Saturday, May 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከተፈጥሮ ምርቶች የተቀመመ የሞሪናጋና የሌሎችም ግብዓቶች የታከሉበት የለስላሳ መጠጥ ለገበያ ሊቀርብ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በለስላሳ መጠጥ ኢንዱስትሪው ውስጥ አዳዲስ ነገሮችን ለማስተዋወቅ የተነሳው ኩባንያ፣ የታጠነ ባለጋዝ ውኃን ጨምሮ ከከርከዴ፣ ከሞሪንጋ ቅጠል፣ ከተለያዩ ኸርብስና ከፓሽን ፍሩት የተቀመሙ መጠጦችን ለገበያ ለማቅረብ መዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል፡፡

በ200 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት በሰንዳፋ አካባቢ የተገነባውና በውስጡም የቅርብ ጊዜ ሥሪት አዳዲስ የጀርመን ሥሪት ማሽነሪዎችን የተከለው ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት ለገበያ ካዋላቸው የታሸጉ የማዕድን ውኃና የታጠነ ባለጋዝ ውኃ በተጨማሪ፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለገበያ የሚያቀርባቸውን የለስላሳ መጠጦችንም በማዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡

የዘቢም ኩባንያ ባለቤትና መሥራች አቶ ዘለዓለም ሙሉቀን (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በፋብሪካው የሚመረቱት የለስላሳ መጠጦች ሙሉ በሙሉ ከተፈጥሮ ፍራፍሬዎችና ዕፅዋቶች በተቀመሙ ግብዓቶች የሚዘጋጁ በመሆናቸው፣ ለሰውነት ጤናም ጥቅም እንደሚሰጡ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ከርከዴ በማር›› የተሰኘው የለስላሳ ምርት ከከርከዴ አበባና ቅጠል የሚዘጋጅ ነው፡፡ ‹‹ዶክተር ሞሪንጋ›› ሌላኛው የለስላሳ መጠጥ ዓይነት ሲሆን፣ ሌሎች የኸርብስ ዓይነቶች ተቀላቅለውበት የሚሰናዳና የፋብሪካው ዋነኛ ምርት እንደሆነም አቶ ዘለዓለም አብራርተዋል፡፡ ፓሽን ፍሩት ከተሰኘው ፍራፍሬ የሚዘጋጀው ለስላሳም ሙሉ ለሙሉ ከፍሬው በሚወጣ ጭማቂ እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል፡፡ ምርቶቹ ሌሎች የማጣፈጫና የማቅለሚያ ኬሚካሎች ሳይገባባቸው በተፈጥሮ እንደሚቀመሙም አብራርተዋል፡፡

ኩባንያው ‹‹መልካም ቀን›› የሚል መጠሪያ የተሰኘውንና ከመሬት ውስጥ በሚገኝ አለት ዙሪያውን የተከበበ የማዕድን ውኃ በማውጣት አጣርቶ ማቅረብ እንደጀመረ የሚገልጹት አቶ ዘለዓለም፣ ባለጋዝ ውኃውን አገርኛ ቃና ባለው አቀራረብ የጋዝ መጠኑን በመቀነስ አምርቶ ለገበያ ማቅረብ እንደተቻለ ይናገራሉ፡፡ የታጠነ ባለጋዝ ውኃው፣ ልክ በታጠነ እንሥራ የሚቀመጥ ውኃን ዓይነት የጭስ ቃና ኖሮት እንዲመረት መደረጉንም አብራርተዋል፡፡

እነዚህን ጨምሮ ሌሎችም እንደ ብርቱካን፣ ፓፓያ፣ ማንጎ የመሳሰሉትን በርካታ የለስላሳ መጠጦች የማምረት ውጥን የያዙት አቶ ዘለዓለም፣ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ አሁን በ15 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነባውን ፋብሪካ በእጥፍ የማሳደግ ዓላማ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ለማስፋፊያ ግንባታ እስከ ሦስት ሔክታር መሬት ጠይቆ እስኪሰጠው እየተጠባበቀ እንደሚገኝም ተጠቅሷል፡፡

ተጨማሪ የ200 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት በማካሔድ፣ በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው ያለውን በዓመት የ700 ሺሕ ሔክቶ ሊትር የማምረት አቅም ወደ 2.2 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር የማሳደግ ዕቅድ አላቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሰዓት 16 ሺሕ ጠርሙስ ለስላሳ መጠጦችንም ሆነ ውኃ የማሸግ አቅም ያለው ይህ ፋብሪካ ምርቶቹን ከኢትዮጵያ ባሻገር ወደ ጂቡቲ፣ ሶማሌላንድ እንዲሁም ደቡብ ሱዳን የሚልክበትን የገበያ ጥናት እንደሠራም ተብራርቷል፡፡

ለፋብሪካው የተተከሉት የጀርመን ማሽኖችን ተግባርና የቴክሎጂ ደረጃ ያብራሩት፣ የምርት ጥራት ቁጥጥርና የምግብ ደኅንነት ኃላፊዋ አዲስዓለም ዋለ እንዲሁም የምርት እሴት ሰንሰለት ኃላፊው አቶ ኤልያስ ኃይሉ (ኢንጂነር)፣ ክሮስ ከተሰኘው የጀርመን ኩባንያ የተገዙት ማሽሪዎች እ.ኤ.አ. በ2016/17 የተመረቱ ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያ የመጀመርያዎቹ እንደሆኑ የተነገረላቸው ማሽኖች በአፍሪካ በጥቂት አገሮች ብቻ የተተከሉ ሲሆኑ፣ ሙሉ በሙሉ የምርት ሒደትን ከሰው ንክኪ ነፃ ያደረጉ ስለመሆናቸው ሁለቱ ባለሙያዎች አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም የምርት ጥሬ ዕቃን እንደሚፈለገው መጠን በመቀላቀልና በማደባለቅ፣ የሚፈለገውን የጥራት ደረጃ ይዞ እንዲወጣ የሚያግዙት ማሽኖች፣ ምርት ለማሸግ የሚውሉ ለፕላስቲክ ጠርሙሶችን ፕሪፎርም እንደሚፈለገው ቅርጽና መጠን ከማዘጋጀት ጀምሮ፣ የምርት መለያ ወይም ሌብል የመለጠፍ፣ የመሙላት፣ የማሸግና ምርቱን የማውጣት ሥራን ሙሉ በሙሉ ያከናውናሉ፡፡

ፋብሪካው ሁሉምን የጥራት ደረጃዎች የሚያረጋግጡ የምርት የፍተሻና የጥራት ማስጠበቂያ ደረጃዎችን ስለማሟላታቸው ሲያብራሩም ሪቨርስ ኦይስሞይሲስ፣ አልትራ ቫዮሌት የማጣሪያ ሒደት፣ የኦዞን ማጣሪያ ሒደቶችን ጨምሮ በዝቅጠትና በሌሎችም ሒደቶችን ባክቴሪያና ጀርሞችን፣ ፈንገስን እንዲሁም ቫይረስና ሌሎችንም በማጣራትና በማከም ጤናማነታቸው የተረጋገጡ ምርቶችን እንደሚያወጡ ባለሙያዎቹ አብራርተዋል፡፡

የኩባንያው ባለቤት አቶ ዘለዓለምን ጨምሮ አብዛኞቹ በአስተዳደር ዘርፍ የተሰማሩ የዘቢም ኩባንያ ባለሟሎች ሜታ ቢራን ጨምሮ በሌሎችም ትልልቅ የመጠጥ ፋብሪካዎች ውስጥ ለረጅም ጊዜ የመሥራት ልምድ ያካበቱ ስለመሆናቸው የኋላ ታሪካቸው ያመላክታል፡፡ አቶ ዘለዓለም በመጠጥ ኢንዱስትሪው ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ ያካበቱት ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ለገበያ ያቀረቧቸውና ለማቅረብ እያዘጋጇቸው የሚገኙት ምርቶች በራሳቸው የተቀመሙ፣ የንግድና የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት ምዝገባ ማረጋጋጫ እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ለገበያ መቅረብ የጀመሩትን የባለጋዝ የታጠነ ውኃና የማዕድን ውኃው ከወዲሁ ወደተለያዩ የክልል ከተሞች ማሰራጨት የጀመሩ ሲሆን፣ የለስላሳ መጠጦቹ የማሸጊያና የምርት ጥራት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት በቅርቡ ተጠናቆ ለገበያ መቅረብ እንደሚጀምሩ ተገልጿል፡፡  

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች