ቴዎድሮስ ገብረ እግዚአብሔር (የአባቱ ስም ተቀይሯል) በ2010 ዓ.ም. የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የአግሪካልቸር ዲፓርትመንት ተማሪ እንደሆነ፣ ‹‹መስከረም 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ዩኒቨርሲቲ ብንገባም እስካሁን ድረስ ትክክለኛ የማስተማር ሥራ አልተጀመረም›› ሲል ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ መጀመርያ አካባቢ ከመውጫ ፈተናው ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎች እንደነበሩ ያስታውሳል፡፡ ‹‹ከመውጫ ፈተናው ጋር በተያያዘ ከዩኒቨርሲቲው አመራር ጋር ተነጋግረን ስምምነት ላይ ብንደርስም፣ አንዳንድ ተማሪዎች ወደ ክፍል እንዳትገቡ እያሉ ያንገራግሩን ነበር፤›› ይላል፡፡ ‹‹ይህን ሁሉ ችለን ብንቆይም ባለፈው ሳምንት በአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ከተከሰው ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሕይወታችን አሥጊ ደረጃ ላይ በመድረሱ ከሰማኒያ በላይ የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች ሐሙስ ታኅሳስ 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ትምህርት ሚኒስቴር ሄደን ጥያቄ አቅርበናል፤›› ብሏል፡፡
የትምህርት ማስረጃቸውንና ሙሉ ልብሳቸውን ትተው እንደመጡ የገለጸው ተማሪው፣ ትምህርት ሚኒስቴር ችግራችንን ሊረዳልን ይገባል ብለው ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት እንደመጡ ይናገራል፡፡ ሪፖርተር ሐሙስ ታኅሳስ 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ትምህርት ሚኒስቴር ሄዶ እንዳረጋገጠው፣ ከ20 የሚበልጡ ተማሪዎች ሻንጣቸውንና የትምህርት ማስረጃቸውን ሳይዙ ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ መጥተዋል፡፡ ተማሪዎቹ የሚመገቡበት ገንዘብና የሚያድሩበት ቤት እንደሌላቸው ለትምህርት ሚኒስቴር ገልጸው ለጊዜው ምላሸ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ወደፊትም በዩኒቨርሲቲው ያለው የፀጥታ ችግር እስኪፈታ ድረስ መማር መጀመር እንደማይፈልጉ ተማሪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
2010 ዓ.ም. ከገባ ማግሥት ጀምሮ በአገሪቱ እየተከሰተ ባለው ቀውስ የበርካቶች ሕይወት አልፏል፡፡ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ደግሞ ከመኖሪያ ቀዬአያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከተነሳው ግጭት ጋር ተያይዞ በሁለቱ ክልሎች የሚማሩ ተማሪዎች ጥያቄ ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡ በተለይ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ከዩኒቨርሲቲው ለቅቀው እንዲወጡ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ያለው የፀጥታ ጉዳይ አስተማማኝ እስኪሆን ድረስ፣ ተማሪዎቹ ወደ ራሳቸው ክልልና ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንዲበተኑ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ተማሪዎች አዳዲስ ምደባ ተሠርቶላቸዋል፡፡
በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ያለው ግጭት ሙሉ በሙሉ ባለመቆሙ የተነሳም፣ የኦሮሚያ ክልል ተማሪዎች ከፍተኛ ጥያቄና ተቃውሞ ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡ ጉዳዩ ወደ መቱ ዩኒቨርሲቲ በመዛመቱ ለረጅም ሳምንታት በዩኒቨርሲቲው የነበረው የመማር ማስተማር ሒደት ተቋርጦ ከመቆየቱም በላይ፣ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ከዩኒቨርሲቲው ወጥተው ቆይተዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር በ2011 ዓ.ም ጀምሮ ዕጩ ምሩቃን ተመርቀው ከመውጣታቸው በፊት የመውጫ ፈተና እንደሚወስዱ ባሳወቀበት ጊዜ አንስቶ፣ በበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች እየተቃወሙ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በኦሮሞና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ ከነበረው ግጭት፣ ከመውጫ ፈተናውና ከሰሞኑ ግጭት ጋር በተያያዘ ከዘጠኝ በላይ ዩኒቨርሲቲዎች የማስተማር ሥራቸው ሙሉ በሙሉና በከፊል እንደተቋረጠ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ሐሙስ ታኅሳሰ 5 ቀን 2010 ዓ.ም. መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡
በአምቦ፣ በመቱና በሐረማያ እንዲሁም በጅማ ዩኒቨርሲቲ በከፊል ትምህርት ተቋርጦ መቆየቱን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ የማስተማር ሥራቸውን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ያቋረጡ ዩኒቨርሲቲዎች ዘጠኝ ደርሰዋል፡፡ ዶ/ር ሳሙኤል፣ ‹‹በተለያዩ ምክንያቶች በዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት በትክከል ሲቋረጥ ነበር፡፡ በ26 ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት በትክክል እየተሰጠ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል በ16 ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ ለአንድም ቀን ተቋርጦ አያውቅም፤›› ብለዋል፡፡
ትምህርት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ከተቋረጠባቸው ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ሐረማያ፣ ጅማ፣ አምቦ፣ ወለጋ፣ መቱ፣ አዲግራት፣ ደብረ ታቦር፣ ባህር ዳርና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዓርብ ኅዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም. የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በአገር አቀፍ ደረጃ በተከበረበት ወቅት በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ በተፈጠረ ግጭት የአንድ ተማሪ ሕይወት ማለፉን፣ የትግራይ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረ ሚካኤል መለስ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከተፈጠረው ግጭት ጋር በተያያዘ በወልድያ፣ በወለጋ፣ በአምቦ፣ በባህር ዳር፣ በደብረ ታቦር፣ ጎንደርና በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛና መለስተኛ ግጭቶች ተፈጥረው ነበር፡፡
በወልድያ ዩኒቨርሲቲ በተቀሰቀሰ ግጭትም ትምህርት ሙሉ በሙሉ ከመቋረጡ በተጨማሪ፣ በዩኒቨርሲቲው ሕንፃ ላይ የመቃጠል አደጋ ደርሷል፡፡ አብዛኛው ተማሪዎችም ዩኒቨርሲቲውን ለቀው እንደወጡ የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣን እንደተናገሩት በወልዲያ፣ በጎንደርና በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲዎች በተማሪዎች ላይ የአካል ጉዳት ከመድረሱ ባሻገር ንብረት ወድሟል፡፡ አብዛኛው የክልሉ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲዎች መውጣታቸውንም አረጋገጠዋል፡፡
የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ያለው እንዳወቅ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ከዚያ ዩኒቨርሲቲ እንደዚህ ሆኗል፡፡ ከዚያም እንደዚህ በሚሉ አሉባልታዎች የተጀመረ አለመረጋጋት ነው፡፡ መማር ማስተማሩ ተቋርጧል፡፡ ተማሪዎቹ ሁሉም ሰላም ናቸው፡፡ ሆኖም ሰባት ልጆች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ሁለቱ ላይ ከበድ ያለ፣ ቀሪዎቹ ላይ ደግሞ ቀለል ያለ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ታክመው ወጥተዋል፤›› ብለዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደምሴ ደስታ፣ ‹‹ታኅሳስ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠዋት አካባቢ በተወሰኑ ግቢዎች በተለይም ማራኪና አፄ ቴዎድሮስ ግቢዎች የተወሰኑ ችግሮች ነበሩ፡፡ እንደ ምክንያት የሚነሳው ከሰሞኑ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተከሰቱ የተባሉ ሁከቶችን ተከተሎ ነው፡፡ እኛም አካባቢ ይህ ነገር ነው የተከሰተው፡፡ በግብርና ኮሌጅ ላይ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡ መማር ማስተማሩ ባይቀጥልም የተከሰተ ችግር የለም፤›› በማለት ሰሞኑን ገልጸው ነበር፡፡
በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በተመሳሳይ ተከስቶ በነበረው ግጭት የአንድ ተማሪ ሕይወት እንደጠፋ መረጃዎች ቢያመለክቱም፣ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ወይም ከሌሎች የመንግሥት ኃላፊዎች ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ተከስቶ በነበረው ግጭትም የሁለት ተማሪዎች ሕይወት እንደጠፋ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ የመማር ማስተማር ሒደቱ እንደተቋረጠ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የሐረሚያ፣ የመቱ፣ የአምቦ፣ የጅማና የወለጋ ዩኒቨርሲቲዎች መማር ማስተማሩ በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ እንደተቋረጠ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዩኒቨርሲቲዎች እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች ባለፉት 26 ዓመታት ከነበሩት የተለየ እንደሆነ የትምህርት ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ለረጅም ዓመታት ከዝቅተኛ ባለሙያነት እስከ አመራርነት ሲሠሩ እንደቆዩ የሚናገሩት አቶ ብርሃኑ ገብረ እግዚአብሔር በዩኒቨርሲቲዎች እየተከሰተ ያለው፣ ባለፉት 26 ዓመታት ከታዩት ችግሮች የተለየና ከበድ ያለ መልዕክት ያለው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በንጉሠ ነገሥቱም ሆነ በደርግ ሥርዓት ተማሪዎች የሚቃወሙት መንግሥትን እንደነበር ያስታወሱት አቶ ብርሃኑ፣ ተማሪዎች ብሔርን መሠረት አድርገው እርስ በርሳቸው የሚጋጩበት ጊዜ ላይ መደረሱ አሳሳቢ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹በብሔርና በሃይማኖት የሚመጣ ግጭት የሚያስከትለው ቀውስ ከባድ ነው፡፡ ብሔርህን መዝዘህ ትልቁን ኢትዮጵያዊነት መሠረት ትተህ ስትጋጭ ከባድ ፈተና ነው፤›› ብለዋል፡፡
ለችግሮቹ መንስዔዎች ብለው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከልም ኢትዮጵያዊነትን ከማቀንቀን ይልቅ ለብሔርተኝነት ትኩረት በመስጠት የቆዩ አብሮ የመኖር እሴቶች እየተረሱና እየተዘነጉ መምጣት፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአገራዊ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ጠንካራ ሥራዎችን አለመሥራት የሚሉት እንደሚገኙበት አስረድተዋል፡፡
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ወሊሶ ካምፓስ መምህር አቶ ሥዩም ተሾመ በበኩላቸው፣ በአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች መንስዔያቸው መንግሥት የሄደበት መንገድ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹እነዚህ ችግሮች የዚህ መገለጫዎች ናቸው›› ብለዋል፡፡ ‹‹እንደ አገር ከምንከተለው የፖለቲካ አቅጣጫ በተጨማሪ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የትምህርት ሚኒስቴርና የዩኒቨርሲቲ አስተዳደሮች ችግሮች ሲከሰቱ መፍትሔ ለመስጠት የሚያደርጉት ጥረት አነስተኛ በመሆኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ብሔርን መሠረት አድርጎ ጥቃት ሲፈጸም የሚወሰድ ዕርምጃ ባለመኖሩ የተነሳ፣ ችግሮች እየሰፉና መጠናቸው እየጨመረ እንደመጣ የገለጹት አቶ ሥዩም፣ ትምህርት ሚኒስቴር በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ሥራ ማከናወንና ችግሮች ሲፈጠሩም አፋጣኝ ዕርምጃ መውሰድ ነበረበት ይላሉ፡፡
‹‹በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ከ60 በላይ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የሆኑ መምህራን ለትምህርት ሚኒስቴር ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሆነ ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ትምህርት ሚኒስቴር የሰጣቸው ምላሽ አልነበረም፡፡ ችግሩ በቀጣይ ወደ መቱ ዩኒቨርሲቲ ተስፋፍቶ ሌላ ቀውስና ችግር አስከተለ፡፡ መማር ማስተማሩ ከመቋረጡ ባሻገር የትግራይ ብሔር ተወላጆች ዩኒቨርሲቲውን ለቀው ወጡ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ትምህርት ሚኒስቴር የወሰደው ዕርምጃ አልነበረም፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡
‹‹ቀስ እያሉ ችግሮች እየሰፉና እየገዘፉ በመምጣት በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ተከስተዋል፤›› ብለዋል አቶ ሥዩም፡፡ ለችግሮች መከሰት ሁለተኛ ምክንያት አድርገው የጠቀሱት የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች በብሔራቸው ምክንያት በፕሬዚዳንትነት መሾማቸው እንደሆነ አውስተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ አካባቢዎች ቢቋቋሙምና እየተቋቋሙ ቢሆኑም፣ በፕሬዚዳንትነት የሚሾሙት ዩኒቨርሲቲዎች በተቋቋሙበት አካባቢ ብሔርን መሠረት ተደርጎ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህ አሠራር በራሱ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የብሔርተኝነት ስሜት እያየለ ኢትዮጵያዊነት እየተሸረሸረ እንዲመጣ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
ሦስተኛ ምክንያት አድርገው ያቀረቡት ደግሞ የአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን በሚያራምዱት አመለካከት ምክንያት እንደሆነ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹አንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በተለያዩ ችግሮች ከሞተ የእኔ ብሔር ነው የሞተው እያልን በቁጥር ላይ እየተጫወትን ነው፡፡ የራሳችን ብሔር ከሆነ አጉልተን እናወጣለን፡፡ የሌሎችን ችግር እያዳፈንን የራሳችንን ብሶት ብቻ እያራገብን ነው፤›› ብለዋል፡፡
ለአሥር ዓመታት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሲያስተምሩ እንደቆዩና እንደዚህ ዓይነት ችግር አይተው እንደማያውቁ የተናገሩት አቶ ሥዩም፣ ዛሬ ነገ ሳይባል መንግሥትም ሆነ የሚመለከተው አካል ትኩረት በመስጠት መፍትሔ መፈለግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ችግሮችን ለመፍታትም የፖለቲካ ልሂቃኑ የጋራ መግባባት መፍጠር እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች አመዳደብ ጀምሮ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በአዲግራት ተጀምሮ ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የተዛመተውን ግጭት ለማብረድ እየተሠራ መሆኑን፣ የትግራይ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረ ሚካኤል መለስ ዓርብ ታኅሳስ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹በአክሱምና በመቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደት እንዳይታወክ የክልሉ መንግሥት እየሠራ ነው፡፡ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ያለው ክስተት በአክሱምና በመቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች ባሉ ተማሪዎች ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድርባቸው የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የዩኒቨርሲቲ የቦርድ አመራሮችና ኃላፊዎች በትኩረት እየሠሩ ነው፡፡ በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች በሰው ሕይወትም ሆነ በአካል የደረሰ ጉዳት የለም፡፡ የሚናፈሱ ወሬዎች ይኖራሉ፡፡ መደበኛ የማስተማር ሥራም ለደቂቃ አልቆመም፤›› ብለዋል፡፡
በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ያለውን ጉዳይ በተመለከተም፣ ‹‹የተረጋጋ የመማር ማስተማር ሥራ ተጀምሯል፡፡ ከዚህ የተሻለ ለማድረግ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አመራሮችና የተቋሙ ማኅበረሰብ እየሠሩ ነው፡፡ በሁሉም የትምህርት መስኮች የማስተማር ሥራ ተጀምሯል፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ገብረ ሚካኤል ይህንን ይበሉ እንጂ፣ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እንደተናገሩት የማስተማር ሥራ ያልተጀመረባቸው የትምህርት ክፍሎች አሉ፡፡ ተማሪዎቹ ወደ ምግብ ቤትና ወደ ዶርማቸው የሚንቀሳቀሱት በመከላከያ ኃይል ታጅበው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በርካታ ተማሪዎችም ግቢውን ለቅቀው ወደ መጡበት አካባቢ መመለሳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ተማሪ ዓርብ ታኀሳስ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገረው፣ በሌሊት ከግቢ በመውጣት ወደ መጣበት አካባቢ ተመልሷል፡፡ ተማሪዎች ያለ መከላከያ ኃይል መንቀሳቀስ እንደማይችሉም አስረድቷል፡፡
አቶ ገብረ ሚካኤል ተማሪዎች በሥጋት ምክንያት ከግቢው እየወጡ ስለመሆኑ ለተጠየቁት ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በተከሰተው ግጭት በመደናገጥና በመፍራት ከግቢ የወጡ ትንሽ ተማሪዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ዩኒቨርሰቲው ተማሪዎች ወደ ግቢያቸው ተመልሰው መማር እንዲጀምሩ ከፍተኛ ሥራ እያከናወነ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተጀምሮ ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የተዛመተው የተማሪዎች ግጭትና ሁከት በወላጆች ላይ ከፍተኛ የሆነ ችግር እያስከተለ ነው፡፡ ችግሩ ተፈትቶ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራቸው እንዲገቡ እየተሠራ መሆኑን ዶ/ር ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡ ‹‹ትምህርት በመቋረጡ የትምህርት ጥራቱንም ሆነ የተማሪዎችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ እየጎዳ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከሥጋት ነፃ ሆኖ ትምህርቱ መቀጠል አለበት፡፡ የእኛ የመጀመሪያ ሥራ የሚሆነው ትምህርቱን ለማስቀጠል የተማሪዎችን ደኅንነት ማስጠበቅና የወላጆችን ሥጋት መቅረፍ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ በሁሉም ተቋሞቻችን የፌዴራል መንግሥቱ የፀጥታ ኃይሎች እንዲሰማሩና የተማሪዎችን ደኅንነት እንዲያስጠብቁ ለማድረግ እየሠራን እንገኛለን፤›› ብለዋል፡፡
የተቋረጠውን የማስተማር ሥራ ከማስቀጠል ባሻገር የተማሪዎችንና የወላጆችን ሥጋት በቀላሉ ማስወገድ እንዳልተቻለ ግን እየተነገረ ነው፡፡ ችግር በተፈጠረባቸውም ሆነ ባልተፈጠረባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከመውጫ ፈተናው ጀምሮ እስከ ብሔር ተኮሩ ግጭት ያለው ጉዳይ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱንና ችግሩን ለመፍታትም ውስብስብ እንደሆነ እየተሰጠ ነው፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ችግሩን ለመፍታት ኮማንድ ፖስት እንዳቋቋመ ቢናገርም፣ በዩኒቨርሲቲዎች ያለው ውጥረት አለመርገቡን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ኮማንድ ፖስቱ የተፈጠረውን ችግር ሙሉ በሙሉ በመፍታት ዩኒቨርሲቲዎችን ወደ ትክክለኛ የማስተማር ሥራቸው የመመለስ ተልዕኮ እንደተሰጠው ግን ታውቋል፡፡