የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ እሸቱ ፋንታዬ፣ ለባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ የሥራ ስንብት ደብዳቤ በማቅረብ ከኃላፊነት የለቀቁት ያለፍላጎታቸው መሆኑ ተጠቆመ፡፡
ከባንኩ ምሥረታ ጀምሮ ባንኩን በፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ እሸቱ ከኃላፊነታቸው የለቀቁት በፈቃዳቸው የሥራ መልቀቂያ በማስገባታቸው ነው ቢባልም፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ግን በባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ግፊት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
በአቶ እሸቱና በአንዳንድ የቦርድ አባላት መካከል በተደጋጋሚ አለመግባባቶች ተከስተው እንደነበር የሚገልጹት ምንጮች፣ ልዩነታቸው እየሰፋ በመምጣቱ ከኃላፊነታቸው እንዲለቁ ተደርጓል፡፡
የባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት የፕሬዚዳንቱ ስንብት ያልተጠበቀ እንደሆነ እየተገለጸ ሲሆን፣ ቢያንስ ስንብቱ ጠቅላላ ጉባዔውን እንዳይጠብቅ የተደረገው በተፈጠረው ልዩነት ነው የሚሉም አሉ፡፡
አቶ እሸቱ በሥራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸው ገለጹ የተባለው፣ ባለፈው ዓመት በመኪና አደጋ ምክንያት ባጋጠማቸው ጉዳትና በሌላ ሕመም ሥራቸውን ማከናወን አለመቻላቸውን ነው፡፡
አቶ እሸቱ ባለፈው የካቲት 2008 ዓ.ም. ባጋጠማቸው የመኪና አደጋ ምክንያት ለወራት በሥራ ገበታቸው ላይ እንዳልነበሩም ታውቋል፡፡
በሥራ ገበታቸው ላይ ባልነበሩበት ወቅት በእርሳቸው የኃላፊነት ቦታ ላይ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩትን አቶ ታደሰ ጪንክል በተጠባባቂ ፕሬዚዳንትነት እንዲሠሩ መድቧል፡፡ በአቶ እሸቱና በአንዳንድ የቦርድ አባላት መካከል የተፈጠረው ያለመግባባት መንስዔ አልተገለጸም፡፡
አቶ እሸቱ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ35 ዓመታት በላይ ያገለገሉ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ንግድና ፋይናንስ እንዲሁም በኢኮኖሚክስ ሁለት ዲግሪዎች አሉዋቸው፡፡ የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ሲያገለግሉ ነበር፡፡ በተጠባባቂነት የተሰየሙት ፕሬዚዳንት ደግሞ በቢዝነስ ማኔጅመንት ቢኤ ድግሪ ሲኖራቸው፣ በዘርፉ ከ40 ዓመታት በላይ የሠሩ ናቸው፡፡ ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ በ2001 ዓ.ም. በ110 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት በሥራው ውስጥ ቆይቷል፡፡
ባንኩ ከ12 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖችን ሲኖራት፣ በ2008 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት ከ255 ሚሊዮን ብር ማትረፉ ታውቋል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡