Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበውዝግብ የተጀመረው የአትሌቲክሱ ጉባኤ የመጀመርያ ቀን ውሎ

በውዝግብ የተጀመረው የአትሌቲክሱ ጉባኤ የመጀመርያ ቀን ውሎ

ቀን:

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሸን ዓመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ጥቅምት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን፣ ጥቅምት 27 ቀን በሚያካሂደው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን የሚመሩት ይታወቃሉ፡፡

ባለፈው ዓርብ በግዮን ሆቴል በተጀመረው የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ 20ኛው ዓመታዊ ጉባኤ፣ የስፖርቱን ባለቤቶች አትሌቶችን ለምርጫ በማሳተፍ የመጀመርያ እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡ በመጀመርያ ቀን ውሎው ቀደም ሲል በነባር አትሌቶችና በፌዴሬሽኑ መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በብዙ መልኩ የጉባኤውን ተሳታፊዎች ያነጋገረና ትኩረትም የሳበ እንደነበርም ታይቷል፡፡ ይኸም በአስገራሚ አኳኋን ከተሳታፊዎች ዘንድ የሐሳብ ፍንጭ እንዲንሸራሸር ምክንያት ሆኖ ቀርቧል፡፡

ከሪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት ጀምሮ በነባር አትሌቶች ሲደመጡ የነበሩ የአሠራር ክፍተቶች፣ የአትሌቲክሱን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ መሆናቸው እየታወቀ፣ ነገር ግን ቅሬታቸውን ለመፍታት በፌዴሬሽኑ በኩል የተሄደበት አግባብ ትክክል እንዳልነበር ከክልሎች ከመጡ ተሳታፊዎች አስተያየቶች ሲቀርቡ ተደምጧል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በበኩሉ ለአትሌቶቹ ጥያቄና ቅሬታ ፌዴሬሽኑ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶ ለማስተናገድ የሄደበት መንገድ እንደነበረ፣ ሆኖም አንዳንዶቹ ጥያቄዎች ከተቋሙ ደንብና መመርያ አኳያ ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑ ለልዩነቱ ምክንያት ሆኖ መቆየቱን አብራርቷል፡፡

ጉባኤው ሲከፈት አንዱና በትልቁ ሲንፀባረቅ የተስተዋለው ይኼው የቀድሞ አትሌቶች ጉዳይ መሆኑ እንደተጠበቀ፣ በተጓዳኝ መድረኩን ከሚመራው ነባሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም ሆነ ከተወሰኑ የክልል ፌዴሬሽን አመራሮች የአትሌቶቹ መነሻ ‹‹ስፖርቱን ማዕከል ያደረገ አልነበረም›› በሚል ጥያቄያቸውን ለማጣጣል ጥረት ሲደረግ ተስተውሏል፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ይህ የፌዴሬሽኑና የአንዳንድ ጉባኤተኞች አካሄድ ለአትሌቲክሱ እንደማይበጅ በመጠቆም አትሌቶቹን ማቅረብና ማወያየት እንደሚያስፈልግ ጭምር የተናገሩም ነበሩ፡፡ በዚህ መነሻነት ከዕቅዱ አፈጻጸም ጋር የተያያዙ ክፍተቶች እንደነበሩ፣ እነዚሁ ክፍተቶች ይህ አመራር ኃላፊነቱን ከተረከበበት ከአራት ዓመት በፊት ጀምሮ በየዓመቱ በተደረጉ መደበኛ ጉባኤዎች ሲቀርቡ መቆየታቸው አሁንም በተመሳሳይ እየቀረበ መሆኑ የፌዴሬሽኑን የማስፈጸም አቅም ውስንነት የሚያመላክት እንደሆነም ሲነገር ተደምጧል፡፡

ሌላው ለአትሌቲክሱ የውጤት ማሽቆልቆል በምክንያትነት ከቀረቡት መካከል የውድድር ዕድል መጥፋት፣ አትሌቲክስ ሲባል ሩጫ ብቻ ተደርጎ መታየቱና ፕሮጀክቶች በወረቀት ላይ ካልሆነ በተግባር ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት መጥፋት፣ ወጥነት ያለው የሥልጠና ሥርዓት መጥፋትና በስፖርቱ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት በዋነኛነት ከተነሱት ናቸው፡፡

ከሥልጠናና መሰል ችግሮች ጋር ተያይዞ ለተነሱት የጉባኤው አስተያየቶች፣ በፌዴሬሽኑ በኩል ችግሩ እንዳለ ሆኖም የመፍትሔ ዕርምጃ ለመውሰድ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች በተጀመሩበት ጊዜ፣ ከራሱ ከፌዴሬሽኑ ሠራተኞች በተለይ ‹‹መሠረታዊ የአሠራር ሒደት ለውጥ›› ትግበራው ውጤት አያመጣም በሚል ተቃውሞ ገጥሞት መቆየቱም ተነግሯል፡፡ ይኼ ጉዳይ ለአንዳንድ ታዋቂ አትሌቶች ተቃውሞ መነሻም ሆኖ መቆየቱ የጉባኤው የመጀመርያ ቀን ውሎ ከተመለከታቸው ይጠቀሳል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አምበሳው እንየው ጉባኤው የአገሪቱን የአትሌቲክስ ዕጣ ፈንታ የሚወስን ነው ብለውታል፡፡

ፌዴሬሽኑ በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ከአዲስ አበባ፣ አቶ ዳኛቸው ሺፈራው ከኦሮሚያ፣ አቶ ተፈራ ሙሳ ከደቡብ፣ አቶ ወልደገብርኤል መዝገቡ ከትግራይ ዕጩ ሆነው መቅረባቸው ታውቋል፡፡

ለሥራ አስፈጻሚነት በዕጩነት ከቀረቡት የቀድሞ አትሌቶች መካከል የትግራዩ  ገብረ እግዚአብሔር ገብረማርያምና የኦሮሚያው ገዛኸኝ አበራ ይገኙበታል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ