Thursday, February 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የምን መንከርፈፍ ነው?

እነሆ መንገድ። ከመርካቶ ወደ ፒያሳ ልንጓዝ ተሳፍረናል። የአዳም ዘሮች በአቤልና በቃየል ጎራ ተከፍለው በዚህች ቋት በሌላት ዓለም ውስጥ ዛሬም መንገዱን አጣበውታል። በዚህ በእኛው መንገድም ሰምተን የምንደግመውን፣ ዓይተን መልሰን እንደ አዲስ እግዚኦ የምንባባልበትን ወግ በወል እንገምዳለን። ወጉ የሚገመደው አቤላውያን ስለፍቅር አሳልፈው በሚሰጡት መብት፣ ቃየላውያን ያለርህራሔ በሚረግጡትና በሚያጠፉት ሕይወት ነው። የአንዱ መስዋዕት ሲሸተት፣ ሲወደስና ሲገን፣ የአንዱ እየተነወረና እየተነቀፈ ዛሬም እንደ ትናንቱ በተኬደበት አካሄድ የድርሻችንን አሻራ እናትማለን። የዚህኛው ተራ ሲያልፍ ደግሞ የመጪው ይደረባል። ቀሪያችን ንግርት ብቻ ናት። ተረት ናት። ወሬና ጨዋታ በቀር ያልተኬደበት መንገድ የለም። ለብቻችን የምናሰምረው የሌለን መስመር አልባ ነን። ድግግሞሹን አተኩሮ ላጠናው ከንቱነት ነፍስን መሰደጃ ያሳጣታል።

ዳሩ መርሳት ውሎ ይግባና እንዳልተቆረቆርን ተራችንን ልንቆረቁር፣ እንዳልተሰደድን ተራችንን ልናሰድድ፣ እንዳልተገፋን ልንገፋ ተስፋ በሚባል የማይላላ መቀነት ወገባችንን ታጥቀን ደግሞ እንጋፋለን። አሮጌውን እንደ አዲስ ቀደን ለመስፋት በፈቀድነው ልክ ልቦናችንን ባስወረስነው የተስፋ ዳዋ በአዲስ ጉልበት፣ በአዲስ ዕቅድ፣ በአዲስ ሥልት እንወጣለን እንወርዳለን። መውጣትና መውረድ እንደ ፀጋ ተቆጥሮ የሚወዱንን ስንገዘግዝ ከግዑዛን ጋር እናመሳስላቸዋለን። አመሳስለን ደግሞ ሳንጨርስ ሳይዘሩ፣ ሳያጭዱና ሳይከምሩ የሚመገቡት አዕዋፋት እንደ መልስ ምት ለማነፃፀሪያ ይቀርቡልናል። መስማማት እያቃተን ዓለም እንዲችው በጭሰኞችና በአስገባሪዎች ጎራ ተከፍላ ስታዋክብ ታኖረናለች። ይህ ተጋኖ በደማቁ ሲነገር ፍትሕ፣ ሰላም፣ ፍትሐዊ የሀሰብት ክፍፍል፣ ወዘተ ወዘተን በደማቅ የጥያቄ ምልክት እያጻፈ ከትውልድ እስከ ትውልድ ሲያወዛግብ ይኖራል፡፡ ይህም ደግሞ ከንቱ ንፋስን እንደመከተል ብለን እንዳንተወው ቢጨክኑበት መልሶ በእጥፍ የሚጨክነው ሆዳችን እየጮኸ፣ በእዬዬም ሲደላ ቅኝት እንሳፈራለን እንወርዳለን። መንገድ ውሎ ይግባና!

ጉዟችን ተጀምሯል። ጋቢና የተሰየሙ ወጣቶች የአንድ ጓደኛቸውን ንግርት እያነሱ ጉድ ይላሉ። ተሳፋሪው ጆሮውን ቀስሮ ያዳምጣል። “አንተ እናቱ እኮ የተቀበሩት ገና ሳምንት አልሞላቸውም። እሱን የት ባገኘው ጥሩ ነው? እዚህ . . . . እ . . . ማነው የሚባለው ባር አለ አይደል በቀደም እንዲያውም እኔና አንተ ጠጥተን ሳንከፍል የወጣንበት ቤት።  . . . እእእ .  . .እዛ ጂኑን ይዞ ዳንኪራውን ሲረግጥ ያመሻል። አይገርምም?” ይላል አንደኛው እጆቹን አፉ ላይ ጭኖ። ጉልበቷ ላይ የተቀደደ ጂንስ የለበሰች ወጣት በጆሮዬ፣ “አርባቸው ወጥቶ ቢሆን ኖሮ ሰማንያቸውን ሳያወጣ ብሎ ማማቱ አይቀርም ነበር፤” ስትለኝ ከጀርባ የተሰየመ ጎልማሳ ሰምቷት፣ “ሳይከፍሉ የወጡትን ሒሳብ ረሳሽው እንዴ?” ብሎ ይጠይቃታል። ወጣቶቹ ሐሜቱ አመቻችቷቸው “ከሰዓቱን ለምን የሆነ ቦታ ተመቻችተን አናሳልፈውም?” እያሉ ዕቅድ ማውጣት ጀምረዋል።

አንደኛው መልሶ፣ “ተወኝ እባክህ ይኼ ጥቅምት የሚባል ወር አልፎ አንዴ የዓመቱን ግብር ሳልከፍል ሰላም የለኝም። በዛ ላይ ምን እንደሆኑ አላውቅም ሒሳብ ሠራተኞቼ የሆነ ደረሰኝ አምታተው ሠርተውብኝ ሒሳቡ ልክ አልመጣ ብሎኛል፤” ይለዋል። ጓደኛው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ይኼማ ታዲያ ሳንፈርሽ ይሆናል እንዴ? ላፕቶፕህን ይዘህ ናና እያደቀቅን ታስተካክለዋለህ፤” የሚል ሐሳብ ያቀርባል። ይኼኔ ጎልማሳው አንድ ቀልድ መጫወት ጀመረ። “ከአንዱ ክልል ነው አሉ። ስም አልጠራም። በቃ በጀት በማባከን እያስቸገረ የፌደራል መንግሥት ጠራው አሉ። እና ሁነኛ ኢኮኖሚስት ይመደብለታል። ‘የገባበት ገብተህ፣ ጫት ቤት ነው ምን ቤት ነው ሳትል፣ በጀት አለቃቀቅና አያያዝ አሳየው’ ተባለ። ጭንቅ የማይችለው ያ በጀት አባካኝ ላፕቶፑን ይዞ ኢኮኖሚስቱን ጫት ቤት ይዞት ገብቶ ሲማር ቆየና ሲጨርስ ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው?” ብሎ ሁላችንን ከቃኘ በኋላ፣ “አቦ ይመችህ ብሎ ሃያ ሺሕ ብር ለቀቀበታ፤” ሲል ታክሲው በሳቅ ተናጋ። በጀት አያያዝና  ኑሮ ለአንዱ ለቅሶ፣ ለአንዱ ሐሜት፣ ለአንዱ ሰቆቃ ማለት ይኼ አይደል!

ጉዟችን ቀጥሏል። ተሳፋሪ ይወርዳል ተሳፋሪ ይጫናል፡፡ ወያላው በወረዱት ፋንታ ታክሲዋን ለመሙላት ይጣራል። ሲገኝም ትርፍ ይደርባል። “ይቅርታ እዚህ ጋ ጠጋ ትሉላት?” ፊት መቀመጫ ያሉትን ያስቸግራል። “ደርብብን ኧረ! ‘ላለው ይጨመርለታል’ አይደል የሚባለው?” አለው ጎልማሳው። የምትደረበዋ ልጅ ቀበል አድርጋ፣ “ታዲያስ! እንዲህ ታክሲ ወንበር ላይ ካልተለማመድነው ነገ ከነገ ወዲያ የመተካካት ፖለቲካ ይሰምርልናል?” ብላ ፈገግ አሰኘችን። “ጨዋታ ትችያለሽ እ? ለእንዳንቺ ዓይነቷስ እንኳን መጠጋት ብነሳም አይቆጨኝ። አሁን እስኪ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ እንዲህ ያለ ነገር ታወሪያለሽ?” አለ ጎልማሳው። “አመሰግናለሁ፤” ከማለቷ ጎልማሳው ወዲያው ቀጠል አድርጎ፣ “አሉ እንጂ ወይ ጨዋታ አያውቁ ወይ ጨዋታ አይወዱ! በሕዝብ ወንበር የባለንብረትነት ስሜት የሚሰማቸው። አይደለም እንዴ? አጋጥመውሽ አያውቁም?” አላት።

“ፍርድ እንደ ራስ ነው። የአንዳንዱ ሰው የታክሲ ውስጥ አቀማመጥ ከአኗኗሩና ከመጣበት አድካሚ መንገድ ጋር ሲገናኝ ታዝቤያለሁ፤” አለችው። “እሱስ ልክ ነሽ። እኛም የሰውን አቀማመጥ ከአመጣጡ ጋር አገናዝበን መቀበል አበዛን መሰለኝ፣ በሰላም ተሳፍሮ በሰላም እንዳይወርድ በሽብር ተሳፍሮ በነውጥ መውረድ የሚመኘውን እናበረታታለን፤” አለ ጎልማሳው። ግራ ገብቶን መላው የታክሲ ተሳፋሪዎች እርስ በርስ ተያየን። “በቀኝ አሳይቶ በግራ ሸጠው ማለትስ አሁን ነው፤” የምትለኝ እኔ አጠገብ ያለችው ናት። ከጀርባ የተሰየሙ አዛውንት ተሳፋሪዎች በበኩላቸው፣ “አላድለን ብሎ እንጂ እስኪ አሁን ስለወንበር ይኼን ያህል ዘመን መንገዋለል ነበረብን?” ይባባላሉ። ጉድ እኮ ነው!   

መንገዱ ከተጋመሰ ቆይቷል። ወያላችን ሒሳቡን ሰብስቦ መልስ በመመለስ ተጠምዷል። አንዳንዱ አፍንጫውን ይዞ መልስ ሲቀበለው ለአንዳንዱ የመልስ ሳንቲሙን ለመስጠት ወያላው ራሱ ይለምናል። “ኧረ ተቀበለኝ ወንድሜ!” ይላል ወያላው መጨረሻ ወንበር በጥግ በኩል በሁለቱም ጆሮዎቹ ‘ኢርፎን’ ሰክቶ ‘ስማርት’ ስልኩን እየጎረጎረ ዓለምን ወደረሳው ታዳጊ አስግጎ። በስንት ጉትጎታ አጠገቡ ባሉት ተሳፋሪዎች ጉሰማ ልጁ ጆሮውን የደፈነበትን ገመድ ነቅሎ መልሱን ተቀበለ። “ይኼ ትውልድ እኮ በዚህ ዓይነት እንኳን ለአዲስ አሠራርና ዓላማ ጥያቄ ሊጠይቅ ለአሮጌው ጥያቄ መልሱ ሲመጣም ግድ የለውም ማለት ነው፤” አሉ አንደኛው አዛውንት። እዚያው አካባቢ ጠየም አጠር ያለች የደስደስ ያላት ልጅ “ምን ይደረግ! በደጉ ዘመን ሰው ከፍቶ ሲያስከፋው ፈረሱንና በቅሎውን ኮርቻ ይጭናል። የአሁኑ በተራው እያየ ላለማየት፣ እየሰማ ላለመስማት ሲመኝ ‘በዳውንሎድ’ ጥበብ ስልኩን በመጫን ይጠመዳል፤” አለች።

አዛውንቱ እኛ የገባን የገባቸው አይመስሉም። ሒደት ቀለሟን ስትቀያይር በቋንቋም ታደንቋቁረን ይዛለች። ታዳጊው በተራው ነገሩን በዝምታ ሊያልፈው አልወድ ብሎ፣ “ታዲያ የሰው ልጅ በማሰብ ችሎታዬ በሥልጣኔ እዚህ አደረስኳት የሚላት ዓለም እያደር የጦርነት፣ የሽብር፣ የክፋት አውድማ ከሆነች ምን ማድረግ አለብን?” ብሎ ጠይቆ ሲያበቃ በአካባቢው ያሉትን ተሳፋሪዎች ገላመጣቸው። “እውነት ነው! ‘ቫይበር’ እና ‘ፌስቡክ’ ባይኖሩን ኖሮ ምን እንሆን ነበር? ዓለም እንደሆነች ይኼን ያህል ሺሕ ዘመን ፍትሕ የማታውቅ በፖለቲካ ቁማር የሕዝቦች ሰላማዊ ኑሮን ማመስ ያልሰለቻት ሆነች። ደግሞስ እንኳን ፍትሕን የዓለም ዋንጫን አራት ዓመት እየጠበቅን መሳተፍ ህልም የሆነብን ከዚህ በላይ ብንዘጋጋ ይገርማል?” አለች ጠይሟ ወጣት። እንደኖሩት ኖረው እንደሚሰነብቱት እየሰነበቱ ያሉት አዛውንት በበኩላቸው ዝምታን መርጠዋል። እንዲህ እንዲህ ያለው ሰዓት ላይ ዝምታው ብዙ ይላል!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። አዛውንቱ ገንዘብ ለመቀበል ከሄዱበት እየተመለሱ መሆናቸውን ያወራሉ። ጋቢና የተቀመጠ ደላላ አልሸጥ ስላለው ቤት እያነሳ፣ “ምነው ሰውን ነፈሰበት?” ሲል እንሰማዋለን። “እንዴት አይነፍስበት በየሄደበት የሚያስተነፍሰው በዝቶ፤” ትለኛለች ከጎኔ የተቀመጠችዋ ልጅ። “ያለው ማማሩ የሌለው መደበሩ ሆነና አመዳሞች በዛን። ይህ አልበቃ ብሎን በኢኮኖሚ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገብን መሆናችን ጠዋት ማታ ይበሰርልናል። ኧረ ጎበዝ በእድር ድክመት እንጂ ከሞትን የቆየን እኮ በዝተናል፤” ሲል መጨረሻ ወንበር ላይ የተቀመጠ ወጣት ታክሲያችን በሳቅ አሽካካች። ወዲያው ሾፌራችን ቦታ ይዞ ስትቆም ደግሞ ወያላው “መጨረሻ” ብሎ በሩን ከፈተው።

ተንጋግተን ከመውረዳችን ከየት መጣ የሚያስብል ድንገተኛ ዝናብ ስለያዘን ታክሲ ውስጥ የነበርን ሁሉ አብረን በአንድ ስፍራ የመጠለል ዕድል ገጠመን። ደግሞ ይኼን ጊዜ በግል አውቶሞቢል ዘና ቀብረር ብለው ወደሚሄዱበት የሚያዘግሙትን እየታዘበ (ያው ልጅ) “ያለው ምን አለበት?” ከማለቱ አጠገቡ የቆመው ያ ጎልማሳ፣ “ያለውማ ምን አለበት? የሌለው ነው እንጂ የሚያብላላበት። የሰው ከማየትና ከመመኘት የራሳችንን መኖሩ አይሻልም?” አለው። ዝናቡ ይለዋል። ወጣቱ፣ “መቼ ወደን ሆነ ወዳጄ። ቅድም ያቺ ልጅ  ያለችው እየረበሸን እንጂ፤” አለው። “ምንድን ነበር እሱ?” ቢለው ጎልማሳው፣ “በማጭበርበርና በሌብነት እንደ ጎማ የሚያስተነፍሰን በዛ!’ ስትል አልሰማሃትም እንዴ?” ብሎት ዝም አለ። አባርቶ እንስክንለያይ ከዚያ በኋላ ምንም ቃል አልወጣውም። ዘመኑ የአቤል ይሁን የቃየል መለየት ከበደን እኮ? እስኪ ለማንኛውም መጀመሪያ ያለንን በአግባቡ መያዝ ይልመድብን። አለበለዚያ፣ ‹‹ለምን አይሰረቅ ለምን አይዘረፍ፣ የማያውቅበትን ይዞ ሲንከረፈፍ፤›› ተብሎ ይዘፈንብናል፡፡ መልካም ጉዞ! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት