Sunday, September 24, 2023

ምሁራኑ ካቢኔውን ይታደጉት ይሆን?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹በአንድ ትውልድ የተጣመመ የፖለቲካ ግንኙነት ነው እዚህ አገር ውስጥ ያለው፡፡ ይህ የተጣመመ የፖለቲካ ግንኙነት እየቀጠለ ነው ያለው፡፡ ሁላችሁም እንደምታውቁት በአገራችን የፖለቲካ ፓርቲ መሥርተው የሚታገሉት አብዛኞቹ የግራ ፖለቲካ አራማጅ የነበሩ ናቸው፡፡ የዚያን ጊዜ የነበረ ቁርሾ መቀጠል አለበት? እንዴት ነው አዲሱ ትውልድ የዚህ ቁርሾ ተሸካሚ እንዳይሆን ማድረግ የምንችለው? በራሱ የሚያስብና ራሱ ባመነጨው አዲስ አስተሳሰብ ውስጥ የሚኖር ትውልድ እንዴት ነው መፍጠር የምንችለው?››

ከላይ የተጠቀሰው ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በመጋቢት ወር 2008 ዓ.ም. ከዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ከሌሎች ተመራማሪዎች ጋር አገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ በተወያዩበት ወቅት ለውይይቱ መጀመሪያ ያደረጉት ጥያቄ አዘል ዲስኩር ነው፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድንገተኛ ሕልፈትን ተከትሎ የተፈጠረውን የሥልጣን ክፍተት እንዲሞሉ አቶ ኃይለ ማርያም መመረጣቸው ይታወሳል፡፡

በ2007 ዓ.ም. ግንቦት ወር የተካሄደውን ምርጫ መቶ በመቶ ያሸነፈው ኢሕአዴግ ለሙሉ የአምስት ዓመታት የሥልጣን ዘመን አገሪቱን እንዲመሩ አቶ ኃይለ ማርያምን መርጧቸዋል፡፡

በመስከረም 2008 ዓ.ም. ካቢኔያቸውን መሥርተው የሥልጣን ዘመናቸውን የጀመሩት አቶ ኃይለ ማርያም ከጥቂት ወራት በኋላ ከመሬት አስተዳደርና ከማንነት ጉዳዮች ጋር የተያያዙ መሰናክሎች ገጥመዋቸዋል፡፡

የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞችና ዩኒቨርሲቲዎች ግጭት ያዘለ ተቃውሞ ሲቀሰቀስ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደግሞ፣ ከቅማንት የማንነት ጥያቄ አለመመለስ ጋር ተያይዞ ደም ያፈሰሰና የበርካታ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ግጭት ተቀስቅሶ ነበር፡፡

ለሁለቱም ፖለቲካዊ ቀውሶች መፍትሔ ከተበጀ በኋላ ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በመጋቢት ወር ከአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራንን ሰብስበው በአገራዊ የህዳሴ ጉዳይ ውይይት ያደረጉት፡፡

‹‹ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብና ዴሞክራሲያዊ ባህል መገንባት ለዚህች አገር የዕጣ ፈንታ ጉዳይ ነው፡፡ እውነት ለመናገር በዚህ ረገድ እኛ ብዙ ጉድለቶች አሉብን፡፡ ብዙ ጊዜ መንግሥት ላይ ስለሚነጣጠር ነው እንጂ የኅብረተሰቡ ጉድለቶችም ናቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ መንግሥት ጉድለቶቹን የማረም የመሪነት ሚና እንዳለው ሳልክድ ማለት ነው፡፡ በአገራችን ሥር የሰደደ አገራዊ መግባባት የለም፡፡ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ እንዴት መግባባት አይኖረንም? ምሁራን በዚህ ረገድ የሚጫወቱት ሚና ምን መሆን አለበት? ምሁራን መሸሻቸውን አቁመው የራሳቸውን ፓርቲ አቋቁመው እንዴት ነው አስተዋጽኦ የሚያደርጉት የሚል ጥያቄ ይመላለስብኛል፡፡ የዳር ተመልካች መሆን ለዚህች አገር አይበጅም የሚል እምነት ስለያዝኩ ነው በድፍረት የምጠይቃችሁ፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መድረኩን ለውይይት ክፍት አድርገው ነበር፡፡

ምሁራኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍላጎት ዕውን እንዲሆን የእነርሱም መሻት መሆኑን ቢያምኑም፣ ነባራዊው የፖለቲካ ከባቢ በታፈነበት ሁኔታ እንዴት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችሉ ጠይቀዋቸው ነበር፡፡

ከዚህ ለየት ያለ ጥያቄ ያቀረቡት ዶ/ር መሐሪ ረዳኢ በበኩላቸው፣ ትኩረታቸውን በገዢው ፓርቲ በራሱ የተገለጹ ችግሮች ላይ አነጣጥረው ጥያቄዎችን አቅርበው ነበር፡፡

የ2007 ዓ.ም. ምርጫን ተከትሎ የገዢው ፓርቲ ድርጅቶች በተናጠል ባካሄዱት ስብሰባ፣ እንዲሁም በመቐለ ከተማ ኢሕአዴግ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ከፍተኛ ችግር እንዳለበት በይፋ አምኖ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ችግሩ በታችኛው አመራር ላይ ሳይሆን በከፍተኛ አመራሩ ላይ መሆኑ በይፋ ለሕዝብ ተነግሮ እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር መሐሪ፣ ‹‹መስከረም ወር 2008 ዓ.ም. ላይ እርስዎ ካቢኔዎትን ሲያዋቅሩ ያው የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮችን ነው ያየነው፡፡ በሚኒስትርነት ያላካተቷቸውንም አማካሪ ብለው ወደ እርስዎ ነው የወሰዷቸው፡፡ ስለዚህ ለውጥ አልታየም፡፡ አሁን በመጋቢት ወርም ለውጥ አልታየም፤›› ሲሉ ጠይቀዋቸው ነበር፡፡

በማከልም ታሟል የተባለው የላይኛው አመራር እንደሆነ ተገልጾ ለውጥ እየተካሄደ ያለው ግን ታች ባለው አመራር ላይ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ጠይቀዋል፡፡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ መስጠት የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በወቅቱ ተካሂዶ በነበረው ግምገማ የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩን፣ እያቆጠቆጠ ያለ ሙስና ስለመኖሩና ሊወገዱ እንደሚገባ ተገምግሞ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ለካቢኔ ሹመኞችን ያቀረቡት ለማወቅ በሚችሉት ደረጃ ገምግመው ያመኑባቸውን መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ ልጠየቅ የምገባው እገሌ የሚባል የሚታወቅ ሌባ ነው የሾምከው ተብሎ ነው፡፡ ይኼ ባልሆነበት ሁኔታ እኔ ምን ላድርግ?›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ በጥቅሉ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ ስለተባለ ነባር አመራሮች መሾም የለባቸውም ማለት እንዳልሆነ አስረግጠው ተናግረው ነበር፡፡

በ2008 ዓ.ም. ያቀረቡት ካቢኔ ውስጥ 30 በመቶ የሚሆኑት አዳዲስ መሆናቸውን ጠቁመው ነበር፡፡ ኢሕአዴግ በተተኪነት ለሌሎች ፓርቲዎች ሥልጣን እስከሚያስረክብ ድረስ የራሱን ውስጣዊ አሠራር ተከትሎ በመረጃዎች እንደሚመለምል ጠቁመዋል፡፡

‹‹ከጥያቄው ይዘት ትንሽ የገባኝ የፓርቲ አባል ብቻ ለምንድነው የምትሾሙት? ለምንድነው ከሌሎች አካባቢዎች የማትሾሙት? የሚል በግልጽ ያልወጣ ጥያቄ ያዘለ ይመስለኛል፤›› በማለት ለዚሁ ምላሽ የሰጡት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ይህ ከሆነ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ግንኙነት የለንም፡፡ በሒደት ግንኙነት እየመሠረትን ከምሁራንም ከሌሎችም አካባቢዎች ለመሾም እንሞክራለን፡፡ አሁን ግን ጊዜው አይደለም፤›› ብለው ነበር፡፡

ከዚህ የምሁራንና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውይይት ጥቂት ወራት በኋላ በተመሳሳይ ሁለት አካባቢዎች ግጭትና ተቃውሞ ከቀድሞው የበለጠ አይሎ ተቀስቅሷል፡፡

በአማራ ክልል በተመሳሳይ ሰሜን ጎንደር ዞን ከወልቃይት የማንነትና የወሰን ለውጥ ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተቀሰቀሰው የፖለቲካ ተቃውሞ መልኩን ቀይሮ አገራዊ የፖለቲካ ሥርዓቱን በመቃወም ቀጠለ፡፡ በኦሮሚያም ረገብ ብሎ የነበረውን ተቃውሞ ዳግም እንዲቀሰቀስ ምክንያት መሆኑ ይታወሳል፡፡ የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላኑን ምክንያት ያደረገው ተቃውሞ መልኩን ቀይሮ በኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት ላይ ያነጣጠረ ፖለቲካዊ ተቃውሞ ወደ ግጭትና ደም መፋሰስ ተሸጋግሯል፡፡

የበርካታ መቶዎች ሕይወት ሲያልፍ እንደዚሁም ከፍተኛ ውድመት በውጭና በአገር ውስጥ ባለሀብቶች ኢንቨስትመንቶችና ንብረቶቹ ላይ ደርሷል፡፡ ሁኔታው ያሳሰበው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊቀመንበርነት የሚመራው ኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴውን ሰብስቦ ባካሄደው ውይይት፣ የወቅታዊው ችግር መንስዔ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግር መሆኑን ጠንከር በማለት አስቀምጦታል፡፡

የመንግሥት ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል፣ በሥልጣን መባለግና የሕዝብ ጥያቄዎችን በአግባቡና በፍጥነት ያለመመለስ ችግር መኖሩን፣ የወጣቶች ሥራ አጥነት መስፋፋቱን የችግር መንስዔ አድርጓል፡፡

በመፍትሔነት በጥልቀት የመታደስ ፕሮግራም ማስቀመጡን የጠቀሰው ፓርቲው፣ በዚህ ፕሮግራም ውስጥ ከተካተቱት መካከል የመንግሥት ካቢኔ ሹም ሽር አንዱ መሆኑን መጠቆሙ ይታወሳል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ጥቅምት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ካቢኔያቸውን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መልሰው አዋቅረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2008 ዓ.ም. ካቋቋሙት 30 አባላትን የያዘ ካቢኔ ውስጥ ዘጠኝ የሚሆኑትን በነበሩበት ቦታ እንዲቆዩ በማድረግ፣ ሌሎች አምስት የቀድሞ ካቢኔ አባላትን እንዲሸጋሸጉ ወይም በሌላ ኃላፊነት እንዲሾሙ አድርገዋል፡፡

ሌሎች 13 አዳዲስ የካቢኔ አባላትንም በካቢኔያቸው አካተው በፓርላማው አፀድቀዋል፡፡ ከእነዚህ አዳዲስ 13 አባላት ውስጥ አሥር የሚሆኑት ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ እንዲሁም ከፖለቲካ ውጪ በሆኑ የመንግሥት ድርጅቶች ውስጥ ሲያገለግሉ የነበሩ ከፍተኛ ምሁራንን በካቢኔ አባልነት ሹመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርየም አዲስ ስለተቀላቀሉት የካቢኔ አባላት በተለይም ምሁራንን ለማካተት ስላስፈለገበት ጉዳይ ሲያብራሩ፣ የአገሪቱ የዕድገት ደረጃ የሚጠይቀው ዝንባሌ፣ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸውን መሾም ማስፈለጉን ጠቁመዋል፡፡

አዲሶቹ የካቢኔ አባላት እነማን ናቸው?

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲሱ ካቢኔያቸው እንዲካተቱ ካደረጓቸው 13 አዳዲስ ሚኒስትሮች ውስጥ አሥሩ በከፍተኛው የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተካተው የማያውቁ፣ ይልቁንም በርካታ ጊዜያቸውን በምርምርና በማስተማር ላይ ያሳለፉ ናቸው፡፡

የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ሲሆኑ በብሔራቸው ኦሮሞ ናቸው፡፡ እንዲሁም በኃይድሮሊክስና በውኃ ሀብት ምህንድስና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እንዳገኙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በሹመቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡ በቀድሞው የአርባ ምንጭ ውኃ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከጀማሪ መምህርነት እስከ ዲን የሠሩ ናቸው፡፡ በኋላም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እስኪመሠረት ድረስ ምሥረታውን በኃላፊነት የመሩ ናቸው፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሥረታ በሚካሄድበት ወቅት ጥብቅ ወዳጅነት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር እንደነበራቸው ይነገራል፡፡ ዶ/ር ስለሺ ለዶክትሬት ዲግሪያቸው ወደ ውጭ አገር በሄዱበት ጊዜ አቶ ኃይለ ማርያም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ስለሺ ከዚህ በኋላ በዩኒቨርሲቲ መምህርነት አልቀጠሉም፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ከውኃ ጋር የተያያዙ ሙያዊ አገልግሎቶችን ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የውኃና የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ባለሙያ፣ እንዲሁም በኒውዮርክ የተመድ የዘላቂ ልማት ግቦች የአቅም ግንባታና የውኃና ኢነርጂ አማካሪ በመሆን እስከ አሁኑ ሹመታቸው ድረስ ቆይተዋል፡፡

ከዶ/ር ስለሺ ጋር በህዳሴ ግድብ አማካይነት እንደሚተዋወቁ፣ የህዳሴው ግድብ ተደራዳሪ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንጂነር ጌድዮን አስፋው ይገልጻሉ፡፡ የህዳሴው ግድብን በተመለከተ የኢትዮጵያ የባለሙያዎች ቡድንን በማደራጀት በሊቀመንበርነት የመሩ ከፍተኛ የማስተባበር ችሎታ ያላቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ከውኃ ጋር የተያያዙ በርካታ ጠቃሚ ጥናቶችን ያቀረቡና ብቃት ያላቸው ባለሙያ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

በንግድ ሚኒስትርነት የተሾሙት ደግሞ ዶ/ር በቀለ ቡላዶ ናቸው፡፡ ዶ/ር በቀለ በቢዝነስ ሳይንስ የማስትሬት ዲግሪያቸውን ከአየርላንድ ዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም በስትራቴጂክ ማኔጅመንትና ቢዝነስ ፖሊሲ ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

ከሥራ ልምዶቻቸው መካከል የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ደኢሕዴን) ኢንዶውመንት ድርጅት የሆነው የወንዶ ንግድ ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚ ነበሩ፡፡ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከመጋቢት 2008 ዓ.ም. በኋላ የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ሲያገለግሉ ነበር፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ተደርገው የተሾሙት ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነ ናቸው፡፡ በብሔራቸው አማራ ናቸው፡፡ በሕክምና የዶክትሬት ዲግሪ ያገኙ ሲሆን፣ በአካዳሚ ማዕረጋቸው የማሕፀንና ፅንስ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሴኔት አባልና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ሆነው የመሩ፣ እንዲሁም ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የአዲስ አበባ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡

የፕሮፌሰር ይፍሩን የአመራርነት ብቃት በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕፃናት ሕክምና ትምህርት ክፍል በማገልገል ላይ የሚገኙት ፕሮፌሰር አምሓ መካሻ፣ ‹‹ጠንካራ ሠራተኛ›› ሲሉ ይገልጿቸዋል፡፡

በማኔጅመንት ደረጃ ከፕሮፌሰር ይፍሩ ጋር የሠሩበት ጊዜ አጭር ቢሆንም፣ በጥቁር አንበሳ በነበሩበት ጊዜ እንደ አመራር ግልጽ፣ ቀናና ከሰዎች ጋር ተግባብተው መሥራት የሚችሉ ታታሪ ሠራተኛ መሆናቸውን እንደተገነዘቡ ገልጸዋል፡፡

‹‹ከጎናቸው ቀናና ጠንካራ ለለውጥ የሚተጋ ሰው ካገኙ በጤናው ዘርፍ ትልቅ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ፤›› ብለዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ደግሞ ዶ/ር ሒሩት ወልደ ማርያም ናቸው፡፡ በሥነ ልሳንና የቋንቋ ጥናት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በማግኘት በዘርፉ ያስተማሩና የተመራመሩ፣ እንዲሁም እስከ ሹመታቸው ጊዜ ድረስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ሲያገለግሉ ነበር፡፡

የሥነ ልሳንና ቋንቋ ጥናት መምህርና ተመራማሪ በመሆን ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉት ፕሮፌሰር ባዬ ይማም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሆነው ስለተሾሙት ዶ/ር ሒሩት ለሪፖርተር ሲናገሩ፣ ‹‹ላመነችበት ወደኋላ እንደማትል አውቃለሁ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ዶ/ር ሒሩትን ተማሪዬ ሆና አውቃታለሁ፡፡ ባልደረባዬም ሆና፣ እንዲሁም አለቃዬም ሆና አውቃታለሁ፤›› የሚሉት ፕሮፌሰር ባዬ፣ ዶ/ር ሒሩት በተመደቡበት ቦታ ለውጥ ያመጣሉ የሚል እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡

የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ደግሞ ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ ናቸው፡፡ በእንስሳት ዕርባታ የማስትሬት ዲግሪያቸውን፣ እንዲሁም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በወተት ልማት ቴክኖሎጂ ከኖርዌይ አግኝተዋል፡፡

በምግብ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ምርምርና ማስተማር የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ በቀድሞው የደቡብ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአካዴሚ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩ፡፡ ላለፉት አሥር ዓመታት የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ላለፉት ጥቂት ወራት ደግሞ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው እያገለገሉ ነበር፡፡

የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር እያሱ አብረሃ የማስትሬት ዲግሪያቸውን በአግሮ ኢኮኖሚ በማዕረግ ያገኙ ሲሆን፣ በዕፅዋት ሳይንስ ደግሞ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከቼክ ሪፐብሊክ አግኝተዋል፡፡

በትግራይ ክልል ከግብርና ጋር በተገናኙ የተለያዩ ቢሮዎችና የምርምር ተቋማት ያገለገሉ ሲሆኑ፣ ላለፉት አምስት ዓመታትም የትግራይ የእርሻ ምርምር ዋና ዳይሬክተር ነበሩ፡፡

የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ደግሞ ዶ/ር ገመዶ ዳሌ ናቸው፡፡ በባዮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በዕፅዋት ሳይንስ የማስተርስ ዲግሪና በግብርና ሳይንስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙ ናቸው፡፡

ለረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ኢንስቲትዩት ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች የሠሩና የተመራመሩ፣ ላለፉት አምስት ዓመታትም የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡

ስለ ዶ/ር ገመዶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዕፅዋት ሳይንስ ፕሮፌሰርና የዕፅዋት ቤተመዘክር ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው፣ ‹‹የሰው ሐሳብ የሚቀበል፣ በመወያየትና ችግሮችን በመፍታት የሚያምን ብሩህ አመለካከት ያለው ነው፤›› በማለት ይገልጿቸዋል፡፡

‹‹ካለፈው ልምድ ተነስቼ አንድ ሊያዳምጥ የሚችል ሰው መገኘቱን በበጎ አየዋለው፤›› የሚሉት ፕሮፌሰር ሰብስቤ፣ ‹‹እኔ በዶ/ር ገመዶ ላይ እምነት አለኝ፡፡ አንዳንዴ የምታናግረው መሪ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ አሁን የሚያዳምጥ፣ ለመነጋገር የማይከብድ ሰው በመመደቡ ሐሳቤን በግልጽ ለመስጠት ያስችለኛል፤›› ብለዋል፡፡

የመንግሥት ልማት ድርጅት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ግርማ አመንቴ ትምህርታቸውን ከደን ሀብት ልማት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ የሥራ ልምዳቸውም ከዚሁ ጋር የተገናኘ ነበር፡፡ የኦሮሚያ ክልል የደን ልማት ኃላፊ ነበሩ፡፡ የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነውም ያገለገሉ ናቸው፡፡

ከ2007 ዓ.ም. ሹመታቸውን እስካገኙበት ድረስ የምሥራቅ አፍሪካ ዩኒክ የደንና የመሬት አጠቃቀም ዳይሬክተር ነበሩ፡፡ የመንግሥትን የልማት ድርጅት በመምራት ቀጥተኛ ልምድ እንዳላቸው ይነገራል፡፡

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ሲሆኑ፣ እስከ ሦስተኛ ዲግሪያቸው ድረስ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ የተማሩ እንዲሁም የተመራመሩ ናቸው፡፡ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው አገልግለዋል፡፡

ለመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ዲን፣ እንዲሁም መምህር ሆነው ያገለገሉና በጋዜጠኝነት የሥራ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አቶ ርስቱ ይርዳው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ያገለገሉ ናቸው፡፡

ምሁራኑ የካቢኔ አባላት ፋይዳና ተግዳሮት

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በአጭር ወራት ውስጥ ቀድሞ የነበራቸውን አቋም ቀይረው በካቢኔያቸው የፓርቲ አባል ያልሆኑ ምሁራንን አካተዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ምንጮች እንደሚገልጹት፣ ቢያንስ አምስት የሚሆኑት የፓርቲ አባል እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡

አገሪቱ ያለችበት የዕድገት ደረጃና የሚያጋጥሙ ችግሮች ውስብስብነት ሙያዊ ብቃትንና ክህሎትን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የምሁራኑ መካተት አስፈላጊነትን ይገልጻሉ፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተንታኞች እንደሚሉት ደግሞ፣ ምሁራኑ በሙያቸው ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ባልተናነሰ በአሁኑ ወቅት የሚታየውን የገዥው ፓርቲና የመንግሥት መደበላለቅ ይለዩታል የሚል እምነት አላቸው፡፡

እስካሁን በነበረው ሥርዓት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከሞላ ጎደል በሙሉ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ እንደነበሩ፣ ይኸውም በፓርቲውና በመንግሥት መካከል መደበላለቅን ሲፈጥር እንደቆየ ገልጸዋል፡፡ ይህም የፖለቲከኞች ጉልበት ቴክኖክራት (ባለሙያ) የሆኑ የካቢኔ አባላትን ሲያደበዝዝ ቆይቷል የሚል እምነት አላቸው፡፡

በአዲሱ ካቢኔ ከተካተቱት አሥር ከሚሆኑት ምሁራን መካከል የፓርቲ አባል ያልሆኑ መኖራቸው፣ እንዲሁም የፓርቲ አባል የሆኑትም የታችኛው እርከን ላይ የሚገኙ በመሆናቸው በፓርቲ ፖለቲካና በመንግሥት ሥራ አፈጻጸም መካከል የተደበላለቀውን ድንበር ሊለዩ ይችላሉ ብለዋል፡፡

ፕ/ር ባዬ በበኩላቸው ሥጋት ቢኖራቸውም፣ ከፖለቲከኞች የሚገጥማቸውን ተግዳሮት እየተቋቋሙ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ የሚል እምነት አላቸው፡፡

በትምህርት ተቋም ውስጥ አንፃራዊ ነፃነት መኖሩን የሚናገሩት ፕ/ር ባዬ፣ ምሁራኑ ይህንን ነፃነት እንደለመዱ ይናገራሉ፡፡ አሁን የገቡበት ቦታ ይህ ነፃነት ይኖራል ወይ የሚል ጥያቄ ትልቁ ሥጋታቸው ነው፡፡

መንግሥት ምሁራንን የፈለገበትን ምክንያት ስረዳ ‹‹ሙያና ቅን ልቡና የተፈለገ ይመስለኛል፤›› የሚሉት ፕ/ር ባዬ፣ የሚገጥማቸውን ፖለቲካዊ ተግዳሮት አስፈላጊ እስከሆነው ድረስ መጋፈጥ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

መንግሥት ፖሊሲዎቹ እንዲፈጸሙ እንደሚፈልግ ሁሉ ባለሙያዎቹም ይህንን ለመወጣት ፍላጐት ያላቸው በመሆኑ፣ መሰል ችግር የሚፈጥረውን ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ታግለው ውጤታማ እንደሚሆኑ ገምተዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -