Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኤሌክትሪክ ኔትወርክ ማሻሻያ ሥራ በ224 ሚሊዮን ዶላር እየተካሄደ ነው

የኤሌክትሪክ ኔትወርክ ማሻሻያ ሥራ በ224 ሚሊዮን ዶላር እየተካሄደ ነው

ቀን:

የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግርን እንደሚፈታ የታመነበት የአዲስ አበባና የክልል ከተሞች የኃይል ማሰራጫ ኔትወርክ ማሻሻያ ሥራ በ224 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በመፋጠን ላይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጎሳዬ መንግሥቴ ለሪፖርተር እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ ችግሩ የማመንጨት ሳይሆን ከማከፋፈያ መስመሮች ጋር የተያያዘ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኙ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ መስመሮች ከ30 ዓመት በፊት የተዘረጉ መሆኑን የተገለጹት አቶ ጎሳዬ፣ በእነዚህ ዓመታት የሕዝቡ አኗኗር በመቀየሩ የኤሌክትሪክ ፍጆታ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

‹‹የጋራ መኖሪያ ቤቶች በስፋት መገንባት፣ ኅብረተሰቡ ከእንጨት፣ ከከሰልና  ከጋዝ ምድጃዎች ተላቆ ወደ ኤሌክትሪክ ምድጃዎች መግባት፣ ሌሎች በርካታ የኤሌክትሪክ መሣሪያዎች መጠቀም መጀመሩ የኃይል ፍላጎቱን ጨምሯል፡፡ የኤሌክትሪክ መስመሮቹ የተዘረጉት ኅብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለመብራት ብቻ በሚጠቀምበት ወቅት በመሆኑ፣ እያደገ የመጣውን የኤሌክትሪክ ፍላጎት መሸከም አልቻሉም፡፡ የኤሌክትሪክ መስመሮቹ የሚነዱትና ትራንስፎርመሮች የሚፈነዱት በዚህ ምክንያት ነው፤›› ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

      የኢንቨስትመንት መስፋፋትና የኤሌክትሪክ ኃይል በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የማዳረስ መርሐ ግብር የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ፍላጎት እንዲንር አድርጎታል፡፡ በቅርቡ የተሠራ ጥናት የኃይል ፍላጎቱ በየዓመቱ 20 በመቶ በማደግ ላይ መሆኑን ያሳያል፡፡

      ይኼም ሆኖ የአገሪቱ አጠቃላይ የማመንጨት አቅም 4,000 ሜጋ ዋት በመድረሱና የኃይል ፍላጎቱ 2,000 ሜጋ ዋት በመሆኑ የአቅርቦት ችግር እንደሌለ አቶ ጎሳዬ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አሁን ያለው ዋና ችግር የማሰራጫ መስመሮች የኢኮኖሚ ዕድገቱ የፈጠረውን የኃይል ፍላጎት የሚሸከም አለመሆኑ ነው፤›› ያሉት አቶ ጎሳዬ፣ የአዲስ አበባ የኔትወርክ ማሻሻያ ሥራ በመፋጠን ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

      በአዲስ አበባ በተለየ ሁኔታ ዋና ዋና የሥርጭት መስመሩን ሙሉ በሙሉ የመለወጥ ሥራ፣ የትራንስፎርመር አቅም ማሳደግና የማከፋፈያ ጣቢያዎች የመለወጥ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ ጎሳዬ ተናግረዋል፡፡ ያረጁት መስመሮች ያልተሸፈኑ በመሆናቸው አደጋ ሲያስከትሉ ኖረዋል፡፡ አዲስ በመዘርጋት ላይ ያሉት መስመሮች በፕላስቲክ የተሸፈኑ ሆነው እንደየቦታው ሁኔታ በመሬት ውስጥ የሚቀበሩና ከመሬት በላይ በኮንክሪት ምሰሶዎች የሚዘረጉ ናቸው፡፡

      በአዲስ አበባ እንደ አዲስ የሚዘረጋው መስመር ርዝመት ከ400 ኪሎ ሜትር በላይ ሆኖ ሥራው ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከመንገዶች ባለሥልጣንና ከውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ጋር በመነጋገርና በመናበብ በቅንጅት በመከናወን ላይ መሆኑን አቶ ጎሳዬ አስረድተዋል፡፡

      ሥራውን የሚያካሂደው ፓወር ቻይና የተሰኘው ኩባንያ ዘፋ ከተባለ ሌላ የቻይና ኩባንያ ጋር በመተባበር ነው፡፡ ለሥራው የሚያስፈልገው 162 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከቻይና ኤግዚም ባንክ ተገኝቷል፡፡ በተመሳሳይ የሰባት ዋና ዋና የክልል ከተሞች የኤሌክትሪክ ኔትወርክ ማሻሻያ ሥራ ከዓለም ባንክ በተገኘ 62 ሚሊዮን ዶላር ብድር በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ኮንትራቱን የወሰደው ስቴት ግሪድ የተባለው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ትራንስሚሽን መስመር የዘረጋው የቻይና ኩባንያ ነው፡፡

      ፕሮጀክቱ በተያዘው ዓመት መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ የገለጹት አቶ ጎሳዬ፣ ሥራው ሲጠናቀቅ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር በከፍተኛ መጠን እንደሚቀረፍ አመልክተዋል፡፡ ‹‹የኤሌክትሪክ አቅርቦት አገልግሎትን ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሳድጋል፡፡ የኃይል መቆራረጡን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት ባይቻል እንኳን ኅብረተሰቡ ሊቀበለው በሚችለው ደረጃ ያወርዳል፤›› ብለዋል፡፡

      ‹‹የኃይል መቆራረጥ የኅብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ችግር መሆኑ ያበቃል፡፡ አምራች ኢንዱስትሪዎችም በኃይል መቆራረጥ አይቸገሩም፤›› ብለዋል፡፡ አዲስ የሚዘረጋው የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ መስመሮች ያለውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ዕድገት ሊሸከም የሚችል እንደሆነም ተገልጿል፡፡

      የኤሌክትሪክ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም ኤሌክትሪክ ኃይል የኔትወርክ ማሻሻያ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታና የማከፋፈያ መስመሮች ዝርጋታ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

      ‹‹የጊቤ ሦስትን 1,870 ሜጋ ዋት ጨምሮ የአገሪቱ የማመንጨት አቅም 4,000 ሜጋ ዋት ደርሷል፡፡ ኤክስፖርት ሊደረግ የሚችል ትርፍ ኃይል አለ፡፡ ነገር ግን አሁን ርብርብ እየተደረገ ያለው የተመረተውን ኃይል ተሸክመው ወደ ኅብረተሰቡ የሚያደርሱ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች መገንባት ላይ ነው፤›› ብለዋል አቶ ጎሳዬ፡፡

መንግሥት የኃይል ልማት ላይ አተኩሮ ሲሠራ የኔትወርክ ግንባታ በመዘንጋቱ ለተፈጠረው የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግር መንስዔ ሊሆን እንደቻለ የመስኩ ባለሙያዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ የአገሪቱ የማመንጨት አቅም 400 ሜጋ ዋት ብቻ እንደነበር ባለሙያዎቹ አስታውሰዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...