Monday, October 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በተቃውሞ ምክንያት ንብረታቸው ለወደመው ባለሀብቶች ድጋፍ ማድረጊያ ማዕቀፍ ተዘጋጀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቱርክ ኢስታንቡል ከተማ የተካሄደውን የቱርክ፣ አፍሪካ የኢኮኖሚና የቢዝነስ ፎረም የተሳተፉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው፣ በቅርቡ በአገሪቱ በተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጉዳት የደረሰባቸውን ባለሀብቶች ለመርዳት መንግሥት የድጋፍ ማዕቀፍ ማዘጋጀቱን ገለጹ፡፡

አቶ አህመድ መንግሥት የፖለቲካ አደጋዎች እንደማይከሰቱ ማረጋገጫ መስጠት ባይችልም፣ በቅርቡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጉዳት ለደረሰባቸው ኩባንያዎች ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ማዕቀፍ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ይህ ማዕቀፍ ተጨማሪ ብድር መስጠትን፣ የብድር መክፈያ ጊዜን ማራዘም፣ እንዲሁም ጉዳት የደረሱባቸው ማሽኖችን ከውጭ ሲገዙ የሚኖረውን ግብርና ቀረጥ ማስቀረትን ይጨምራል፡፡

ሚኒስትሩ ጉዳት ለደረሰባቸው ኩባንያዎች ሌሎች ማትጊያዎችም እንደተዘጋጁላቸው አመልክተዋል፡፡ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩባንያዎቸ ላይ የደረሰውን ጉዳት መጠን ለማወቅ እያጣራ እንደሆነ ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ደግሞ የፋይናንስ ግምገማ እያካሄደ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በቅርቡ በኦሮሚያ በተፈጠረው አለመረጋጋትና አመጽ 130 ኩባንያዎች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ መውደማቸው ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይ በአማራ ክልል የአበባ እርሻዎችና የውጭ ኩባንያዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ጉዳት የደረሰባቸው አብዛኛዎቹ ኩባንያዎች ካሳ እንዲከፈላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጉዳያቸውን ሲያየው እንደነበር ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ ወቅትና ሁኔታ በርካታ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የቱርኩ ሳይገን ዲማ አክሲዮን ማኅበር ተጠቃሽ ነው፡፡ ማኅበሩ ብድሩን ባለመክፈሉ የንግድ ባንክ ባወጣው የሐራጅ ጨረታ ለኮሜርሻል ኖሚኒስ መሸጡ ይታወሳል፡፡ የኩባንያው ባለቤቶች ከአቶ አህመድ ጋር በዕጣ ፈንታው ላይ ለመነጋገር ሲገናኙ መሸጡ ተነግሯቸዋል፡፡

ሚኒስትሩ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የቱርክ ኩባንያዎች ቀድመው በመምጣትና አደጋ በመጋፈጥ ለወጪ ንግድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ነገር ግን እንደ ሳይገን ዲማ ያሉ ኩባንያዎች በጣም ያረጁ ማሽኖችን በመጠቀም የሚያመርቱት ጨርቃ ጨርቅ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን እንዳልቻለ አመልክተዋል፡፡ ‹‹እንዲህ ዓይነት ኩባንያዎችን ከአሁን በኋላ አንታገስም፡፡ ባንኮቻችን ዕርምጃዎች እንዲወስዱባቸው ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥተናል፤›› ብለዋል፡፡ ከአሁን በኋላ ብቃት ያላቸውን ኩባንያዎች ለመምረጥ አገሪቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደምታደርግም አክለዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በኢስታንቡል በተካሄደው ፎረም ቱርክ በአፍሪካ ካላት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ግማሽ ያህሉን ለያዘችው ኢትዮጵያ አድናቆት ጎርፎላታል፡፡ የቱርክ ባለሥልጣናት ባደረጓቸው ንግግሮች ኢትዮጵያ ጥሩ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን መስክረዋል፡፡ በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ፋቲህ ኡሉሶይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በርካታ የቱርክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የተሳቡ ሲሆን፣ የቱርክ ኢንቨስትመንቶች እየጨመሩ ይሄዳሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 የቱርክ ኩባንያዎች ወጪ ንግድ 400 ሚሊዮን ዶላር ያስመዘገበ ሲሆን፣ በቅርቡ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቅዷል፡፡

ቱርክ ከኢትዮጵያ ጋር ነፃ የንግድ ዞን ስለመገንባት የተወያየች ቢሆንም፣ በቅርቡ ይህን ለማሳካት አስቸጋሪ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በቱርክ-አፍሪካ የኢኮኖሚና የቢዝነስ ፎረም ላይ ንግግር ያደረጉት የቱርክ ፕሬዚዳንት ሪሴፕ ታይፕ ኤርዶጋን ምዕራባውያን ሉላዊነትን እንደ መሣሪያ በመጠቀም የቅኝ ግዛት አጀንዳ እያራመዱ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡ የዕድገት ሞዴላቸውንና የፖለቲካ ሥርዓታቸውን በተለያዩ አገሮች ላይ እየጫኑ ነው ሲሉም ወቅሰዋል፡፡ በአፍሪካ ላይ ያላቸውን ጫናም ‹‹ዘመናዊ ባርነት›› ብለውታል፡፡ ቱርክ ከአፍሪካ ጋር በወንድማማችነት መንፈስ በጋራ መሥራት እንደምትፈልግም ገልጸዋል፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ቱርክ በአፍሪካ ያላት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 3.9 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ በቱርክና በአፍሪካ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ መጠን ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2005 ሰባት ቢሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2015 ግን ወደ 17.5 ቢሊዮን ዶላር አድጓል፡፡

በፎረሙ ከአፍሪካ አገሮች መካከል ግማሽ ያህሉ በሚኒስትር ደረጃ ተወክለዋል፡፡ ፎርሙ በሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት፣ በቱርክና አፍሪካ ኢንቨስትመንትና በመሠረተ ልማት ግንባታና በነፃ የንግድ ቀጣና ዙሪያ መክሯል፡፡    

  በዘካርያስ ስንታየሁ፣ ኢስታንቡል፣ ቱርክ

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች