Sunday, September 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የተጀመረው ሹም ሽር ወደ ታችም ይውረድ!

አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ካቢኔ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሁንታ አግኝቶ ሥራውን በይፋ ጀምሯል፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብን እንዲያገለግል ከፍተኛ አደራ የተጣለበት ካቢኔ፣ በመካከለኛና በዝቅተኛ ደረጃ በሚገኙ ብቃት ባላቸው አስፈጻሚዎችና ፈጻሚዎች ካልታገዘ እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ሊያስመዘግብ አይችልም፡፡ ከኅብረተሰቡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው የታችኛው መዋቅር በብልሹ አሠራርና በከፋ የሥነ ምግባር ችግር የተጠቃ ሲሆን፣ ከፍተኛ የሆነ የብቃት ችግርም አለበት፡፡ በከተሞች ውስጥም ሆነ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ ደካማ መዋቅሮች ውስጥ የተሰገሰገው ኃይል ፀድቶ፣ በብቃታቸውና በሥነ ምግባራቸው ምሥጉን በሆኑ ዜጎች መተካት ይኖርበታል፡፡ ለዚህም ሲባል አስፈላጊው ዕርምጃ መወሰድ አለበት፡፡

በፌዴራል ደረጃ፣ በክልሎች፣ በዞኖች፣ በወረዳዎችና በከተማ አስተዳደሮች ውስጥ በፖለቲካ ፓርቲ አባልነትና ታማኝነት መሥፈርት ተደላድሎ የተቀመጠው ብቃት አልባ ኃይል ለመልካም አስተዳደር መጥፋት፣ ለፍትሕ መጓደል፣ ለሕገወጥ ተግባራት መበራከትና በአጠቃላይ ለዜጎች ምሬት ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ ግብር ከፋዩ ሕዝብ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዳያገኝ በማድረግ፣ የወጣቶች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዳይኖር መሰናክል በመፍጠር፣ ብልሹ አሠራሮችን በማስፋፋት፣ ሐሰተኛ ሪፖርቶች በመፈብረክ የተሳሳቱ መረጃዎች በማቅረብ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን በመጣስ፣ የሕግ የበላይነትን በመጋፋት፣ ወዘተ. ሕዝብን በማስመረር ወደር የሌለው ይህ ከንቱ ኃይል ከቢሮክራሲው ውስጥ መውጣት አለበት፡፡ በምትኩም ብቃትን መሠረት ያደረገ ሹመት ሊሰጥ ይገባል፡፡ የግድ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ የተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በየደረጃው ባሉ አመራሮችና ፈጻሚዎች ምክንያት የመልካም አስተዳደር ዕጦት መስፋፋቱን፣ ያላግባብ መበልፀግ መበራከቱን፣ ፍትሕ መጓደሉን፣ የሕዝብና የመንግሥት ግንኙነት ችግር ውስጥ መውደቁንና ሕገወጥ ተግባራት መበራከታቸውን በየጊዜው ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡ ሕዝቡ መንግሥትን በአፉ ብቻ ሳይሆን በእጁ ጭምር ወግድ እያለው መሆኑ ጭምር ተወስቷል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ ሁከት ተቀስቅሶ ለበርካታ ዜጎቻችን መሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለአገር ሀብት ውድመት መንስዔ ሆኗል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሕዝብ ሰላም ተናግቷል፡፡ የአገር ህልውናም አደጋ ውስጥ ገብቷል፡፡ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ችግሮችን ማስቆም ባለመቻሉም አገሪቱ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥራ ላይ ውሎባታል፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር አገር ላይ ተጋርጦ መታሰብ ያለበት ለዘለቄታዊ መፍትሔዎች ነው፡፡

ከዘለቄታዊ መፍትሔዎች መካከል አንደኛው መንግሥት ራሱን በራሱ በማረም የተበለሻሸውን ጓዳውን ማፅዳት ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተናጋውን አንፃራዊ ሰላም ከማስመለስና መረጋጋት ከመፍጠር ውጪ ሌላ ዓላማ ሊኖረው አይገባም፡፡ ስለዚህ በኦሮሚያ ክልልና በፌዴራል ደረጃ እንደተጀመረው፣ በመላ አገሪቱ ከላይ እስከ ታች ባሉ መዋቅሮች ውስጥ መጠነ ሰፊ ሹም ሽርና ሽግሽግ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በላይኛው የሥልጣን እርከኖች ላይ ከተወሰደው ዕርምጃ በተጨማሪ በታችኛው መዋቅር ውስጥ ተቀምጠው ሕዝቡን በቀጥታ የሚያገኙት ሹማምንት ብቃት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሥነ ምግባር ሊላበሱ ይገባል፡፡ የእነሱ የፓርቲ ደብተር ዜጎች ከያዙት መታወቂያ በታች እንደሆነ በተግባር ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ የሥልጣን ባለቤት የሆነውን ሕዝብ በአገልጋይነት መንፈስ መቅረብ ካልቻሉ ለቦታው እንደማይመጥኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ሕዝቡ ላቀረባቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች መንግሥት መልስ መስጠት የሚጀምረው ከታች ከወረዳ ጀምሮ ስለሆነ በታችኛው መዋቅር ውስጥ በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በሥራ ልምዳቸው፣ በሥነ ምግባራቸው፣ በአገር ወዳድነታቸውና በመሳሰሉት የተመሰከረላቸው ዜጎች መመደብ አለባቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ደካማ የሆኑትን መንግሥታዊ መዋቅሮች በኔትወርክ የተቆጣጠሩ ኃይሎች ያደረሱት ጥፋት እንዳይደገምና አገሪቱም ሌላ ዙር አጣብቂኝ ውስጥ እንዳትገባ፣ ከወሬ ይልቅ በሥራ አፈጻጸማቸው አርኪ ውጤት የሚያመጡ ዜጎች ይፈለጉ፡፡ አገር በመፈክር የትም አትደርስም፡፡ አገር በማይጨበጡ ምኞቶችና ተስፋዎች አታድግም፡፡ አገር ሰላም የምትሆነው፣ የምትበለፅገው፣ ዜጎቿ በኩራት አንገታቸውን ቀና የሚያደርጉባት፣ ዴሞክራሲ በተግባር የሚረጋገጥባትና ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠርባት በወሬ ሳይሆን፣ ሠርተው በሚያሠሩ ምሥጉን መሪዎች ስትመራ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ብቃት ወሳኝ ነው፡፡ ሥነ ምግባር ወሳኝ ነው፡፡ የአገር ፍቅር ስሜት ወሳኝ ነው፡፡ እንዲህ ሲታሰብ ሁሉንም ወገን ያግባባል፡፡

በየደረጃው ባሉ መንግሥታዊ መዋቅሮች ውስጥ ኃላፊነት ተቀብሎ ለመምራት ከብቃትና ከሥነ ምግባር በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ልቦና ዝግጅት ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም ለመሪነት የሚያበቃ ሰብዕና መኖር አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ ጥቅማቸውን ብቻ እያነፈነፉና በሕዝብ ስም እየማሉ ማጭበርበር ኋላቀርነት ነው፡፡ ሌብነት የዝቅጠት ማሳያ ነው፡፡ ውሸታምነት የክስረት ምልክት ነው፡፡ ወሬኛነት የሥራ ፈቶች ተግባር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ የተከበረ ኩሩ ሕዝብ ነው፡፡ ለአገሩ ከፍተኛ ፍቅር ያለውና እርስ በርሱ ባለው ግንኙነት ብሔር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነትም ሆነ ሌላ ጉዳይ ሳይገድበው ልዩነቶቹን አቻችሎ በፍቅርና በመተሳሰብ የሚኖር ጨዋ ሕዝብ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ ተጋብቶና ተዋልዶ ዘመናትን የተሻገረ የተከበረ ሕዝብ ነው፡፡ ይህንን ኩሩና ታላቅ ሕዝብ በአግባቡ ማስተዳደር አለመቻል በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ በፍትሕ አዋቂነታቸው፣ በአስታራቂነታቸው፣ በመካሪነታቸውና በአርቆ አሳቢነታቸው በኅብረተሰቡ ውስጥ የተመሰከረላቸው አረጋውያንን ጨምሮ አገሩን ቀንና ሌሊት እያገለገለ ለማበልፀግ የሚችል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት ያላት ይህች ድንቅ አገር በአግባቡ መመራት አለባት፡፡ ለዚህም ብቃትና ከፍተኛ የሆነ ዝግጅት ያላቸው ዜጎቿ ወደ ሥልጣን መንበሩ ይጠሩ፡፡ በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች ገብተው ያገልግሉ፡፡ የተጀመረው ሹም ሽር በዚህ መንፈስ ወደ ታችም ይውረድ!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...