Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊበበጀት እጦት የተሽመደመዱ የወጣት ማኅበራት

  በበጀት እጦት የተሽመደመዱ የወጣት ማኅበራት

  ቀን:

  ለወላጅ አልባ ሕፃናት የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች፣ የሥነ ተዋልዶ፣ የክህሎት፣ የአመራርና የመሳሰሉትን ሥልጠናዎችና ድጋፍ የሚሰጠውን ‹‹የደቡብ ክልል ፍቅር በሕይወት ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትና ወጣቶች ማኅበር›› ከሰባት ጓደኞቹ ጋር ሆኖ የመሠረተው ገና የ14 ዓመት ታዳጊ ሳለ ነበር፡፡ ታሪኩ እንደዚህ ነው፡፡ አብርሃም መሓሪ የ12 ዓመት ታዳጊ ሳለ ነው ወላጆቹን በሞት የተነጠቀው፡፡ ኃላፊነቱን ወስዶ ሊያሳድገው የሚችል ሰው ባለመኖሩ፣ ወላጆቻቸውን በኤችአይቪ ኤድስ ያጡ ሕፃናትን ለሚረዳ ድርጅት ተሰጠ፡፡

  እዚያ ሁለት ዓመት ያህል ከቆየ በኋላ ከተረጂነት ለመላቀቅ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የፀረ ኤድስ ቡድን ለማቋቋም ቻለ፡፡ ነገሮች ግን አልጋ በአልጋ አልሆኑም፡፡ በወቅቱ የታዳጊዎቹን እንቅስቃሴ በጥርጣሬ ይመለከቱ የነበሩ የተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች፣ ልጅነታቸውን በመመልከት ‹‹ገንዘብ ቢያታልላቸውስ›› በሚል ድጋፍ ለመስጠት ያንገራግሩ እንደነበር ያስታዉሳል፡፡ ነገር ግን የሚደረግላቸውን ውስን ድጋፍ ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ እንዲውል በማድረግ በብዙዎች ዘንድ ተአማኒነትን አተረፉ፡፡ ከሁለት ዓመታት በኋላም በማኅበር መልክ ሊደራጁ ቻሉ፡፡

  ማኅበሩ ከተቋቋመ አሥር ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የአባላቶቹ ቁጥርም ከ3,000 በላይ ደርሶ ነበር፡፡ መቀመጫውን ያደረገው በሐዋሳ ሲሆን፣ በአሥር ዞኖችና በሦስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ይሠራል፡፡ ይሁንና በገጠሙት የተለያዩ ችግሮች እንደ ቀድሞው ፕሮጀክቶችን ቀርፆ በሥራ ላይ ከማዋል ተገድቧል፡፡ እንዲያዉም ፕሮጀክቶችን ለማጠፍ ሚገደዱባቸው ጊዜያት መኖራቸውን አብርሃም ይናገራል፡፡ ‹‹በፊት አብረን እንሥራ ይሉ የነበሩ ተቋማት አሁን የሉም፡፡ አቅምም የለንም፡፡ ይኽም የምንሠራቸው ፕሮጀክቶች እንዲወሰኑ አድርጓል፤›› ይላል፡፡

  አብርሃም እንደሚለው፣ ለተለያዩ ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ የሚሆን ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ ተቋማት ወደ ስደት፣ ድርቅና አካባቢ ጥበቃ ፊታቸውን አዙረዋል፡፡ ይህ የሆነው ግን  በኤችአይቪ እና በሌሎችም የጤና ጉዳዮች ዙሪያ የተሠሩት ሥራዎች በቂ ሆነው አይደለም፡፡ አሁንም ከፍተኛ የሆነ ክፍተት አለ፡፡ ድርጅቶቹም ለመሥራት የሚያስችላቸው በጀት ስላጡ በከተማው እስከ 40 የሚሆኑ በኤችአይቪ ኤድስ ዙሪያ ይሠሩ የነበሩ ክበባት፣ ማኅበራትና ሌሎች ተቋማት ሊፈርሱ ችለዋል፡፡

  ‹‹እኛም ጠንካራ ሆነን እንጂ እስካሁን እንበታተን ነበር፤›› የሚለው አብርሃም፣ በአንድ ወቅት ሙሉ ትኩረት ተደርጎባቸው  ይሠሩ የነበሩ ጤናና ወጣቶች ላይ ያተኮሩ  ጉዳዮች ወደ ጎን በመባላቸው በጉዳዩ ይሠሩ የነበሩ ተቋማት እየተዘጉ መሆኑን፣ የተቀሩት አንዳንዶችም አስፈላጊውን ድጋፍ ካላገኙ በቅርቡ ሊዘጉ እንደሚችሉ፣ ይህም ወጣቶች ከድርጅቶቹ ያገኙት የነበረውን ልዩልዩ ክህሎቶች እንደሚያሳጣ ይናገራል፡፡

  ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአገሪቱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ወጣቶች መሆናቸው ይነገራል፡፡ ይህንን ያህል ድርሻ የሚይዙትን የኅብረተሰቡን ክፍሎች በተለያዩ ማኅበራዊና ልማታዊ ጉዳዮች ብቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማስቻል በወጣቶች ላይ ትኩረታቸውን አድርገው የሚሠሩ እንደ ፍቅር በሕይወት ያሉ ተቋማት ያላቸው ሚና የላቀ ነው፡፡

  ለበርካታ ወጣቶች ባለውለታ የሆኑ በየቀበሌውና በየትምህርት ቤቱ የነበሩ የፀረ ኤድስና የሥነ ጥበብ ክበባት፣ ትውልዱን ከመቅረጽ አኳያ የማይናቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ወጣቶች ከትምህርትና ከሌሎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸው ጎን ለጎን በክበባት በመታቀፍ የጤናና የሕይወት ክህሎት እንዲያዳብሩም አስችሏል፡፡

  የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራትን የተመለከተው አዋጅ ከወጣ በኋላም በወጣቶች ዙሪያ የሚሠሩ ድርጀቶች በተለያዩ መሥፈርቶችና አሠራር ተዋቅረው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ የመጀመርያዎቹ በኢትዮጵያ ማኅበራት ውስጥ የሚመደቡትና 90 በመቶ የሚሆነውን ገቢያቸውን ከአገር ውስጥ የሚያሰባስቡ በመብት ዙሪያ የሚሠሩት ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ነዋሪዎች ሥር የሚመደቡት ደግሞ 90 በመቶ የሚሆነውን ገቢያቸውን ከውጭ የሚሰበስቡት ናቸው፡፡

  ተቋማቱ የተለያዩ ፕሮክቶችን ቀርጸው ተግባራዊ በማድረግ በተቻላቸው መጠን ወጣቱን ብቁ ለማድረግ ይሠራሉ፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ባለባቸው የአቅም ውስንነት የሚቀርጿቸውን ፕሮጀክቶች ለማጠፍ እየተገደዱ እንደሆነ፣ በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ነዋሪ ማኅበራት የሚመደቡት ጥቂት የማይባሉ እየተዘጉ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የብዙዎቹ ሕልውናም ሥጋት ውስጥ ወድቋል፡፡

  ለዚህም የለጋሽ ተቋማት በተወሰኑ እንደ ድርቅ፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ሥደት ያሉ ጉዳዮች ላይ ብቻ ማተኮራቸውና ከዚህ ቀደም ይሠሩባቸው የነበሩ ጉዳዮችን ወደ ጎን ከማለታቸው በተጨማሪም፣ የለጋሾች መስፈርት ከተቋማቱ ጋር አብሮ የማይሄድ መሆኑም ሌላው ችግር ነው፡፡

  በአዳማ የሚገኘው ደላሳል ሪፕሮዳክቲቭ ሔልዝ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ከእነዚህ ተቋማት መካከል ነው፡፡ ደላሳል የኢትዮጵያ ነዋሪ በጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን 90 በመቶ የሚሆነውን ገቢውን ከውጭ አገር፣ አሥር በመቶ የሚሆነውን ደግሞ ከአገር ውስጥ ያሰባስባል፡፡ የድርጅቱ መሥራችና አስተባባሪ ሰለሞን ግደይ እንደሚለው፣ ድርጅቱ ባሉበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች እና የበጀት እጥረት ለጋሾች በሚፈልጉት መልኩ  አደረጃጀቱንና ትኩረት አድርጎ የሚሠራባቸውን ጉዳዮች ለመቀያየር ተገድዷል፡፡ 

  1997 ዓ.ም ሲቋቋም የሥነ ተዋልዶና የፀረ ኤድስ ክበብ በሚል ነበር፡፡ ከዚያም ደለሳል ሪፕሮዳክቲቭ ኤንድ ሔልዝ አሶሴሽን በሚል ወደ ማኅበርነት ከፍ ብሎ እንዲቋቋም ሆነ፡፡ ቀጥሎም ወደ ድርጅትነት ተለወጠ፡፡ ‹‹ጠንካራ ፈንድ ለማግኘት ስንል ነው ወደ ማኅበርነት ከዚያም ወደ ድርጅትነት ከፍ ያልነው›› የሚለው ሰለሞን፣ ከመንግሥት በተሰጠው 2,500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እናቶችና ሕፃናት በከተማ ግብርና እንዲተዳደሩ ማስቻሉን፣ 15 ክፍሎች ያሉት የመዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤት ማስገንባቱን፣ 600 ሕፃናት መርዳት የሚችል የትምህርት ማበልፀጊያ ተቋም መገንባቱን ይናገራል፡፡ ሥራው በአዳማ ብቻ የተወሰነ  ሳይሆን፣ በሌሎችም የክልል ከተሞች ይከናወናል፡፡

  ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ከዚህ ቀደም እንደነበረው ውጤታማ አይደለም፡፡  ለጋሽ ድርጅቶች እንደቀድሞው አለመኖር ጠንካራ አቅም ያላቸው ሠራተኞችን ቀጥሮ ለማሠራት እንዲቸገሩ፣ ድጋፍ መጠየቂያ ፕሮፖዛል የመቅረጽ አቅማቸው ደካማ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ በበጀት ማነስ የሚቀረፁ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እንዲታጠፉ ሆኗል፡

  እየተሠሩ ያሉት ፕሮጀክቶችም ከቀድሞው ጋር ሲተያዩ በእጅጉ ቀንሰዋል፡፡ 600 ሕፃናት ይረዳ የነበረው ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ያለው አቅም 60 ሕፃናትን ከመርዳት ያለፈ አይደለም፡፡ በድርጅቱ ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች ቁጥርም ከ24 ወደ ስድስት ወርዷል፡፡ የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ቁጥርም በእጅጉ ቀንሷል፡፡ ‹‹በከተማው ውስጥ የነበሩት አብዛኞቹ ወጣቶች ከእኛ ጋር ይሠሩ ነበር፤›› ያለው ሰለሞን በአሁኑ ወቅት ድርጅቱን በማገልገል ላይ ያሉት በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች 100 ብቻ መሆናቸውን ይናገራል፡፡

  ተቋማቱን የሚፈትኑ ሁኔታዎች የተበራከቱት የበጎ አድራጎት ማኅበራትን የሚያስተዳድረው ሕግ ከወጣ በኋላ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ ሕጉ በኢትዮጵያ ማኅበራት ሥር የተደራጁ፣ 90 በመቶ የሚሆን ገቢያቸውን ከአገር ውስጥ እንዲያሰባስቡ የተደረጉ የወጣት ማኅበራት ከሌላው በተለየ ተጎጂ እንዲሆኑ ማድረጉን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

  90 በመቶ ከቻሉ 100 በመቶ የሚሆን ገቢያቸውን ከአገር ውስጥ እንዲያሰባስቡ የተደረገበት ሁኔታ ማኅበረሰቡ ካለው ‹‹ዝቅተኛ የመለገስ ባህል›› ጋር በጥልቀት የታየ አይደለም፡፡ ይህ ግን የማኅበረሰቡ ችግር ብቻ ሳይሆን ተቋማቱ ከአገር ውስጥ ገቢ የማሰባሰብ እውቀታቸው ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው ሲሉ የሚከራከሩም አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የለጋሽ ድርጅቶች ፍላጎት የኢትዮጵያ ነዋሪ ድርጀቶች ጋር የማይጣጣም በመሆኑ እነሱም በበጀት ዕጦት እንዲቸገሩና ፕሮጀክቶቻቸውን እንዲሠርዙ  እየተገደዱ ይገኛሉ፡፡  

  ኮንሰርቲየም ኦፍ ዩዝ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ኢትዮጵያ ሰኔ 2008 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው ጥናት፣ በወጣት ዙሪያ የሚሠሩ ተቋማትና ማኅበራት በበጀት ዕጥረትና በውስጥ አመራር ብቃት ማነስ እየተቸገሩ እንደሚገኙ፤ እ.ኤ.አ. በ2009 የወጣው ማኅበራትን የሚገዛው ሕግ ክፍተትም የማኅበራቱን ህልሙና እየተፈታተነ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡ በወጣት ዙሪያ የሚሠሩ ተቋማት እ.ኤ.አ. በ2011 ከውጭ ድርጅቶች ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ አግኝተው ነበር፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የገንዘቡ መጠን በግማሽ ሊቀንስ መቻሉን በጥናቱ ተካቷል፡፡

  በአሁኑ ወቅት የሚለቀቅላቸው በጀት እንደ ፕሮጀክት እንኳን ለማስፈጻም አቅም እያነሰው ይገኛል፡ በ1997 ዓ.ም. የተቋቋመው ጤና ቀበና ግንፍሌን እናፅዳ የወጣቶች ማኅበር በአራት ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ በጉሊት ንግድ የተሠማሩ 100 ሰዎችን መድረስ የሚችል ፕሮጀክት ነድፎ እየሠራ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ሲሆን አንድ ሚሊዮን ብር ያስፈልገዋል፡፡ ይሁንና ማግኘት የተቻለው የገንዘብ ድጋፍ ለስድስት ወራት ብቻ የሚሆናቸውን 600,000 ብር ብቻ መሆኑን ዳይሬክተሩ ደሳለኝ ፍሬው ይናገራል፡፡

  በኮንሰርቲየም ኦፍ ዮዝ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናዜሽንስ ኢን ኢትዮጵያ ኤክስኪዩቲቭ ዳሬክተሯ ወጣት የአብሥራ ቦጋለ እንደምትለው፣ የወጣት አደረጃጀቶቹ መኖር ለጤናማ የአገር ልማት ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ በአገሪቱ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ወጣቶች እንደመሆናቸው ያለውን እምቅ አቅም በሥራ ላይ ለማዋል እንደ አቅማቸውና ፍላጎቶቻቸው ለያይቶ በልማት እንዲሳተፉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

   ‹‹በእኛ አገር ከ10 እስከ 29 ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ይመደባሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ተማሪ፣ ሠራተኛ፣ ያገባ፣ ያላገባ ወጣት ይገኛል፡፡ እንደየፍላጎታቸውና አቅማቸው ተለያይተው ካልተቀመጡ የቱን ለምን ልማት ማዋል እንደሚቻል ግልጽ አይሆንም፤›› የምትለው የአብስራ፣ በተለያዩ ወጣቱን በሚመለከቱ ጉዳዮች ለማሳተፍ በተገቢው መልኩ ልዩነታቸውን ለይቶ ማውጣት ግድ እንደሆነ፣ ይኼንንም ሚና መጫወት የሚችሉት የወጣት አደረጃጀቶች መሆናቸውን ትናገራለች፡፡

  በአሁኑ ወቅት ከድርጅቱ ጋር አብረው የሚሠሩ 14 የኢትዮጵያ ነዋሪ ድርጅቶች ይገኛሉ፡፡ በሁሉም ክልሎች የሚሠሩ ሲሆን፣ የተለያዩ ቴክኒካል ድጋፎችና የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ይሰጣቸዋል፡፡ ይሁንና ይኼ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ድጋፍ እየተደረገላቸው ያሉት አደረጃጀቶችም እየተዳከሙ ይገኛሉ፡፡

  ‹‹ራሳቸው መሥራት ያለባቸውን ነገሮች ያለመሥራት አለ፤›› የሚሉት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፋንቱ ገዛኸኝ፣ እስካሁን የተዘጉ የኢትዮጵያ ወጣት ማኅበራት አለመኖራቸውን፣ ነገር ግን የኢትዮጵያ ነዋሪዎች ድርጅት ሥር የሚገኙ የወጣት ድርቶች በራሳቸው ችግር የተዘጉ መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

  90 በመቶ ገቢያቸውን ከአገር ውስጥ እንዲያሰባስቡ የተፈቀደላቸው በመብት ዙሪያ የሚሰሩ ማኅበራትን በተመለከተ ዳይሬክተሯ፣ አባላቱን በሚገባ የማንቀሳቀስ፣ ፍላጎት እንዲኖራቸውና መዋጮ እንዲያወጡ የማድረግና የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞችን የማዘጋጀት የአቅም ውስንነቶች መኖራቸውንና ይኽም ተቋማቱን ደካማ እንዳደረገ ተናግረዋል፡፡

  ‹‹ገቢ ማስገኛ በሚሆን ንግድ ለመሰማራት ቢፈልጉ ለሚመለከታቸው አካላት የድጋፍ ደብዳቤ እንጽፋለን፡፡ የሚያገኙት ትርፍም ለድርጅታቸው ይሆናል›› ያሉት ዳይሬክተሯ፣ ድርጅቶቹ በዕድሉ ለመጠቀም ያላቸው ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይሁንና እስከአሁን የተዘጉ በኢትዮጵያ ማኅበራት ሥር የሚገኙ የወጣት ማኅበራት አለመኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

  በኢትዮጵያ ነዋሪዎች ሥር የተመዘገቡ የወጣት አደረጃጀቶች ግን ‹‹ሥራዎችን መሥራት ሲያቅታቸው እንዝጋ ብለው ወደ እኛ ይመጣሉ›› ሲሉ የተቋቋሙበትን ዓላማ መወጣት ሲያቅታቸው ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ የሚጠይቁ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

  ኤጀንሲው የተቋማቱን እንቅስቃሴ በየጊዜው እንደሚመረምር በቂ የሆነ ሥራ መሥራት ያልቻሉትን ጠርቶ እንደሚያነጋግር፣ ችግሮቹን ማሻሻል የሚቻል ከሆነም ሁለተኛ ዕድል እንደሚሠጥ ወ/ሮ ፋንቱ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውጪም በፍላጎት ለመዝጋት ጥያቄ ሲቀርብ የሚዘጉበት አግባብ መኖሩን አክለዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img