክን የዶላር መመናዘሪያ ከጥቁሩ ገበያ ልክ ጋር ለማቀራረብ)፣ የብር ዋጋ ዝቅ ቢደረግ ዕርምጃው ማቻቻያ መፍትሔ ደርቦ እስካልመጣ ድረስ የኀብረተሰቡን ተቀማጭ ገንዘብና የተቀጣሪን እውነተኛ ደመወዝ ዝቅ ማድረግ ይሆናል፡፡ ከዚያ ላይ ቀንሶ ኮንትሮባንድን መመከት ወይም ወደ ውጭ ላኪን ማበረታት የፍትሐዊነት ጥያቄም አለበት፡፡ ይህም ሆኖ ደግሞ ከችግሩ ወጥመድ ለመውጣት አያበቃም፡፡ በጎረቤቶቻችን አካባቢ በየትኛውም ውድ ዋጋ ከኢትዮጵያ ምርት እያሾለኩ ችግርን ለመወጣት የሚያስገድድ ቀውስ ወይም በተሸጋጋሪ የኮንትሮባንድ ንግድ የማትረፍ መረብ እስካለ ድረስ፣ የብርን ዋጋ ማቅለል የፈለግነውን ኮንትሮባንድን የማምከን ውጤት አያስገኝልንም፡፡ ከምንሸጠው ይበልጥ የውጭ ሸቀጥ አስገቢ የመሆናችን እውነታ እስካልተቀየረ ድረስም የብር ዋጋ ሲወድቅ ከበፊቱ በበለጠ በብዙ ብር ዶላርን እየገዛን ሸቀጥ ከማስገባት አጣብቂኝ አናመልጥም፡፡ የተወሰኑ ነገሮችን በውድነታቸው ከመግዛት ብንቆጠብም፣ የአገር ውስጥ መተኪያ የሌላቸውንና ልናኮርፋቸው የማንችላቸውን ሸቀጦች እየተነጫነጭንም በውድ ዋጋ ለመግዛት እንገደዳለን፡፡ ይህ ደግሞ የበለጠ የኑሮ ድቀትንና ፖለቲካዊ ቅሬታን ያስከትላል፡፡

ለዚህ ነው በተደጋጋሚ እንደምንለው፣ ሸንካፋ የኢኮኖሚ መዋቅርን በአግባቡ በማስተካከል ጉዞ ውስጥ የሕዝብ ድጋፍንና ውዴታን መደረብ እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው፡፡ በውስጥም በውጭም ያሉ የአገር ልጆችን ድጋፍ በሰፊው ማግኘት ችግርን ታግሶ ለመቋቋም፣ ኮንትሮባንድን ለመጋተርና የውጭ ምንዛሪ ችግርን ለማቅለል ከማስቻልም በላይ፣ ሁለገብ ልማትን በሚጠቅሙ የዘመናዊ ልምድ፣ የእውቀት፣ የፈጠራና የምክር ርብርብ ለመታጀብ ያበቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ የሆኑትን እነዚህን ጥቅሞች ለማሟላት የማይዋደቅ ወይም የሚያስተጓጉል ፖለቲካ ፈጽሞ ተራማጅ ነኝ ለማለት አይችልም፡፡

 የሚዘልቅ ፈጣን ልማት በቅዋሜ አለመዳፋትንና የሕዝቦችን መተቃቀፍ ይሻል፡፡ ይህንን ስኬት የመቀዳጀት ነገር መብቶችን ከማክበርና አገራዊ መግባባት ላይ ከመድረስ ውጪ የማይታሰብ ነው፡፡ አዲስ ራዕይ (የካቲት – መጋቢት ዕትም፣2009) እንዳለው፣ ኢሕአዴጎች ምርጫው ወይ መዳን ወይ መጥፋት የሆነበት መስቀለኛ መንገድ ላይ ደርሰዋል፡፡ የ2008 ዓ.ም. ቅዋሜን ተከትሎ “ጥልቅ ተሃድሶ/ዴሞክራሲን ማጥለቅ” እያሉ ቢያወሩም እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስም ከመስቀለኛው መንገድ ፈተና አልወጡም፡፡ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿም በመስቀለኛው መንገድ ፈተና ውስጥ ናቸው፡፡ ይህ ኢሕአዴግም የኢትዮጵያ ሕዝቦችም ላይ የተደቀነ ፈተና “ስህተቶቼንና ጥፋቶቼን በጥልቀት አርሜ አመራር ልሰጣችሁ ተዘጋጅቻለሁ” እያሉ በውድም በግድም ሥልጣን ላይ በመቆየት አሮጌ ዘዴ የሚታለፍ አይደለም፡፡ የሕዝቦችን አንድ ላይ የገጠመ ነፃ መነሳሳትና ውዴታቸውን የተመረኮዘ የፖለቲካ ማሻሻያ ውስጥ መግባትን ይጠይቃል፡፡ እዚህም እዚያም የሚንፀባረቁት የጥርጣሬ ስሜቶችና የመተነኳኮል ብልጭታዎች ሲታሰቡ፣ ስለሕዝቦች አንድ ላይ በአንድ አቅጣጫ መትመም ማውራት ስለህልም ማውራት ሊመስል ይችላል፡፡ ግን በዕውን ሊፈጸም የሚችል ነው፣ ፍጥነት ካለ፡፡

ይህንን ጽሑፍ ጀምሬ ያዝ ለቀቅ በማደርግበት ወቅት የአገራችንን ዴሞክራሲ የማጎልበቱ ተግባር የ2012 ዓ.ም. ምርጫን ከቀዳሚዎቹ በጣም የተሻለ ነፃና ፍትሐዊ ውድድር ያለበት ከማድረግ ጋር ተያይዞ ሊካሄድ ይችላል የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የግጭት ቀዳዳዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው፣ በተለይም በእግር ኳስ ቲፎዞነት ውስጥ ሲጫጫስ የቆየው ጥላቻ የመረዘው ጎሰኝነት ያገጠጠ የአደባባይ ትርምስና ጥፋት እስከ መውለድ መድረሱ፣ ችግሮች ጊዜ የማይሰጥ አስተዳደግ እያመጡ መሆናቸውን የሚጠቁም ነው፡፡ እነዚህን አደጋዎች የሚያመክን ፖለቲካዊ መፍትሔ ከመንግሥት ብንጠብቅም ከፕሮፓጋንዳ በቀር የሚወጣው አልሆነም፡፡ በዚሁ ግንዛቤ መሠረት የሚከተሉት የለውጥ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ ሐሳብ አቀርባለሁ፡፡

  • ያለንበትን አሳሳቢ ሁኔታ በማጤን የታሰሩ ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን ፈትቶ በነፃ የመደራጀትንና የመንቀሳቀስን በር ከበፊቱ ይበልጥ በማስፋት የዴሞክራሲ ግንባታ ሒደትን መክፈት፣
  • ፓርቲዎች፣ ምሁራንና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበትና በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚመክር (የገዥው ፓርቲ ሌላ መልክ ያልሆነ) ጉባዔ ማዘጋጀት፣
  • ከዚሁ ጋር በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ውስጥ ሰላማዊና የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ እንዲኖር ለማስቻል አስተዳደሮች፣ የፀጥታ ኃይሎችና ሕዝቦች ተባብረው እንዲሠሩ አደራ መስጠት፣
  • በጉባዔው አማካይነት ባለው መንግሥት ሥር ከፓርቲዎች፣ ከምሁራንና ከሕዝብ ጋር በተባበረ እንቅስቃሴ በቶሎ መጀመር/መከናወን ያለባቸውን ተግባራት፣ ለመጪው አዲስ ምክር ቤት መተው ያለባቸውንና ረዘም ያለ ጥናትና መብላላት የሚሹ ጉዳዮችን የለየ መርሐ ግብር ማዘጋጀት፣
  • በመርሃ ግብሩም ውስጥ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ነባሩ የተወካዮች ምክር ቤት ተወካይነት እድሳት አግኝቶም ሆነ እንዳለ ተበትኖና በአዲስ ተቀይሮ፣ በትኩስ የለውጥ መንፈስ የዴሞክራሲና የአዲስ ባህል ግንባታ የሚቀጥልበትን ሐሳብ ለሕዝብና ለመንግሥት የማቅረብን ተልዕኮ ማካተት፣
  • እናም ብዙኃኑ በወደደው መንገድ ለውጡን ማራመድ፡፡

አገሪቱና ሕዝቦቿ ከዚህ ያላነሰ የለውጥ ጉዞን ይሻሉ፡፡ ኢሕአዴጎችስ ይይችን ታህል ተራማጅነት ለማሳየት ዝግጁ ናቸው?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...