Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምአስከፊው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫና መራጩ ሕዝብ

አስከፊው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫና መራጩ ሕዝብ

ቀን:

በዓለም ኃያሏ አገር አሜሪካ፣ አሜሪካውያን ፕሬዚዳንታቸውን ለመምረጥ የወጡ ሲሆን፣ ለኅትመት እስከገባንበት ጥቅምት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት ድረስ የነበረው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ባለመጠናቀቁ አሸናፊውን ማወቅ አልተቻለም ነበር፡፡ የምርጫ ሒደቱ ከመነሻው በተለያዩ ውንጀላዎችና ስም ማጥፋቶች የታጀበ ስለነበር አስከፊው የምርጫ ውድድር የሚል ስያሜ አግኝቷል፡፡

ለምርጫው ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕና ዴሞክራቷ ሒላሪ ክሊንተን በየፓርቲያቸው ለፕሬዚዳንትነት ከታጩ ከሐምሌ 2008 ዓ.ም. በኋላ፣ ፕሬዚዳንት የመሆን ሒደቱ የተለያዩ ክስተቶችን አስተናግዷል፡፡ አሜሪካ ፕሬዚዳንቷን መረጠች ማለት የአገሪቱን መሪ መረጠች ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም ትልቁንና ቀዳሚውን የአሜሪካ መከላከያ ኃይል የሚመራውንም መረጠች ማለት በመሆኑ በመራጮች ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ቀላል ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፡፡ የአሜሪካ ሕግ ከባድ ኃላፊነት የሚሰጠውን ፕሬዚዳንት መምረጥም ለአሜሪካውያኑ መራጮች፣ ለፕሬዝዳንቱ የተሰጠውን ኃላፊነት ያህል ወሳኝ ነው፡፡ ደኅንነታቸውንና ኃያልነታቸውን የሚያስጠብቅ መሪ ይፈልጋሉ፡፡

አሜሪካ ከሕዝቧ ብዛት አንፃር ዝቅተኛ መራጭ የሚመዘገብባት አገር ስትሆን፣ በአጀንዳዎች ላይ የመከራከር ባህላቸው ግን የዳበረ ነው፡፡ 45ኛው ፕሬዚዳንት ለመሆን እ.ኤ.አ. በ2016 ምርጫ ዕጩ የሆኑትን ሒላሪንና ትራምፕን ከአጀንዳዎች ይልቅ የእርስ በርስ ጥላቻቸው ወደ አፍ እላፊ መቀየሩ ነው ሲያወዛግባቸው የቆየው፡፡

በምርጫ ዘመቻ ወቅት ሕዝቡን ያነጋገሩ አጀንዳዎች

የሪፐብሊካኑ መሪ ዶናልድ ትራምፕ ፓርቲያቸው በሐምሌ ጠቅላላ ጉባዔውን አካሂዶ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት ዕጩ ካደረጋቸው በኋላ፣ ብዙ መነጋገሪያ የሆኑ ንግግሮችን አድርገዋል፡፡ ደፋርና የሚዲያውን ቀልብ መሳብ የሚችል ጉዳይ የሚያነሱት ትራምፕ፣ ዕጩ ሆነው እንደተመረጡ የቅስቀሳ ዘመቻቸውን የጀመሩት ‹‹በአሜሪካ የሚኖሩ የሜክሲኮ ስደተኞች ደፋሪዎችና ወንጀለኞች ናቸው፤›› በማለት ነበር፡፡ በምርጫ ዘመቻቸው በሙሉ በተቀናቃኛቸው ሒላሪ ክሊንተን፣ በሚዲያዎች፣ በሕግ አካላት፣ በወታደር ቤተሰቦች፣ በጥቁሮች፣ በሙስሊም እምነት ተከታዮች ላይ የጦርነት ቃላት ሲሰነዝሩ ቢከርሙም፣ በተለያዩ ተቋማት በተደረጉ የቅድመ ምርጫ ትንበያዎች ከሒላሪ ጋር የተቀራረበ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡

የትራምፕ አጀንዳዎች የብዙ አሜሪካውያን የውስጥ ፍላጎቶች ናቸው እስኪባል ድረስ በቅድመ ምርጫ ትንበያ በሒላሪ የተበለጡት በጎላ ልዩነት አልነበረም፡፡ ሒላሪ 46 በመቶ ሲሆኑ፣ ትራምፕ 45 በመቶ የሆኑበት ትንበያም ተደምጧል፡፡

መክፈል የነበረባቸውን የፌዴራል የገቢ ግብር ለ18 ዓመታት ያህል አለመክፈላቸው፣ እሳቸውም መክፈል አይገባኝም ብለው መከራከራቸው፣ ታክስ በመክፈል አቋማቸው የሚታወቁት አሜሪካውያንን ይህንንም ያህል ሲያስደነብራቸውም አልተሰማም፡፡ ተቀናቃኛቸው ሒላሪ በምርጫ ክርክር ወቅት ጉዳዩን ይዘው ብቅ ቢሉም፣ በነበረው የቅድመ ምርጫ ትንበያ ላይ የጎላ ልዩነት አላመጣም፡፡ ትራምፕ ከነአወዛጋቢ ንግግሮቻቸው ተከታዮቻቸውን ይዘው ዘልቀዋል፡፡ ምርጫው ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ‹‹ትራምፕ ጎንትሎናል›› ያሉ 11 ሴቶች ለሚዲያ ቃላቸውን የሰጡ ቢሆንም፣ ትራምፕ ግን ከቁብ አልቆጠሯቸውም፡፡ ይልቁንም አንዳንዶቹ ለእኔ ፍላጎት የሚመጥኑ አልነበሩም ሲሉም በሚዲያው ተሰምተዋል፡፡

ዴሞክራቷ ሒላሪም አሜሪካ ለመንግሥት ተቋማትና ባለሥልጣናት መጠቀሚያ ከዘረጋችው ሰርቨር ውጪ፣ የራሳቸውን ሰርቨር መጠቀማቸው መነጋገሪያ ከመሆን አልፎ ለምን ድብብቆሽና ሚስጥር ውስጥ ገቡ በሚል አስተችቷቸዋል፡፡ ለባለሥልጣናት የተቀመጠውን የኢሜይል አጠቃቀም ሕግ በመተላለፋቸውም እ.ኤ.አ. ከ2009 እስከ 2012 የነበራቸውን የኢሜይል ልውውጥ ለአሜሪካ ደኅንነት ቢሮ እንዲያስረክቡ ተጠይቀው፣ በኢሜይላቸው ከነበሩት ከ60 ሺሕ በላይ መልዕክቶች 33 ሺሕ ያህሉን አጥፍተውና የመንግሥት ጉዳይ ናቸው ባሏቸው ከ20 ሺሕ በላይ መልዕክቶች ላይ ምርመራ ተደርጓል፡፡ ሒላሪን የሕግ ተጠያቂ የሚያደርጋቸው የመልዕክት ልውውጥ ባይገኝም የጠፉት መልዕክቶች ግን የሚዲያው፣ የደጋፊዎችና የትራምፕም መነጋገሪያ ነበሩ፡፡ ሒላሪ ኢሜይሎቹ የግል ጉዳዮቼ ናቸው ቢሉም፣ በአሜሪካ ላይ ድብብቆሽ ሲጫወቱ ከርመዋል በሚል እንዲጠረጠሩ፣ ደጋፊዎቻቸውም እውነቱ ይውጣ እንዲሉ አድርጓል፡፡

በተለይ ለምርጫው ሳምንት ሲቀረው የደኅንነት ቢሮው ለቀጣይ ጥናት ፍንጭ ሊሰጠኝ የሚችል ኢሜይል አግኝቻለሁ ማለቱ፣ ሪፐብሊካኑንም ሆነ ዴሞክራቱን ገራ አወዛግቦ ነበር፡፡ ቢሮው የምርጫ ሕግን በመጣስ ከመንግሥት ተቋም የማይጠበቅ ተግባር በዕጩዋ ላይ ፈጽሟል የሚሉና ሒላሪ ትክክለኛ መሪያችን ናት ብለን እንድንመርጥ እውነቱ ይገለጥ ያሉ ሐሳቦች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተሰንዝረዋል፡፡ ምርጫው ሰዓታት ሲቀሩት ደግሞ የሒላሪ ኢሜይሎች ምንም ሊያስጠይቃቸው የሚችል ጉዳዮች እንዳልነበረባቸው ማረጋገጡን ቢሮው መልሶ አሳውቋል፡፡

ቢል ክሊንተን በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ከሴት ጋር ግንኙነት ፈጽመዋል ተብለው መወንጀላቸውን ትራምፕ በማስታወስ በሒላሪ ማንነት ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ ዊኪሊክስ ከሒላሪ ኢሜይል የተጠለፉ ኢሜይሎችን ጠቅሶ ከምርጫ ዘመቻ አስተባባሪ ቡድን ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ይፋ በማድረግም በተከታዮቻቸው ዘንድ ብዥታን ፈጥሮ አልፏል፡፡ ሆኖም እነዚህ ሒላሪን በቅድመ ምርጫ ትንበያዎች ከትራምፕ እንዲያንሱ አላደረጋቸውም፡፡ የጎላ ልዩነት ባይኖርም ትራምፕን እየመሩ ከርመዋል፡፡

የምርጫ ተሳታፊዎች

ትራምፕም ሆኑ ሒላሪ በምርጫ ዘመቻ ወቅት ጥያቄ ባስነሱባቸው ጉዳዮች ተወጥረው የከረሙ ቢሆንም፣ ሚዲያው የተረሳ ታሪክ ቢመዝም፣ ለመምረጥ ዕድሜ ከደረሱ አሜሪካውያን ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ናቸው ለምርጫ የወጡት፡፡ የአሜሪካ ታሪክ የሚያሳየውም ለመራጭነት ከደረሱት ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ናቸው ለምርጫ የሚወጡት፡፡ ማክሰኞ ሌሊት በተካሄደው ምርጫም ከ80 ሚሊዮን እስከ 100 ሚሊዮን የሚደርሱ አሜሪካውያን ፕሬዚዳንታቸውን ለመምረጥ እንደማይወጡ ቪኦኤክስ በድረ ገጹ አስፍሯል፡፡

ቢቢሲ ‹‹ቆንጆ ሕዝብ አስጠሊታ ምርጫ›› በሚለው የአሜሪካ ምርጫ፣ አሜሪካውያን ለምን ለምርጫ እንደማይወጡ የተለያዩ ጥናቶችን ጠቅሶ ቪኦኤክስ አስፍሯል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 ለነበረው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመምረጥ ዕድሜ ውስጥ ከነበሩ 241 ሚሊዮን አሜሪካውያን 129.1 ሚሊዮኑ ብቻ መርጠዋል፡፡ በ2016 ደግሞ መራጩ በ2012 ከነበረው በጥቂቱ ይቀንሳል ተብሏል፡፡

ባለፉት 40 ዓመታት በነበሩ የአሜሪካ የምርጫ ታሪኮችም የመራጮች ቁጥር ዝቅተኛ እንደሆነ ዘልቋል፡፡ የፖለቲካ ሳይንቲስቶቹ የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲው ዶናልድ ግሪንና የቴምፕል ዩኒቨርሲቲው ዴቪድ ኒከርሳን በአሜሪካ የመራጮች ቁጥር ከዓለም አቀፉ ሁኔታ ሲነፃፀር አናሳ የሆነባቸውን ምክንያቶች ያስቀምጣሉ፡፡

በአሜሪካ የመራጮች ምዝገባ እንደየግዛቱ የሚለያይ መሆኑ አንዱ ችግር ነው፡፡ ቀድሞውንም በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ለመምረጥ ፍላጎት በማያሳዩበት አገር፣ የተለያየና ሕዝቡን በአንዴ የማይደርስ የመራጭ ምዝገባ ሥርዓት መኖሩ፣ ሕዝቡ የመመዝገቢያ ጊዜውን እንዲረሳ አድርጎታል፡፡

ከመኖሪያ ሕጎች ጋር ተያይዞም ብዙዎቹ ለመራጭነት ብቁ እንሆናለን ብለው አያስቡም፡፡ በሌላ በኩል ስዊድን ወይም ጀርመን ዕድሜው ለምርጫ የደረሰን በሙሉ ከመረጃ ቋት በቀጥታ የሚመዘግቡበት አሠራር ሲኖራቸው፣ በአሜሪካ ይህ የለም፡፡ መራጩ በአካል እንዲገኝ፣ ከምርጫው በፊት ወይም በምርጫ ቀን እንዲመዘገብ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥርዓቶች በተለያዩ ግዛቶች አሉ፡፡ አሜሪካውያን ደግሞ ይህንን ተከታትለው አይፈጽሙትም፡፡ አብዛኞቹም ይረሱታል፡፡ ምርጫው ሳምንት እስኪቀረው ድረስ ስለምርጫው የማያውቁ መኖራቸውንም የፖለቲካ ተንታኙ ሚስተር ኒከርሳን ይናገራሉ፡፡

ብዙ አሜሪካውያን ምርጫ በአገራቸው ለውጥ ያመጣል ብለው አለማመናቸውም ሌላው ምክንያት ነው፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከሪፐብሊካን ወይም ከዴሞክራቲክ ፓርቲ  የሚመረጥ መሆኑም እንደ ችግር ይጠቀሳል፡፡ የአሸናፊው ፕሬዚዳንት ፓርቲ ሁሉንም ጠቅልሎ መውሰዱም የተቃራኒውን ፓርቲ ደጋፊዎች የማያስደስት በመሆኑ፣ ብዙዎች ለምርጫ እንዳይወጡ አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል ፕሬዚዳንቱ ለአራት ዓመት ያህል የሚመራ ቢሆንም፣ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ነዋሪው ለፌዴራል ለግዛቶች፣ እንዲሁም ለአጥቢያ ምርጫዎች እንዲሳተፍ መጠየቁ መራጩን ያሰለቸዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2016 ምርጫ የተስተዋለውም የመራጮች ቁጥር መቀነስ ከእነዚሁ ምክንያቶች ጋር በተያያዘ መሆኑን የፖለቲካ ሳይንቲስቶቹ ይስማማሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ አሁን ውጤቱ በይፋ በታወቀበት ምርጫ የሁለቱ ዕጩዎች አስከፊ ንትርክና አጀንዳ አልባ ፉክክር ብዙዎችን ማሰላቸቱም ተሰምቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...