በደጀኔ አሰፋ ዳምጠው
እንደሚታወቀው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን በተከሰተው ከፍተኛ አለመረጋጋት ሳቢያ አገሪቱ ወደ ከፋ አደጋ ከመድረሷ በፊት ሰላም፣ ደኅንነትና መረጋጋትን ማስፈን ተገቢ ነው በሚል ዕሳቤ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ አዋጁ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በተለመዱት የሕግ አግባቦችና አተገባበሮች ብቻ አገርን ለማረጋጋት እንደማይቻል በመንግሥት ዘንድ መታሰቡ ነው፡፡ አዋጁም በፓርላማ ፀድቆ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ እነሆ አንድ ወር ገደማ ሆኖታል፡፡
ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብዙ ተብሏል፡፡ አስተያየቶችም ከተለያየ አቅጣጫ ፈስሰዋል፡፡ ብዙ ሊባል ተፈልጎም ብዙ ሳይባል ቀርቶ ይሆናል፡፡ እንደኔ ዕይታ ይህ አዋጅ አገሬን በሚገባ የሚያረጋጋ፣ ሰላምን የሚያስመልስና ደኅንነትን የሚያረጋግጥ ከሆነ ሰላምና ደኅንነት ለአንድ አገር እጅግ ወሳኝ ነገር በመሆኑ ሊደገፍ የሚችል ነው፡፡ ሆኖም ግን አገር ከተረጋጋና ሰላም ከተመለስ በኋላ አግባብነት ላላቸው የሕዝብ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ አጥጋቢ መልስ እንዲያገኙ በቂ መድረክ ሊፈጥር ይገባዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ከታየ አብዛኛውን አገር ወዳድ ሊያስማማ የሚችል ይሆናል፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለመተቸት ሳይሆን፣ መንግሥት አሳታፊ የሆኑ ተቋማዊ አሠራሮችን በሁሉም ረገድ ተግባራዊ እንዲያደርግ ለማሳሳብ ነው፡፡ ቢሆንም ግን እግረ መንገዱን ከአዋጁ ጋር የተያያዙ ጥቂት ነጥቦችን ለውይይት ያነሳል፡፡ ለምሳሌ በአገሪቱ የነበረው አለመረጋጋትና ቀውስ በአንድ ቀን እንዳልተፈጠረ ይታወቃል፡፡ ሁኔታዎችም አደገኛ አዝማሚያ ማሳየትና ለመቆጣጠር ፈታኝ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመላካች ነገሮች መታየት ከጀመሩ መሰነባበታቸውን እንኳን የአገርን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ተቀዳሚ ተግባሩ ለሆነው መንግሥት ይቅርና ለማንኛውም ሰው ግልጽ ነበሩ፡፡ ለወደፊት የሚሆን ትምህርትን ከመውሰድ አንፃር በዚህ ወቅት ቆም ተብሎ መጠየቅ ካለባቸው ብዙ ጥያቄዎች ሊኖሩ ቢችሉም ጽሑፉ ሦስቱን ለማንሳት ይሞክራል፡፡ እነኝህም፣
- በተወሰኑ አካባቢዎች የሕዝብ ጥያቄዎችና አለመረጋጋቶች በየፊናቸው መታየት በጀመሩበት ወቅት፣ ወቅታዊ መፍትሔዎችን አፈላልጎ ከመተግበር አንፃር የመንግሥት ሚና እንዴት ይታያል?
- ነገሮች ከተከሰቱ በኋላ በሒደት ሁኔታዎች ተባብሰውና ወዳልታሰበ አቅጣጫ ፈሰው አላስፈላጊ ጉዳቶችን ከማስከተላቸው በፊት ወይም የደረሰውን ኪሳራ ከመቀነስ አኳያ የመንግሥት ዝግጅትና ድርሻ ምን ሊሆን ይገባው ነበር?
- ሁኔታዎች እዚህ ደረጃ (የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ) ከመድረሳቸው በፊት ሕዝብን መሠረት ያደረጉና በተግባር የተፈተኑ አዋጭ ሥልቶችን በመጠቀም ረገድ መንግሥት ድርሻውን በሚገባ ተወጥቶ ነበር የሚያስብሉ ማሳያዎች አሉን? የሚሉት ናቸው፡፡
ምንም እንኳን ለእነዚህ ጥያቄዎች ሁሉም ከራሱ ዕይታ አንፃር እንደ መልስ የሚያቀርበው ነገር እንደሚኖር ባይጠረጠርም ጸሐፊው እንደ ዜጋ የራሱን አተያይ ለማካፈል ይሞክራል፡፡ የመጀመሪያ ነጥብ የሚሆነው ተቋማዊ አሠራሮችን ይመለከታል፡፡ በተለይም የሕዝብ ጥያቄዎችን በሚገባ መቀበልና ማስተናገድ ስለሚችል ወጥ እና ጠንካራ አሳታፊ ተቋማዊ አሠራር፡፡ ጽሑፉ ወደ ዋና ርዕሰ ጉዳዩ ከማለፉ በፊት እንደ መነሻ የሚቀጥለውን የመንደርደሪያ ሐሳብ ያቀርባል፡፡ እንደሚታወቀው የሚሊኒየሙ የልማት ግቦች የተነደፉት እ.ኤ.አ. በ2002 መጀመሪያ ላይ ሲሆን የተጠናቀቀው ደግሞ በ2015 ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች ከመቀበልና ከማስፈጸም ጋር በተያያዘ የወጣውን የሚሊኒየም ስምምነት ሰነድ ከፈረሙትና ከተቀበሉት 189 አገሮች አንዷ ስትሆን፣ ግቦቹን ለማስፈጸምም መጠነ ሰፊ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ፣ የዜጎችን ተሳትፎና ልማታዊነትን የሚያረጋግጡ አገራዊ ፖሊሲዎች እንዲነደፉ በማድረግ፣ የሰው ኃይልና ቁሳዊ ካፒታል በማቅረብና በመፈጸም ከስምንቱ የምዕተ ዓመቱ ግቦች ስድስት ያህሉን በማሳካት አመርቂ ውጤት ማስመዝገቧ ይታወቃል፡፡
በተከታይነት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተነደፈው ደግሞ ዘለቄታዊ የልማት ግቦች (Sustainable Development Goals) ይባላል፡፡ ይህም አሁን ካለንበት እ.ኤ.አ. ከ2016 እስከ 2030 በአጠቃላይ ለሚቀጥሉት 15 ዓመታት የሚተገበሩ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው 17 የሚሆኑ የልማት ግቦችን የያዘ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በሴፕቴምበር 2015 በኒውዮርክ በመገኘት ይህንን የስምምነት ሰነድ ከፈረሙትና ከተቀበሉት አገሮች አነዷ ደግሞ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ከእነዚህ ሉላዊ (ግሎባል) ግቦች ጋር በተጣጣመ መንገድ ደግሞ አገራችን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (1 እና 2) በማለት የሰየመቻቸውን የአምስት ዓመታት የልማት ዕቅዶችን በመንደፍ የመጀመሪያውን አጠናቃ ሁለተኛውን መተግበር ጀምራለች፡፡
ከአገራችን የልማት ዕቅድ ሰነዶች መረዳት የሚቻለው ደግሞ የተተለሙትን ግቦች ለማረጋገጥ ማለትም አገራችን በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች መልካም ስምና ገጽታ እንዲኖራት ተገቢውን ሥልት ነድፎ በፅናት መሥራትን እንደሚጠይቅና ይኸው እንደሚደረግ ነው፡፡ በተለይም የዜጎችን ተሳትፎና ልማታዊነትን ከሚያረጋግጡ ሥልቶች መካከል አንዱ በፊዚካላዊ ሀብቶች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በሰውና በማኅበረሰቡ ተቋማት ላይ አግባብ ያለው አሳታፊ የልማት ዕቅድ ዝግጅት አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም አሳታፊ የሆነ የልማት ዕቅድ ዝግጅት የሚጀምረው ኅብረተሰቡ ካለበት ከታች ነው፡፡ የአካባቢው አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ ነጋዴዎች፣ መሬት ያላቸውና የሌላቸው፣ ሥራ ያላቸውና የሌላቸው፣ ኑሮአቸውን በየትኛውም ዓይነት መንገድ የመሠረቱ፣ በየትኛውም ዕድሜ ክልል ያሉ፣ ሁሉንም ፆታዎች ያካተተ፣ ከየትኛውም ሃይማኖት ያሉ የማኀበረሰብ አባላት በሙሉ በዕቅድ ዝግጅት ከመጀመሪያው ጀምሮ መሳተፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ሥራውን የሚሠሩትና ውጤቱን ይዘው ተጠቃሚ የሚሆኑት እነሱ ስለሆኑ ነው፡፡ በተመሳሳይም ሒደቱ እነዚህ የማኀበረሰብ አካላት በክትትልና ግምገማ ላይ ያላቸውን ድርሻ በውል ያገናዘበና ያሳተፈ ሊሆን ይገባዋል፡፡
የአሳታፊ ዕቅድና በጀት ብጀታ ጽንሰ ሐሳባዊ ትርጉም
አሳታፊ ዕቅድና በጀት ብጀታ የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ከመተንተናችን በፊት፣ ዕቅድ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በጥቅሉ እንመልከት:: ማቀድ በአጭሩ ዛሬ ላይ ቆሞ ቀጥሎ መሆን ስለሚገባው ወይም የሚፈለገውን ነገር ሥልታዊ በሆነ መንገድ ማሰብ እንደማለት ነው፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ከማቀድ ጋር በተያያዘ እንዲህ የሚል አባባል አለ፡፡ “If you fail to plan, you plan to fail” ‹‹ማቀድ ካልቻልክ ለመውደቅ አቅደሃል›› እንደማለት ነው፡፡ ከዚህ አባባል መረዳት የሚቻለው ምንም እንኳን ያቀደ ሁሉ ሙሉ በሙሉ ይሳካለታል ማለት ባይቻልም አለማቀድ ግን የውድቀት ቅድመ ሁናቴ እንደሆነ ነው:: ስለዚህ ‹‹ዕቅድ›› ማለት የስኬት ወይም የውድቀት ቁልፍ ነገር መሆኑን እናስተውላለን::
በአጠቃላይ የማቀድ መሠረታዊ ጠቀሜታዎች ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉትን ያካትታል፡፡ ስለወደፊቱ አስቦ ለሚመጣው ነገር ለመዘጋጀትና ትክክለኛውን አቅጣጫ ለመያዝ፣ ወደፊት ምላሽ ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ጉዳዮች ለማወቅና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ለመተንተን፣ አንድ እንዲደረስበት የታለመ ጉዳይ ሊከናወን መቻል አለመቻሉን ለመገመት፣ ራዕይና ግብን ለመለየትና ትልቁን ውጤት ለማስመዝገብ፣ ለትግበራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለመለየት፣ ምን ያህል እንደሚያስፈልግና የት እንደሚገኙ ለማወቅ፣ እንዴት መሰብሰብ እንዳለብንና በአግባቡ ለመመደብና ለመጠቀም፣ ካሉት የትግበራ አማራጮች መካከል ለመምረጥና አንድን ነገር ለማድረግ ምክንያቱን ለማስቀመጥና የዕቅዱን ትግበራዎች በአግባቡ ለመምራትና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲከናወን ማስቻሉ የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በተያያዥም አሳታፊ ዕቅድና በጀት ብጀታ በአጭርና በቀላል አገላለጽ ከንድፈ ሐሳቡ ወይም ከጉዳዩ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቁርኝት ያለው ግለሰብ፣ በአካል ወይም በውክልና በጉዳዩ ምንነትና የበጀት ምደባ ሒደት ላይ ድምፁን የሚያሰማበትና ብሎም የውሳኔ ሰጭነት ሚናን የሚወጣበት ሥርዓት ነው፡፡ በመሆኑም ዕቅዱን ወይም ፕሮጀክቱን በበላይነት የሚያስተባብሩ አካላትና የሴክተር ባለሙያዎች ከላይኛው ክፍል እስከ ታች ያሉትንና የተገለሉ የማኅበረሰብ አካላትን፣ የልማት ሠራተኞችን፣ በጉዳዩ መሳተፍ የሚፈልጉ ዜጐችን፣ በንቃት ተሳታፊ የሆኑ አካላትንና ሌሎች ተያያዥ ተቋማትን ያሳትፋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ዕቅዱ በአንድ አልያም በሁለት ግለሰቦች በበላይነት የሚሽከረከር ሳይሆን ማንኛውንም የማኅበረሰብ አካል ያማከለ ሊሆን ይገባል፡፡
አሳታፊ ዕቅድ በሐሳብ ደረጃ ያለው ምሥል ይህ ሲሆን ተግባራዊ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ የሚሆንበት ሁኔታ አለ፡፡ ይኸውም ግለሰቦች አንድም ዕቅድ የማዘጋጀቱ ሒደት ከሚፈጥረው የሥራ ጫና ወይም ከሚወስደው ጊዜ አንፃር ፍላጐት ላያሳዩ ይችሉ ይሆናል፡፡ አልያም በዕቅዱ ወይም በዕቅዱ ትግበራ፣ ክትትልና ግምገማ ላይ ግለሰቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ባለመደረጉ ምክንያት የመገለል ስሜት ሊያዳብሩ ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የተሰወኑ ግለሰቦች የተሻለ ተሰሚነትና ድርሻ አላቸው በሚል ስሜት አንዳንድ ግለሰቦች ለዕቅድ ዝግጅቱም ሆነ ለትግበራው እንግዳ እንደሆኑ የሚቀሩበት ሁኔታ አለ፡፡ እንግዲህ በዚህና በመሰል ሁኔታዎች ነው አሳታፊ እንዲሆን የታስበው የዕቅድ ዝግጅት ከሁሉን አቀፍ ወደ ምንም አቀፍ የሚሸጋገረው፡፡
በዚህ ሁሉ መሀል ልብ ልንለው የሚገባን ቁልፍ ጉዳይ ቢኖር ‹‹አሳታፊ›› የሚለውን ሐሳብ ነው፡፡ አሳታፊ ስንል አንድን የሥራ ክንውን ከመሥራታችን በፊት የሌሎች ግለሰቦችን አስተያየት ማካተት ብቻ ሳይሆን፣ ግለሰቦቹ በሥራው ሒደት ላይ ዓይነተኛ ሚና እንዲኖራቸው የማድረግ ጽንስ ሐሳብ ነው፡፡ እውነተኛ የሆነው የአሳታፊ ሥነ ዘዴ የሚገለጸው የሁሉንም ተሳታፊ አካላት ስሜትና ሐሳብ ያገናዘበ እንደሆነ ነው፡፡ ይህ ማለት ሌሎች በሚያቀርቡት ሐሳብ ዙሪያ የሚደረግ ክርክርና በውይይቱ የሚካተቱና የሚቀሩ ሐሳቦች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ይህም ሆኖ የሁሉም አካል ሐሳብና አመለካከት ሊደመጥና መድረክ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምክንያቱም በጉዳዩ ዙሪያ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች አልያም በጣም የተማሩ ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች ብቻ እንደ ውኃ ልክ የሚያስቀምጡት መፍትሔ ባለመኖሩ ነው፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ታሳታፊ አካል ድርሻውን መወጣትና በሒደቱ ዙሪያ የውሳኔ ሰጭነት ሚናውን መጠቀም ይኖርበታል፡፡
የዜጎችን ተሳትፎ የሚያረጋግጡ አገራዊ የፖሊሲ ማዕቀፎች ዳሰሳ
ኢትዮጵያ ከሰው ሀብት ልማት ጋር በተያያዘ ብዙ የሚባሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰነዶችና የአፍሪካ ኅብረት ስምምነቶችን ፈርማ የተቀበለች አገር ናት፡፡ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያላቸውን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከመገንጠል ያረጋገጠ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕጎችን ማውጣትና ተፈጻሚ እንዲሆኑ ማድረግ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣኑ ነው፡፡ የትኛውም ዓይነት አገራዊ ፖሊሲም ይሁን ከበጀት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚያወጣውና የሚያፀድቀው የአገሪቱ ፓርላማ ነው፡፡ እነዚህና ሌሎች ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ባሉበትና የዜጎችን ተሳትፎ የሚያረጋግጡና የሁሉም ፍላጎቶች በእኩል የሚስተናገዱባት አንዲት ኢትዮጵያን ለመፍጠር መንግሥት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በተሳትፎ ላይ የተመሠረተ ልማታዊነት መንግሥት የነደፈው አገራዊ የልማት ሞዴል ሲሆን፣ የተፋጠነ የሀብት ፈጠራና ክምችት፣ እንዲሁም ኢንዱስትሪ መር የሆነ የልማት ፕሮግራም እንዲኖር ማረጋገጥ የሞዴሉ አንኳር ተልዕኮዎች ናቸው፡፡
የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሰነዶች በተቀረፁበት ጊዜ ምንም እንኳን የኤስፒአርፒ እና የፓስዴፕ ተሞክሮና ልምዶችን እንደ ግብዓት ቢጠቀምም፣ ሒደቱ አሳታፊነት ባለው ሁኔታ መሠራታቸውና ብዙ ወረዳዎችን ያካተቱ መሆናቸው የተሳካ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ግን ሙሉ በሙሉ አሳታፊ ነበር ወይም እንከን አልባ ነበር ለማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም በሒደቱ ውስጥ በተለይም ዕድል የተነፈጋቸውና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ አካላት ያልተካተቱ በመሆናቸውና የበጀት ብጀታው ሒደት አሳታፊነቱን በሚመለከት ገና ብዙ ያልተኬደበት መሆኑ ነው፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ ግን ድሆችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፖሊሲዎች በመነደፋቸውና ድህነትን ታሪክ በማድረግ ላይ ያተኮሩ ፈርጀ ብዙ ተግባራት ላይ ወጪ በመደረጉ፣ ድሆች መሠረታዊ አገልግሎቶችን መጠቀም የሚችሉበት ሰፊ ዕድል የፈጠረላቸው ሲሆን፣ በማኅበራዊ ልማት ዘርፍ ለመተግበር በተቀመጡ ውጤት ጠቋሚዎች ትልሞች ላይ ከፍተኛ መሻሻልን አሳይቷል፡፡ መንግሥት የማኅበራዊ ልማትን ለማሻሻል ቁርጠኝነቱን ያሳየ ሲሆን፣ በተለይም መሠረታዊ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ ከማድረግ አንፃር እንቅስቃሴዎችን የአገሪቱን ወረዳዎች መሠረት ባደረገ ሁኔታ ከነብዙ ችግሮቹ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህ የምንረዳው አሳታፊ ዕቅድን ለማከናወንና በአገሪቱ ተግባራዊ ለማድረግ መንግሥት የሄደበትን ርቀትና ይህንን ሒደት የሚደግፍ በአገር ደረጃ እየተተገበረ ያለ የሕግ ማዕቀፍ መኖሩን ነው፡፡ ይህም መንግሥት ምን ያህል በአሳታፊነት ላይ የተመሠረተ ዕቅድ ለማውጣትና የተሻለ ግብን ለመምታት መታቀዱን ያሳያል፡፡ ከዚህ የፖሊሲ ማዕቀፍ የምንረዳው አሳታፊ የልማት ዕቅድ በውስጡ ከሚያቅፋቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል የዜጎችን ፍላጐትና ግብዓቶችን የመለየት ቅድመ ክንውን፣ ምዘና፣ ክትትልና ተያያዥ ግምገማዎችን፣ መዋቅራዊ አደራጀጀቶችን፣ ዕቅድና የዕቅድ አፈጻጸሞችን ያካትታል፡፡
ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የአሳታፊ ተቋማዊ አሠራር ጠቀሜታና አንድምታ
አሳታፊ የሆነ ተቋማዊ አሠራር ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ከዚህ ጽሑፍ ዓላማና አገራችን ካጋጠማት ፈተና ጋር በተያያዘ ጽሑፉ ጥቂት ነጥቦችን ብቻ በዋናነት ይዳስሳል፡፡ ለምሳሌ መንግሥት አሳታፊነትን በመጠቀም ‹‹ጥያቄ አለኝ›› ከሚለው ሕዝብ ጋር በጥልቀት እንዲወያይ ያስችለዋል፡፡ በመወያያየትና በመደማመጥ ደግሞ በጋራ የታመኑባቸውንና ለአብዛኛው ጠቃሚ ይሆናሉ ተብለው የሚነሱ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለመተለም ያስችላሉ፡፡ እነዚህን የመፍትሔ አቅጣጫዎች ደግሞ ደረጃ በደረጃ በመተግበር ሁኔታዎችን ለማስተካከል የሚያስችል ምቹ ከባቢን እንዲፈጠር ያግዛል፡፡ ምቹ ከባቢ መፈጠሩ ደግሞ መንግሥት ከሚያስተዳደረው ሕዝብ ጋር የበለጠ እንዲጣበቅ ያስችለዋል፡፡ ሁሉም እንደ ባለድርሻ የራሱን የቤት ሥራ እንዲወስድ ያደርጋል፡፡ ይህም ሁሉም ዜጋ ለአገሪቱ ሰላምና ደኅንነት ዘብ እንዲቆምና የድርሻውን እንዲወጣ ያደርገዋል፡፡ በአንፃሩም ‹‹የአገሪቱን ሰላምና ብልፅግና አይፈልጉም›› ተብለው የተፈረጁ ኃይሎች በአገሪቱ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንዳይችሉ በር ይዘጋል፡፡ ይህ መሆን ከቻለ ደግሞ መንግሥት ሌሎች የልማትና አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር ዕድል ይፈጥርለታል፡፡
ሆኖም ይህ አሳታፊ ተቋማዊ አሠራር በአገራችን በሁሉም ዘንድ ተግባራዊ ነበሩ የሚያስብሉ ሁኔታዎች አልነበሩም፡፡ በእርግጥ ብቅ ጥልቅ የሚሉ፣ በግብር ይውጣ መልክ የሚታዩ፣ ወጥነት (uniformity) የሌላቸው፣ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑና በሆነ ጊዜ ብቻ የሚከወኑ አሳታፊ የልማት ዕቅድ ዝግጅቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ተጀምረው የነበሩትም ቢሆን በተወሰኑ አካላት የሚፈጸሙ በመሆናቸው አሳታፊነት የሚባለው ጉዳይ በአስፈጻሚ አካላት ፍላጎት (goodwill) ላይ የተንጠለጠለ እንዲሆን አስገድዶታል፡፡ ከዚህ አንፃር አሳታፊነት በሁለንተናዊ መልኩ እንደ ተቋማዊ አሠራር (Institutionalization) በማስረፅና በሁሉም ረገድ በመተግበር ዙሪያ ጉልህ ክፍተቶች ተስተውለዋል፡፡ ይህም ዜጎች በአገራቸው በሚከናወኑ የልማት እንቅስቃሴዎች ባይተዋር እንዲሆኑና የባለቤትነት ስሜት እንዳይሰማቸው ያደርጋቸዋል፡፡
በሌላ አነጋገር አሳታፊነት እንደ ተቋማዊ አሠራር ቢሰርፅና ቢተገበር ኖሮ፣ በየጊዜው የሚነሱ የትኞቹንም ዓይነት የሕዝብ ጥያቄዎች ከሥር ከሥር በመፍታት ነገሮች እንዳይወሳሰቡ፣ ጥያቄዎችም ቅርፅ አልባ (Amorphous) እንዳይሆኑና ብሎም ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይፈሱ ባደረጉ ነበር፡፡ የሕዝቡ ጥያቄ በሌላ ሦስተኛ ወገን እንዳይነጠቅና ማብሪያና ማጥፊያው ከቤት ውጪ ባልተሰቀለም ነበር፡፡ አሳታፊነት ቅድሚያ ቢሰጠው ኖሮ አገሪቱ ያለፈችበትን አጣብቂኝ ሁኔታ ቢያንስ መቀነስ ያስችሉ ነበር፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ! በአንፃሩ መንግሥት የሕዝቡን ተሳትፎ በዘላቂነት ሳያረጋግጥ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ወዲህና ወዲያ ሲል ይስተዋላል፡፡ በነገራችን ላይ ‹‹ተሳታፊነት›› ከ‹‹ተጠቃሚነት›› እንደሚቀድም ልብ ሊባል ይገባዋል፡፡ ለአብነት የቀላል ባቡር መስመር ዝርጋታን በተመለከተ ምንም ውይይት ከሕዝቡ ጋር ሳይካሄድ፣ የባቡሩ ቀለም ምን እንዲሆን ትፈልጋላችሁ የሚል ጥያቄ ለነዋሪዎች መቅረቡ እንደ ትዝብት የሚጠቀስ ሆኖ ይታወሳል፡፡ ብቻ እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩ ተግባራት በመንግሥት ዘንድ በውል ባለመተግበራቸውና በሌሎች ምክንያቶች ሳቢያ ይመስላል አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን) ትተዳደር ዘንድ የዳረጋት፣ ወይም ላላስፈላጊ ኪሳራዎች ተጋልጣ እንድታልፍ ያደረጋት፡፡ ለምሳሌ ልማቱ የእኔ ነው ብሎ ቢያስብ ኖሮ ሕዝቡ ራሱ የጠፉትን መሠረተ ልማቶችም ሆኑ ፋብሪካዎች… ወዘተ ከጥፋት ይጠብቃቸው ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፊት ተከስተው የነበሩ አደገኛ ሁኔታዎችና አለመረጋጋቶች የቀን ተቀን መስተጋብር ሆነው በታዩበት ወቅት፣ በተግባር የተስተዋለው የመንግሥት ድርሻ አናሳ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አግባብነት አላቸው ተብለው የታመነባቸውን የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት የተወሰዱ ዕርምጃዎች ኢምንትነት (ዝምታውን ጨምሮ)፣ እግር በእግር ተከታትሎ ካለመፍታት ጋር ተያይዞ የታዩ ችግሮች ነበሩ፡፡ ይህንንም ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች በቴሌቪዥን ቀርበው የተናገሩት ክፍተት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ድርሻ ከዚህ የተለየ ሊሆን ይገባው ነበር ማለት ነው፡፡ አሊያም ለተነሱት ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች አንድ መልክ ብቻ እንዳላቸው በማሰብ ተመሳሳይ የሆነ መልስ ለመስጠት ባልተሞከረም ነበር የሚል ዕይታ አለኝ፡፡ በነገራችን ላይ ከየትኛውም የመፍትሕ ዕርምጃ በፊት ጥያቄዎችን በሚገባ መመርመርና መረዳት የመጀመሪያ ቁልፍ ተግባር ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይህም አግባብነት ያላቸው፣ ውጤታማ የሆኑና በሕዝብ ተቀባይነት ያላቸውን የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለመተለም ይረዳናል፡፡
ካልሆነ ግን ‹‹ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል›› እንደሚሉት ዓይነት ዘለቄታዊነት የሌለው መፍትሔን እንድንወስድ ሊያደርገን ይችላል፡፡ ይህም ‹‹ጉልቻ ቢለዋወጥ…›› እንደሚባለው ዓይነት እውነትና ቅንነት በሌለው መንገድ የፖለቲካ ትርፍን ለማግኘት በሚመስል መልኩ የግለሰቦች የኃላፊነት ቦታ ብቻ በመቀያየር፣ ዘላቂ መፍትሔ ይመጣል የሚልም ሆነ እውነተኛ ለውጥ እንደመጣ ለማሳያነት በቂ ማስረጃ ይሆናል የሚል ግምት የለኝም፡፡ አሁን በጨረፍታ እንዳየነው አገሪቱ በአንድ ዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ የካቢኔ ሚኒስተሮች ሹመትን አከናውናለች፡፡ በእርግጥ ይኼኛው ሹመት የ‹‹አቶ›› ዎችን ቁጥር ከማሳነስ ረገድ አመርቂ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች (በአብዛኛው በዶክተሮችና በፕሮፌሰሮች ከመመራታቸው ጋር ተያይዞ) የሚነሳውን ትችት ከመመከት አንፃር ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥ አሁን የተነሱት ሚኒስትሮች በፖለቲካው ውስጥ የነበራቸውን የሕይወት ልምድም ሆነ ያላቸውን የፖለቲካ ‹‹ኮንስቲቱዌንሲ›› መሠረት ስንመለከት ብዙም እንዳልሆነ ልንገምት እንችላለን፡፡ በመሆኑም መነሳታቸው በፓርቲው ውስጥ ሊፈጥር የሚችለው ውጥረት እምብዛም እንዳልሆነ በማሰብም ሊሆን ይችላል እንደ ጦስ ዶሮ የፓርቲው ቤዛ የተደረጉት፡፡ በአንፃሩ አዳዲሶቹ ሹመኞች የመጡበት ብሔር ሞቅ ተደርጎ የቀረበ መሆኑን ሳስብና ካላቸው ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ልምድ ይልቅ ያቀረቧቸው ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ መተኮሩ ምናልባት ሌላ የፖለቲካ ጨዋታ ይኖረው ይሆን የሚል ሥጋትን ጭሮብኛል፡፡ በዚህ ክንውንም የሕዝቡ ጥያቄ እንደተመለሰ መገመት ለባሰ ስህተት የሚዳርግ ይመስለኛል፡፡ ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ…›› እንዲሉ!
ከዚህ ይልቅ ግን ሕዝቡን በጥሞና ማዳመጥና ለሕዝቡ ጥያቄ የሚመጥን መልስ ለመስጠት መዘጋጀትና ቁርጠኝነት ማሳየት እንጂ፣ እንዲህ ዓይነቱ በውል ያልተጤነ ክንውን አንድ ዓመት እንኳን ሊቀጥል እንደሚችል ምንም ዋስትና ያለው አይመስልም፡፡ ካስተዋልነው የሹመት ሥነ ሥርዓት ኩነቶች በመነሳት ማለቴ ነው፡፡ እንደኔ ዕይታ መንግሥት የሕዝብ አባት ነውና በልበ ሰፊነት እየታገሰ፣ ሕዝብ የሚባለውን የአገር ምንነት እያከበረ፣ አገር የሚባለውን ትልቅ ምሥል አርቆ እየተመለከተ (እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ሳይል)፣ የአገሪቱን ዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማክበርና በማስከበር የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ ተቀዳሚ ሥራው ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው የሕዝብን ጥያቄዎች (ጥያቄዎቹ በውጭ ኃይሎች የተቀመሩ አሊያም የተሳሳቱ ናቸው ቢባል እንኳን) እንደ ጥያቄ በማክበር ለጥያቄዎቹ ዕውቅና መስጠት፡፡ ከሕዝቡ ጋር በመነጋገገር እንደ ስህተት የሚነቀሱ ጉዳዮችን ማመን፡፡ ለጥያቄዎቹ ተገቢውን ምላሽ ደረጃ በደረጃ እየሰጠና ለማስተካከልም እውነተኛ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እንዳለው በማረጋገጥ በዋናነት ከሕዝቡ ጋር ያለውን ግንኙነት ጤናማና ጠንካራ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ይህን ስል የትኛውም ለውጥ በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ ሊሆን ይገባዋል የሚለውን ለማስመር ነው፡፡ በዚህም አገርን ከጥፋት ለመታደግ፣ ተዓማኒነት ያለውን የአሠራርም ሆነ የአመራር ሽግግር (ለውጥ) ዕውን ለማድረግ ይረዳል በሚል ነው፡፡ ካልሆነ ግን ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› የሚለው ብሂል እንደ ትንቢት በእኛ ላይ ሲፈጸም ይኖራል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ብሔራዊ የምክክር መድረኮች (National Dialogue Forums) ወይም የምክክር ጉባዔዎች በሚገባ ቢከናወኑ የተሻለ ነው እላለሁ፡፡ በእነዚህም ጉባዔዎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ያሉ ሁሉንም ወገኖች ማካተት፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችንም ተሳትፎ ማሳደግና ትርጉም ያለው እንዲሆን ማረጋገጥና በአገሪቱ መፃኢ ዕድል ላይ እንዲመክሩና ብሎም የውሳኔ ሰጭነት ሚና እንዲኖራቸው ማስቻል የማይተካ ሚና ይኖረዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ እስከ ዛሬ ድረስ ከፖለቲካ ምህዋሩ ተገልሎ የቆየውን የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማትን (CSOs) በማቅረብና እንደ አንድ ጠቃሚ ባለድርሻ በመውሰድ፣ በአገሪቱ ጉዳይ ላይ እንዲወስኑ እውነተኛ ተሳትፎአቸውን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ በነገራችን ላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት የሌሉበት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሁልጊዜም ዴሞክራሲያዊነቱ በጥያቄ ምልክት ውስጥ እንደወደቀ ነው፡፡
በተመሳሳይ በየፊናው ለተሰማሩ የአገሪቱ ምሁራን ቦታ በመስጠት ድምፃቸውና ምክረ ሐሳቦቻቸው እንዲሰማ ማስቻል የለውጥ ሒደት ፍሰቱን ይጨምራል፡፡ በመደብ የተደራጁ የሙያ ማኅበራትን (ለምሳሌ የመምህራን፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ የጠበቆች፣ የሕክምና ባለሞያዎች፣ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች፣ የደራሲያን፣ የአርቲስቶች፣ ወዘተ…) በሚገባ ማሳተፍ ጠቀሜታው የትየለሌ ነው፡፡ የምርምር ተቋማትንና በቁጥር ምንም ውስን ቢሆኑም ያሉትን ገለልተኛ የሆኑ የፖሊሲ ቲንክ ታንኮች ፖለቲካዊ ሚና እንዲጫወቱ ማስቻል የሒደቱን አመክንዮ ያረጋግጣል፡፡ ወጤቱም በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረውም ያግዛል፡፡ የእምነት ተቋማትም ነፃ በሆነ አሠራር ከእምነት ልጆቻቸው ጋር በመወያየት የሚያፈልቁትን ምክረ ሐሳብ በውል ማዳመጥና ማጤን ያስፈልጋል፡፡
ወጣቱ፣ ሴቱ፣ አዛውንቱ፣ የንግዱ ማኅበረሰቡ፣ አገር በቀል የማኅበረሰብ ተቋማት፣ ሕፃናትን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ የጎዳና ወጣቶችን፣ ፆታዊ ተዳዳሪዎችንና ሌሎች የተለያዩ የማኅበረሰብ አካላትን የሚወክሉ ማኅበራትን በሚመለከታቸው ጉዳዮች ማሳተፍና ብሎም በዚህ ጽሑፍ ያልተገለጹ ሌሎች አደረጃጀቶችና ወገኖች ተሳትፎአቸውን ማሳደግና ድምፃቸው በሚገባ መሰማቱን ማረጋገጥ የለውጥ/ሽግግር ሒደቱን ያሳልጣል፡፡ ዋጋውንም ከፍ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት አፅንዖት በመስጠት ምላሽ እንዲያገኙ መጣር ያለበት በሠልፍ (በቡድን) ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ብቻ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ለሚመጡ አቤቱታዎችም ሊሆን ይገባዋል፡፡ በየትኛውም ተቋም ለመገልገል የሚመጡ ግለሰቦችን እንደ ትልቅ ባለጉዳይና የአገሪቱ ባለድርሻ በመመልከት እንደሚገባ መቀበልና ማስተናገድ መንግሥት ለዜጎቹ ያለውን የክብር ቦታ የሚያመላክት በመሆኑ፣ ዜጎች በመንግሥት ላይ የሚኖራቸውን አመለካከት የተሻለ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ሕዝብ ማለት የግለሰቦች ድምር እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡
እዚህ ላይ ከምሠራው ሥራ ጋር በተያያዘ አንድ ነገር ለአብነት ማንሳት እወዳለሁ፡፡ አሁን ባለንበት የበጀት ዓመት መንግሥት ለአገሪቱ ወጣት ‹‹የተሻለ›› የሚባል በጀት (አሥር ቢሊዮን ብር ተንቀሳቃሽ ፈንድ) በመመደብ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የኢኮኖሚ ደረጃውን ለማሻሻል መታቀዱ ይታወቃል፡፡ ይህም በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ በእርግጥ ሚኒስትሩ ለአንድ ዓመት ገና ቢሮውን እየለመዱ ባሉበት ወቅት በዚህኛው ሹም ሽር ቢሻሩም፣ የዚህ አዲስ ተቋም መደራጀት ወጣት ላይ ተገቢውን ኢንቨስትመንት ለማድረግና አበክሮ ለመሥራት በመንግሥት ዘንድ የተያዘውን አቅጣጫና ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ተገልጿል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጅምሮች ደግም ሊመሠገኑና በጣም ሊበረታቱ ይገባቸዋል፡፡ ሆኖም ግን ይህንን በጀት በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ብቻ ማፍሰስ የወጣቱ ችግር አንድ ዓይነት መልክ እንዳለው ብቻ ታስቧል ወደሚል መላ ምት ይወስደናል፡፡ ይህ ደግሞ ስህተት ነው፡፡
በእርግጥ የአገራችን አብዛኛው ወጣት የኢኮኖሚ ችግር ሊኖርበት እንደሚችል ዕሙን ቢሆንም ችግሩ ግን ኢኮኖሚያዊ ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ ዘርፈ ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ እነዚህን አንገብጋቢ ተግዳሮቶችን በውል ለመተንተን ደግሞ ሁሉም ወጣት በያለበት አደረጃጀት ድምፁ ሊሰማለት ይገባል፡፡ ፍላጎቱ ምን እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ከዚያም የተሻለ የሚባልና የወጣቱን ትክክለኛ ፍላጎት መሠረት ያደረገ ዕቅድ ማውጣት ያስችላል፡፡ የተመደበውን በጀት በተመለከተ እንዴት መውረድ እንዳለበትም ሆነ አጠቃቀሙን በሚመለከት አዋጭ የሚባሉ የአተገባበርና የበጀቲንግ ሥልቶችን ለመንደፍ ያግዛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወጣቱ ያለበትን ችግር ብቻ ሳይሆን ያለውንም ዕምቅ ኃይል እንዲገነዘብና እንዴት መጠቀም እንዳለበት ለማበረታታት መንገድ ከፋች ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ወጣት ላይ የሚሠሩ የሲቪክ ማኅበራት ሚና ቀላል አይሆንም፡፡ ስለዚህም የሲቪክ ማኅበራትን ተሳትፎ ማበረታታትና ተቀራርቦ ለመሥራት የሚያስችሉ መድረኮችን መፍጠር ከመንግሥትም ሆነ ከማኅበራቱ ይጠበቃል፡፡
ምንም እንኳን ከላይ በተጠቃቀሱት ጉዳዮች ዙሪያ የጠለቀ ትንታኔ ማቅረብ ባልችልም፣ እንደ አንድ አገር ወዳድ ሰው ሳስበው ግን ባለፉት ጊዜያት መንግሥት በብዙ ጉዳዮች ዙሪያ በቂ ዝግጅት እንዳልነበረው ይሰማኛል፡፡ ስለዚህም የተነሱትን ጉዳዮች ዕውን ለማድረግ (ክፍተትን ለመሙላት) መንግሥት የቱንም ዓይነት መስዋዕትነት እንዲከፍል ሊያስገድደው ቢችልም፣ የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ ግን ከየትኛውም ጊዜ በላይ ፖለቲካዊ ዝግጁነትና የአመራሩ ቁርጠኝነት ይፈለጋል፡፡ ወጣም ወረደ ግን እነዚህና መሰል የተስተዋሉ ክፍተቶች እንደ ትምህርት ቢወሰዱና ተቋማዊ አሠራሮች በሚገባ ተግባራዊ ቢሆኑ፣ እንደ ሌሎች የሠለጠኑ አገሮችና መንግሥታት ችግሮቻችንን በመነጋገር ለመፍታትና አላስፈላጊ አገራዊ ጉዳቶችን ለመቀነስ ይረዱናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ቸር እንሰንብት!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡