Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየተመድ ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ በኢትዮጵያ አዲስ ድርቅ መከሰቱን ይፋ አደረገ

የተመድ ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ በኢትዮጵያ አዲስ ድርቅ መከሰቱን ይፋ አደረገ

ቀን:

– የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ተመድ ያወጣው ሪፖርት የተቻኮለ ነው ብሏል

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፣ በኢትዮጵያ ደቡብ ምሥራቃዊ ክፍል አዲስ ድርቅ በድጋሚ መከሰቱን ይፋ አደረገ፡፡

ተመድ ያሠራጨው መረጃ እንደሚያመለክተው በአብዛኛው በሶማሌ ክልል፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል ውስጥ ከሚገኙ 212 ወረዳዎች ውስጥ 93 ያህሉ የመኸር ምርታቸው የተበላሸ እንደሚሆን፣ ይህም በዝናብ እጥረት ምክንያት እንደሚከሰት ይጠበቃል፡፡ በሦስቱ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች አማካይ የምርት ውጤት የሚጠብቁ 47 ወረዳዎች ሲሆኑ፣ 72 ወረዳዎች ደግሞ ጥሩ ምርት እንደሚጠብቁ በተደረገ ጥናት መሠረት መታወቁን የተመድ ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

አዲሱ ድርቅ በተለይ በሶማሌ ክልል ዳዪር እንዲሁም ሃጋያ እየተባለ የሚጠራው የመኸር ዝናብ በመዛባቱ የተከሰተ መሆኑን ተመድ ይፋ አድርጓል፡፡ በተመድና በኮሚሽኑ የጋራ ትብብር የድርቅ ሁኔታው ቅኝት የተካሄደው ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ እንደነበርም የተመድ መረጃ ይጠቁማል፡፡

ምንም እንኳ የተከሰተው ድርቅ የተረጋገጠው በተመድ ጽሕፈት ቤትና በብሔራዊ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መካከል በጋራ በተካሄደ ጥናት እንደሆነ ተመድ ቢገልጽም፣ ኮሚሽኑ ግን በዚህ አልተስማማም፡፡

ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ለሪፖርተር እንዳብራሩት ከሆነ፣ የወጣው ሪፖርት ትክክለኛነት የሚረጋገጠው በኅዳርና በታኅሳስ በሚካሄዱ የመኸር ወቅት ቅኝቶች በመሆኑ የተመድ ሰብዓዊ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ያወጣው የድርቅ ሪፖርት ያለጊዜው ተቻኩሎ የወጣ ነው፡፡

የመኸር ዝናብ መቅረቱ በደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍሎች የሚረጋገጠው በኅዳር ወቅት በሚካሄድ ቅኝት ሲሆን፣ ይህም በተለይ በሰብል ምርቶች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማረጋገጥ እንደሚረዳም ኮሚሽነር ምትኩ አብራርተዋል፡፡ በአርሶ አደሮች አካባቢ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በታኅሳስ ወቅት የሚካሄደው ቅኝት ትክክለኛውን መረጃ ለማወቅ እንደሚረዳ ያስረዱት ኮሚሽነሩ፣ በእንስሳትና በግጦሽ መሬቶች ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት በዚህ ወቅት ሊረጋገጥ እንደሚችል ጠቁመው፣ አዲሱ ድርቅ ገና አለመረጋገጡን አስታውቀዋል፡፡

ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ የተከሰተው መጠነ ሰፊ ድርቅ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ ፈላጊዎች እንዲሆኑ አስገድዷል፡፡ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ለስንዴ ግዥ የዋለ ሲሆን፣ በርካታ እንስሳት በድርቁ መሞታቸው ይታወሳል፡፡ በ1996 ዓ.ም. በተመሳሳይ ከ11 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ለዕለት ደራሽ ዕርዳታ ያጋለጠ ከፍተኛ ድርቅ መከሰቱ ይታወሳል፡፡ እስካሁንም ከስድስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች በሴፍቲኔት መርሐ ግብር ታቅፈው ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

አምና ተስፋፍቶ ከቆየው ድርቅ በተጨማሪ፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎች በአጣዳፊ የተቅማጥና የትውከት (አተት) በሽታ መመታታቸው አይዘነጋም፡፡ እንደ ሶማሌ ያሉ ክልሎች አሁንም ድረስ ከዚህ በሽታ ወረርሽኝ ለመላቀቅ እየተጣጣሩ እንደሚገኙ ተመድ ያወጣው ሪፖርት አመላክቷል፡፡

                  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...