ከ16ቱ የግል ባንኮች የባንክ ኢንዱስትሪውን ዘግይቶ የተቀላቀለው ደቡብ ግሎባል ባንክ በ2009 ሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 67.7 ሚሊዮን ብር እንዳተረፈ አስታወቀ፡፡ የተከፈለ ካፒታሉንም 500 ሚሊዮን ብር አደርሳለሁ ብሏል፡፡
ባንኩ ዛሬ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ይፋ ካደረገው ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርቱ መረዳት እንደተቻለው ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ ከቀደመው ዓመት በ0.4 በመቶ ቀንሷል፡፡ በቀደመው ዓመት ባንኩ ከታክስ በፊት አግኝቶ የነበረው ትርፍ 67.9 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህም ከሌሎች ባንኮች አንጻር አነስተኛው የትርፍ መጠን ነው፡፡
የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ኑረዲን አወል በሒሳብ ዓመቱ የባንኩን ክዋኔ አስመልክተው ባቀረቡት ሪፖርት የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ 1.4 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ አስታውቀዋል፡፡ የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከቀዳሚው ዓመት በ64.2 በመቶ ወይም በ559.8 ሚሊዮን ብር ጨምሯል፡፡
የአስቀማጮች ቁጥር በ68.3 በመቶ ማደጉን የሚገልጸው የባንኩ ሪፖርት አሁን አጠቃላይ የአስቀማጮች ቁጥር 61630 መድረሱንም አመልክተዋል፡፡
የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 2.1 ቢሊዮን ብር እንደደረሰም የሒሳብ ዓመቱ ሪፖርት ያመላክታል፡፡ በቀደመው ዓመት የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 1.3 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡
የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 351.2 ሚሊዮን ብር የደረሰ ቢሆንም ብሔራዊ ባንክ ባንኮች መጀመሪያ የተከፈለ ካፒታላቸውን 500 ሚሊዮን ብር ማድረስ እንዳለባቸው ያሳለፈውን መመሪያ ያላሟላ ነው፡፡
ይህንኑ የካፒታል መጠን በተመለከተ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ በሪፖርታቸው በአሁኑ ወቅት እልህ አስጨራሽ በሆነ መልኩ የቦርድ አባላት፣ ማኔጅመንትና ሠራተኞች ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ ከሪቴይንድ ኧርኒንግ (retained earning) ጋር በአሁኑ ወቅት የባንኩ የተከፈለ ካፒታል የሚሟላ ይሆናል ብለዋል፡፡
ሆኖም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸውን 500 ሚሊዮን ብር እንዲያደርሱ የሰጠው የጊዜ ገደብ ነሐሴ 2009 ዓ.ም. ያለፈ እንደሆነ ቢታወቅም ባንኩ በዛሬው የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንዳስታወቀው በዚህኛው የሒሳብ ዓመት የተፈረመ ካፒታሉን በማሰባሰብ 620 ሚሊዮን ብር አድርሳለሁ ብሏል፡፡