Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህል‹‹የሸማ መኪና››

‹‹የሸማ መኪና››

ቀን:

በኢትዮጵያ ግዛት የመጀመሪያው ማተሚያ ቤት የቱ ነበር?

‹‹ዕድሜ ለምኑ እንጅ ለአልጋ ወራሻችን

የሸማ መኪና ልናይነው ባይናችን

- Advertisement -

ሕይወት ለተፈሪ ለአልጋ ወራሻችን

ብርሃንና ሰላም ገባ በሃገራችን››

ከዘጠና ሁለት ዓመት በፊት ‹‹ብርሃንና ሰላም›› ሳምንታዊ ጋዜጣ መታተም መጀመሩን ተከትሎ፣ ከዚያ በፊት ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን ማተሚያ ቤት›› ይባል የነበረው ተቋም መጠርያው ወደ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሲቀየር፣ ጋዜጣው ካቀረበው የሙገሳ ግጥም የተገኘ አንድ አንጓ ነው መንደርደርያችንን ያደረግነው፡፡

ከሰማንያ ስድስት ዓመት በፊት፣ ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም. ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከመንገሣቸው ዘጠኝ ዓመት በፊት፣ ልዑል አልጋወራሽ ተፈሪ መኰንን በሚባሉበት ጊዜ በግቢያቸው ውስጥ አንድ ማተሚያ ቤት አቋቁመው መጻሕፍትን ማሳተም የጀመሩበት ነበር፡፡

በብራና ላይ እየተጻፉ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፉ የነበሩ ቅዱሳን መጻሕፍት፣ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች የተጻፉ መጻሕፍት የዘመናዊው ኅትመት መሣሪያ ትሩፋት ተቋዳሽ ሆነው በግእዝና በአማርኛ ቋንቋዎች እየታተሙ የወጡበት ዘመን ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በማተሚያ ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተሙት መጻሕፍት በአራተኛው ምታመት መጨረሻና በአምስተኛው መጀመሪያ የነበረው ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ የጻፈው ድርሳናትና ተግሣጽ፣ የሰባተኛው ምታመት ማር ይስሐቅ ሲሆኑ፣ ከዚያም ቀጥሎ አራቱ ወንጌልና የሰሎሞን ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ከደራስያንም ወገን ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ድርሰታቸውን አሳትመውበታል፡፡

ይሁን እንጂ ‹‹የሸማ መኪና›› የተባለው ዘመናዊ የማተሚያ መሣርያ አዲስ አበባ ከተማ የገባው፣ መዲናዪቱ በተቆረቆረችበት በ1879 ዓ.ም. እንደሆነ ብላታ መርስኤ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ‹‹የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በንግሥት ዘውዲቱ ዘመን›› በሚለው ድርሳናቸው ገልጸውታል፡፡

እንዲህም አሉ፡፡

‹‹ዳግማዊ ምኒልክ በሙሴ ሽፋኔ በኩል አንድ ትንሽ የጽሕፈት ማተሚያ መኪና ከአውሮጳ አስመጥተው በጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ጽሕፈት ቤት አቆሙት፡፡ በዚህ ጊዜ ዳግማዊ ምኒልክ ጋዜጣውን ʻአእምሮʼ ብለው ሲሰይሙት ማተሚያ ቤቱንም ʻመርሐ ጥበብʼ  ብለውት ነበር፡፡››

በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን (1881- 1906) ሃያኛው ምታመት መባቱን ተከትሎ ከበርቴዎች በአዲስ አበባ ከተማ በአታሚነት መሥራት ጀምረዋል፡፡ በዋዜማው በ1900 ዓ.ም. ፈረንሣዊው ሙሴ ደባዥ የማተሚያ መኪና ከአውሮጳ አስመጥቶ አዲስ አበባ ላይ ለንግድ ሥራ በፈረንጅ ፊደል ያትም እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

ሦስት ባለሀብቶች ሙሴ ሸፋኔ፣ ሙሴ ባልዳሣሪያና ሙሴ አትናቴዎስ በማኅበር ባቋቋሙት የንግድ ማተሚያ ቤትም በአማርኛ ፊደል ያሳትሙ እንደነበር ይወሳል፡፡

በልጅ ኢያሱ ዘመን (1906-1909) የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በ1907 ዓ.ም. በተቋቋመ ጊዜ የማተሚያውን መኪና ከነጋዴዎች በመግዛት ማስታወቂያዎችንና ‹‹የአጥቢያ ኮከብ›› እና ‹‹አእምሮ›› የሚባሉ ጋዜጦች፣ ሌላም ነገር ሁለት ዓመት ያህል ሲያሳትም መቆየቱን የብላታ መርስኤ ኀዘን ድርሳን ያትታል፡፡

ልጅ ኢያሱ ከመንበረ ሥልጣናቸው በ1909 ዓ.ም. ከተነሡና ልዑል ራስ ተፈሪ መኰንን አልጋ ወራሽ ከሆኑ በኋላ የወሰዱት ዕርምጃ፣ በጽሕፈት ሚኒስቴርና በማዘጋጃ ቤት የነበሩትን የማተሚያ መሣሪያዎች በ1912 ዓ.ም. በአንድነት ተጠቃለው በጽሕፈት ሚኒስቴር ሥር እንዲሆኑ ማድረጋቸው ነው፡፡

የማተሚያ ቤት ስሙም ታድሶ ‹‹መርሐ ጥበብ›› ሲባል ከአምስት ዓመት ቆይታ በኋላ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመን (1909-1923)፣ ሙሉ መጠርያው ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ማተሚያ ቤት መርሐ ጥበብ›› የሚባል ሆኖአል፡፡

ከአዲስ አበባ የሚቀድሙት ማተሚያ ቤቶች

ከ577 ዓመታት በፊት በሀገረ ጀርመን በዮሐንስ ጉተንበርግ የተፈለሰፈው ተንቀሳቃሽ የማተሚያ መኪና በአውሮፓ ምድር የማተሚያ አብዮትን ፈጥሯል፡፡

በወቅቱ ዘመናዊ የነበረው የማተሚያ መኪና ከመፈጠሩ በፊት የጽሑፍ ውጤቶች ለንባብ ይበቁ የነበሩት በእጅ ጽሕፈት ሆኖ በቁም ጽሕፈት በብራና ላይ እየተጻፉ ይሠራጩ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ከዘመነ አክሱም ከአራተኛው ምታመት ጀምሮ ልዩ ልዩ ጽሑፎች ይዘጋጁ የነበሩት በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍት በብራና ላይ ነበር፡፡

በአሁኑ ጊዜ በዓድዋ እንዳ አባገሪማ ገዳም የሚገኘውና ከ1,500 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ‹‹አርባዕቱ ወንጌል›› (አራቱ የወንጌል መጻሕፍት) በብራና ላይ ይጻፉት ከነበሩት ይጠቀሳል፡፡

በዘመናዊው የማተሚያ መኪና ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ቋንቋና ፊደል የታተመው ከ503 ዓመታት በፊት ሲሆን፣ መጽሐፉም የግእዝ መዝሙረ ዳዊት ነው፡፡ አርትዖት አድርጎለት ጁን 30 ቀን 1513 ያሳተመው ጆሃን ፖትከን በኮለኝ (ጀርመን) የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ካህን ነበር፡፡

በዘመኑ በሮም (ቫቲካን) የኢትዮጵያውያንን ቅዳሴ፣ ዝማሬና የቅድስት ማርያም፣ የሐዋርያትና የቅዱሳንን ስም መስማቱ ልሳነ ግእዝን ለመማር አነሳሳውና ተማረው፣ አወቀውም፡፡ በኢትዮጵያውያኑ ካህናት ረዳትነትም መዝሙረ ዳዊትን አብሮም መኃልየ መኃልየ ዘሰሎሞንን፣ የተለያዩ ጸሎቶችና መዛሙርን ለኅትመት ማብቃቱ ይወሳል፡፡

በሌላ በኩል እ.ኤ.አ. በ1816 በኢትዮጵያ አካባቢ የመጀመሪያው ማተሚያ ቤት በምፅዋ የተቋቋመው፣ በኢጣሊያዊው የላዛሪስት ሚሲዮናዊ አባ ቢያንኬሪ አማካይነት ነበር፡፡ ሁለተኛው ማተሚያ ቤትም ከ10 ዓመት በኋላ በከረን ያቋቋሙት የፈረንሣይ ላዛሪስቶች ሲሆኑ፣ ለስብከት አገልግሎት የሚያስፈልጓቸውን መጻሕፍት እ.ኤ.አ. ከ1879 ጀምሮ ማሳተም ጀመሩ፡፡ በአማርኛ ከታተሙት መካከል መዝሙረ ዳዊትና የመዝሙር መጽሐፍ፣ የግእዝ – አማርኛ ሰዋሰው (ግራመር) እና በርካታ ሃይማኖታዊ ሥራዎች ይገኙባቸዋል፡፡ አንዱ መጽሐፍ ስለ ክርስትና አስተምህሮ የሚያወሳው ‹‹ኢሚታስዮ›› (ክርስቶስን ስለመምሰል) ከአማርኛ በተጨማሪ በትግርኛ ታትሟል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1884 በአፄ ዮሐንስ አራተኛ ዘመን (1863-1881)፣ ከእንግሊዝና ከግብፅ ጋር በተደረገው የሦስትዮሽ ስምምነት ከረን የሚገኝበት የቦጎስ አውራጃ ወደ ኢትዮጵያ ሲካለልም የኅትመት ሥራው ቀጥሏል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ግዛት የተመሠረተ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ማተሚያ ቤት እንደሆነ፣ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ‹‹History of Education Printing and Literacy in Ethiopia›› በተሰኘው ድርሳናቸው ጽፈዋል፡፡ በ1888 ከረን በኢጣልያኖች እጅ ስትወድቅ ሚሲዮናውያኑ ማስታወቂያቸው ያሳትሙና ለኢጣሊያ ባለሥልጣኖች ያቀርቡ የነበረው በኢጣሊያንኛና በአማርኛ ነበር፡፡

ማተሚያ ቤቱ ጥቂት ዓመታት ቆይቶ በ1900 አካባቢ ወደ ኤርትራ መዲና አስመራ ተዛውሯል፡፡ የስዊድን ወንጌላዊት ሚሲዮንም የመጀመሪያውን ማተሚያ ቤቱን ከምፅዋ አጠገብ በምትገኘው ምንኵሉ በ1885 ቢያቋቁምም ከአሥር ዓመት በኋላ ወደ አስመራ ተዛውሯል፡፡

በምፅዋ በዚያው ዘመን ሦስት የተለያዩ ማተሚያ ቤቶችም ቆመው ነበር፡፡ በዚያን ዘመን ይታተሙ የነበሩት መጻሕፍት በግእዝ፣ በአማርኛ፣ በትግርኛና በኦሮምኛ የተዘጋጁ ነበረ፡፡ ከታተሙት መጻሕፍት መካከል በአለቃ ታዬ ገብረ ማርያም አማካይነት የተዘጋጀውና በምንኵሉ የታተመው የግእዝ አማርኛ መጽሐፍ፣ እስካሁን በአዲስ አበባ በተደጋጋሚ እየታተመ በገበያ ላይ እየዋለ ነው፡፡  

በምሥራቅ ኢትዮጵያ በሐረር በፈረንሣይ ሚሲዮናዊ በ1889 የተቋቋመው ማተሚያ ቤት ከሁለት ዓመት በኋላ ወደ ድሬዳዋ መዛወሩ ይታወቃል፡፡

ፈረንሣውያን ለኢትዮጵያ በባህል፣ በትምህርት፣ በቋንቋ፣ በሳይንስ፣ በቴክኒክ ብዙ ተግባራትን ማከናወናቸውን የሚያብራራው ‹‹የመቶ ዓመት ወዳጅነት›› የተሰኘውና በዶ/ር ኃይሉ ሀብቱ የተተረጐመው መድበል፣ ፈረንሣውያን በአገሪቱ ማተሚያ ቤት በመክፈት አስተዋጽዖ አድርገዋል ይላል፡፡ ዕውቀትና ዕድገት እንዲስፋፋ ለማድረግ በተለይ በኅትመት ዘርፍ ያደረጉትንም ጥረት መጽሐፉ እንዲህ ያትታል፡-

‹‹በአንቷን ዳባዲ መሪነት በ1843 ዓ.ም. ፓሪስ በሚገኘው ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የተቀረፀውን የግእዝ ፊደል ኅትመት ሞንዶን ወደ ኢትዮጵያ አምጥቶ አለማመደው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ የኅትመት ፊደል ለኢትዮጵያ ጽሕፈት አጣጣል ሥርዓት ዋነኛ መለኪያና ማነፃፀሪያ ሊሆን ችሏል፡፡ የማተሚያ ቤት ሥራ መጀመር ለኢትዮጵያ የአብዮት ያህል የሚቆጠር ነበር፡፡››

አንጋፋው ጋዜጠኛና የጆርናሊዝም መምህሩ አቶ ማዕረጉ በዛብህ በአንድ ድርሳናቸው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤትን ‹‹በጥቁሮቹ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በጥንታዊነቱና በትልቅነቱ የታወቀው›› ይሉታል፡፡ የመጀመሪያ ጥንስሱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አልጋ ወራሽ በነበሩበት በ1917 ዓ.ም. ከአባታቸው ከራስ መኰንን በወረሱት፣ ዛሬ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚገኝበት፣ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥታቸው ማቋቋማቸው በስሙም ጋዜጣ መመሥረታቸው ይታወቃል፡፡

ሐምሌ 9 ቀን 1917 ዓ.ም. የወጣው ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ስለ አልጋ ወራሹ ውለታ ባወጣው የሙገሳ ግጥም፡-

‹‹ዕድሜ ለምኑ እንጅ ለአልጋ ወራሻችን

የሸማ መኪና ልናይ ነው ባይናችን››

በማለት ብቻ አልተወሰነም፡፡ እንዲህም ጨመረበት፡፡

‹‹ልዑል አልጋወራሽ ልብ አድርጎ ላየዎ

ብርሃንና ሰላም አለ ከፊትዎ

ብርሃንና ሰላም ብሎ የሰየመው ማነው ጋዜጣዎን

ብርሃንና ሰላም ማለትስ እርስዎን፡፡››     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...