Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ግብርና ምርምሩን እጀ ሰባራ ያደረገ የቅንጅት ችግር

ተዛማጅ ፅሁፎች

በስልሳዎቹ መጨረሻ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት አርሶ አደር ጫላ መርጊያ፣ በምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ ባኮ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው የበቆሎ ማሳቸው ውስጥ ሆነው ለአጨዳ የደረሰውን የበቆሎ አገዳ እያሻሹ ስለዘንድሮ የምርት ውጤት ፈገግታ በተላበሰ ገጽታቸው ለጎብኚዎቻቸው ያስረዳሉ፡፡

‹‹የአምናውም፣ የካቻምናውም ጥሩ ነበር፡፡ የዘንድሮው ግን የፍሬ አያያዙና የአገዳው ጥንካሬን ሳየው ይበልጥ የተለየ ነው፤›› በማለት በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስተባባሪነት በተዘጋጀው ጉብኝት ለተሳተፉ ታዳሚዎቻቸው አዲስ ተሻሽሎ ስለተለቀቀው የበቆሎ ዝርያ ያስረዱት፡፡

ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ባኮ ወረዳ በበቆሎ ምርቷ ከመታወቋ ባሻገር፣ የኢትዮጵያ የበቆሎ ሰብል ዕምብርት ተደርጋ ትቆጠራለች፡፡ ለዚህም ሲባል ነበር በ1950ዎቹ ገደማ የባኮ ግብርና ምርምር ማዕከል በአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት የተቋቋመው፡፡ ዛሬም ድረስ ይኼው የምርምር ማዕከል በበቆሎ ላይ የምርምር፣ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በፌዴራሉ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሥር ከሚገኙ 17 የምርምር ማዕከላት ውስጥ አንዱ የሆነው የባኮ ግብርና ምርምር፣ በበቆሎ ሰብል ላይ ለሚደረጉ ምርምሮች እንደ ብሔራዊ ማስተባባሪያ ማዕከል በመሆንም ያገለግላል፡፡

አቶ ጫላን ጨምሮ ከአካባቢው አልፎ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ አርሶ አደሮችም ከባኮ ግብርና ምርምር ማዕከል ከሚለቀቁ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡ ለምርት የተዘጋጀው የአቶ ጫላ በቆሎ፣ በምርምር ማዕከሉ በቅርቡ የተለቀቀውና የተሻለ ምርታማነትን በመስጠት፣ በሽታን በማቋቋም ባህሪው ከዚህ በፊት ከተለቀቁ ድቅል ዝርያዎች ውስጥ የሚመደበው ቢኤች 646 (BH 646) የተባለው ዝርያ ነው፡፡ ይኼን ዝርያ ለመጀመርያ ጊዜ በሁለት ሔክታር ማሳ ላይ ያበቀሉት አቶ ጫላ፣ ከ60 እስከ 70 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ በደስታ ቢገልጹም፣ የምርት ዘሩን ማግኘት አስቸጋሪ እንደነበር ግን አልሸሸጉም፡፡

የግብርና ባለሙያዎችም ቢሆኑ የተሻለ ምርት የሚያስገኙ የዘር ቴክኖሎጂዎችን የማፍለቁ ሥራ የመሻሻሉን ያህል በአርሶ አደሩ የተጠቀሱት የዘር አቅርቦትና ተያያዥ የግብዓት ችግሮች መኖራቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ ከምርምር ማዕከሉ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በምርምር ተቋማት የተሻሻሉ የበቆሎ ቴክኖሎጂዎች የዓመቱ ምርት ላይ ለውጥ እያመጡ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ዓመታዊ ምርት ወደ 70 ሚሊዮን ኩንታል ደርሷል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ አማካኝ ምርታማነቱም ቀደም ብሎ በ1990ዎቹ አካባቢ በሔክታር ይገኝ ከነበረው 12 ኩንታል አሁን ወደ 35 ኩንታል ከፍ በማለት 180 በመቶ በላይ ማደጉ ይገለጻል፡፡ ከ45 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ሕዝብም በምግብነትም ሆነ በገቢ ምንጭነት በበቆሎ ላይ ኑሮውን እንደመሠረተ ይታመናል፡፡

እንደ ባኮ ሁሉ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች በቆሎ ይመረታል፡፡ እየተመረተ ካለው ዓመታዊ ምርት በእጥፍ ማምረት የሚያስችል ተስማሚና ሰፊ የመሬት ሀብት መኖሩም ይገለጻል፡፡ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ እንኳንስ በመላ አገሪቱ ተመርቶ፣ በባኮና አካባቢው  በሚመረት በቆሎ ብቻ መላውን ኢትዮጵያ መመገብ ይቻላል፡፡

በሌላውም የሰብልና የሌላ ዓይነት የግብርና ምርት ረገድ እምቅ ሀብት በኢትዮጵያ ስለመኖሩ ይነገራል፡፡ ለአብነትም በስንዴና በገብስ ምርት ተዋቂ የሆኑት የአርሲና የባሌ ረባዳ መሬቶች አሁን ከሚያበቅሉት በላይ እጥፍ ማምረት የሚያስችል ዕምቅ አቅም ስላላቸው ከአገሪቱ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ሊቀርብ የሚችል ምርት ለማምረት ተፈጥሯዊ ፀጋ እንዳላቸው ይታመናል፡፡ በሌላ መልኩ ከዚህ በፊት እምብዛም የማይመረትበት የታችኛው አዋሽ ተፋሰስ በሚባለው የአፋር ክልል እንኳ በአግባቡ ቢመረት፣ ሊያስገኝ የሚችለው የስንዴ ምርት ከአገሪቱ ተርፎ አፍሪካን ለመመገብ የሚያስችል እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

የበቆሎ ምድር እንደሆነው እንደ ባኮ ሁሉ፣ በጤፍ ምርታማነታቸው ቀድሞውኑ የሚታወቁት የምንጃርና ሸንኮራ፣ አድኣ ሎሚና ተጎራባች አካባቢዎች በደብረ ዘይት ምርምር ማዕከል በሚደረጉ ምርምሮችና የቴክኖሎጂ አቅርቦቶች የተነሳ አበረታች ውጤቶች ይታይባቸዋል፡፡ እስካሁን በርካታ የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎች ከደብረ ዘይት የምርምር ማዕከል ተለቀዋል፡፡ ለበርካታ ዓመታት በአርሶ አደሮች እጅ ኡዴ በመባል የሚታወቀው ዝርያን ጨምሮ ምርታማነታቸውና በሽታን የመቋቋም አቅማቸው ጠንካራ የሆኑ እንደ ተስፋይ፣ ኡቱባና ዓለም ጤና የተባሉ አዳዲስ ዝርያዎች መውጣታቸውን ለአብነት የሚጠቅሱት የማዕከሉ ተመራማሪ ክበበው አሰፋ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ከነዚህ ሁሉ የተሻለውና በአምራች ኢንዱስትሪዎች በኩል ተፈላጊ የሆኑ አዲስ የምርምር ውጤቶች ተፈትሸው ወደ ዘር ማምረቱ ሥራ ተገብቷል ብለዋል፡፡

በአካባቢው በ1990 ዓ.ም. ገደማ በሔክታር 12 ኩንታል የነበረውን ምርታማነት   ወደ 35 ኩንታል ማሳደግ የሚችሉ ዝርያዎች ተለቀዋል፡፡ የቅርቡን መመልከት ቢያስፈልግ ኡቱባ የተባለውና በፊት ከተለቀቁት ሁሉ የምርምር ሥራውን አስመስጋኝ ያደረገ ምርት እንደማሳያነት በደብረ ዘይት ማዕከል በሚገኙ ተመራማሪዎች ዘንድ ይጠቀሳል፡፡

ሌላኛው ታዋቂ የምርምር ተቋም የመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከልም እንዲሁ በተለያዩ የሰብል ዝርያዎች፣ የቆላ ጥራጥሬዎችን፣ የቆላ ፍራፍሬዎችንና የአትክልት ዓይነቶችን የማዘመን ሥራ በመሥራትና ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ተግባራት ውስጥ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡

ከበርካታ ምርምሮቹ አንዱ የሆነው በቆሎን የማዳቀል ሥራ ይገኝበታል፡፡ በባኮ ከሚደረገው ምርምር በተጨማሪ በመልካሳ ማዕከል ብቻ ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ የበቆሎ ምርምሮች ተካሂደው በአጭር ጊዜ የሚደርሱ የተሻሻሉ ምርቶች ተለቀዋል፡፡ እነዚህም የተሻሻሉ ዝርያዎች በሔክታር ቀድሞ ይመረት ከነበረው ምርት ከሦስት እጥፍ በላይ ከፍ ያለ ምርት ማስገኘት መቻላቸውን ነው የማዕከሉ ተመራማሪዎች የሚገልጹት፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አሁን በመልካሳ ምርምር ጊቢ ውስጥ አዳዲስ የበቆሎ ድቅል ዝርያዎችን የማውጣት ሥራ ላይ መጠመዳቸውን ምርምሩን የሚያስተባብሩት አቶ ለዓለም ጥላሁን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እንደ ተመራማሪው ማብራርያ፣ ከዝናብ በተጨማሪ የአዋሽ ወንዝን በመጠቀም ከአሜሪካ፣ ከታይላንድና ከሌሎችም አገሮች ማዕከሉ ያስመጣቸውን ዝርያዎች በአገር ውስጥ ለማላመድ በሙከራ ላይ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ እየተላመዱ ከሚገኙት ዝርያዎች ውስጥ የአሜሪካ ግዙፍ የዘር አምራች ከሆነው ሞሳንቶ ኩባንያ የተገኘ ዝርያም ይገኝበታል፡፡

የተስፋው ሥጋት

በፌዴራል መንግሥት በሚተዳደሩ አገር አቀፍ የምርምር ተቋማትና በሌሎቹም  የግብርና ምርምር ጥረቶችና የተሻሻሉ ዝርያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ለአምራቹ አርሶ አደር ለማቅረብ የተደረጉ ጥረቶች ተስፋ እንደሚሰጡ ማየት ይቻላል፡፡ እንደ አዝርዕት ሁሉ የተሻሻሉ የእንስሳትና የዶሮ እርባታ ሥራዎችንም ለማሻሻል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እየተለቀቁ ነው፡፡

ምንም እንኳ የግብርና ምርምርን የማዘመኑ ጥረት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ቢዘልም የአገሪቱ ግብርና ግን ብዙ እንደሚቀረው ይስተዋላል፡፡ በምርት ብዛትም ሆነ በጥራት ብዙ ይቀራል፡፡ ይህ ደግሞ የአገሪቱን የምግብ ዋስትና የማረጋገጡ ጉዳይ እስካሁን አለመሳካቱ ጥያቄ እያስነሳ ቀጥሏል፡፡ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥን በተመለከተና ከበቂ በላይ በማምረት ግብርናው የአገሪቱን ኢኮኖሚ በተለይም አምራች ኢንዱስትሪውን መደገፍ የሚችልበት ደረጃ ማድረስ የመንግሥት ትኩረት ሆኖ ቆይቷል፡፡ አገሪቱ በተደጋጋሚ በድርቅ ከመጠቃቷና በረሃብ ከመታወቋ አንፃር መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱ በአወንታዊነት ይጠቀሳል፡፡

ለግብርና የተሰጠው ትኩረት ከግብርና ምርምሩ እስከ አመራረት ዘዴ ዝማኔ፣ ከአመራረት ባህሉ እስከ የተሻለ የምርት አማራጮች፣ ከዝናብ ጥገኝነት ወጥቶ መስኖ እስከመጠቀም፣ ለራስ ብቻ ከማምረት አልፎ በውጭ ገበያ ላይ ማተኮር፣ የምርት ዓይነቶች እንዲሁም ከባህላዊ የማምረቻ ዘዴ በመውጣት ዘመናዊ መሣሪያዎችና የተሻሻሉ ግብዓቶች ላይ ትኩረት መስጠቱ ይካተታል፡፡

ከመንግሥት በኩልም በተለይ ባለፉት 10 እና 15 ዓመታት ውስጥ ለግብርናው ዘርፍ የተደረገው ትኩረትና ኢንቨስትመንት ከአሥር ዓመታት በላይ ለቀጠለው የኢኮኖሚው ዕድገት ቁልፍ ሚና መጫወቱም ይጠቀሳል፡፡ ነገር ግን ዘርፉ ተሰጥቶታል ከተባለው ትኩረትና የኢንቨስትመንት መጠን አንፃር ተመዝግቧል የተባለው ስኬት ተመጣጣኝነትን በተመለከተ ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም፡፡

የግብርናው ምርምርና ከምርምሩ ውጤት (የቴክኖሎጂ ማፍለቁ) የአገሪቱ ምርታማነት ምን ያህል ተመጣጥኖ ውጤታማ መሆን ችሏል የሚለው አንዱ ጥያቄ ነው፡፡ ለማሳያ ያህልም ከምርምር ተቋማት የተለቀቁ ዝርያዎች ከቤተ ሙከራና ከመነሻ የዘር ማባዣ ማሳዎች አልፈው፣ በበቂ መጠን ተባዝተው አርሶ አደሩ በሚፈለገው መጠንና ዓይነት መቅረብ አለመቻላቸው ይጠቀሳል፡፡

በቅርቡ ሪፖርተር በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በተዘዋወረበት ወቅት ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች፣ የወረዳ አመራሮችና ተመራማሪዎች በጋራ የሚስማሙበት አገራዊ ችግር ይኸው መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል፡፡ እንዲሁም ሪፖርተር ያነጋገራቸው የምንጃርና ሸንኮራ አርሶ አደሮችም ተመሳሳይ ሐሳብ አንፀባርቀዋል፡፡

2010 ዓ.ም. የተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን መከፈትን በማብሰር ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) መስከረም 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሁለቱ ምክር ቤቶች ያቀረቡትን የመክፈቻ ንግግርን በማስመልከት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በምክር ቤቱ አራተኛ መደበኛ ስብሰባ፣ ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ላይ ተገኝተው ማብራርያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ ከዚሁ ግብርናን ከማዘመንና ምርታማነትን ከማሳደግ ጋር በተገናኘ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡም፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ ተቀስቅሶ የነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞና መጠነ ሰፊ ችግሮች ከዋና ዋና መንስዔዎች ውስጥ አንዱ የሥራ አጥነት ችግር መሆኑን አውስተው ነበር፡፡ ከአምና ጀምሮ በፌዴራል መንግሥት በቀጥታ በተመደበ 10 ቢሊዮን ብር ተንቀሳቃሽ የወጣቶች ፈንድ ይፋ ማድረጉም ይታወሳል፡፡ ከዚህ ተንቀሳቃሽ ፈንድ ውስጥ 60 በመቶው በጀት በግብርናው ዘርፍ ተሰማርተው ሥራ ለሚፈጥሩ ወጣቶች እንደሚውል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አስታውቀው ነበር፡፡

ወትሮውንም ለግብርናው ዘርፍ ስለሚሰጠው ልዩ ትኩረት በተደጋጋሚ ሳይገልጹ የማያልፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ ዓመትም ‹‹በተለይም በግብዓት አቅርቦትና በቴክኖሎጂ በተደገፉ ምርምሮች ግብርናችንን የማሳደግ ሥራ በፕሬዚዳንቱ ንግግር እንደተገለጸው ተጠናክሮ ይቀጥላል፤›› ብለዋል፡፡ የግብዓት አቅርቦት እያደገ ስለመምጣቱና ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የግብርና ግብዓቶችን በተመለከተ ለቢራ ተክል የሚውለውን የገብስ ምርት ዋቢ በማድርግ አስረድተው ነበር፡፡ ለአርሶ አደሮች በቂና የተሻሻለ የምርት ዘር ማቅረብ በመቻሉ፣ የቢራ ገብስ ከውጭ ማስገባት እንደቆመና የፋብሪካዎች ፍላጎት በአገር ውስጥ ምርት እየተሟላ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ጠቅሰዋል፡፡

ነገር ግን ወደ በቆጂ በተጓዝንበት ወቅት፣ ትልቁና አንጋፋው የቢራ ብቅል አምራቹ የአሳላ ብቅል ፋብሪካ ከአገር ውስጥ የሚቀርብለት ገብስ እየተሻሻለ ቢመጣም፣ አሁንም ድረስ በተወሰነ መጠን ከውጭ እያስገባ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አበራ መኰንን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፋብሪካው ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ ብቅል ለማምረት ለዓመታት የተቸገረው ከግብዓት (የብቅል ገብስ) አቅርቦት ጋር በተያያዘ እንደሆነ በመግለጽ፣ ባለፈው ዓመት ብቻ ፍላጎቱን ሙሉ በሙሉ ከአገር ውስጥ ማሟላት ቢፈልግም ከውጭ ማምጣቱ አልቀረም፡፡ ለአብነትም በ2008 ዓ.ም. 175 ሺሕ ኩንታል፣ በ2009 ዓ.ም. 220 ሺሕ ኩንታል የቢራ ገብስ ከውጭ አገር ፋብሪካው ማስገባቱን አውስተዋል፡፡

ከውጭ አስገብቶም ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ሲያመርት እንዳልነበረ የሚገልጹት አቶ አበራ፣ በ2009 ዓ.ም. ከውጭ ባያስገባም፣ በዚህ ዓመት ግን የሚያስፈልጉት ግብዓቶች መጠን 500 ሺሕ ኩንታል ገደማ ነው፡፡ የብቅል ፋብሪካው ከአገር ውስጥ የ350 ሺሕ ኩንታል ብቻ ግዥ ለመፈጸም ከዩኒየን ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር ውል ገብቷል፡፡ ቀሪውን 150 ሺሕ ኩንታል ግን ከውጭ ገበያ እንደሚሸፍን ገልጸዋል፡፡

የብቅል ፋብሪካው የግብዓት እጥረት ያጋጥመው እንጂ፣ ለቢራ የሚያስፈልገውን ገብስ ጥራት በተመለከተ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቁሉምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ተሻሽለው እየተለቀቁ የሚገኙት ዝርያዎች ተስፋ እንደሚጣልባቸውና በጥራት በኩል ያለው ችግርም መፍትሔ ወደ ማግኘቱ መቃረቡን  ዋና ሥራ አስኪያጁ በአድናቆት ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ከማዕከሉ ጋር ተቀራርበው እየሠሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

በማዕከሉ ከፍተኛ የብስ ተመራማሪ አቶ ሽመልስ ገዛኸኝ በበኩላቸው ከምርምር ማዕከሉ የሚለቀቁት ቴክኖሎጂዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዳበሩ በመምጣታቸው ለምግብነትም ሆነ ለቢራ ምርት የሚውሉ የገብስ ምርቶች ላይ ለዓመታት ከጥራት በኩል የሚነሱ ችግሮች እየተቀረፉ  ስለመሆናቸው  ይጠቅሳሉ፡፡ ነገር ግን ከምርምር ማዕከሉ የሚለቀቁ ቴክኖሎጂዎች ወይም የተሻሻሉ የገብስ ዝርያዎችን በተመለከተ የሚነሳው ችግር እንደ ሌሎች አዝዕርት ሁሉ ከመነሻ ዘር በኋላ ተመሳሳይ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይኼውም ከዘር ማባዛቱ ወደ አርሶ አደሩ እስከ ማድረስ ያለው ሥራ ላይ ውሱንነት መኖሩ ነው፡፡ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት የዘር እጥረት መከሰት ወይም የግብዓት አቅርቦት ሰንሰለቱ ወጥነት የሚጎድለው መሆኑ አጠቃላይ የግብርናው ዘርፍ የታለመለትን ትራንስፎርሜሽን እንዳያሳካ ከሚያጓትቱት ችግሮች አንዱ ነው፡፡

 በዚህ ዓመት መጨረሻ የግብርና ምርትን ወደ ውጭ በመላክ በድምሩ አራት ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚጠበቅ ፕሬዚዳንቱ ገልጸው ነበር፡፡ ነገር ግን ቅርብ ዓመታት ልምድ እንደሚያሳየው ዓመታዊ የኤክስፖርት አፈጻጸሙ ከዕቅዱ በብዙ የሚራራቅ ነው፡፡ ለድክመቱ ከመንግሥት በሚሰጡ ተመሳሳይና አሰልች ምክንያት ሲሰጥ፣ ድክመትን ለመሸፈን ሲሞከር ይስተዋላል፡፡ ለአብነትም ምርታማነቱ በታቀደው ልክ አለመሆኑ የውጭ ገበያ ፍላጎት ማነስ አልያም የዋጋ መውረድ ወዘተ. የሚሉትን ሰበብ በመፍጠር በቅንጅት መጓደል የአመራርና የአፈጻጸም ጉድለትን መሸፈን እየተለመደ መጥቷል፡፡ ለዓመታት ኢትዮጵያን ረሃብ የሚያስጥል የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ያልቻለው የግብርና ዘርፍ ውስጥ በዘር ቴክኖሎጂ ረገድ የሚታየው ምርምር አበረታች ቢሆንም ቴክኖሎጂው ከተለቀቀ በኋላ ዘር ማባዛቱንና ወደ አምራቹ እንዳይደርስ ማነቆ የሆኑ ችግሮች የመንግሥትም ሆነ የሌሎች ባለድርሻዎች ትኩረት እንደሚሹ እየተገለጸ ይገኛል፡፡

ይኼ ማነቆ ካልተፈታ በተለይ በአርሶ አደሩ በኩል የሚነሳው የምርጥ ዘር እጥረት በየምርት ዓመቱ መጀመርያ ላይ ጥያቄው መስተጋባቱን ይቀጥላል፡፡ በዚህም የሚመረተው ምርት በመጠንም በጥራትም ሳይሻሻል አሁንም የምግብ ዋስትና ማረጋገጡ ህልም ሆኖ ይቀራል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ባለፈው ወር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የዘር እጥረት (የተሻሻለ ምርጥ ዘር) በመቅረፍ በመንግሥት በኩል ራሱን የቻለ ‹‹የዘር ባንክ›› ማቋቋም ስምምነት ተደርሶ ባንኩን ማቋቋም የሚቻልበት  አሠራር እየተጠና እንደሚገኝ ገልጸው ነበር፡፡

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ የዘር እጥረት እንዲሁም ተያያዥ የግብዓት ችግሮች በአግባቡ ካልተፈቱ አጠቃላይ አገራዊ ምርትንም ሆነ የምግብ ዋስትና ማረጋገጡ ያስቸግራል፡፡ እንዲሁም ለውጭ ገበያ የሚውል በቂ ምርት ማቅረብንም ሆነ ግብርናው ኢንዱስትሪውን ሊመግብ የሚችልበት አቅም እንደማይኖረው ይገጻል፡፡

እነዚህ ነባር ችግሮች ለዓመታት አመርቂ በሆነ መንገድ ባይፈቱም፣ መንግሥት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን 30 ቢሊዮን ብር  በላይ መድቦ በማስገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ከግብዓት ጋር የተገናኙ እጥረቶችና የአመራር ሳንካዎች እልባት ካላገኙ ወይም ችግሮችን መቀነስ ካልተቻለ ለሚገነቡ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች፣ አምራ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ተመሳሳይ ፈተና መፈጠሩ እንደማይቀር ባለሙያዎች ሥጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

እነዚህ ችግሮች መቅረፍ መንግሥት ትል የቤት ሥራ ው፡፡ ለዚህ ደግሞ ቀዳሚ ድርሻውን የሚወስደውና የዘርፉ ዋነኛ ባለቤት የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በሥሩ የሚገኙ መሥሪያ ቤቶች ናቸው፡፡ በርግጥ ግብርናው እንደ እርሻ ሁሉ የእንስሳት እርባታና ልማቱንም የሚያጠቃልል በመሆኑ፣ የእንስሳት የዓሣ ሀብት ሚኒስቴር ወሳኝ ድርሻ ይል፡፡ ሚኒስቴሮቹ ዘርፉን አጠቃላይ ማዋቅር በመፈተሽ የቅንጅት ሥራውን ማሻሻል መንቀሳቀሳቸው ዜ የማይሰጠው ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ብዙዎች የሚናገሩት ነው፡፡ ይኼ ባልሆነበት ወቅት ምርታማነት በዕቅድ ብቻ እንዲያድግ መመኘቱ ውጤት ስለሌለው በምርምር ላይ የሚፈሰው ሀብት ከቤተ ሙከራና ከማሳያ ማሳዎች አልፎ በሰፊ እርሻዎች እንደልብ ካልተመረተም ልፋቱ ሁሉ ከንቱ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተ አቶ ፍስሐ ዘገየ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የምርምር ውጤቶችን በተገቢው ቦታ ደርሰው አርሶ አደሩንም ሆነ አገሪቱን መጥቀም ካልቻ ‹‹ተመራማሪውንም ቢሆን እጀ ሰባራ ማድረግ ነው፡፡››

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች