Wednesday, October 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የታየው ዓይነት የምርጫ ፋና ወጊነት በሌሎችም መስኮች በስፋት ይቀጥል!

ዝነኛው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በፕሬዚዳንትነት እንዲመራ በመመረጡ፣ ከፍተኛ የሆነ ሕዝባዊ ድጋፍ ተሰምቷል፡፡ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ከ1979 ዓ.ም. ጀምሮ ለ29 ዓመታት ባደረጋቸው 400 የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ውድድሮች 80 በመቶ ያህሉን በበላይነት ያጠናቀቀ፣ በሁለት ኦሊምፒኮች ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያጠለቀና በታላላቅ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች 27 ክብረ ወሰኖችን የሰባበረ ጀግና አትሌት ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም. ራሱን ከአትሌቲክስ ውድድር ቢያገልም፣ ከአትሌቲክስ ስፖርት ሳይርቅ ቆይቶ ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት የሚያስችለውን በቂ ድምፅ አግኝቷል፡፡ ኃይሌ በአፍሪካ አኅጉር ስምና ዝና ያተረፈውን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መሥራችና ባለቤት ሲሆን፣ በዚህ በየዓመቱ በሚካሄድ ውድድር ምክንያት ለአገሪቱ በርካታ አትሌቶችን ያፈራ ነው፡፡ ሩጫን መሮጥ ብቻ ሳይሆን የሚኖረው በመሆኑ፣ በከፍተኛ ጥረት አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ለመምራት የሚያስችለውን ሕዝባዊ ተቀባይነትና ውጤት አግኝቷል፡፡ የሕዝብ ድጋፍም ጎርፎለታል፡፡ ይህ ዓይነቱ የምርጫ ፋና ወጊነት በዚህች አገር ሊለመድ ይገባል፡፡

ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ከአገር ቤት አልፎ በመላው ዓለም ያለው ስምና ዝና ከፍተኛ በመሆኑ፣ በፕሬዚዳንትነት መመረጡ በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ይህንን ዓይነቱን መልካም አጋጣሚ ከራስ ጥቅምና ፍላጎት በላይ አግዝፎ ለሚያይ ማንኛውም ዜጋ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ብቃት አለን የሚሉ ዜጎች ቆርጠው ከተነሱ ይሳካላቸዋል ማለት ነው? ምኞት ከቅዠት በላይ ዕውን መሆን ይችላል እንዴ? ኢትዮጵያ ስሟ በበጎ የሚወሳና እንዲህ ዓይነት ዕድል የምትሰጥ አገር ናት ወይ? ወደፊትም በተለያዩ መስኮች አገራቸውን ለማገልገል የሚፈልጉ ብቃት ያላቸው ዜጎች ይበረታታሉ ወይ? በተለየዩ ምክንያቶች በሚፈጠሩ ችግሮች ሳቢያ አገሪቷ ስሟና ገጽታዋ ቢደበዝዝም በሌላ በኩል ተስፋ ሰጪ ነገሮች መታየት ይችላሉ ለካ? ወዘተ. የሚሉ ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ ያገኛሉ፡፡ በሙያ ማኅበራት፣ በሲቪክ ተቋማት፣ በየደረጃው ባሉ መንግሥታዊ መዋቅሮችና በመሳሰሉት ሳይቀር ትልልቅ አስተዋጽኦዎችን የሚያበረክቱ ዜጎችን በብዛት ለማግኘት እንደ መንደርደሪያ ይጠቅማል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በዳበረ ልምዳቸውና በገንዘባቸው ሳይቀር አገራቸውን ለማገልገል ፍላጎት ያላቸው ዜጎች እንዲበረታቱና እኛም አለን እንዲሉ የሚረዳ በጎ ጅምር ነው፡፡

የአሁኑ ጅምር በእግር ኳስ ፌዴሬሽንና በሌሎችም የስፖርት ዘርፎች መቀጠል አለበት፡፡ ከዚያ በመለስ በትምህርት፣ በጤና፣ በትራንስፖርት፣ በንግድ፣ በውጭ ጉዳይ፣ በሲቪል ሰርቪስ፣ በአገር አስተዳደር፣ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች፣ ወዘተ. በፖሊሲና በስትራቴጂካዊ ጉዳዮች በማማከር፣ በማሠልጠን፣ አመራር በመስጠትና በመሳሰሉት አንቱ የሚያስብል ዕውቀትና ሙያ ያላቸውን ዜጎች ግማሽ መንገድ ሄዶ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ በተለይ የሙሉ ጊዜ አመራር በሚፈልጉና እስካሁን ውጤት በማይታይባቸው መስኮች ላይ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ለአገሪቱ ሲባል በአትሌቲክስም ሆነ በተለያዩ መስኮች ሕዝባዊ ተቀባይነት ያላቸው፣ በሥራቸው ውጤታማ የሆኑ፣ በብቃታቸው የተመሰከረላቸው፣ ሠርተው ማሠራት የሚችሉ፣ አገራቸውን ከልብ የሚወዱ፣ ከግል ጥቅማቸውና ዝናቸው ይልቅ አገርንና ሕዝብን የሚያስቀድሙ፣ ብልሹ አሠራሮችን የሚያስወግዱ፣ በራሳቸው የሚተማመኑና ትክክለኛ ውሳኔ ለመስጠት የማያንገራግሩ ኩሩ ዜጎች ዕድሉን ሊያገኙ ይገባል፡፡   

በተለያዩ ጊዜያት ለመታዘብ እንደተቻለው በስፖርቱ ውስጥም ሆነ በተለያዩ ዘርፎች ከሙያ ይልቅ የጥቅም ትስስርን፣ የመንደር ልጅነትንና አምቻ ጋብቻን ማስቀደም የተለመደ ነው፡፡ በዕውቀታቸው፣ በልምዳቸው፣ በሥነ ምግባራቸውና በሕዝብ ተቀባይነታቸው የሚታወቁ እየተገፉ የጥቅማ ጥቅም አሳዳጆች መፈንጫ ሆነው ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም ጥያቄዎች ሲቀርቡ በቀጥታ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ማስፈራራትና ማደናገር፣ የሀቀኛ ዜጎችን ስም ማጥፋት፣ በሐሰተኛ ሪፖርት ከመድረኩ ማባረር እንዲሁ የተለመደ አጉል ተግባር ነበር፡፡ የሰዎች መመዘኛ በተሰጣቸው ኃላፊነት ምን ያህል ውጤታማ መሆናቸው መሆን ሲገባው፣ በየጊዜው በስፖርቱ ውስጥም ሆነ በሌሎች ዘርፎች አጥፊዎች ለበለጠ ሹመት መታጨታቸው የተለመደ ስለሆነ ተስፋ አስቆራጭ ነበር፡፡ አሁን በሻለቃ ኃይሌና በጓደኞቹ ከፍተኛ ጥረት ጭላንጭል መታየቱ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ በተጨማሪም በዝናም ሆነ በሀብት ታዋቂ የሆነ ሰው ካስመዘገበው አመርቂ ውጤት ጋር የአመራሩን ሥፍራ ሲይዝ ደስ ያሰኛል፡፡ ከፍተኛ የሆነ ዕገዛም ሊደረግለት ይገባል፡፡ የተለመደው ጠልፎ የመጣል አባዜ ውስጥ መግባት ነውር ነው፡፡ መወገዝ አለበት፡፡

ኃይሌ ስፖርት የትርፍ ሰዓት ሥራ ነው እየተባለ የአገሪቱ አትሌቲክስ ወደኋላ መጎተቱን፣ እሱ ግን የሙሉ ጊዜ ሥራ በማድረግ የሚያስተዳድራቸውን የግል ድርጅቶቹን ትቶ አገሩን ለማገልገል ራሱን ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም በአትሌቲክሱ ውስጥ ያሉትን ችግሮች በመንቀስ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት መዘጋጀቱንም እንዲሁ፡፡ ይህም የሥራ ዘመኑ ፈተና እንደሚሆንም ገልጿል፡፡ አዲሱ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ለውጥ ለማምጣት ሲነሳ ከፍተኛ ዕገዛ ይፈልጋል፡፡ በተለይ በሥራ አስፈጻሚነት አብረውት የተመረጡ የቀድሞ አትሌቶችና ሌሎች ባለሙያዎች መሠረታዊ ለውጥ እንዲመጣ በጋለ መንፈስ መሥራት አለባቸው፡፡ በአትሌቲክሱ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ደግሞ በመጀመሪያ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት የሚባሉት መርሆዎች መኖር አለባቸው፡፡ አለበለዚያ በእነዚህ መርሆዎች መጓደል ምክንያት የተለመደው አደናቃፊነትና አሻጥር ይንሰራፋል፡፡ ይህ በአገሪቱ የተለመደ ችግር ሥር ነቀል ለውጥ ይፈልጋል፡፡ አድርባዮችና አስመሳዮች የተሰገሰጉበት የስፖርት ዘርፍ ደግሞ የሚጠራው በሥር ነቀል ለውጥ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ከአዲሱ ተመራጭ ጎን መቆም አለባቸው፡፡ ለውጥ የሚገኘው ሕዝባዊ ድጋፍ ሲታከልበት ብቻ ነው፡፡

በአጠቃላይ ለአገሪቱ ሰላም፣ ብልጽግና፣ ዴሞክራሲና ዘለቄታዊነት ሲባል ሕዝብ ለሚፈልጋቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው በአግባቡ መመራት፣ መዳኘትና ሰላምና ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ነው፡፡ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ ነው፡፡ በዚህም የመንግሥትም ሆነ የማኅበራት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሚፈለጉ ዜጎች ነፃነታቸው ተጠብቆ በተጠያቂነት መንፈስ እንዲሠሩ ዕድሉ ይመቻች፡፡ ከሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ የራሳቸውንና የቢጤዎቻቸውን ጥቅም ከማግበስበስ የተለየ ዓላማ የሌላቸው ከንቱዎች ደግሞ ከመድረኩ ይራቁ፡፡ ለሕዝብና ለአገር የሚያስቡ የሕዝብ ልጆች በሙያቸውና በልምዳቸው አገራቸውን ያገልግሉ፡፡ ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ለፕሬዚዳንትነት የተመረጠበት የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምርጫ ዓይነት ፋና ወጊነት በሌሎችም መስኮች በስፋት ይቀጥል!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...

የመከፋት ስሜት!

ከቤላ ወደ ጊዮርጊስ ልንጓዝ ነው፡፡ መውሊድና መስቀልን በተከታታይ ቀናት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግጭቶች በሙሉ ሁሉን አሳታፊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተገቶ የተስፋ ጭላንጭል መታየት ሲጀምር፣ በአማራ ክልል ሌላ ዙር ዕልቂትና ውድመት ሊያደርስ የሚችል ግጭት መነሳቱ ብዙዎችን ያሳስባቸዋል፡፡ በአማራ...

የባለሥልጣናትና የባለሀብቶች ግንኙነት ሥርዓት ይኑረው!

በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ የሚመሠርተው መንግሥት ከምንም ነገር በፊት ለሕግና ለሥርዓት መከበር ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ኃላፊነት በሚገባ ሊወጣ የሚችለው ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት...

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...