Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

​የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አዲሱ መኖሪያ

ትኩስ ፅሁፎች

ለተመራጩ ፕሬዚዳንት ሥልጣናቸውን እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 1 ቀን 2017 የሚያስረክቡት ባራክ ኦባማ ከዋይት ሐውስ ሲወጡ ይገቡበታል የተባለው ቪላ ይህ ነው፡፡ ቪላው የሚገኘው በዋሽንግተን ዲሲ ካሎራማ በሚባለው አካባቢ ሲሆን፣ ከ2,700 ካሬ ሜትር በላይ በሚሆን ይዞታ ላይ ያረፈ ነው፡፡ ባራክ ኦባማና ባለቤታቸው ሚሼል ኦባማ ከዋይት ሐውስ በኋላ ዋሽንግተን ዲሲ ለመቆየት ያሰቡት ትንሿ ልጃቸው ሳሻ እዚያው ትምህርቷን እንድታጠናቅቅ ለማድረግ መሆኑን የዘገበው ማንሺን ግሎባል ነው፡፡ የኦባማ ቤተሰቦች ቪላውን በኪራይ የሚገቡበት ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ዋጋው 6.3 ሚሊዮን ዶላር መሆኑ ታውቋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1928 መገንባቱ የተነገረለት ይህ ግዙፍ ቪላ እ.ኤ.አ. በ2014 ለአሁኖቹ ባለቤቶቹ የተሸጠው በ5.3 ሚሊዮን ዶላር ነበር ተብሏል፡፡

***

ድርቅ (ቦና)

በልጅነት ዕድሜ በጮርቃነታችን

ለፍጥረት በማሰብ አልፈን ከራሳችን

እንጋብዝ ነበር እንል ነበር ድሮ

‹‹አንበጣ

ና ሾርባ ጠጣ

በሚጥሚጣ፡፡››

ዛሬ አደግንና ሁሉም ተቀይሮ

እንኳንስ ለአንበጣ እንኳንስ ሚጥሚጣ

ለእኛም ለራሳችን ምግቡ ከየት ይምጣ?!

  • ፋሲል ተካልኝ ‹‹ጡዘት›› (2008)

* * *

‹‹ማዕበሉ ያልፋል መፀውም ይመጣል››

‹‹በአንድ የክረምት ወቅት አስታውሳለሁ አባቴ የማገዶ እንጨት ሲፈልግ አንድ የሞተ ዛፍ ያገኝና ይቆርጠዋል፡፡ [መፀው] ሲመጣ በተቆረጠው ዛፍ ግንድ ዙሪያ ማቆጥቆጥ አየ፡፡ እንዲህም አለኝ፡- ‹‹ዛፉ እንደሞተ ቆጥሬ ነበር፤ በክረምቱ ቅጠሎቹ ረግፈው ነበር፤ ቅርንጫፎቹ ሁሉ ከቅዝቃዜው የተነሳ ጭራሮ ሆነው ደርቀው በዛፉ ላይ ሕይወት የሚባል ነገር አይታይም ነበር፡፡ አሁን ግን በዋናው ሥር ላይ እስካሁን ድረስ ሕይወት አያለሁ፤›› አለ፡፡

ከዚያ ቀና ብሎ አየኝና እንዲህ አለኝ፡- ‹‹ቦብ፣ ይህን አስፈላጊ ትምህርት እንዳትረሳ፣ በክረምት ወቅት ዛፍን አትቁረጥ፤ ነገሮች በከፉም ሰዓት አሉታዊ ውሳኔ አትውሰድ፤ ልብህ በወደቀበት ሰዓት በመልካም መንፈስ ውስጥ በሌለህበት ጊዜ አስፈላጊ ውሳኔዎችን አትወስን፡፡ ጠብቅ፤ ታገስ፡፡ ማዕበሉ ያልፋል፡፡ መፀውም ይመጣልና፤›› አለኝ፡፡

  • ኃይል ከበደ ‹‹ጉርሻ እና ፌሽታ›› (2006)

* * *

ኧረ የልጁ ነገር ከምን ደረሰ?

አንዲት እናት ልጅዋ በእኩለ ሌሊት ነቅቶ እያለቀሰ ስላስቸገራት ‹‹ዝም በል አንተ ለቅሶህንም አላቆም ካልህ አውጥቼ ለጅብ ነው የምሰጥህ፡፡ ና ብላው አያ ጅቦ›› ስትል ልጁ ፈርቶ ዝም አለ፡፡ ነገር ግን ለካስ አንድ ጅብ በጓሮ በኩል ደፍጦ ሲያዳምጥ ካሁን አሁን አውጥተው ይጥሉታል ብሎ በመጠበቅ ላይ ነበርና በር ተንኳኳ፡፡ ‹‹ማነህ?›› ሲባል፣ ‹‹ኧረ የልጁ ጉዳይ ከምን ደረሰ?›› አለ ይባላል፡፡

  • መክብብ አጥናው ‹‹ሁለገብ የአእምሮ ማዝናኛ›› (2005)

***

‹‹ድንቼ የሚሉሽ ሊልጡሽ እንጂ ነው››

አንዲት አጠር፣ ደልደል ያለች ደባካ መሳይ የአለቃ ገብረሐና ጎረቤት፣ ‹‹አባ ሰው ሁሉ ድንቼ፤ የኔ ድንች እያለ ያቆላምጠኛል›› ብትላቸው፣ ‹‹አዬ ሞኝት፣ እውነት መስሎሽ ነው? ድንቼ፣ ድንቼ የሚሉሽ ሊልጡሽ እንጂ ነው አሉዋት፡፡›› ድንቡሼዋ ጐረቤታቸው አዲስ ልብስዋን ልታስመርቅ እየሮጠች ወደቤታቸው ስትመጣ አመለጣትና መአዛው ቤቱን አወደው፡፡ አለቃ ገብረሐና ግን እንዳላወቀ ሰው ‹‹በውኃ ይለቅልሽ፤ ጥሎሽ ይሂድ›› ብለው ከመረቋት በኋላ ‹‹እንግዲህ ይህችን ከሰው ዘንድ ስትደርሽ ብን እያደረግሽ ኩሪ፤›› ብለው አሰናበቷት፡፡

ድንቡሼም ለአቅመ ሔዋን እንደደረሰች አንድ አህያ ነጂ አገባች፡፡ ታዲያ ገብረሐና ይንቁት ኖሮ አንድ ቀን ሰውየው አህዮች እየነዳ ባጠገባቸው ሲያልፍ፤ ‹‹ጤና ይስጥልኝ አባ›› ብሎ የእግዜር ሰላምታ ቢያቀርብላቸው፤ ‹‹እግዚአብሔር ይመስገን፤ እንደምን ዋላችሁ?›› በማለት መለሱለት፡፡ አህያ ነጂውም በዚህ ተበሳጭቶ ስለነበር ቤታቸው እስኪገቡ ጠብቆ ገላጋይ በሌለበት ቀጠቀጣቸው፡፡ ዱላው ክፉኛ ጐድቷቸው ስለነበርም ታመው ተኙ፡፡ አመሻሹ ላይ እያነከሱ ከውጭ ሲመለሱ አህያ ነጂው ድንቡሼን አስከትሎ እንዳላወቀ ሰው ሊጠይቃቸው መጣ፡፡ ‹‹አለቃ ምን ሆኑ?›› ሲልም ጠየቃቸው፡፡ ‹‹አህያ ረግጦኝ ነው ልጄ፤›› አሉት ፈጠን ብለው፡፡

  • አረፈዓይኔ ሐጎስ ‹‹አለቃ ገብረሐና እና አስቂኝ ቀልዶቻቸው›› (1979)

* * *

ፀሐይ በነበረችበት እንድትቀጥል አምላክን የመከረው ማን ነው?

ከሥነ ፍጥረት ጀምሮ ፈጣሪ ለሰዎች ቅርብ ነበር፡፡ ሁልጊዜም ያነጋግራቸው ነበር፡፡ በጣም ብዙ ዓይነት ሰዎች ብዙ የተለያዩ ሐሳብ ያላቸውና የተለያዩ ምኞት ያላቸው ሰዎች ሁልጊዜ ያጉረመረሙ ነበር፡፡

ብዙውን ጊዜ ፀሐይ ስትወጣ አንዱ ሰው “አምላክ ሆይ እባክህ የጠዋቱ እንቅልፍ በጣም ጣፋጭ ስለሆነ ፀሐይዋ አሁን ሳይሆን ትንሽ ቆይታ ትውጣ፤” ይላል፡፡ አምላክም “እውነትህን ነው፡፡ እንግዲያው ትንሽ አቆያታለሁ፤” ይላል፡፡ በሌላ በኩል ፀሐይዋን በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት የፈለጋት ሰው ደግሞ “እባክህ ለምንድነው ፀሐይዋን ያዘገየሀት? ፀሐይዋ ለምንድነው የማትወጣው?” ይላል፡፡

ከዚያም ፈጣሪ ፀሐይዋን ያወጣታል፡፡

በቀን ደግሞ በሞቃት ፀሐይ ውስጥ የሚሄድ ሰው “አምላኬ ሆይ እባክህ በሙቀቱ ምክንያት በጣም ስለደከመኝና ፀሐይዋም በጣም ስለምታቃጥል ትጥለቅ፤” ይላል፡፡

አምላክም ወዲያው ፀሐይዋ እንድትጠልቅ ያደርጋል፡፡

ሌላኛው ሰው ደግሞ ወደ ሩቅ ቦታ እየተጓዘ ሳለ ከሥፍራው ከመድረሱ በፊት እሱም “አምላኬ ሆይ ፀሐይዋ ለምን እንድትጠልቅ አደረክ? ከምሄድበት ሥፍራ እስክደርስ ድረስ ትንሽ ከፍ አድርጋት፤” እያለ ያላዝናል፡፡ ፀሐይዋም ያ ሰው ካሰበው ሥፍራ እስኪደርስ ትንሽ ከፍ ብላ ትቆያለች፡፡

በዚህ ሁኔታ ማንገራገሩ በጣም ስለበዛ አምላክ በጣም ተቸገረ፡፡ አንዱ አንድ ነገር ሲል አምላክ ይሰማዋል፤ ሌላው ሌላ ነገር ሲል አምላክ ይሰማዋል፡፡ ስለዚህ ከብዙ ሰዎች በሚመጣ የተለያየ ጥያቄ ፈጣሪ ግራ ገባው፡፡

በዚህ ጊዜ ብልጡ ቀበሮ “ፈጣሪ ሆይ ለሰዎች ቅርብ እስከሆንክ ድረስ ሁልጊዜም ስለምታዳምጣቸው ሁሌም ትረበሻለህ፡፡ ከሰዎች ራቅ፡፡ አትስማቸውም፡፡ ሁልጊዜም በተዘዋዋሪ መንገድ ስጣቸው፡፡ አንተ የሰው ፍጡር አይደለህም፡፡ አንተ በሥፍራህ አምላክ ነህና የእነዚህን ሰዎች ልዩ ልዩ ችግሮች አትስማ፡፡ ከእኛ ርቀህ ሂድና በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ብቻ ባርከን፡፡ ፍጥረታትህ የአንተ ፍጥረታት ስለሆኑ አንተ መረበሽ የለብህም፤” አለው፡፡

ከዚህም በኋላ ፀሐይ በነበረችበት ቀጠለች፤ እየወጣችና እየገባች፡፡

  • በራምሴ ሽዎል የተተረከ የኑዌር ተረት

*** 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች