Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ለሜትር ታክሲዎች የተመደበላቸው ታሪፍ ሲበዛ ነው››

አቶ ካሣሁን ኃይለ ማርያም፣ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር

አቶ ካሣሁን ኃይለ ማርያም ላለፉት 18 ዓመታት የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከመመደባቸው ቀደም ብሎ በዚሁ መሥሪያ ቤት ከኤክስፐርት እስከ መምርያ ሥራ አስኪያጅነት ባሉ የተለያዩ የኃላፊነት መደቦች አገልግለዋል፡፡ ውስብስብ ችግሮች እንዳሉበት የሚነገረውን ይህንን የትራንስፖርት ዘርፍ በተመለከተ የቆየ ልምድ ያላቸው አቶ ካሣሁን፣ ዘርፉን ለዘመናዊ አገልግሎት የተመቻቸ ለማድረግ የሚመሩት መሥሪያ ቤት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ስለመሆኑ ይገልጻሉ፡፡ በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎትን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ለማዳረስ የተሠሩ ሥራዎች ቢኖሩም፣ አሁንም ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህ ዘርፍ የሚነሱ ብዙ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ከትራንስፖርት አገልግሎት በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የትራንስፖርት እጥረት፣ አማራሪ እየሆነ የመጣውን የአዲስ አበባ ከተማ የትሪፊክ መጨናነቅ፣ እንዲሁም በመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮችና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ዳዊት ታዬ አቶ ካሣሁንን አነጋግሯቸዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎትና ተደራሽ ለማድረግ የተያዘው ዕቅድ ምን ያህል እየተሠራበት ነው?

አቶ ካሣሁን፡- በእያንዳንዱ የአገሪቱ ክፍሎች የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማዳረስ ብዙ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ የመንገድ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ተዘርግቷል፡፡ እየተዘረጋም ነው፡፡ በአምስት ዓመታት 70 ሺሕ ኪሎ ሜትር የገጠር መንገዶች ተገንብተዋል፡፡ በአስፋልት በሚገነቡት መንገዶች ላይ ደግሞ በየዓመቱ አዳዲስ ሥምሪት አለን፡፡ ከአዲስ አበባ ወደተለያዩ አቅጣጫዎች በየጊዜው አዳዲስ የትራንስፖርት ሥምሪቶች ስላሉን ተደራሽነቱ እየሰፋ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የፍላጎቱን ያህል የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ወደ ሥምሪት እየገቡ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ካሣሁን፡- ይገባሉ፡፡ የግል ባለሀብቱ ካመቻቸህለት ያስገባል፡፡ የዚህ ትራንስፖርት ዘርፍ ጥሩ ጎኑ እንደሌላው ኢንቨስትመንት አይደለም፡፡ ሌላው ኢንቨስትመንት መሬት ይፈልጋል፡፡ የግንባታ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ሌሎች ብዙ ነገሮችን ይፈልጋል፡፡ ትራንስፖርት ግን ገንዘብ ካለህ ቴክኖሎጂ ትገዛለህ፡፡ ብቻህን ስለማትሠራና የተደራጀ አካል ስላለ በቀላሉ ወደ ሥራውም ትገባለህ፡፡ ከዚያም ወደ ሥራ በገባህ በሁለተኛው ቀን ገቢ የምታገኝበትም ዘርፍ ነው፡፡ እንደ ሌላው ዘርፍ በጣም አትራፊ ባይሆንም፣ ሕዝብ እያገለገለ ተመጣጣኝ ትርፍ እያገኘህ የምትሠራው ነው፡፡ ወደ ሥራው በቀላሉ የምትገባበትና በቀላሉ የምትወጣበት መሆኑም ይለየዋል፡፡ ይህንን ዕድል በመጠቀም ብዙ ባለሀብቶች እየገቡ በመሆኑ አዳዲስ ሥምሪቶቻችንን ቀጥለናል፡፡ የፍላጎትና የአቅርቦት ያለመጣጣም አለ ከተባለ አዲስ አበባ ላይ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ግን የአቅርቦት ችግር ብቻ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የአገር አቋራጭ ትራንፖርት ፍላጎት ተሟልቷል ብሎ ለመናገር ይቻላል?

አቶ ካሣሁን፡- አገር አቋራጩ እየተሟላ እየሄደ ነው የምንለው ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ለአገር አቋራጭ ትራንስፖርት ከአንድ ሺሕ ያላነሱ አውቶብሶች ገብተዋል፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎቱ በተሽከርካሪዎች ብቃት ደረጃ ወጥቶላቸው እንዲሠሩ መደረግ ከጀመረ በኋላ 980 አዳዲስ አውቶብሶች ገብተው እየሠሩ ነው፡፡ እንዲያውም አሮጌዎቹ ለመወዳደር እያቃታቸው እየወጡ ነው፡፡ የዛሬ አምስት ዓመት ደረጃ አንድ የተሰጣቸው ቁጥራቸው በጣም ትንሽ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን በሚያህል አገር በአምስት ዓመት አንድ ሺሕ አውቶብሶች ብቻ ብዙ ናቸው ሊባሉ ይቻላል?

አቶ ካሣሁን፡- ተሽከርካሪዎችን በደረጃ ለይተን መሥራት ስንጀምር ደረጃ አንድ ብለን የለየናቸው አውቶብሶች ቁጥር እኮ አሥራ አንድ ነበር፡፡ ዕድሜያቸው ከሰባት ዓመት በታች ሆነው የተገኙትና ሌሎች መሥፈርቶችን ያሟሉ የነበሩ እነዚህ ብቻ ነበሩ፡፡ ነገር ግን አሠራሩን በማሻሻላችን ውድድርም ስለነበር ባለሀብቱ በዚህ በተመቻቸው አሠራር ተጠቅሞ በዚህ በአጭር ጊዜ የደረጃ አንድ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ከ900 በላይ ደርሷል፡፡ የደረጃ ሦስት ተሽከርካሪዎች ቁጥር ደግሞ እየቀነሰ ነው፡፡ ምክንያቱም ከተወሰነ ዓመት በኋላ ከደረጃ አንድ ወደ ሁለት ከሁለት ወደ ሦስተኛ ደረጃ እየወረደ ሄዶ መጨረሻ ላይ ከሥምሪት  ይወጣል፡፡   

ሪፖርተር፡- ከደረጃ ሦስት ሥምሪት  ከወጣ በኋላ ዕጣ ፋንታው ምንድነው?

አቶ ካሣሁን፡- ከሦስተኛ ደረጃ በኋላ ይወጣና የሰርቪስ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ወደ ገጠር ይሄዳል፡፡ ደረጃ ሦስት ማለት መኪናው የተሟላ አይደለም ማለት አይደለም፡፡ ለመንገደኛው ሥጋት ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ ግን ደረጃ ስታስቀምጥ ውድድር መኖር አለበት፡፡ አዲስ የገዛው ባለሀብትና ብዙ ዓመት መኪናውን የተጠቀመበት ባለሀብት እኩል ወረፋ ጠብቁ አይባልም፡፡ ምክንያቱም አዲሱን ያመጣው ብዙ ገንዘብ አውጥቶበታል፣ ቶሎ መሥራት አለበት፡፡ ገንዘቡን መመለስ አለበት፡፡ በዚህ ዓይነት በየደረጃዎቹ መካከል በተፈጠረ ውድድር ሕዝቡም ደረጃ አንድን እየመረጠ ስለመጣ፣ እነዚያም ባለሀብቶች በቀጣይ መቀጠል እንደማይችሉ ስላወቁ ወደ ደረጃ አንድ እየመጡ ነው፡፡ እውነት ለመናገር ኢትዮጵያ 100 ሚሊዮን ያህል ሕዝብ ኖሯት፣ ያለው ግን በቂ ነው ማለት አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ ክርክር ከሚያስነሱ ጉዳዮች አንዱ ኢትዮጵያ ያሉዋት የተሽከርካሪዎች ቁጥር ብዙ ነው ብዙ አይደለም የሚለው ነው፡፡ በአደጋ ቀዳሚ ነች እየተባለ በአንፃሩ ደግሞ በኢትዮጵያ ያለው ተሽከርካሪ ቁጥር እኮ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ይባላል፡፡ እንዲያው ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ተሽከርካሪዎች አሉ? የተሽከርካሪ ቁጥር በምን ያህል ደረጃ እያደገ ነውስ ይባላል?

አቶ ካሣሁን፡- በአጠቃላይ 708 ሺሕ አካባቢ ተሽከርካሪዎች እንዳሉ ይታመናል፡፡ ከተወሰኑ ክልሎች በበቂ ሁኔታ የተሰበሰበ መረጃ ባይኖርም ቁጥሩ ትንሽ ሊጨምር ይችላል፡፡ ይህንን ካሰብን 750 ሺሕ ያህል ተሽከርካሪዎች አሉ፡፡ እኛ ዘንድ በዳታ ቤዝ ያለው ግን 708 ሺሕ ተሽከርካሪዎች እንዳሉ ነው፡፡ አሁን ያለውን የተሽከርካሪ ቁጥር ከስድስት ዓመት አካባቢ ከነበረው ጋር ሲታይ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል፡፡ በዓመት እስከ 100 ሺሕ ተሽከርካሪዎች እየገቡ ነው፡፡ ኢኮኖሚው እያደገ ሲመጣ በየዓመቱ የሚገባው ተሽከርካሪ ቁጥሩም እየጨመረ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ያህል ተሽከርካሪ ካለ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የምናየው አማራሪ የትራፊክ መጨናነቅ ለምን ይፈጠራል ወደሚለው ጥያቄ ይወስደናል፡፡ በአዲስ አበባ በሚታየው የትራፊክ መጨናነቅ መንገዶቹ ተሽከርካሪዎችን መሸከም ያቃታቸው አስመስሎታል፡፡

አቶ ካሣሁን፡- እውነት ለመናገር በዓለም ላይ ይህንን ያህል ሕዝብ ኖሮዋቸው ትንሽ መኪና ያለን እኛ ነን ማለት ይቻላል፡፡ ብዙ አገሮች ከእኛ የተሻለ ብዙ ቁጥር ያለው ተሽከርካሪ አላቸው፡፡ ያለን መንገድ ደግሞ በርዝመትም በስፋትም ቀላል ሊባል አይችልም፡፡ ትልቁ ነገር በጋራ ሆነን ማስተካከል ያለብን የመንገድ አጠቃቀማችንን ነው፡፡ መንገዶች ይሠራሉ፡፡ ቦሌ ላይ ባለ ሦስት መስመር መንገድ አለ፡፡ ችግሩ ግን ፓርኪንግ ነው፡፡ የፓርኪንግ አጠቃቀማችን ችግር አለው፡፡ መንገድ ላይ መኪና ይቆማል፣ ይደራረባል፡፡ ከዚያ ተሳፋሪ የሚያወርዱ ተሽከርካሪዎች ይቀጥላሉ፡፡ ይህ ችግር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገር ካለ ችግር ይኖራል፡፡ አዲሱ የፍጥነት መንገድ በቀን 20 ሺሕ ተሽከርካሪ እየተስተናገደ ነው፡፡ ነገር ግን አንድም ተሽከርካሪ ሲቆም አይታይም፡፡ መንገዱ ላይ ለመቆም ቢፈቀድ ኖሮ ከዚያ መንገድ የበለጠ የሚጨናነቅ አልነበረም፡፡ ስለዚህ በአዲስ አበባም ያለው ችግር አንዱ ምክንንያት ይህ ሲሆን፣ ሌሎችም ምክንያቶች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ስለአዲስ አበባ መንገድ መጨናነቅና መተረማመስ ካነሳን ብዙ ነገሮችን መጥቀስ እንችላለን፡፡ ችግሩ ሰፍቶ ሕዝቡን እያማረረ ነው፡፡ ችግሩ ግልጽ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት እየሠራን ነው ካላችሁ እንዴት? ችግሩን ለማቃለል የታሰበው ምንድነው?

አቶ ካሣሁን፡- በአዲስ አበባ ያለውን ችግር ለመቀየር የታሰበው የትራፊክ ማኔጅመንቱን ሙሉ በሙሉ በመቀየር ነው፡፡ የፓርኪንግ ፖሊሲያችን ሙሉ ለሙሉ መቀየር አለበት፡፡ መንገድ ፓርኪንግ መሆን የለበትም ተብሎ የፓርኪንግ ሕንፃ ይገነባል፡፡ የሜዳ ፓርኪንጎችም ይገነባሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ሥራዎችን የሚመለከቱ ጥናቶች አሉ፡፡ ችግሩን ለማስቀረት ይህንንና መሰል ሥራዎች ለመሥራት ዝግጅቶች ተጠናቀዋል፡፡ የተጀመሩም ሥራዎች አሉ፡፡ ሥራው እጅግ ሰፊ ነው፡፡ በመብራት መቃለል ካለበት በዚያ መንገድ እንዲሠራ፣ ማሳለጫ የሚያስፈልጋቸውም ከሆነ እሱ ይሠራል፡፡ በአጠቃላይ የትሪፊክ ፍሰቱ እንዳይቆም የተለያዩ ዲዛይኖች እየቀያየርክ የምትሠራው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ዕቅድ ነው፡፡ ሐሳብ ነው፡፡ ይህንን ወደ መሬት ለማውረድ ምን ያህል እየተሠራበት ነው? ማነው የሚያስፈጽመው?

አቶ ካሣሁን፡- ይህንን በባለቤትነት ለመሥራት፣ ይህንን ሥራ ብቻ የሚሠራ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ተቋቁሟል፡፡ ሥራው አሁን ያለውን ችግር መቅረፍና የተመቻቸ የትራፊክ ፍሰት እንዲመጣ ማድረግ ነው፡፡ ሌላ ሥራ የለውም፡፡ እንዴት ተሽከርካሪዎች በአጭር ጊዜ ይጓጓዛሉ የሚለውን ሥራ የሚሠራ ነው፡፡ መጨናነቅ ያለባቸውን እንደ ኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ ያሉትን አደባባዮች እንዴት ለትራፊክ ምቹ ይሁኑ የሚለውን እያየ የሚሠራ ነው፡፡ ከተማውን አንቀው የያዙትን አደባባዮች ችግሮች መፍታት ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ አደባባዮችን ማፍረስ ተጀምሯል፡፡ የኤጀንሲው ሥራ ይኼ ብቻ አይደለም፡፡ የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል ያቋቁማል፡፡ በከተማ ውስጥ በሚተክላቸው ካሜራዎች የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ ይቆጣጠራል፡፡ መጨናነቅ ከተከሰተ ወዲያው መፍትሔ የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ አሠራር በሌላው ዓለም የሚሠራበት ነው፡፡ እኛ ዘንድ ግን የእኛ ዝግጅትና የመኪኖች ቁጥር ተበላለጠ፡፡ በአንዴ ቁጥሩ ለጨመረው ተሽከርካሪ የሚሆን በበቂ ሁኔታ ቀደም ብለን አልተዘጋጀንም ነበር፡፡ አሁን ግን መንግሥት ከፍተኛ በጀት አፍስሶ ወደ ሥራ እየገባ ነው፡፡ ማዕከሉንም ወደ መገንባት ገብቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ይገነባል ስለሚባለው ማዕከል ይንገሩኝ፡፡ ኤጀንሲው በጀት ከየት ያመጣል?

አቶ ካሣሁን፡- ለዚህ ሥራ የሚሆነው ጥናት ሰፊ ነው፡፡ ሥራው ትልቅ ስለሆነ ይህንን ሥራ ለመሥራት የሚፈለገው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ፣ በሌሎች አካላት መደገፍ ስላለበት ጥናቱን ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አቀረብን፡፡ እሱም ለዓለም ባንክ አቅርቦ 300 ሚሊዮን ዶላር ተፈቀደ፡፡ ከዚህ ገንዘብ በፌዴራል ደረጃ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥን ለማዘመን ለሚያስችለው ሥራ 92 ሚሊዮን ዶላር ሲመደብ፣ ቀሪው ለአዲስ አበባ ለታሰበው ሥራ የሚውል ነው፡፡ በፌዴራል ደረጃ የታሰበው ሥራ በአገሪቱ በሙሉ ያለውን የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥና አሠራር በአንድ ማዕከል የሚያገናኝ ነው፡፡ ለአዲስ አበባው የተመደበው ደግሞ የትራፊክ ማኔጅመንትን ከመተግበር በተያያዘ ለመብራት ተከላ፣ ለማሳለጫ ግንባታዎችና ለመሳሰሉ ሥራዎች ድጋፍ የሚደረግ ነው፡፡ የፓርኪንግ ግንባታዎች ይከናወናሉ፡፡ በዚህ ጥናት ውስጥ የአንበሳ አውቶብስን አሠራር ጭምር ይቀይራል፡፡

ሪፖርተር፡- የአንበሳ አውቶብስ አሠራር እንዴት ነው የሚቀየረው?

አቶ ካሣሁን፡- ለምሳሌ የቲኬት አሠራሩ ይቀየራል፡፡ ኤሌክትሮኒክ ቲኬት ይሆናል፡፡ የማኔጅመንት ሲስተሙና አጠቃላይ የአገልግሎት አሰጣጡን ለመቀየር ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግር ይቀረፋል የሚባለው በአውቶብሶች ነው፡፡ ታክሲዎችን ለማስቀረትም ይታሰባል ይባላል፡፡ መንግሥት ወደ አውቶብሶቹ ያተኮረው እንዴት ነው?

አቶ ካሣሁን፡- ልክ ነው፡፡ ከተማ እያደገ ሲመጣ መጠቀም ያለብህ ማስ ትራንስፖርት ነው፡፡ አቅም ቢኖር ባቡርን በመሬት እንጠቀም ነበር፡፡ እስከዚያው ድረስ ቀላል ባቡር እንጠቀማለን፡፡ በአንድ ጊዜ ብዙ ሰው የሚይዝ ትራንስፖርት ይዘህ ካላጓጓዝክ ትንንሽ መኪኖችን የፈለግከውን ያህል ብታስገባ ችግሩን አታቃልልም፡፡ ስለዚህ ትኩረታችን ሙሉ ለሙሉ ከትንንሽ ተሽከርካሪዎች ወጥቶ ወደ ትልልቅ አውቶብሶች መግባት ነው፡፡ አንድ አውቶብስ የሰባትና የስምንት ታክሲዎች ተሳፋሪ ይይዛል፡፡ መፍትሔም ይሆናል፡፡ እንዲህ ማድረጋችን ብዙ ጥቅም አለው፡፡ ስለዚህ ከአውቶብስና ከባቡር ውጪ ሌላ መፍትሔ የለም፡፡ ይህንን ለማስፋት ባለሀብቶች ከቀረጥ ነፃ አውቶብስ ያስገባሉ፡፡ አሁን 500 አውቶብሶች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ እያደረግን ነው፡፡ ታክሲዎችም ወደዚህ መግባት አለባቸው፡፡ ለእነሱ የታሰበ ዕድል ነው፡፡ ተደራጅተው ወደዚህ መግባት አለላቸው ታክሲዎቹ በዚህ መዝለቅ አይችሉም፡፡ ካልሆነ ከከተማ ውጪ ያለውን ሥራ ያግዛሉ፡፡ ማቀባበል ነው፡፡ ለዚህ ሲባል ነው ሸገር የሚባለው አውቶብስ የመጣው፡፡ የግል ባለሀብቱም እንዲገባ እያደረግን ነው፡፡ ከቀረጥ ነፃ ከሚገቡት ሌላ ሸገር 300 አውቶብሶች ይጨምራል፡፡ የአንበሳም ቁጥር ይጨምራል፡፡

ሪፖርተር፡- በነገራችን ላይ ለታክሲ ፈቃድ መስጠት ተከልክሏል?

አቶ ካሣሁን፡- ፈቃድ አልከለከልንም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ፍላጎቱ ስላለ አንከለክልም፡፡ አውቶብስም እኮ ገና ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ሦስትና አራት ሺሕ አውቶብሶች ያስፈልጋሉ እኮ፡፡

ሪፖርተር፡- የታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው፡፡ ቢዝነሱ አዋጭ ባለመሆኑ ነው ይባላል፡፡

አቶ ካሣሁን፡- በቁጥር አልቀነሰም፡፡ በደንብ ላስረዳህ፡፡ ኮድ አንድ ታክሲ ቁጥር ቀንሷል፡፡ ኮድ ሦስት ቁጥር ጨምሯል፡፡ ሽፍት ነው ያደረገው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ለምን ተቀያየረ?

አቶ ካሣሁን፡- ሦስት ቁጥር ከሆነ እንደ ታክሲም ይሠራል፡፡ ከከተማ ውጭ ወጥቶም ስለሚሠራ ኮድ አንድ የነበሩት ወደ ኮድ ሦስት ቀየሩ፡፡ ዛሬ ኮድ ሦስት ታርጋ ይዘው አዲስ አበባ የሚሠሩት ኮድ አንድ የነበሩት ናቸው፡፡ ስለዚህ ከለር ነው የተቀየረው፡፡ ስለዚህ አንድ አንድ ሆኖ ከመሥራት እንደ ልቡ ለመሆን ኮድ ሦስትን ይቀይራል፡፡ አሁን አዲስ አበባ ውስጥ ታክሲ መቀየር አይቻልም፡፡ ግን ታክሲውን ለክልል ገዥ ይሸጠዋል፡፡ ተመልሶ ግን የሚሠራው እዚህ መጥቶ ነው፡፡ ይህንን ለማስተካከል ገና ነን፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን አልያንስ ኩባንያና አዲስ ትራንስፖርት ከቀረጥ ነፃ አውቶብሶች እንዲያስገቡ አድርጋችኋል፡፡ ከዚህ በኋላ ይህ ዕድል አለ?

አቶ ካሣሁን፡- እነዚህ መኪኖች በተበጣጠሰ ሁኔታ ቢገቡ አያዋጡም፡፡ ባንክ ለእነዚህ አያበድርም፡፡ በኩባንያ ደረጃ ከመጡ ግን ያበድራል፡፡ አልያንስ ብድር ያገኘው ኩባንያ ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ኩባንያ እንዲገቡ ነው፡፡ ይህንን ዕድል ለማግኘት 50 አውቶብሶች መግዛት መቻል አለብህ፡፡ ተመሳሳይ ዕድል ለማግኘት አሁን ውጤቱ ታይቶ ድጋሚ ጥያቄው ይቀርባል፡፡ መንግሥትን ማስፈቀድ ይጠይቃል፡፡ መንግሥት ይህንን ገንዘብ የመደበውም ከሌላው ልማት ላይ ቀንሶ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ውጤቱን ዓይተን በድጋሚ ሊጠየቅ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ በትራፊክ መጨናነቅ ተቆላልፋለች፡፡ ተጨንቃለች፡፡ ችግሩ እየሰፋ ነው፡፡ መፍትሔው ያስጨንቃል፡፡ እርስዎ ደግሞ ይፈታል እያሉኝ ነው፡፡ ይህ ከሆነ አዲስ አበባን ሰንጐ ከያዛት መጨናነቅ ለማላቀቅ ምን ያህል ጊዜ ይወስድባችኋል?

አቶ ካሣሁን፡- ጊዜ አይወስድም፡፡ ከተያዘው 2009 ዓ.ም. የዘለለ ጊዜ አይወስድም፡፡ በዚህ ዓመት ይስተካከላል፡፡ ምክንያቱም አደረጃጀቱ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ሁሉ መኪና ተገዝቷል፡፡ ይህንን ሁሉ ሀብት በመንግሥት እያፈሰሰ ለውጥ የማይመጣ ከሆነ ሌላ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ በ2009 ዓ.ም. እነዚህ ችግሮች በሙሉ መስመር መያዝ አለባቸው፡፡ ስለዚህ ይህንን ለማድረግ ከፍተኛ ሩጫ ነው ያለው፡፡ አዲስ አበባ አደረጃጀቱ ተፈጥሮ ባለሙያ ተመድቦ ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ መኪኖቹ እየመጡ ናቸው፡፡ አሁን እነዚህ ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ የተፈቀዱት በትክክል ሥምሪት  ከሰጠሃቸው በቀን 500 ሺሕ ሰው የማጓጓዝ አቅም ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ መንገድ ላይ ተሠልፎ የምታየው 500 ሺሕ ሰው አይሞላም፡፡ በደንብ ከተጠቀምክበት መፍትሔው ይኸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ የትራፊክ መጨናነቅና ያለው የትራንስፖርት እጥረት እየባሰ በመሄዱ ሳቢያ መንግሥት ቢያደርግ ተብሎ ከሚሰጡ አስተያየቶች መካከል አንዱ፣ ለሠራተኞች የሥራ መግቢያ ሰዓት በማሻሻል ተማሪዎች ከሚጓጓዙበት ሰዓት እንዲለይ ማድረግ ነው፡፡ ይህም መፍትሔ ይሆናል ይባላል፡፡ እንዲህ ያለውን ሐሳብ እናንተ እንዴት አገኛችሁት?

አቶ ካሣሁን፡- ትክክል ነው፡፡ ሐሳቡ ነበር፡፡ አንድ ሰሞን በዚሁ ጉዳይ ላይ ጥናት አድርገን ነበር፡፡ ቢያንስ የሠራተኛውና የተማሪው መግቢያ ሰዓት ይለያይ፣ ይቀያየር ለማለት ማየት ያለብን ነገሮች ነበሩ፡፡ ሙከራ አድርገናል፡፡ ትምህርት ቤቶች የት ናቸው ብለን ስንፈትሽ አብዛኛው የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች በመኖሪያ አካባቢዎች ናቸው፡፡ ትራንስፖርት የሚጠቀሙት ደግሞ የግል ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ ምክንያቱም የተሻለ ገቢ ያለው ትምህርት ቤት ስለሚመርጥም ነው፡፡ አብዛኛው የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በመኖሪያ አካባቢዎች ስለሆኑ ተማሪዎቹም ትራንስፖርት የሚፈልጉ አይደለም፡፡ እነዚህ ትራንስፖርት ቢጠቀሙ ኖሮ ችግሩ እጅግ የከፋ ይሆን ነበር፡፡ እንግዲህ በዚህ ዓመት የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ችግርና መጨናነቅ ለማስቀረት ከታሰቡት ውስጥ ‹‹ስኩል ባስ ሲስተምን›› መተግበር ነው፡፡ በሌላው አገር ‹‹ስኩል ባስ›› ራሱን የቻለ ነው፡፡ ከመደበኛው ትራንስፖርት ጋር አይጋፉም፡፡ በከለርም በአገልግሎት አሰጣጥም ይለያል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ሲስተም ልትጀምሩ ነው ማለት ነው? አገልግሎቱን በባለቤትነት የሚያስተዳድረውስ ማነው? በማን ይሠራል? 

አቶ ካሣሁን፡- ይህንን አሠራር የምንተገብረው ከየትምህርት ቤቶቹ ጋር በመነጋገር ነው፡፡ በሌሎች አገሮች የስኩል ባስ አገልግሎት ብቻ የሚሰጡ ኩባንያዎች አሉ፡፡ በአንዳንዶቹ ደግሞ ትምህርት ቤቶቹ ራሳቸው ያዘጋጀሉ፡፡ በፑል ይሠራሉ፡፡ የተለያዩ አሠራሮች አሉ፡፡ ለእኛ አገር የትኛው ነው የሚሻለው? ካለው አቅም አንፃር የትኛው እንደሚሻል ከትምህርት ቤቶቹ ጋር ተነጋግሮ፣ ከትምህርት ቤቶቹ አቅም የሚመነጭ ከሆነ እንዴት ወደ ሥራ እንደሚገባ እናያለን፡፡ ካልሆነ እንደ ፐብሊክ ትራንስፖርት የሚሠራበትን መንገድ መፈለግ ነው፡፡ ፐብሊክ የሠራተኛውን ችግር ፈትቷል፡፡ በጣም መኪና የሚፈልግ ደግሞ ሜትር ታክስ መጥቶለታል፡፡ መደበኛው ተጓዥ ደግሞ ተማሪው ነው፡፡ ለዚህም መፍትሔ ይበጃል፡፡ ስለዚህ ችግሩን ለማቃለል የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ አንዱ ብቻ አይበቃም፡፡ መፍትሔውን ለማምጣት እየተደረገ ባለው ጥናት ሕዝብ ለምንድነው የሚጓጓዘው የሚለውን ጭምር እያየን ነው፡፡ የሚጓጓዘው ገበያ ፍለጋ ከሆነ ገበያውን በአካባቢው መፍጠር አለብህ ማለት ነው፡፡ እንቅስቃሴውን መቀነስ አለብህ፡፡ ሰዎች የሚጓጓዙበትን ምክንያት ካወቅክ ያንን ፍላጎት ማቅረብ አለብህ፡፡ ስለዚህ ያንን ምክንያት ሳታጠና መንገድ በመገንባት ብቻ አትዘልቅም፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ ፍላጎት እየጨመረ ነው የሚሄደው፡፡ ፍላጎቱ ሲጣመር እንቅስቃሴ ይጨመራል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለውን ችግር እግር በእግር እየተከታተልክ መፍታት ነው፡፡ እነዚህን ብዙ የመፍትሔ አማራጮች ለመጠቀም ደግሞ መናበብ ይጠይቃል፡፡  

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ ካሣሁን፡- ለምሳሌ ከከተማ ልማት ሚኒስቴር ጋር መሥራት፡፡ ይህንን ሁሉ ቤት ገንብተህ በርካታ ሺሕ ቤቶች ገንብተህ ጠባብ መንገድ ብትሠራ ችግር መሆኑን አውቀህ ቀድመህ ስትዘጋጅ ልማቱ ደስ ይላል፡፡ በእነዚህ ልማቶች መሀል ገበያ፣ ጤና ጣቢያ፣ መንጃ ፈቃድ ማደሻ፣ የውኃና የኤሌክትሪክ መክፈያ ጣቢያዎች የመሳሰሉት እዚያው ማለቅ አለባቸው፡፡ አሁን ደግሞ መንግሥት የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን እየከለሰ ነው፡፡ እንዲህም በማድረግ ችግሩ ይቀረፋል፡፡ በትክክል አይተን የማገናኘት ክፍተቶች አሉ፡፡ ትራንስፖርተሮች የተሻለ ታሪፍ ወደሚያገኙበት መስመር መሄድም የችግሩ አካል ነው፡፡ አሁን የማኔጅመንቱን ችግር ስትፈታለት ይስተካከላል፡፡ የተወሰኑ ሙከራዎችን አድርገን ውጤቱን በማየታችን ነው፡፡ የፓይለት ሙከራዎች አድርገን አይተናል፡፡ በደንብ ወጥረህ ስትይዝና ቁጥጥር ስታደርግ፣ ታክሲዎቹ እንዳይቆሙ ስታደርግ፣ መንገዶች ላይ እንዳይቆሙ ስትከለክል፣ ስትከታተል ፍሰቱ ይስተካከላል፡፡ እንዲህ እንዲህ ያለውን ነገር ከሠራን እርግጠኛ ነኝ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ሲስተም ይቀየራል፡፡ ለባቡሩም ተጨማሪ ፉርጎ እየተገዛለት ነው፡፡ ሁለተኛ ምዕራፍ ይኖረዋል፡፡ በሁለተኛ ምዕራፍ የባቡር መስመር ግንባታ ቦታው ይመረጣል፡፡ የተለያዩ አማራጮች እየመጡ ነው፡፡ ስለዚህ የትራፊክ ማኔጅመንታችንን ስናስተካክልንና በአግባቡ ስናስተዳድር፣ ተጨማሪ መኪኖችን አስወጥተን በትክክለኛው ቦታ ስናስቀምጥ፣ አሁን የምታያቸው ችግሮች በሙሉ ይቀረፋሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን እየነገሩኝ ካለው ገለጻ ችግሩን ለመቅረፍ ዝግጅቱም ሆነ ተስፋም አለ እያሉኝ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ጥያቄ ልደግም ነው፡፡ አሁን እየተሠራ ባለው ሥራ መፍትሔ ይገኛል?

አቶ ካሣሁን፡- አንተ ከጀሞ ለመምጣት ሰዓታት ወሰደብኝ አልክ፤ ሰሞኑን እንደሰማኸው ለከተማው የትራፊክ መጨናነቅ አንዱ ሰበብ የከተማው አደባባዮች ናቸውና እንዲፈርሱ እየተደረገ ነው፡፡ ከዚያ ደግሞ ተላላፊ መንገድ ይሠራል፡፡ አደባባዩ ፈርሶ በመብራት ሲስተናገዱ ለውጥ ይመጣል፡፡ አደባባዮች ይፍረሱ ብዬም ተናግሬያለሁ፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ሌላው ማስተካከል ያለብን የታክሲ መቆሚያዎችን ነው፡፡ ታክሲዎች መንገድ ላይ ቆመው ነው የሚያሳፍሩት፡፡ ከመንገድ አላቀሃቸው ገባ ብታደርጋቸው በቀላሉ ለውጥ ይመጣል፡፡ በዚህ ሥራ ትንሽ ነገር በመለወጥ ጭምር የምትስተካከላቸው ነገሮችም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በትራፊክ መጨናነቁም ሆነ በትራንስፖርት እጦቱ የተማረረ ሁሉ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ የመፍትሔ ያለህ እያለ ነው፡፡ ይህ አቤቱታ እናንተ ዘንድም ስለመምጣቱ ገልጸዋል፡፡ እርስዎ ደግሞ ግድ የለም መፍትሔው በእጃችን ነው፣ እየሠራንበትም ነው ይላሉ፡፡ ይኼንን ሁሉ እሮሮ የሚያስቆም ነገር ይፈጠራል ብለው እርግጠኛ መሆን ይችላሉ?

አቶ ካሣሁን፡- በእርግጠኝነት፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ሜትር ታክሲዎች ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ነገር ግን ለአገልግሎታቸው የመደባችሁላቸው ታሪፍ ውዝግብ ፈጥሯል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በአጠቃቀሙ ላይ ብዥታ አለ፡፡

አቶ ካሣሁን፡- ሜትር ታክሲ በኢትዮጵያ ሲተገበር የመጀመሪያው ነው፡፡ ቀደም ሲል የነበረ አሠራር አንድ ተገልጋይ ወደ ታክሲው ሄዶ ዋጋ ተደራድሮ ነው የሚጓጓዘው፡፡ መታወቅ ያለበት ትራንስፖርት በድርድር አይሠራም፡፡ የከተማ ትራንስፖርት በድርድር የምታከናውነው ሥርዓት አይደለም፡፡ ልዩ ፍላጎት ካለህ በድርድር ሊሠራ ይችላል፡፡ የተለየ ነገር ከፈለግክ ማለት ነው፡፡ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በመጓጓዝ ሳይሆን፣ መኪናውን ተኮናትረክ በየቦታው እየተዝናናህ እየቆምክ እንደ ግልህ አድርገህ የምትጠቀምበት ከሆነ በዚህ ልትደራደር ትችላለህ፡፡ ነገር ግን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመጓጓዝ ግን ድርድር ብሎ ነገር የለም፡፡ ሥርዓት መኖር አለበት፡፡ ምክንያቱም ያወቀው ሲደራደር ያላወቀው ሳይደራደር በተፈለገው ዋጋ የምትጭን ከሆነ፣ ሰዎች ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ለመጓጓዝ ይቸገራሉ፡፡ ስለዚህ አገልግሎቱ በሌሎች ፍላጎት ላይ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን መኪኖች ለማስመጣት መንግሥት ከፍተኛ ቀረጥ ነው የተወው፡፡ የመኪናውን ዋጋ 165 በመቶ ነው የተወው፡፡ ይህንን ሲያደርግ አዲስ ሥርዓት እንዘረጋለን ከማለት ጭምር ነው፡፡ ሌሎች አገሮች ስትሄድ እጅህን ዘርግተህ ይቆማል፡፡ እንደገባህ ትነካለህ ዋጋ አትደራደርም፣ ዋጋውን አይተህ መክፈል ነው፡፡ ይህንን ያህል ትከፍለኛለህ አትከፍለኝም ብሎ ነገር የለም፡፡ ዋጋው ተቀምጦልሃል እሱን ትከፍላለህ፡፡ እንግዲህ አዲስ አበባም የአፍሪካ መዲና ነች፡፡ ስለዚህ ይህንን ማድረግ ነው፡፡

በነገራችን ላይ ሁሉም የትራንስፖርት አገልግሎት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቁጥጥር የሚደረግበት ነው፡፡ ወደ ጂቡቲም ጭምር ለማጓጓዣ የሚከፈለው ዋጋ ቁጥጥር አለበት፡፡ ምክንያቱም ትራንስፖርት ዋጋ ተወደደ ማለት ኢኮኖሚው ላይ ጫና ፈጠርክ ማለት ነው፡፡ ትራንስፖርት ማትረፍ አለበት፡፡ ኢኮኖሚው ካላደገ ደግሞ እነሱም አይጠቀሙም፡፡ ትራንስፖርት መጠቀም የሚችለው በኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ጊዜ ትልቅ ዋጋ ተቀብለህ ወይም ተጠቅመህ ልቁም ካልክ፣ ዋጋውን አስወድደህ ከሠራህ ኢኮኖሚው ይቆማል፡፡ አንተም ትቆማለህ፡፡ ምክንያቱም ትራንስፖርት በእንቅስቃሴ ላይ የተመሠረተ ሕይወት ነው እንጂ በመቀመጥ ላይ የመሠረተ አይደለም፡፡ ይህ የትራንስፖርት ባህሪ ነው፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ ውድ ነገር መጥላት ነው ያለበት፡፡ ውድ ነገር አይጠቅመውም፡፡ 

ሪፖርተር፡- ወደ ሜትር ታክሲዎቹ ታሪፍ ልመልስዎት፡፡ አሁን የተፈጠረው ያለመግባባት መጨረሻው ምንድነው?

አቶ ካሣሁን፡- ሜትር ታክሲዎቹ ከመጡ በኋላ ባለን አሠራር መሠረት ታሪፍ አወጣን፡፡ አገልግሎቱ አዲስ ስለሆነ በተቻለ መጠን እንዲበረታቱ ስለፈለግን ብዙ ነገሮችን ትተናል፡፡ ለምሳሌ መኪና ማሳጠብ አለብን ተብሎ ለመኪና ማሳጠቢያ 11 ሺሕ ብር ይያዝልን ብለው አድርገናል፡፡ ለመኪና ማሳደሪያ ስድስት ሺሕ ብር ወጪ ይያዝልን ተባለ እሺ አልን፡፡ ግን ባለቤቱ ራሱ መኪናውን ቤቱ ቢያሳድር ምን ነበረበት? እንዲህ ያሉት ነገሮች ሁሉ ተይዘው ነው ታሪፍ ያወጣነው፡፡ በኪሎ ሜትር አሥር ብር ብዙ ነው፡፡ ግን ይበረታቱ ብለን ነው ያደረግነው፡፡ በሚኒባስ ብትሄድ 4 ብር ከ50 የምትከፍለውን 10 ኪሎ ሜትር እነርሱ ከ100 እስከ 120 ብር እንዲያገኙ ነው ያደረግነው፡፡ ይህ እኮ እንደኔ ያለ የመንግሥት ሠራተኛ የሚችለው አይደለም፡፡ እንዲያውም የመደብነው ታሪፍ ውድ ነው፡፡ አንዳንዶች አነሰ ብለው የሚከራከሩት አንሶዋቸው አይደለም፡፡ የአመለካከት ችግር ነው፡፡ በእኔ ግምት አንዳንዶቹ ከዚህ በፊት ታክሲውን ይዘው ይቆማሉ፣ ድንገት አንተ ቸግሮህ ትሄዳለህ፡፡ ለአጭር ጉዞ መቶ ብር ይልሃል፡፡ አንተ ደግሞ የታመመ ይዘሃልና አማራጭ ስለሌለህ ትከፍላለህ፡፡ ስለዚህ አሁንም በዚያው ሥሌት ለመሄድ ነው የታሰበው፡፡ ይኼ አይሠራም፡፡ ማነው የሚጠቀማቸው ለምሳሌ ከዚህ (ስቴዲየም) 4.5 ኪሎ ሜትር ነው፡፡ ወደ ቦሌ ለመሄድ መነሻ 10 ብር አለው፡፡ ቦሌ ደርሶ ለመምጣት 100 ብር ትከፍላለህ፡፡ መደበኛው ግን አምስት ብር ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- እነሱ ግን ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ ምላሹ ምንድነው?

አቶ ካሣሁን፡- ማንም ሰው እነዚህን ታክሲዎች መጠቀም ይችላል፡፡ እነሱ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ በባለሥልጣኑ በኩል ቀርጥ ነው፡፡ ለሜትር ታክሲዎች የተመደበላቸው ታሪፍ ሲበዛ ነው፡፡ ሥራውን ለማለማመድ በቂ ነው፡፡ ምናልባት ሥራው እስኪለማመድ ድረስ እንዳይጐዱ የሚደግፍ ነው፡፡ ሥራው ከተለመደ በየመንገዱ ያለውን ሰው በፍጥነት እያጓጓዙ ብዙ ነው የሚሠሩት፡፡ በነገራችን ላይ በቀን የያዝንላቸው 120 ኪሎ ሜትር ነው፡፡ በሌላው ዓለም አንድ ሜትር ታክሲ ከ300 እስከ 400 ኪሎ ሜትር በቀን ይሠራል፡፡ እነሱ ግን በቀን አንድ ወይም ሁለት ሰው ማጓጓዝ ስለለመዱ ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ አንሄድም ነው ያሉት፡፡ እኛ የሚቀመጥ ትራንስፖርት አይደለም የምንፈልገው፡፡ አንተ ፈልገኸው የምታገኘው ሳይሆን እሱ ፈልጐህ የሚያገኝህ መሆን አለበት፡፡ ይኼ ካልሆነ ትራንስፖርት አይደለም፡፡ አንድ ቦታ ቆሞ የሚጠብቅ ከሆነ ሱቅ ነው ማለት ነው፡፡ ትራንስፖርት የት ጋ ነው ሰው ያለው ብሎ ይፈልጋል፡፡ በቀን 300 ኪሎ ሜትር ከሠራ በገንዘብ ስትመታው ብዙ ነው፡፡ በዚህ ታሪፍ የሚከፍል ሰው ደግሞ አለ፡፡ ይህንን ገበያ ሠርታችሁ አግኙ ነው ያልነው፡፡ ወዲህ እንዲገቡ የተወሰነ ፍትጊያ ቢኖርም መተማመናችን አይቀርም፡፡ እነርሱም በኋላ እኛን ያመሰግናሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በሜትር ታክሲ አገልግሎት ሌላው ብዥታ ደግሞ አንድ ሰው ወይም አራት ሰው ሲጭኑ አራቱም ተሳፋሪ በኪሎ ሜትር ለየብቻው ይከፍላሉ? ወይስ አንዱ ነው የሚለው ነገር አልጠራም፡፡

አቶ ካሣሁን፡- አንድ ሰው ብትሆንም ልጆችህን ይዘህ ብትሳፈርም የምትከፍለው አንድ ነው፡፡ ለአራቱም ለብቻ ለብቻ ብሎ ነገር የለም፡፡ አንተ እኮ ነው ኮንትራቱን የያዝከው፡፡ ከፈለግክ አንተ ሌላ ሰው ልትጭን ትችላለህ፡፡ ይኼ በሌላ አገርም ይሠራበታል፡፡ ነገር ግን ፈቅደህ ከገባህ በኋላ ሼር ማድረግ አትችልም፡፡

ሪፖርተር፡- በትራንስፖርት አገልግሎቱ ትልቅ በሽታ ሆኖ የዘለቀው የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ነው፡፡ ምንድነው ችግሩ? መፍትሔውስ?

አቶ ካሣሁን፡- አዎ በሽታ ነው፡፡ እውነት ለመናገር በሽታው ከእኔ ጀምሮ ውስጣችን ያለ መጥፎ አስተሳሰብ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቢያብራሩልኝ?

አቶ ካሣሁን፡- ምን ማለት መሰለህ እኔ ይህንን ስናገር በድፍረት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያላት የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሕግ በእውነት ከሌሎች አገሮች ሁሉ የተሻለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በምን? መረጃውስ?

አቶ ካሣሁን፡- ለምሳሌ በእኛ አገር መንጃ ፈቃድ ሲሰጥ በአንድ ጊዜ የጭነት መኪና መንጃ ፈቃድ ይወሰዳል፡፡ ግን ዱባይም ሄድክ አሜሪካ አሠራሩ ይኼ ነው፡፡ ግን ሕጉ አንድ ቢሆንም መንጃ ፈቃዱ ቤቱ ቢመጣለት ደስ የሚለው ሰው አሰ፡፡ ይኼ ነው ገዳይ አስተሳሰብ፡፡ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ስላለ ወደ ትምህርት ቤት ሄዶ ለመማር አይፈለግም፡፡ የትምህርት ሕግ አወጣን፡፡ ትምህርት ቤቶቹ ገንዘብ ከከፈሉዋቸው (ሁሉም አይደሉም) ተከታትለው ማስተማር ሲገባቸው አያደርጉም፡፡ ስለዚህ ሠልጣኙም መማር አይፈልግም፡፡ ትምህርት ቤቶቹም የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት አለባቸው፡፡ በዚህ ጦርነት መሀል ነው ችግር ውስጥ የገባነው፡፡ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን መንጃ ፈቃድ አይሰጥም፡፡ ክልሎች ነው የሚሰጡት፡፡ ሄደን እንቆጣጠራለን፡፡ ባለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት ሦስት አራት ጊዜ ነው ሕጉን የቀየርነው፡፡ አሁንም ቢሆን ቤቱ ቁጭ ብሎ መንጃ ፈቃድ የሚወስድ እንዳለ እሰማለሁ፡፡ ግማሹ የውሸት ወረቀት ይዞ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ሐሰተኛ (ፎርጅድ) ማለት ነው?

አቶ ካሣሁን፡- አዎ፡፡ በኋላ ስታጣራ ፋይል የሌላቸው ሆነው ይገኛሉ፡፡ ወደ 33 በመቶ ሾፌሮች ፋይል የሌላቸው ናቸው፡፡ ይህንን ያጠናነው በሁለት ሙከራዎች ነው፡፡ አንዱ ህዳሴ ግድብ ላይ ሾፌር ለመቅጠር ተፈለገ፡፡ የ900 የተወዳዳሪ ሾፌሮች መንጃ ፈቃድ እንድናጣራ ከተላከልን፡፡ ከ300 በላይ የሚሆኑት መንጃ ፈቃዶች ፋይል የላቸውም፡፡ ሰዎቹ ጠፉ፣ አድራሻ የላቸውም፡፡ ፋይል ስለሌላቸው እንዴት እናግኛቸው? ወደኋላ ሄደን እንዳናይ የለም፡፡ ፋይላቸው መርካቶ ነው ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያሉትን ነገሮች በመያዝ ነው የትራፊክ ዳታ ቤዝ ያደራጀነው፡፡ ይህ ሲሆን የምትፈልገውን ታገኛለህ፡፡

ሪፖርተር፡- ከመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር ያለው ችግር ከዚህም በላይ ነው፡፡ ዋናው ግን መፍትሔ ነው፡፡ በቀጣይ የታሰበው ምንድነው?

አቶ ካሣሁን፡- ሕጉን እንደገና መቀየር ነው፡፡ የትምህርት ሥርዓቱን ለመቀየር ሕጉን አሻሽለናል፡፡ ረቂቁ አልቆ ለመንግሥት አቅርበናል፡፡ በዚህ የትምህርት ደረጃውን፣ የትምህርት አሰጣጡንና ሌሎችንም ቀይረናል፡፡ ነገር ግን እውነት ለመናገር ይህ ሁሉ ቢደረግም ጭንቅላታችንን፣ አመለካከታችን ካልቀየርነው አሁንም ችግር ነው፡፡ ሌላ አገር መንጃ ፈቃድ እንዲሁ አይሰጥም፡፡ ዛሬ እኮ መንጃ ፈቃድ ቤቶ መጥቶልኛል ብሎ እንደ ጀግና ለቅሶ ቤት ይነገራል፡፡ ይህ አመለካከት መቅረት አለበት፡፡ እየገደሉን ያሉት እነዚህ ናቸው፡፡ ወገኖቻችንን እየገደለ የሚያልፈው እንዲህ ያለው ነው፡፡ ይህንን ድርጊት ሁሉም መፀየፍ አለበት፡፡ ሌላው ትልቁ ችግር መቀየር ያለበት ነገር ሾፌርነት አነስተኛ ሙያ ተደርጐ የመወሰዱ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን በየትኛውም ዓለም ይህ አመለካከት የለም፡፡ እንደ አገር የሾፌርን ያህል ኃላፊነት የሚወስድ የለም፡፡ ከፍተኛ ግምት ያለውን ሀብት ከአገር ወደ ውጭ፣ ከውጭ ወደ አገር የሚያጓጉዘው ሾፌር ነው፡፡ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ይንቀሳቀሳል፡፡ ማኅበራዊ ኃላፊነቱ ከፍተኛ ነው፡፡ እንደ ሾፌር ትልቅ ሙያ የለም፡፡ ስለዚህ ሰዎች ለሾፌር የሚሰጡት ግምት አነስተኛ በመሆኑ፣ እሱም ራሱን ዝቅ ስለሚያደርግ የሥነ ምግባር መጓደል ይመጣል፡፡ እልኸኛ ይሆናል፡፡

ከአንድ የትልቅ መሥሪያ ቤት ኃላፊ በላይ ግን ሾፌር ትልቅ ሥልጣን አለው፡፡ ኢኮኖሚን ከማሳለጥና የዜጎችን ደኅንነት ከመጠበቅ አኳያ ብዙ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሾፌር የተከበረ ሙያ ነው፡፡ የተከበረ ሙያ ደግሞ በዚያው ልክ የተከበረ ትምህርት ሊኖረው ይገባል፡፡ ሾፌሩም በዚያው ልክ ራሱን ማስቀመጥ አለበት፡፡ ይህ ጉድለት አለብን፡፡ ሕጉ አለን፡፡ ሥራ ከጠፋ በቃ መንጃ ፈቃድ አውጣ ማለትና አሳንሶ የማየት ነገር መቅረት አለበት፡፡ በዚህ ረገድ ያለውን ክፍተት ለመቅረፍ የተለያዩ አማራጮችን እንጠቀማለን፡፡ ሌላው ቀርቶ ትምህርቱ ከሥር እንዲጀመር የትምህርት ካሪኩለሙ ላይ ለማስገባት እየታገልን ነው፡፡ መንጃ ፈቃዳችን ግን በየትኛውም አገር ይሠራል፡፡ ትልቅ ሙያ ነው፡፡ ዋናው ነገር አመለካከትን መቀየር ነው፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...