በተጠናቀቀው የ2008 በጀት ዓመት ከአቻ ባንኮች አፈጻጸምና ከቀዳሚው በጀት ዓመት አኳያ ሲነፃፀርም ከፍተኛ የተባለ ውጤት እንዳስመዘገቡ ከተጠቀሱ የግል ባንኮች መካከል አንዱ ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ ነው፡፡ ባንኩ የ2008 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን የሚያመላክት ሪፖርት፣ ቅዳሜ ጥቅምት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ይፋ ሲደረግ እንደተጠቀሰው፣ በበጀት ዓመቱ ያሳየው አፈጻጸም በባንክ ኢንዱስትሪው ዋና ዋና መለኪያዎች ሲመዘን ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት ሆኖ ተገኝቷል፡፡
የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ዓለምሰገድ እንዳገለጹት፣ ባንኩ ያገኘው ውጤት በአብዛኛው ከፍተኛ ለውጥ የታየበት ነው፡፡ ባንኩ በትርፍ፣ በብድር፣ በአጠቃላይ ገቢው መጠንና በሌሎች አገልግሎቶቹ ያገኘው ዕድገት ከሌሎችም ባንኮች አካያ ሲታይ ከፍተኛ ሊባል የሚችል ነው፡፡ በተለይ በጀት ዓመቱ ባንኩ ያገኘው የትርፍ መጠን ከቀደመው በጀት ዓመት በ152 በመቶ ማደጉ አንድ የልዩኘቱ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡
ይህ የትርፍ ዕድገት በበጀት ዓመቱ ሌሎች ባንኮች ካስመዘገቡት የትርፍ ዕድገት ጋር ሲነጻጸር በኢንዱስትሪው የተመዘገበ ከፍተኛው የትርፍ ዕድገት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛው የትርፍ መጠን ዕድገት ሆኖ የተመዘገበው በአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ሲሆን፣ ባንኩ አስመዝግቦት የነበረው የትርፍ ዕድገት 110 በመቶ ነበር፡፡
የብርሃን ባንክ የበጀት ዓመቱ የትርፍ ዕድገት ባንኩ ወደ ሥራ ከገባ ጀምሮ ያላስመዘገበው አዲስ ሪከርድ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የባንኩ የአምስት ተከታታይ ዓመታት አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ የየዓመቱ የትርፍ ዕድገት ከ40 በመቶ ያልበለጠ እንደነበር ነው፡፡ እንደ ባንኩ መረጃ በ2004 ዓ.ም. ከታክስ በፊት አስመዝግቦት የነበረው 46 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ በ2005 ዓ.ም. ደግሞ 70 ሚሊዮን ብር አትርፎ ነበር፡፡ ይሁንና በሁለቱ ዓመታት መካከል የነበረው ዕድገት ከ20 በመቶ ያነሰ መሆኑን መረጃው ያሳያል፡፡
በ2006 ዓ.ም. ከታክስ በፊት 122 ሚሊዮን አትርፏል፡፡ በ2007 ደግሞ 138 ሚሊዮን ብር ማትረፍ የቻለ ሲሆን፣ ዘንድሮ ግን ከታክስ በፊት 350 ሚሊዮን ብር ሊያተርፍ ችሏል፡፡ ከባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለውም በበጀት ዓመቱ የተገኘው የትርፍ መጠን ዕድገት ለባአክሲዮኖች የሚከፋፈለውን የትርፍ ድርሻ መጠንም አሳድጓል፡፡ በአንድ አክሲዮን የሚከፈለውን ድርሻ ወደ 39.9 በመቶ ከፍ በማድረግ ለመክፈል ያስቻለው ሲሆን፣ በቀደመው ዓመት ለአንድ አክሲዮን ተከፍሎ የነበረው 20.7 በመቶ በመሆኑ የዚህ ዓመት ትርፍ ድርሻ ከፍ ማለቱን ያሳያል፡፡
ከፍተኛ ውጤት እንደተገኘባቸው በዝርዝር ከተቀመጡት ዘርፎች ውስጥ የባንኩ አጠቃላይ የገቢ መጠን ዕድገት ተጠቃሽ ነው፡፡ ባንኩ በበጀት ዓመቱ ያገኘው አጠቃላይ ገቢ 786 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህ ገቢ በቀደመው ዓመት ከተገኘው የ373 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ413.5 ሚሊዮን ብር ጭማሪ ወይም የ111 በመቶ ዕድገት ሊያስመዘግብ መቻሉን ያመለክታል፡፡ ይህ የዕድገት መጠንም በኢንዱስትሪው ከፍተኛ ሆኖ እንደሚጠቀስ በባንኩ ተገልጿል፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪ ብርሃን ባንክ በ2008 በጀት ዓመት ለደንበኞች የሰጠው ብድር በ98 በመቶ፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑንም በ72.8 በመቶ አሳድጎ 5.3 ቢሊዮን ብር አድርሷል፡፡ የደንበኞቹን ቁጥር በ80.5 በመቶ በማሳደግ 195,412 ማድረስ መቻሉ በመግለጽም በጀት ዓመቱ ለባንኩ የቀና እንደነበር አሰይቷል፡፡ በሌሎች የባንኩ እንቅስቃሴዎች አኳያም ከባንኩ ምሥረታ ጀምሮ ያልተመዘገቡ የዕድገት ውጤት የታየባቸው ሆነው የተገኙ ናቸው፡፡ እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችለው ባንኩ በያመቱ የሚሰጠው የብድር መጠን ነው፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ማለትም በ2004 ዓ.ም. ባንኩ ለደንበኞቹ ሰጥቶ የነበረው ብድር ግማሽ ቢሊዮን ብር ገደማ ነበር፡፡ ይሁንና በ2007 ዓ.ም. የሰጠውን የብድር መጠን 1.9 ቢሊዮን ብር አድርሶ ነበር፡፡ በ2008 በጀት ዓመት ግን የባንኩ የብድር ክምችት 3.7 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡
ባንኩ የሰጠውን ብድር የተመለከተው ዝርዝር መረጃ እንደሚጠቁመውም የብድር ክምችቱ 3.76 ቢሊዮን መድረሱን የሚያሳይ ነው፡፡ ከቀደመው በጀት ዓመት በ1.86 ቢሊዮን ብር ወይም በ98.8 በመቶ አድጓል፡፡ በበጀት ዓመቱ ከተሰጠው ብድር በአገር ውስጥ ንግድና አገልግሎት መስክ የዋለው የ29 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡
በኢንዱስትሪው ዋና ዋና አፈጻጸም መለኪያዎች ሲታይ ያስመዘገብኩት ውጤት የተሳካ ነበረ ያለው ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በበጀት ዓመቱ በኢንዱስትሪው ከፍተኛውን ወጪ ያወጣ ባንክም ሆኗል፡፡ በ2008 ዓ.ም. የባንኩ የወጪ መጠን ዕድገት ከባንኩ ዕድሜ አኳይ ሲታይ ከፍተኛ የዕድገት መጠን አሳይቷል፡፡ በሪፖርቱ እንደተገለጸው በ2008 በጀት ዓመት የባንኩ ወጪ በ86.4 በመቶ ዕድገት አሳይቶ 486 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ የቀደመው ዓመት ወጪው 234.1 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህም የባንኩ ወጪ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በ202.3 ሚሊዮን ብር መጨመሩን ያሳያል፡፡ እንደ ባንኩ ፕሬዚዳንት ገለጻ፣ የወጣው ብዛት ከሥራ እንቅስቃሴዎች ዕድገት ጋር የተያያዘ ነው፡፡
የውጭ ምንዛሪ ግኝቱም ቢሆን በበጀት ዓመቱ 130.8 ሚሊዮን ዶላር በማሰባሰብ የ88 በመቶ ዕድገት ያሳየበት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠን በሦስት ቢሊዮን ብር በጨመር 7.2 ቢሊዮን ብር መድረሱና በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ የ72.5 በመቶ ዕድገት በማስመዝገቡ የባንኩ የበጀት ዓመት ስኬት የተለየ አድርጎታል፡፡
እንደ ብርሃን ባንክ ቦርድ ዳይሬክተሮች ሊቀመንበር ማብራሪያ፣ ባንኩ በበጀት ዓመቱ ያሳያው ከፍተኛ አፈጻጸም ሊመዘገብ የቻለው በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ በቦርዱ የፀደቀውን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ሥራ ላይ መዋል በመቻሉ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የተሻሻለው ድርጅታዊ መዋቅር በአግባቡ በመተግበሩ ውጤታማ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡
በቀረበላቸው ሪፖርት መርካታቸውን ባለአክሲዮኖቸ የገለጹ ሲሆን፣ ይህ ዕድገት አሁንም ቀጣይ እንዲሆን የሚያስችሉ መሠረቶች መጣላቸውን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አብርሃም አላሮ ጠቅሰዋል፡፡ ብርሃን ባንክ 9,600 በላይ ባለአክሲዮኖችን የያዘና በ110 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የተከፈለ ካፒታሉን ወደ 731 ሚሊዮን ብር አድርሷል፡፡ 105 ቅርንጫፎችንም በአገሪቱ ከፍቶ እየሠራ ይገኛል፡፡
ባንኩ በቀጣዩ ዓመት ለሚካሄደው የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ፣ ባለፈው ቅዳሜ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት የዳይሬክተሮች ቦርድ አስመራጭ ኮሚቴ አባላትን መርጦ ጉባዔውን አጠቃሏል፡፡