Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ጥቃቅን ታዳጊና መካከለኛ አሠሪዎች ማኅበር በፌዴሬሽን ደረጃ ተቋቋመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ጥቃቅን፣ ታዳጊና መካከለኛ አሠሪዎች ማኅበር ራሱን ችሎ በፌዴሬሽን ደረጃ መቋቋሙን አስታወቀ፡፡

የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንቱ አቶ ጌታቸው ኃይሌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የጥቃቅን፣ ታዳጊና መካከለኛ ኢንተርፕራዞችን የሚወክሉት ማኅበራት እየተበራከቱ በመምጣታቸውና በሥራቸው የሚያቅፏቸው ሠራተኞችም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ በመምጣታቸው የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነትን ሰላማዊ ለማድረግ ከወዲሁ ማኅበራትን ወደ ፌዴሬሽን ደረጃ በማሳደግ መሥራት እንደሚገባ ስለታመነበት አዲሱ ፌደሬሽን መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡

በመስከረም ወር 2009 ዓ.ም. ከመላው አገሪቱ በጥቃቅን፣ ታዳጊና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በተደራጁ 2,000 ማኅበራት አማካይነት የተመሠረተው የአሠሪዎች ፌዴሬሽን እንዲቋቋም ያስፈለገበት ሌላኛውም ምክንያት ከአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ችግሮች የሚነሱት ከመሆኑ ባሻገር በአደረጃጀት በርካታ ሰንኮፎች ያሉበት ዘርፍ መሆኑን አቶ ጌታቸው አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ለመንግሥት የሚቀርቡ ጥያቄዎች በተናጠልና በማኅበራት አማካይነት በመሆኑ ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች የጊዜና የገንዘብ ብክነት ያጋጥማቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ለሚቀርቡ ጥያቄዎችም ምላሻቸው ይዘገይ ነበር ብለዋል፡፡ ይህንን ዘርፍ የሚወክል የተደራጀ ፌዴሬሽን ባለመኖሩም ድምፁን የሚያሰማበት መድረክ አልነበረውም፡፡ እነዚህና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ወደ ፌዴሬሽን ማደጉ የግድ መሆኑ ስለታመነበት ፌዴሬሽኑ መመሥረቱን አቶ ጌታቸው አብራርተዋል፡፡

ፌደሬሽኑ ከተቋቋመ በኋላ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የሰመረ ከማድረግ ባሻገር፣ ‹‹አሁን የሚታየውን የማምረቻ ቦታ ችግር እንዲሁም የፋይናንስ እጥረት በአንድ ተደራጅቶ ለመፍታትና ድምጻችንን ለማሰማት ከወዲሁ እንቅስቃሴ የጀመርንበት ሲሆን አዲስ ከሚሠሩት የኢንዱስትሪ መንደሮች ቦታ የምናገኝበትን መንገድ እየፈለግን እንገኛለን፤›› በማለት አቶ ጌታቸው ፌዴሬሽኑ የተቋቋመበትን ዓላማ ጠቅሰዋል፡፡

አሠሪዎች ብዙውን ጊዜ የሠራተኛው መደራጀት ራስ ምታት ሲሆንባቸው እንደሚታይ በዚህ በኩል አዲሱ ፌዴሬሽን ግን ለየት ያለ አካሄድ እንደሚከተል የሚገልጹት አቶ ጌታቸው፣ የሠራተኞች መደራጀት አሠሪውንም ስለሚጠቅመው በፀጋ ይቀበለዋል ብለዋል፡፡ ይህ ግን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ጌታቸው፣ አሠሪና ሠራተኛው መብትና ግዴታቸውን ለይተው በማወቅ መግባባትን እንዲፈጥሩ ለማገዝ ፌዴሬሽኑ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

ራሱን ችሎ በፌደሬሽን ደረጃ መቋቋም ስላስፈለገበት ምክንያት ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ጌታቸው ሲያብራሩ ‹‹ይህ ዘርፍ ለየት ያለ ነው፡፡ በሥሩ በርካታ ማኅበራትና የተለያየ የሥራ ባህሪይ ያላቸው አካላት የሚገኙበት ነው፡፡ እንደ ሌሎቹ ወጥ የሥራ ባህሪይ ያለው አይደለም፡፡ ውስጡ ካለው ሰው በስተቀር ማንም ሊመራው አይችልም፤›› በማለት ያብራሩ ሰሆን በዚህ ምክንያትም በአዲስ አበባ ከተማ በ2002 ዓ.ም. የጠቋቋመውን የኢትዮጵያ አነስተኛና ጥቃቅን አሠሪዎች ማኅበርን በማሳደግ፣ እነዚህ ማኅበር ያሉ በክልሎች የተቋቋሙ በርካታ ማኅበራት ጋር ጥምረት በመፍጠር የአዲስ አበባው ማኅበር ከኢትዮጵያ አሠሪዎች ማኅበር ጋር በመሆን አዲሱን ፌዴሬሽን ለማቋቋም ተችሏል ብለዋል፡፡

‹‹መንግሥት ጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራትን የሚያደራጃቸው የፖለቲካ መሣሪያ ለማድረግ ነው ይህንንም አጠናከሮ ለማስቀጠል ነው ወደ ፌዴሬሽን ያሳደጋቸው የሚሉ ወገኖች ትችት ያቀርባሉ፤›› ተብለው ለተጠየቁትም አቶ ጌታቸው ሲናገሩ ‹‹በእርግጥ መንግሥት ነው ያደራጀን፡፡ ለበርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች ገንዘብና የመሥሪያ ቦታ በመስጠት ከድህነት ለማውጣት ከተቀረጹት ፖሊሲዎች አንዱም ይህ ነው፡፡ ይህንን መተግበር ይጠበቅብናል፡፡ ከወጡት ፖሊሲዎች እኛን የሚመለከተው ሥራና ሥራ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ሁለታችንን የሚያገናኘን በማኅበር ተደራጅታችሁ ለመሥራት የወሰዳችሁትን ሥራ ሠርታችኋል አልሠራችሁም የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በቀር የሚያገናኘን ነገር የለም፡፡›› ብለዋል፡፡

ይልቁንም ፌዴሬሽኑ አብዛኛው ግንኙነቱ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር እንደሆነ፣ ኢንተርፕራይዞችም በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸው ጠቅሰዋል፡፡ ማኅበራቱ የመንግሥት ከሆኑ ለምን ፌዴሬሽን ማቋቋም ያስፈልጋቸዋል? በማለትም ጥያቄውን በጥያቄ ይመልሳሉ፡፡ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው አመለካከትም ሊስተካከል እንደሚገባው  አሳስበዋል፡፡

የተቋቋመው ፌዴሬሽን ከዚህ በኋላ የጥቃቅን ታዳጊና የመካከለኛ አሠሪዎች ድምፅ በመሆን ከአቻ ማኅበራት እኩል በመንግሥት የመደመጥ ዕድል እንዲያገኝ የሚሠራ ይሆናል ተብሏል፡፡ በዓለም ካሉ አሠሪ ፌዴሬሽኖች ጋር አብሮ የመሥራት ዕድሉም ሰፊ ነው፡፡ ወደ ፌዴሬሽኑ የተቀላቀሉ አባል ማኅበራትም ፌዴሬሽኑ ራሱን ችሎ እንዲቆም ክፍያና መዋጯቸውን በወቅቱ እንዲከፍሉ፣ በሚጠሩበት ቦታ ሁሉ እንዲገኙና ሌሎችም ያልተቀላቀሉ ማኅበራት ወደ ፌደሬሽኑ በመምጣት ዕድሉን እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች