Sunday, January 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልፈር ያልያዘው የኅትመት ዘርፍ

ፈር ያልያዘው የኅትመት ዘርፍ

ቀን:

ፍላጎት መለስ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ከወንድ ጓደኛዋ ጋር እየሄደች ነበር፡፡ ሁለት ወጣት ሴቶች እየፈሩ እየቸሩ ቀረቧቸው፡፡ ፍላጎትና ጓደኛዋ ቆም ብለው ወጣቶቹ ምን እንደሚፈልጉ ጠየቋቸው፡፡ ወጣቶቹ ጓደኛቸው የግጥም መጽሐፍ እንዳሳተመችና እነሱም በየአካባቢው እየተዘዋወሩ እየሸጡላት እንደሆነ ነገሯቸው፡፡ እነ ፍላጎትም ጸሐፍቷን ለማበረታታት መጽሐፉን በ30 ብር ገዙና በአቅራቢያቸው ያለ ካፌ አረፍ አሉ፡፡ የግጥሙን መጽሐፍም መገላለጽ ጀመሩ፡፡

ግጥሞቹ የተጻፉት በትልልቅ ፎንት ከመሆኑም በላይ ጽሑፉ ወጣ ገባ ነው፡፡  በይዘት ደረጃም ጥሩ አልነበሩም፡፡ እንደዚህ ዓይነት መጽሐፍ ያሳተመና ያተመ ድርጅቶች ማን ናቸው? ብለው መጽሐፉን ቢያገላብጡም የአንዳች ድርጅት ሥም አልተጻፈም፡፡ በመጽሐፉ ጀርባ የጸሐፍቷ ፎቶና አስተያየት መስጫ ስልክ ቁጥር ብቻ ሰፍሯል፡፡

‹‹መጽሐፉ ሙሉ በሙሉ አርትኦት አልተደረገለትም፡፡ ወጣቷ በዘፈቀደ ቤቷ ፕሪንት አድርጋ የጠረዘችው ይመስላል፡፡ የግጥሞቹ ይዘትና የተጻፈበት መንገድም ለኅትመት የሚያበቃው አልነበረም፡፡ ይሔ የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍንና አንባቢያንም መናቅ ይመስላል፤›› ትላለች ፍላጎት፡፡

ከላይ የተጠቀሰው በህትመቱ ዘርፍ ካሉ አያሌ ችግሮች መካከል አንዱ ነው፡፡ መጻሕፍት ወይም ሌሎችም የኅትመት ውጤቶች በዝቅተኛ የጥራት ደረጃ ታትመው ገበያ ላይ መመልከት አዲስ አይደለም፡፡ የመጻሕፍት ኅትመት እንደ ምሳሌ ቢወሰድ፣ በርካቶቹ የአታሚና አሳታሚያቸው ማንነት ሳይገለጽ ይሰራጫሉ፡፡ የመጻሕፍት ሽፋን፣ የወረቀት ጥራት፣ የቀለም አጠቃቀምና ጥረዛ ችግር ከሚስተዋልባቸው ጥቂቱ ናቸው፡፡ በይዘትም ይሁን በቅርጽ አርትኦት ያልተደረገላቸው መጻሕፍት ለአንባብያን ይቀርባሉ፡፡ በሌላ በኩል መጻሕፍቱ ጥሩ ቢሆኑም እንኳን፣ አከፋፋዮችና ሻጮች ደራስያን ለመጽሐፋቸው ከተመኑት ዋጋ በላይ ይጠይቃሉ፡፡ በደራስያን የተሰጠውን ዋጋ በመፋቅና በትክክለኛው ዋጋ ላይ ገንዘብ ጨምሮ በመጻፍ ያልተገባ ጥቅም ያገኛሉ፡፡

እነዚህ የኅትመት ውጤቶች ገበያ ከዋሉ በኃላ ደራስያን እንዲሁም አንባቢዎች የሚገጥሟቸው መሰናክሎች ናቸው፡፡ በአብዛኛው ቅሬታው የሚቀርበው በአሳታሚዎችና አታሚዎች ላይ ቢሆንም፣ አሳታሚዎችና አታሚዎችም በራሳቸው ረገድ ብዙ ውጣ ውረዶች እንዳሉባቸው ይናገራሉ፡፡ የቅድመና ድህረ ህትመት ችግሮች ለሁለቱም ወገኖች ፈታኝ እየሆኑ መምጣታቸውም ግልጽ ነው፡፡

አንባቢዎች ከሚሰነዝሯቸው ጥያቄዎች ቢጀመር፣ ብዙዎች በህትመት ውጤቶች ልዩ ልዩ ቅሬታ ያሰማሉ፡፡ አንድ መጽሐፍ ውስጥ በርካታ የፊደላት፣ የቃላት እንዲሁም የሰዋሰው ስህተት ይስተዋላል፡፡ የተደገሙና የታጠፉ ገጾች፣ ቀለም የበዛባቸው ወይም የደበዘዙ ጽሁፎች የተለመዱ ናቸው፡፡ እነዚህና ሌሎችም ችግሮች ንባብ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያደረጉ መሆኑን የሚገልጸው አማኑኤል ፍስሀ ነው፡፡ በየጊዜው አዳዲስ መጻሕፍትን የመግዛት ልማድ ያለው ሲሆን፣ የኅትመት ዘርፍ ፈር እንዳልያዘ ይናገራል፡፡

‹‹የመጻሕፍት ዋጋ የማይቀመስ ከሆነበት ምክንያት አንዱ ትክክለኛውን ዋጋ ፍቀው ገንዘብ ጨምረው የሚጽፉ ነጋዴዎች ስላሉ ነው፡፡ ጥራታቸውን የጠበቁ ስላልሆኑም ለንባብም አይጋብዙም፤›› ይላል፡፡ አንዳንድ መጻሕፍት ከተለያዩ ድረ ገጾች ተቀነጫጭበው የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ‹‹የእውነት ታሪክ›› በሚል ሽፋን የተጻፉ ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ፈጠራ የሆኑ መጻሕፍት ገጥመውታል፡፡ የታሪክ ቅደም ተከተላቸው የተዛባ የታሪክ መጻሕፍት እንዳሉም ይጠቅሳል፡፡

‹‹አብዛኞቹ ችግሮች የሚፈጠሩት አሳታሚዎች የደራሲያንን ሥራ ለሚገመግሙ ባለሙያዎች አሳይተው፣ ጽሑፉ ታርሞ ስለማይወጣ ነው፡፡ ኅትመቱ ሲካሄድም ጥራቱን ስለመጠበቁ የሚከታተል ባለሙያ ያስፈልጋል፤›› ይላል አማኑኤል፡፡ በእሱ እምነት፣ ዘርፉ በሕገ ወጥ አታሚዎችና አሳታሚዎች በመሞላቱ፣ ያለ ደራስያን ዕውቅናና ፈቃድ ገበያ ላይ የሚውሉ መጻሕፍት ብዙ ናቸው፡፡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ደራስያን ሥራዎች ያለ ጸሐፍቱ ቤተሰቦች ፈቃድ በብዙ ሺሕ ኮፒ ታትመው ይሰራጫሉ፡፡ አሳታሚውና አታሚው አካል ስለማይታወቅም ለሕግ ሲቀርቡ አይታይም፡፡

‹‹የሰዎች ሀሳብ ሲዘረፍ ጠያቂ በሌለበት ሁኔታ የመጻሕፍት ኅትመት ጥራት ላይ መነጋገር ይከብዳል፡፡ በሕገ ወጥ መንገድ የሚያሳትሙ ግለሰቦች ለወረቀትና የመጻሕፍት ሽፋን ጥራት ይጨነቃሉ ማለት አይቻልም፤›› ሲል ይገልጻል፡፡ ደራስያን በሥራዎቻቸው የሚገባቸውን ጥቅም ካላገኙ ለቀጣይ ሥራዎቻቸው ህትመት ተፅዕኖ ያድርባቸዋል፡፡ ደራስያን የሚያሳትሟቸው መጻሕፍት ሲቀንሱ አንባቢያን እንዲሁም ሥነ ፅሁፍ ይጎዳል ይላል፡፡

በህትመት ዘርፍ ከጥሬ ዕቃ አቅርቦት ጀምሮ በተለያየ ደረጃ የተሰማሩ ባለሙያዎች ብዙ ናቸው፡፡ ዘርፉ በአንድ ደረጃ መሰናክል ሲገጥመው በሌላው ደረጃ ማጥላቱም አይቀርም፡፡ የኅትመት ዘርፉ መፈተን ማንኛውም ዓይነት ኅትመት በሚፈልጉ ግለሰቦችና ተቋሞች እንቅፋት ይሆናል፡፡ በዘርፉ ከፍተኛ ችግር ከሚገጥማቸው መካከል ደራስያን ይገኙበታል፡፡ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ሥራ አስፈጻሚና ደራሲ ይታገሱ ጌትነት፣ ‹‹ የኢትዮጵያ ኅትመት ቀደሞ ከነበረው የጥራት ደረጃው እያሽቆለቆለ ነው፤›› ይላል፡፡

ከጥቂት አሠርታት በፊት የኢትዮጵያ ኅትመት ደረጃ ከሌሎች አገሮች ጋር የሚወዳደር ቢሆንም፣ አሁን ግን ዓለም ካለበት በእጅጉ ርቆ ይገኛል፡፡ ዓለም ካለበት ዲጂታል ኅትመት አንፃር የኢትዮጵያ ኅትመት ብዙ እንደሚቀረው ደራሲው ይናገራል፡፡ ማተሚያ ቤቶች ቀድሞ ከነበረው አሠራር ወጥተው ዘመነኛ ኅትመትን ለመቀላቀል ዝግጁ አይደሉም፡፡ እንደ ምሳሌ የሚጠቅሰው፣ የወረቀት መጠንን ነው፡፡ ‹‹አንድ ደራሲ በሚፈልገው የወረቀት መጠን ሳይሆን ማተሚያ ቤቱ አንዴ ባወጣው ልኬት ብቻ ይሰራሉ፤›› ይላል፡፡

በብቁ ባለሙያዎች እጥረት ሳቢያ የፊደል ግድፈትና የሌይአውት (የገጽ ቅንብር) ብልሽት በየጊዜው ያጋጥማል፡፡ ከሙያዊ ሥነ ምግባር ውጪ በሆኑ አካሄዶች ደራስያን ይጉላላሉ፡፡ አንድ ደራሲ ከማተሚያ ቤት ጋር ከተስማማበት ቁጥር በላይ የሆኑ መጻሕፍት ታትመው፣ ያለአግባብ ማተሚያ ቤቶች ተጠቃሚ የሆኑበት አጋጣሚ አለ፡፡ በርካታ መጻሕፍትን የማተም አቅም ያላቸው ማተሚያ ቤቶች ለህትመት የሚጠይቁት ገንዘብ ብዙ ነው፡፡ ‹‹ ዘርፉ ጥቂቶች በበላይነት የያዙት ነው፡፡ ማተሚያ ቤቶች አንዳቸው ከሌላቸው የተሻለ ሥራ ከመስራት ይልቅ እርስ በርስ ተመካክረው በአድማ ውድ ዋጋ ተምነው ደራስያንን አማራጭ ያሳጣሉ፤›› ይላል፡፡

አሳታሚ ነን በሚል ከሚንቀሳቀሱት ተቋሞች አብዛኞቹ ዘርፉ የሚያስፈልገው ባለሙያ የላቸውም፡፡ ከኅትመት በፊትም ይሁን በኃላ የኅትመት ውጤቶችን የመከታተል ነገርም የለም፡፡ ይታገሱ እንደሚለው፣ የጽሑፍ ውጤቶች ለማኅበረሰቡ ያላቸውን ጠቀሜታ ከግምት በማስገባት ከሚሰሩ ተቋሞች ይልቅ ያላግባብ ለመክበር የሚሽቀዳደሙት ቁጥር ያመዝናል፡፡

የመጻሕፍት ሻጮችና አከፋፋዮች አሳታሚ ነን በሚል ከደራስያን በአነስተኛ ዋጋ የመጽሐፍ ረቂቅ ጽሑፍ ገዝተው በውድ በመሸጥ ያለ አግባብ ትርፋማ ይሆናሉ፡፡ ‹‹ፈቃድ ሳይኖራቸው የደራስያንን ሥራዎች በፈለጉበት ጊዜ አሳትመው ያከፋፍላሉ፡፡ ይህ ተስፋ አስቆራጭና ዘርፉን የሚያቀጭጭም ነው፤›› ሲል ይናገራል፡፡ ደራሲያን ማግኘት የሚገባቸው ክፍያ የሚዘገይበትን አጋጣሚ ለመቁጠር ያዳግታል፡፡ ከስምምነታቸው ያነሰ ገንዘብ ሊደርሳቸውም ይችላልም ይላል፡፡

በትምህርት፣ በልብ ወለድ አልያም በሌላ ዘርፍ ላይ ብቻ አተኩረው መስራት የሚፈልጉ ተቋሞች በየዘርፋቸው የተዋጣለት ሥራ መስራት አለባቸው፡፡ ለዚህ ሲባልም በየዘርፉ እጃቸውን ከማስገባት ይልቅ ያላቸውን አቅም ተመርኩዘው በአንዱ ቢያተኩሩ መልካም ነው፡፡

ደራሲው እንደሚለው፣ ዘርፉን ለማስተካከል የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የግድ ነው፡፡ የመጻሕፍት ፖሊሲ ወጥቶ ወደ ዘርፉ የሚገቡ ተቋሞች ከባለሙያና ከግብዓት አንጻር ምን መልክ መያዝ እንዳለባቸው መደንገግ አለበት፡፡ ዘርፉ በሁለት እግሩ እስኪቆም ድረስም መንግሥት ለተቋማት ማነረታቻ መስጠት እንዳለበት ያምናል፡፡

በአገራዊ ሕግና ደንብ አስፈላጊነት የአስቴር ነጋ አሳታሚና የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ዘነበ ደነቀም ይስማማሉ፡፡ ‹‹እንደ አገር ዘርፉ ሕግ ያስፈልገዋል፡፡ ሕጋዊ አሳታሚ፣ አታሚና ሻጮች በሕገወጦች ሳቢያ ከገበያ ውጪ እየሆኑ ስለሆነ አፋጣኝ መፍትሔ ያሻል፤›› ይላሉ፡፡

የኅትመት ግብዓቶች እንደ ልብ አለመገኘታቸውም ከችግሮቹ ይጠቀሳል፡፡ ‹‹በዓለም ገበያ የኅትመት ግብዓቶች ዋጋ ባይጨምርም በአገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ዋጋው እየናረ ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ መጻሕፍት ከኅብረተሰቡ የመግዛት አቅም በላይ እሆኑ ነው፤›› ሲሉ አቶ ዘነበ ያብራራሉ፡፡

በግብዓትና ባለሙያ ውስንነት ሳቢያ ጋዜጣ፣ መጽሐፍና ሌሎችም ህትመቶች ያለ ጥራት ለገበያ ይቀርባሉ፡፡ መጻሕፍት የታተሙበት ቦታና ዓመተ ምሕረት መጻፍ በማይገባው ቦታ ይሰፍራል፡፡ ‹‹መጽሐፍ ላይ መካተት ያለባቸው ቀርተው መጻፍ የማይገባቸው መረጃዎች ይቀመጣሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ኅትመት መሥፈርት የሌሉ ነገሮች በአገራችን ይታያሉ፡፡ ቀጣዩ ትውልድ ይህን የተሳሳተ አካሄድ እንዳይወርስ አሠራሩ መስተካከል አለበት፤›› ይላሉ፡፡

ኅብረተሰቡ ስለ ዘርፉ ግንዛቤ እንዲያገኝ የሕጋዊ አካሄድ ሊኖር ይገባል፡፡ በሕጋዊ መንገድ የሚዘጋጁ የኅትመት ውጤቶች ተደራሽነት እንዲሠፋም ደረጃቸውን የጠበቁ መጻሕፍት ማከፋፋያዎችና ቤተ መጻሕፍት ያስፈልጋሉ፡፡ በዘርፉ የተንሰራፋው ስርቆትና ከሙያዊ ሥነ ምግባር ውጪ የሆነ አሠራር በአግባቡ የሚሠሩ ተቋሞችን እያጠፋ በመሆኑ በአፋጣኝ ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበትም ይጠቁማሉ፡፡

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤትና የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ፕሬዘዳንት አቶ ተካ አባዲ፣ ከህትመት ጥራት ማነስና የኅትመት ውጤቶች ማስረከቢያ ጊዜ መዘግየት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ቅሬታዎች አግባብነት እንዳላቸውና ማተሚያ ቤቶች ካሉባቸው ችግሮች የመነጩ እንደሆኑ ይገለጻሉ፡፡ በዘርፉ ያሉ ተቋሞች በዋነኝነት የሚፈተኑት በተደራራቢ ታክስ ነው ይላሉ፡፡ ምንም እንኳን መንግሥት መጻሕፍት ላይ የነበረውን 15 በመቶ ቫት ቢያነሳም፣ በእያንዳንዱ ግብአት ያለው ቫት ሲደማመር ወጪያቸው ቀላል አይደለም፡፡

‹‹ለዘርፉ ማሽቆልቆል ተጠያቂው መንግሥት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች መካከል በኅትመት ዘርፍ የሚያሰለጥን የለም፤›› ይላሉ፡፡ የሙያተኞች ውስንነት ዘመን አመጣሽ መሳሪያዎችን እንዳይጠቀሙ አድርጓል፡፡ ለችግሩ እንደ ጊዜያዊ መፍትሔ ሊታዩ የሚችሉት በአርቲስቲክና ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤቶች ያሉት ማሰልጠኛዎች ቢሆኑም፣ በተዋቀረ መልኩ የኅትመት ስልጠና የሚሰጥ ተቋም ያስፈልጋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ በብርሃና ሰላም ማተሚያ ቤት በመጀመሪያ ዲግሪ የሚያሰለጥን ተቋም ለማቋቋም የስርዓተ ትምህርት ጥናት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ አቶ ተካ ጠቁመዋል፡፡ የአፍሪካ ፕሪንቲንግ ፌዴሬሽን ለማቋቋም የተጀመረው እንቅስቃሴ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል ልምድ ለመለዋወጥ መልካም መንገድ ይፈጥራል ብለውም ያምናሉ፡፡ እስካሁን ኬንያ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ ፌደሬሽኑን ለመቀላቀል ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡

አቶ ተካ እንደሚሉት፣ ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ለተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ከጥያቄዎቻቸው አንዱና ዋነኛው ለዘርፉ ደረጃ ይውጣለት የሚለው ነው፡፡ ‹‹የህትመት ዘርፍ ደረጃ ስሌለው ብቃቱ ያላቸውም የሌላቸውም በዘፈቀደ ዘርፉን ይቀላቀላሉ፡፡ ዘርፉን የምናውቀው ባለሙያዎች ለደረጃ ምደባ የሚሆን መስፈርት ማዘጋጀት እንዳለብን በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ተገልጾልናል፡፡ በቅርቡ በባለሙያ አስጠንተን መስፈርታችን አዘጋጅተን እናቀርባለን፤›› ሲሉም ይናገራሉ፡፡

ሌላው የኅትመት ኢንዱስትሪ ፓርክ ጉዳይ ሲሆን፣ በህትመት ዘርፍ ያሉ ተቋሞች የተወሰነ ቦታ ተሰጥቷቸው ፓርክ እንዲሰሩ መጠየቃቸውን ይገልጻሉ፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባት ከተቻለ ከህትመት ጋር ተያይዘው የሚነሱ የከባቢ አየር ብክለት ጥያቄዎች ምላሽ ከማግኘታቸው ባሻገር፣ ተቋሞች በሰው ኃይል አቅርቦት እርስ በእርስ ይደጋገፋሉ፡፡

በተያያዥ የአገር ውስጥ ሥራዎች በውጪ ተቋሞች ከሚታተሙ እዚህ ባሉ ተቋሞች እንዲከናወኑ ማድረግን ፕሬዘዳንቱ ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹መንግሥት ለኅትመት ዘርፉ ድጋፍ እያደገ አይደለም፡፡ ትልልቅ በጀት ያላቸው ኅትመቶች ለውጪ ድርጅት እየተሰጡም አገሪቷ የውጪ ምንዛሬ እያጣች ነው፡፡ እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው በቅርቡ 149 ሚሊዮን ዶላር የወጣበት የትምህርት ሚኒስቴር የመማሪያ መጻሕፍት ኅትመት ለውጪ ድርጅቶች መሰጠቱ ነው፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ በኅትመት ዘርፉ መንግሥት የሚያወጣቸው ጨረታዎች የአገር ውስጥ ተቋሞችን ለውድድር በሚያበቃ መልኩ መቀረጽ  እንዳለባቸውም ያክላሉ፡፡

የኅትመት ሥራዎች በጥራትና በፍጥነት እንዲደርሱ ተብሎ ለውጪ ተቋሞች ይሰጣሉ፡፡ አቶ ተካ እንደሚሉት፣ በዘርፉ ያሉ ተቋሞች ካሉባቸው ተግዳሮቶች አንፃር የሚፈልገው ደረጃ ላይ ባይደርሱም፣ ባላቸው አቅም የሚወዳደሩበት መድረክ ሊመቻችላቸው ይገባል፡፡ አሁንም ድረስ ኅብረተሰቡ በኅትመት ዘርፉ ቅሬታ እያሰማ በመሆኑ፣ የዘርፉ ተቋሞች እንዲሁም የመንግሥት ርብርብ መፍትሔ እንደሚያስገኝም ይጠቁማሉ፡፡

የኢትዮጵያ የኅትመት ዘርፉ አጀማር ልዩ ልዩ ሃይማኖቶችን ለማሰራጨት ወደ አገሪቱ ከገቡ ሚሲዮናውያን ጋር የሚያያዝ ሲሆን፣ አንድና ሁለት የነበሩ ማተሚያ ቤቶች ዛሬ ወደ 800 ደርሰዋል፡፡ ወደ 50 የሚደርሱ ድርጅቶች ደግሞ በአሳታሚነት ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ታሪክ እንደሚያስነብበው፣ በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ ማተሚያ ቤት በ1856 ዓ.ም. ቄስ ቢናያንኩሪ በተባሉ ሰው ምጽዋ ከተማ ተቋቁሟል፡፡ ኢትዮጵያ ኅትመትን በመጀመር ከአፍሪካ አራተኛ ከዓለም ደግሞ 46ኛ እንደሆነች ይነገርላታል፡፡

የዛሬው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን የመጀመሪያዎቹን የህትመት ማሽኖች ከጀርመን አስመጥተው በ1914 ዓ.ም. ያቋቋሙት ነው፡፡ በህትመት ዘርፉ ተጠቃሽ የሆኑት አርቲስቲክ፣ ተስፋ ገብረሥላሴና ሌሎችም ተቋሞች ከ1923 ወዲህ የተቋቋሙ ናቸው፡፡ በተለይም አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት በአርትኦት ሥራ አንጋፋ በተባሉ ባለሙያዎቹ ይጠቀሳል፡፡ ሆኖም ዛሬ ላይ የኅትመት ዘርፉ ከታሪኩ በተቃራኒው ተዳክሞ ይታያል፡፡

ስለ ዘርፉ ተግዳሮቶች ጥናት የሰሩት አቶ ጌታቸው በለጠ የሚገልጹትም፣ ይህንን እውነታ ነው፡፡ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን በማተሚያ ቤቶች መሀከል በጥራት ደረጃ ከፍተኛ ውድድር ይደረግ ነበር፡፡ ስለ ህትመት ጥራት ማረጋገጫ ካልተሰጠ በቀርም ለገበያ አይቀርቡም፡፡ በዘመነ ደርግ ቅድመ ምርመራ የህትመት ዘርፉን ተፈታትኖታል፡፡፡ በዕዝ ኢኮኖሚ ማተሚያ ቤቶች በአንድ ኮርፕሬሽን ስር ነበሩ፡፡ በማተሚያ ኮርፕሬሽን የነበረው የህትመት ማሰልጠኛ ተቋም ብዙ የተማረ የሰው ኃይል ማፍራቱ ሳይጠቀስ ግን አይታለፍም፡፡ ለማተሚያ ቤቶች የሚደረገው ድጎማም ለዘርፉ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡

እንደ አጥኚው ገለጻ፣ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ቅድመ ምርመራ መነሳቱ ለህትመቱ መልካም ቢሆንም፣ የህትመት ዋጋ መናር ማነቆ ሆኗል፡፡ ስመጥር ድርጅቶች አቅማቸው ተልፈስፍሶ ከገበያው የወጡትም ዘርፉ ፈር ባለመያዙ ነው፡፡ ‹‹አሁን ባለው አሰራር ሕጋዊና ሕገ ወጡ ተደበላልቋል፡፡ የቱ አሳታሚ የትኛው አታሚ እንደ ሆነም አይታወቅም፤›› ይላሉ፡፡

በዓለም የኅትመት ዘርፉን የሚገዳደሩ የኤሌክትሮኒክስ አማራጮች ተበራክተው ዘርፉ ላይ ተፅዕኖ ቢያሳድሩም፣ የኅትመት ዘርፉ ገቢ በዓለም ገበያ መሪነቱን እንደተቆናጠጠ ነው፡፡ እንደ አሜሪካ፣ ቻይናና ብራዚል ያሉ ሀገሮች መንግስታት ለኅትመት ዘርፉ ትኩረት መስጠታቸው ለዘርፉ ብልጽግና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አቶ ጌታቸው ይገልጻሉ፡፡ ‹‹መንግሥት ፊት የነሳው›› የሚሉት የኢትዮጵያ ኅትመት ዘርፍ እንደሌሎች አገሮች የመንግሥት ድጋፍ ያስፈልገዋል ይላሉ፡፡ ‹‹የኅትመት ዘርፉ የዕለት ጉርስ ለማግኘት ከሚደረግ ሩጫ አልፎ በስፋትና በጥራር ትልልቅ ኅትመቶች የሚካሄዱበት መሆን ይገባዋል፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...