Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የኢንዱስትሪ ፓርኮቹን ምን አፈዘዛቸው?

የአገሪቱን የወጪ ንግድ ገቢ ለማሳደግ ብሎም በአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳርፉ ተስፋ ከተጣለባቸው የመንግሥት ውጥኖች ውስጥ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ይጠቀሳል፡፡ እነዚህ ፓርኮች በልዩ ትኩረትና ክትትል እንደሚገነቡም ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

ወደ ሥራ የገቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ‹‹ፈጣን›› በሚባል ሒደት ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸው ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ የሚገኙት ግን እንደቀደሙት ባለው የግንባታ ፍጥነት እየመጡ እንዳልሆነ እንታዘባለን፡፡ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት ደግሞ የድሬዳዋና የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ናቸው፡፡ የፓርኮቹ የግንባታ የመጠናቀቂያና ሥራ የሚጀምሩበትን ጊዜ በተመለከተ በተደጋጋሚ እንደሰማነው፣ ቢዘገይ በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም. መጨረሻ እንደሚመረቁና ሥራ እንደሚጀምሩ ነበር፡፡ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ግንባታዎቹን በኃላፊነት የሚያስፈጽሙት አካላት ደጋግመው ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ የመገናኛ ብዙኃንም ይህንኑ ሲያሠራጩና ሲያስተጋቡ ቆይተዋል፡፡

ሰሞኑን እንደሰማነው ግን እነዚህ ፓርኮቹ ተገንብተው አልተጠናቀቁም፡፡ የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታው 80 በመቶ ስለመጠናቀቁ፣ የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክም ቢሆን በተመሳሳይ ለምረቃ የሚበቃበት ደረጃ ላይ አለመደረሱን ስለኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የተላለፈው ዘገባ ያስረዳል፡፡

እነዚህ ክስተቶች ብዙ ነገር ያሳዩናል፡፡ ዕቅድና ተግባር ያለመገጣጠማቸውን በግልጽ ያሳብቃሉ፡፡ በዕቅድና በተግባር መካከል የሚስተዋለው ክፍተትም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና ሌሎችም ዘርፎች ውስጥ የተለመደ ነው፡፡ ይሁንና የአዳማና የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ግንባታ ለየት የሚያደርገው ግን በጥቅምት መጨረሻ ይመረቃሉ መባሉ ብቻ ሳይሆን፣ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሚገነቡ ስለመሆናቸው መገለጹ ነው፡፡

ፓርኮቹ በልዩ የክትትል ሥርዓት የሚገነቡና በቶሎ ወደ ምርት እንዲገቡ እንደሚደረጉ በተደጋጋሚ ሲነገርላቸው ከመቆየቱ አንፃር፣ አፈጻጸማቸው እንዲህ መንጠልጠሉ ከፓርኮቹ የሚጠበቀውን ውጤት እንዳያደነቃቅፈው ያሠጋል፡፡ ሥራ ይጀምራሉ በተባለበት ወቅት ግንባታቸው አለመጠናቀቁ በምን አግባብ ክፍተቱ ሊፈጠር እንደቻለ ግልጽ ባይሆንም፣ የፕሮጀክቶቹ መጓተት ሊያስከትል የሚችለው ተፅዕኖው ግን ቀላል አይሆንም፡፡

የፓርኮች ግንባታ በፍጥነት እንዲከናወን የተፈለገበት ብርቱ ምክንያት፣ አገሪቱ በእጅጉ የተቸገረችበትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችሉ የወጪ ንግድ ምርቶች የሚመረቱባቸው በመሆናቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

የግንባታ ጊዜያቸው በተራዘመ ቁጥር ፓርኮቹ ከወጪ ንግድ ጠቀም ያለ ገቢ ያስገኛሉ ተብለው በስንት ውትወታ የሚመጡ ኩባንያዎችን ወደ ፓርኮቹ በማስገባት ምርት ከመጀመር እንዲዘገዩ ያስገድዳቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ኩባንያዎቹ ያስገኛሉ የተባለውን የውጭ ምንዛሪ በወቅቱ እንዳይገኝ፣ የገበያ ክፍተት እንዲፈጠር ብሎም የአገሪቱን ተወዳዳሪነት ችግር ላይ ይጥላል፡፡

በእነዚህ ፓርኮች ዙሪያ እየታየ ያለው ሌላው ሥጋት በፓርኮቹ ግንባታ መዘግየት ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ወደ ሥራ የገቡትም ቢሆኑ የተፈለገውን ያህል ወይም ያስገኛሉ የተባለውን የውጭ ምንዛሪ መጠን እያስገኙ ነው ማለት ከባድ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሥራ የጀመሩት የኢንዱስትሪ ፓርኮች እስካሁን ድረስ ወደ ውጭ የላኩት በዕቅድ ከተቀመጠው ግባቸው ግማሹን እንኳ አለመሙላቱ ነው፡፡ ይህ  እንዴት ነው የሚታየው?

ከኢንዱስትሪ ፓርኮቹ  አስፈላጊነት አንፃር ሥራ የጀመሩት አፈጻጸማቸው ለምን ዝቅ እንዳለ መፈተሽ ግድ ነው፡፡ በግንባታ ላይ ያሉትም ቢሆኑ ለምን በዕቅዳቸው ልክ አልተጠናቀቁም ለሚለው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ መረጃው ለሕዝብ ይፋ መደረግ ይኖርበታል፡፡ መንግሥት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ በመበደር ለፓርኮቹ ግንባታ ማዋሉ ብቻም ሳይሆን፣ የተበደረው ገንዘብ የሚከፈልበት ጊዜ አጭርና የሚከፈለው ወለድም ከሌሎች የብድር ዓይነቶች ይልቅ ውድ የሚባል ነው፡፡ በመሆኑም ምን እየተካሄደ እንዳለ፣ ምን ችግር እንዳጋጠመና ምን ዓይነት ዕርምጃ እንደተወሰደ ማሳወቅ የመንግሥት ግዴታ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ሌላው የእነዚህ ፓርኮች የሥራ አፈጻጸም የታሰበውን ያህል ያለመሆኑ ወደፊት አገሪቱ የምታከናውናቸው ተመሳሳይ ሥራዎች ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ከወዲሁ መመልከትና መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ለውጥ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ፓርኮች ግንባታ፣ ከወዲሁ እርምት እየተደረገበት በትክክል የተቀመጠላቸውን ዓላማ ማሳካት አለማሳካተቸው ሊታይና ሊፈተሽ ይገባዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ኢትዮጵያን የአፍሪካ ኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የተያዘው ውጥን ጥያቄ ውስጥ የሚከት አካሄድ ሊሆን ይችላልና በልዩ ትኩረት ሊታይ ይገባዋል፡፡

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት