Monday, February 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአዲሱ የሙዚቃ መገበያያና የሙዚቀኞቹ ተስፋ

አዲሱ የሙዚቃ መገበያያና የሙዚቀኞቹ ተስፋ

ቀን:

በሞባይል ስልክ ላይ ያለ ገንዘብ (ኤርታይም) በመጠቀም ሙዚቃ መግዛት የሚቻልበት አዲስ የሙዚቃ መገበያያ ሥርዓት ተዘረጋ፡፡ ሥርዓቱ በሞባይል አፕሊኬሽን፣ በዌብአፕሊኬሽንና ዩኤስኤስዲ ሚዲያዎች የሚሠራ ሲሆን፣ ተጠቃሚዎች ለአልበም 15 ብርና ለነጠላ ዜማ ደግሞ 4.50 ብር በመክፈል ማግኘት ይችላሉ፡፡ ሥርዓቱ አንድሮይድ ስልክ ካላቸው ተጠቃሚዎች በተጨማሪ ማንኛውም ዓይነት ሚዲያ ፕለየር ባላቸው ግለሰቦችም ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ አዲስ የተዘረጋው የሙዚቃ መገበያያ ከ1950ዎቹ ወዲህ ያሉ የሙዚቃ ሥራዎችን በድምፃውያን፣ በሙዚቃ አቀናባሪዎች፣ በግጥምና ዜማ ደራሲዎች፣ በአልበም መጠሪያ፣ አልበሙ በወጣበት ዘመን ወይም በፕሮዲውሰሮች ስም ፈልጎ ማግኝት ይቻላል፡፡

ይህንን የሙዚቃ መገበያያ በጥምረት ለሕዝብ ይፋ ያደረጉት አውታር መልቲሚዲያና ኢትዮ ቴሌኮም ሲሆኑ፣ ጥቅምት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ስለ ሥርዓቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አውታር መልቲሚዲያ በዋነኛነት የተቋቋመው በሙዚቀኞች ጥምረት ሲሆን፣ የአይቲ ባለሙያዎችና የቴሌ ሠራተኞችም አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በዕለቱ እንደተመለከተውም፣ አዲሱ የሙዚቃ መገበያያ ሙዚቀኞች የሚገባቸውን ጥቅም የሚያገኙበት ሥርዓት ነው፡፡

ለበርካታ ዓመታት በሙዚቃው ያሉ ባለሙያዎች በሥራቸው ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ይገልጻሉ፡፡ ባለሙያዎችን ባለመብት የሚያደርግ የሕግ ማዕቀፍ ቢኖርም  ሙዚቀኞች መመዝበር አልቀረላቸውም፡፡ በተለይም ዘመኑ ያመጣቸው እንደ ፍላሽና ሚሞሪ ያሉ የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች፣ ሙዚቃ በሕገወጥ መንገድ እንዲሰራጭና ባለሙያዎች እንዲበዘበዙ መንገድ ከፍተዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ዙሪያም ባለሙያዎች ለዓመታት እሮሯቸውን አሰምተዋል፡፡ የፍትሕ ያለህ ሲሉም የመንግሥት ተቋማትና የሙያ ማኅበራትን በርም አንኳኩተዋል፡፡ አዲሱ የግብይት ሥርዓት በአንድ ሙዚቃ ዝግጅት ወቅት ያሉ ባለሙያዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ለችግሩ መፍትሔ እንደሚሰጥ የሙዚቃው ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡

በአውታር መልቲሚዲያ ረገድ ስለ ሥርዓቱ ከተናገሩ ሙዚቀኞች መካከል ኤልያስ መልካ፣ ኃይለሚካኤል ጌትነት (ኃይሌ ሩትስ) እና ዮሐንስ በቀለ (ጆኒ ራጋ) ይገኙበታል፡፡ ኤልያስ እንደገለጸው፣ በሙዚቃው ዘርፍ የባለሙያውን መብት በማስጠበቅ ረገድ ሕጉ አልተተገበረም፡፡ ሙዚቀኞች ስለ ሕጉ ባለማወቅ እንዲሁም በሌሎች  ምክንያቶችም አልተጠቀሙበትም፡፡ ‹‹ብዙ ሙዚቃ አድማጭ ያለበት አገር እንደመሆኑ ሙዚቃ አዋጭ ቢዝነስ ቢሆንም ድምፃውያን፣ ሙዚቃ አቀናባሪዎችና ግጥምና ዜማ ደራሲዎች ሲቸገሩ ይታያል፤›› ሲል ሁኔታውን ገልጾታል፡፡ ነገሮችን ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› ያደረገው ደግሞ የሙዚቀኛውን መብት ለማስጠበቅ በሚል በሕጋዊ መንገድ ተቋቁመው በሕገወጥ ሥራ የተዘፈቁ መኖራቸው እንደሆነም ያክላል፡፡

ሙዚቀኞች በሕጉ መሠረት ሙዚቃቸው ከተለቀቀ በኋላ ተጠቃሚ መሆን በሚገባቸው ወቅት ሲጠቀሙ አይስተዋልም፡፡ እንዲያውም ከዘመናት በፊት በተካሄደ መጠነኛ ክፍያ ሥራዎቻቸው ያላግባብ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ‹‹ሙዚቀኛው በእያንዳንዱ ሥራ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም አላገኘም፡፡ የሙዚቀኛው ሥራ ሲሰራጭ የአሠራጩ መብት እንደሆነ ሁሉ ባለሙያው የሚያገኘው ክፍያ የለም፡፡ ሙዚቀኞች በድህነትና በዕርዳታ ሲኖሩ ሙዚቃውን ያልሠሩት ግን ተጠቃሚ ይሆናሉ፤›› ሲል ኤልያስ ገልጿል፡፡ ይህንን የተዛባ አካሄድ ለማቃናትም አዲሱ የመገበያያ ሥርዓት ጠቀሜታ እንዳለው ይናገራል፡፡ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ተቋም ለሙዚቃ ሥራዎቹ ሲከፍል፣ ሙዚቀኞቹ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

በኤልያስ ገለጻ፣ የገበያ ሥርዓቱ ሰው በሞባይሉ የሚያገኘው ሱቅ እንደማለት ነው፡፡ የሚፈልጉትን ሙዚቃ በኦዲዮና በቪዲዮም አግኝቶ መግዛት ይቻላል፡፡ በሕጉ መሠረት ድምፃውያን፣ የሙዚቃ አቀናባሪዎች፣ የግጥምና ዜማ ደራሲዎችና ፕሮዲውሰሮች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ጊዜ ቢደነገግም በተግባር ሲውል አይስተዋልም፡፡ ሕጉ አንድ የሙዚቃ አልበም ከወጣ ጀምሮ ባሉት አምስት ዓመታት የአልበሙ ፕሮዲውሰር የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንደሚሆንና ከአምስት ዓመት በኋላ ግን ባለመብቶቹ የሙዚቃ ባለሙያዎቹ እንደሆኑ ያትታል፡፡ ይህ መሬት ላይ ወርዶ ሙዚቀኞችን በዕውን ተጠቃሚ አለማድረጉን የገለጸው ኤልያስ፣ ‹‹ሙዚቀኛው ደሃ የሆነው መብቱ ስለሚጣስ እንጂ ደሃ ሆኖ አይደለም፤›› ብሏል፡፡

በተያያዥ የሚነሳው የሮያሊቲ ክፍያ ጉዳይ ነው፡፡ ሙዚቀኞችን በሮያሊቲ ክፍያ ተጠቃሚ የሚያደርገው አዋጅ ቢፀድቅም፣ ሙዚቀኛው ተጠቃሚ አልሆነበትም፡፡ በሙዚቃው ዘርፍ እንደ የኢትዮጵያ ኮፒራይት ሶሳይቲና የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ያሉ የሙዚቃ ማኅበራትም ለውጥ እንዳያመጡ በአቅም ውስንነት ይፈተናሉ፡፡ እነዚህና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉበት የሙዚቃው ዘርፍ በአዲሱ ሥርዓት ቀን ይወጣለታል የሚል አስተያየት የሰጡት ብዙ ሙዚቀኞች ናቸው፡፡

ጆኒ ራጋ እንደሚናገረው፣ የግብዓት ሥርዓቱ ሙዚቀኞች ሥራቸውን በአጭር ጊዜና በቀላሉ ለአድማጭ የሚያበቁበት ነው፡፡ ‹‹ሥርዓቱ ሙዚቀኛው በፍጥነት ሥራዎቹን እንዲለቅ ያስችላል፡፡ ሲዲ ማሳተም ያለውን ወጪና ውጣ ውረድም ይቀንሳል፤›› ሲል ገልጿል፡፡ እስካሁን በአውታር መልቲሚዲያ የተሠሩ ሥራዎችን ሲገልጽም ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች አንስቷል፡፡ የመጀመርያው ሙዚቃዎችን ማሰባሰብ ነው፡፡ ባለፉት አምስት አሠርታት በሸክላ፣ በካሴትና በሲዲ የተለቀቁ የሙዚቃ አልበሞችን ማሰባሰብን ያጠቃልላል፡፡ ሙዚቀኞች አልበሞችን በማሰባሰብ እንዲረባረቡም ጠይቋል፡፡

ሁለተኛው የተሰበሰቡትን ሙዚቃዎች በዲጂታል መንገድ አደራጅቶ ማቅረብ ነው፡፡ ሙዚቃዎቹ ሲደራጁ ከድምፃውያን በተጨማሪ በግጥም፣ በዜማ፣ ቅንብር፣ ፕሮዳክሽንና ኅትመት የተሳተፉ ባለሙያዎችን ባማከለ መንገድ ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘርፍ ከሚደመጡ ቅሬታዎች መካከል፣ በሙዚቃው ያሉ ባለሙያዎች ባጠቃላይ እኩል ዕውቅና አለማግኘታቸው ነው፡፡ እንደ ግጥምና ዜማ ደራስያን ያሉ ባለሙያዎች ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆነው ለሥራቸው ተገቢውን ጥቅም አያገኙም፡፡ አሠራሩ ይህንን በመለወጥ ለባለሙያዎች እኩል ቦታ ይሰጣል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የተጠቀሰው ሙዚቀኛውን በገንዘብ ተጠቃሚ የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ በጆኒ ራጋ ገለጻ፣ አዲሱ ሥርዓት በአንድ በሙዚቃ ሥራ የተሳተፉ ባለሙያዎች ማለትም ለሞራልና ኢኮኖሚ መብት ተጋሪዎች ዕውቅና ይሰጣል፡፡ የመረጃ ክምችቱ ለጥናትና ምርምርም ጥሩ ግብዓት መሆንም ይችላል፡፡

በግብይት ሥርዓቱ መሠረት አንድ ድምፃዊ ሥራውን ለገበያ ካቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ለአምስት ዓመታት ፕሮዲውሰሩ፣ ከዛ በኋላ ግን ድምፃዊውና ሌሎችም በአልበሙ የተሳተፉ ሙዚቀኞች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ሙዚቀኛው አልበሙን ራሱ ፕሮዲውስ ካደረገ ደግሞ አልበሙ ከተለቀቀበት ጊዜ ጀምሮ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ከሽያጩ ከሚገኘው ገቢ መካከል 20 በመቶ የሙዚቀኛው፣ 20 በመቶ ደግሞ የፕሮዲውሰሮች ይሆናል፡፡ ጆኒ ራጋ እንደተናገረው፣ አዳዲስ አልበሞች ሲወጡ ሙዚቀኞችን ለማበረታታትና አልበም ለማሳተም ያለውን ውጣ ውረድ ከግምት በማስገባት፣ አልበሙ ከተለቀቀበት ጊዜ ጀምሮ ለሁለት ወራት ሙሉ በሙሉ ገቢ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡

ተመሳሳይ ሐሳብ የሰነዘረው ኃይሌ ሩትስ፣ የሸክላ፣ የካሴትና የሲዲ ማጫወቻዎች በየዘመናቸው ከገበያ እንደወጡ ገልጾ፣ ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ በመታገዝ የሙዚቃ ግብይትን ማዘመን አስፈላጊ ነው ብሏል፡፡ በእርግጥ አዲሱን የገበያ ሥርዓት የመሰሉ አሠራሮች በመላው ዓለም የተለመዱ ናቸው፡፡ በርካታ አፕሊኬሽኖች ኅብረተሰቡ ሙዚቃ በቀላሉ እንዲያገኝ ከማስቻል ባለፈ፣ የሙዚቀኞችን ተጠቃሚነትም ያረጋግጣሉ፡፡ የሙዚቀኞች ጥቅም ታሳቢ ያደረጉ ዘመን አመጣሽ አሠራሮች እንዳሉ ሁሉ በተቃራኒው ሙዚቀኞች የሚዘረፉባቸው ቴክኖሎጂያዊ አሠራሮች ዘርፉን ይገዳደሩታል፡፡

‹‹ሙዚቀኛው የተጋረጠበትን ችግር ራሱ ሙዚቀኛው መፍታት የሚችለበት የግብይት ሥርዓት ነው፡፡ ሙዚቃን ማንም ሰው እጁ ላይ ባለ ሞባይል ያገኛል፡፡ የኮፒ ራይት ጥሰትንም ይከላከላል፤›› ይላል ኃይሌ ሩትስ፡፡ የአውታር መልቲሚዲያ የቴክኒክ ዳይሬክተር ታዲዮስ አሰፋ፣ ሥርዓቱ ሙዚቃን ከመሸጥ በተጨማሪ ሙዚቃ ነክ መረጃዎችን በማቀበል ያለውን ጠቀሜታ ገልጿል፡፡

ሙዚቃ ነክ ዜናዎች፣ ኮንሰርቶች፣ ፎረሞችና ወርክሾፖችን ማስተዋወቅ ይቻላል፡፡ አድማጮች በብዛት የሚገበዩትን ሙዚቃ ዓይነት ለመመዝገብና ሙዚቃዊ ውድድሮች ሲካሄዱ መረጃ በማቀበልም ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ሙዚቃዎችን ለመፈለግ አማርኛ፣ ትግርኛ ወይም ኦሮምኛ ቋንቋ መጠቀም ይቻላል፡፡ ኢንተርኔት ባይኖርም አገልግሎቱን በዩኤስኤስዲ ማግኘት ይቻላል፡፡ ‹‹ሙዚቃዎቹ የሚቀርቡት ኢንክሪፕት ተደርገው ስለሆነ በብሉቱዝ ወይም ማንኛም መረጃ መለዋወጫ መንገድ ሙዚቃዎቹን ከአንድ ተጠቃሚ ወደ ሌላው መላክ አይቻልም፤›› ይላል፡፡

ሙዚቀኞቹ በገበያ የዋሉ ሥራዎቻቸውን የሽያጭ እንቅስቃሴ መከታተል ይችላሉ፡፡ ተጠቃሚዎችም ግብዓታቸውን የሚከታተሉበት መንገድ አለ፡፡ ‹‹ማን ምን ያህል ሙዚቃ ሸጠ? የትኛው የሙዚቃ ዓይነት የበለጠ ይገዛል? የሚለው መረጃ ለተለያየ ጥቅም ይውላል፤›› ሲል ታዲዮስ ይገልጻል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ኢንዳይሬክት ፓርትነርስ ማኔጀር አቶ ሙሴ ደስታ፣ ተቋሙ ሰዎች በራሳቸው አገልግሎት ፈልገው የሚጠቀሙበት እንዲሁም አገልግሎት እንዲያገኙ የሚጠየቁበት አሠራር እንዳለ ገልጸው፣ የግብዓት ሥርዓቱ ካሉት አማራጮች አንዱን ለመጠቀም እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ እንደ ምሳሌ የጠቀሱት የስልክ ጥሪ ተጠቃሚ በመረጠው ሙዚቃ የሚሆንበት አሠራር ማለትም  ሲአርቢቲ (የድምፅ ማሳመሪያ) ነው፡፡

ለተጠቃሚዎች ኦንላይን የማድመጥ ወይም ገዝቶ የመጫን አማራጭም አለ፡፡ ቴሌ ከአውታር መልቲሚዲያ ውጪ ሌሎች በዘርፉ የመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ተቋሞች ካሉ ማሳተፍ እንደሚቻልም አቶ ሙሴ ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ የተገኙት ሙዚቀኞች ቴሌ ላይ ያሏቸውን ቅሬታዎችና ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ መነጋገሪያ ከሆኑት ጉዳዮች ዋነኛ የነበረው ቴሌ ከሲአርቢቲ 85 በመቶ ተጠቃሚ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ ምንም እንኳን አቶ ሙሴ የሲአርቢቲ የጥቅም ክፍፍል ቴሌ ባወጣው ጨረታ መሠረት መሆኑን ቢገልጹም፣ በክፍፍሉ የቴሌ ድርሻ ብዙ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው የሙዚቃ ግብይት ሥርዓቱ ሙዚቀኛው የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆንበት መሆን እንዳለበትም ባለሙያዎቹ ገልጸዋል፡፡

ከሙዚቀኞቹ መካከል ሔኖክ መሓሪ፣ ሥርዓቱ የሙዚቀኛውን መብት የሚያስጠብቅ መንገድ መከተል እንዳለበት አስረግጧል፡፡ የድምፃውያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ድምፃዊ ፀጋዬ እሸቱም ተመሳሳይ አስተያየት ሰንዝሯል፡፡ ‹‹አሁን ለሙዚቀኛው መፍትሔ በመበጀቱ ትንሽ ብርሃን ታይቷል፡፡ ቴሌ ለኢትዮጵያውያን ማሰብ አለበት፤›› ብሏል፡፡ ሥርዓቱ ሲዘረጋ ሙዚቀኛውን የሚደጉመው ቴሌ ወይስ ቴሌ በሙዚቀኛው የሚረዳ ነው? ሲልም ጠይቋል፡፡ ሙዚቀኛው በቴሌ በኩል የሚያገኘው ጥቅም እንዲከር የጠየቁ ባለሙያዎች፣ በዘርፉ ለዘመናት የደረሰባቸውን መጉላላት በማጣቀስም ነበር፡፡

ለሙዚቀኞቹ ምላሽ የሰጡት የኢትዮ ቴሌኮም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነት አቶ አብዱራሂም አሕመድ፣ ቴሌ የሙዚቃ ባለሙያውን የሚጎዳ አሠራር እንደማያራምድና ሁለቱንም አካሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በዕለቱ አከራካሪ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ ኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚዎች ማኅበር ይጠቀሳል፡፡ በኤልያስ ገለጻ፣ ማኅበሩ በሕገወጥ መንገድ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ የሙዚቀኞችን ጥቅም የሚያስከብሩ ሕጋዊ ድንጋጌዎችን ክፍተት ያላቸው አስመስሎ የማቅረብ ነገርም አለ፡፡ ሙዚቀኛው እክል ሲገጥመው ወደ ሕግ እንዳይሄድ ማድረግም ይስተዋላል ብሏል፡፡ ‹‹ማኅበሩ ሕግ እየጠቀሰ ሙዚቀኞች መካከል ውዥንብር እየፈጠረ ነው፡፡ ለሙዚቀኛው ጥቅም የምታደርጉት ነገር የለም፤›› ሲል ኤልያስ ተችቷል፡፡

በኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚዎች ማኅበር ረገድ መሐመድ አማን ትችቱ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጿል፡፡ ‹‹አሳታሚዎች እንደ ጠላት መቆጠር የለባቸውም፡፡ ማኅበሩ በመንግሥት ዕውቅና ተሰጥቶት የሚሠራ እንጂ ወንበዴ አይደለም፤›› ብሏል፡፡ ማኅበሩ የሙዚቀኞችን መብት ለማስጠበቅ የሚሠራ መሆኑንም አክሏል፡፡

ከላይ የተጠቀሰውን የመሰሉ ውዝግቦችና ሌሎችም በርካታ መሰናክሎች የሙዚቃውን ዘርፍ እየተፈታተኑት ይገኛሉ፡፡ በሙዚቀኞች አስተያየት ግን እነዚህን ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ የመጀመርያ ዕርምጃ የሚሆነው አዲሱ የሙዚቃ መገበያያ ሥርዓት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዳዊት ይፍሩ፣ ‹‹መፍትሔ አጥተን ስንቸገርበት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ ሙዚቀኞች መብታችንን ማስከበር ሲገባን ባለማወቅና በንዝላልነትም ተጎድተናል፡፡ አሠራሩ በመስኩ የተዘነጉ ባለሙያዎችን መብት የሚያስከብር ነው፡፡ ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ሠርተው ያለፉ ሙዚቀኞችን፣ ቤተሰቦችንና የወቅቱ ሙዚቀኞችንም የሚጠቀሙበት ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡  በዕለቱ እንደተገለጸው ሙዚቃ የማሰባሰብ ሥራው ተጠናቆ ከሰባት ወራት በኋላ ሥርዓቱ ይተገበራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቤተክህነት ባቀረበችው የይግባኝ አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለዕሮብ ተቀጠረ

የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገወጥ ነው በተባለው አዲሱ ሲኖዶስና...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...