Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሕንፃ ደኅንነትን ለማስጠበቅ የተናጠል ሥራ አያዛልቅም!

የሕንፃ ግንባታ አዋጅ ሥራ ላይ ከዋለ ከአምስት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በአገሪቱ በየአቅጣጫው የግንባታ ሥራዎች መስፋፋታቸውን ተከትሎ የሚከሰቱትን ችግሮች ለመቅረፍና በሥራ ሒደት የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመቀነስ እንዲያስችል ታስቦ የወጣ አዋጅ ነው፡፡ በግንባታ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ይፈታል፣ የግንባታ ሥራዎች ከንድፋቸው እስከማጠናቀቂያቸው ድረስ ሊከተሉ የሚገባቸውን ትክክለኛ ሒደት በዝርዝር የደነገገ ሕግ ነው፡፡ ይህንኑ አዋጅ ተፈጻሚ የሚያደርጉ መመርያዎችም ወጥተዋል፡፡

በሕግ ከተቀመጠው ውጪ የሚገኘባ ሕንፃ ከተገኘ በአስገንቢውና ግንባታውን በሚያከናውነው ኮንትራክተር ላይ ቅጣት የሚጥሉ ድንጋጌዎችንም አካቷል፡፡ አዋጁን ለማስፈጸም በተለያየ ደረጃ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት በአዋጁ ተጠቅሰዋል፡፡ ክልክል የተባሉ የግንባታ ሒደቶችንም ቁልጭ አድርጎ አስፍሯል፡፡

ለምሳሌ ለሕንፃ ግንባታዎች የሚውሉ መሣሪያዎች በተለይ መወጣጫዎች እንደ የግንባታው ደረጃ በእንጨት አለያም በብረት እንዴት መሠራት እንዳለባቸውና እንደሌለባቸውም ያትታል፡፡ ከሦስትና አራት በላይ ወለል ያላቸው ግንባታዎች ሲካሄዱ ተገቢነት ያላቸው መወጣጫዎች እንዲዘጋጁ ያዛል፡፡ ግንባታዎች በጥራት እንዲገነቡ ለማድረግ በአዋጁ ሥልጣን በተሰጣቸው መሥሪያ ቤቶችና ባለሙያዎች ማረጋገጫ እስካልተሰጠ ድረስ የግንባታ ግብዓቱ ሥራ ላይ መዋል እንደሌለበት በመግለጽ ይከለክላል፡፡ ግንባታዎች ፈቃድ በሌላቸው አካላት እንዳይገነቡም ያግዳል፡፡ አስገንቢዎች ፈቃድ የተሰጣቸውን ኮንትራክተሮች ብቻ የማሠራት ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡

ለምሳሌ ለሕንፃ ግንባታ የሚውለው ብረት በትክክል በንድፉ በተቀመጠው መሠረት መሆኑን ለማረጋገጥ ‹‹የጭቃ ሹም›› የሚል ማዕረግ በተሰጠው ባለሙያ ማረጋገጫ እስካልተሰጠው ድረስ አስገንቢው ያቀረበው ብረት ሥራ ላይ መዋል አይችልም፡፡ ሌሎች የግንባታ ግብዓቶችም በተመሳሳይ መንገድ ማረጋገጫ ካልተሰጣቸው በቀር ለግንባታ ሥራው እንዳይውሉ ይገድባል፡፡ እንዲህ ያሉ በርካታ የመቆጣሪያና የመከታተያ ድንጋጌዎች ያሉት ይህ ሕግ፣ አንድ ሕንፃ ግንባታው መጠናቀቁን የሚያረጋግጥ ሰርተፍኬት ካላገኘም ለአገልግሎት እንደማይውል ጭምር የሚከለክል ነው፡፡

እንዲህ ያሉት የአዋጁ ድንጋጌዎች ለአገሪቱ የግንባታ ዘርፍ መስተካከል የጎላ ሚና እንደሚጫወቱ ያስገነዝበናል፡፡ ይሁን እንጂ አዋጁና መመርያዎቹ ከአምስት ዓመት በኋላ ምን አስገኙ? ምን ያህል ዓላማውን አሳኩ? ብለን ብንመረምር ጠብ የሚል መልስ ልናገኝ አንችልም፡፡

በዚህ የተነሳ ለመልካም ውጤት ተነድፈው የተፈጻሚነት አቅም ካነሳቸው ወይም አስፈጻሚ ያጡ ግን ደግሞ ጥሩ ይዘት ካላቸው አዋጆች መካከል አንዱ ይሄው የሕንፃ ግንባታ አዋጅ ነው፡፡ የሕንፃ ግንባታ ሕግና ማስፈጸሚያ ደንቦች በአግባቡ ያለመተግበራቸው ጉዳይ ሊያነጋግረን ይገባል፡፡ አዋጁ ተፈጻሚ በአግባቡ ተፈጻሚ ቢሆን ኑሮ በተለያዩ የሥራ ቦታዎች የሚከሰተው አደጋ ባልበዛም ነበር፡፡ ሠራተኞች የአደጋ መከላከያ እንዲያደርጉ የሚያስገድደውን አዋጅ ማስተግበር ባለመቻሉና አሠሪዎችም ራሳቸው ሠራተኞችም ተገቢውን ጥንቃቄዎች ባለመደረጋቸው ሳቢያ የስንቶች ሕይወት ለሞትና ለከፋ ጉዳት እየተዳረገ አይተናል፡፡ ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕንፃ አዋጅን በሚመለከት አንድ ጉዳይን የሚያስታውሰኝ ዘገባ ሰማሁ፡፡

ከግንባታ ሥራዎች ጋር በተያያዘ የሚደርሰው ጉዳት በተለይ ከመወጣጫዎች ጋር በተገናኘ በሠራተኞች ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ ከተቻለም ለመከላከል አስተዳደሩ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ዘገባው ይገልጻል፡፡ ለዚህ ሲባልም የሕንፃ አዋጁ ማስፈጸሚያ መመርያ ላይ ካሉት አንቀጾች አንዱን ማሻሻል ይገባል ተብሏል፡፡ ይህም ከአራትና አምስት ፎቅ በላይ ያሉ ሕንፃዎች መወጣጫ (ስካፎልዲንግ) ከብረት የተሠራ ብቻ እንዲሆን ለማድረግ ይገባል የሚል ነው፡፡ ሐሳቡ ባይከፋም ከዘገባው በመነሳት በአዋጁ ውስጥ የተቀመጡትን ሌሎች አንቀጾች ትቶ በአንዱ ላይ ብቻ ትኩረት መሰጠቱ ለምን? የሚል ጥያቄ አጭሮብኛል፡፡

ይሻሻል የተባለው አንቀጽ በእርግጥ አስፈላጊ ቢሆንም፣ የአገራችን የሕንፃ ግንባታ ችግር የሚፈታው መወጣጫዎች ከብረት መሠራታቸው ወይም ያለመሠራታቸው ብቻ አይደለም፡፡ በአገሪቱ የሚገነቡ ሕንፃዎች ደረጃቸውን በጠበቁ ግብዓቶች፣ በቀረበላቸው መሥፈርትና ለመኪያ መሠረት ሕንፃዎች መገንባት አለመገንባታቸውን ለመከታተል አሁን ባለው ሕግ አማካይነት ለምን ማስፈጸም ሳይቻል እንደቀረ ሊገለጽ ይገባል፡፡

ግንባታዎች ፈቃድ ባላቸው ኮንትራክተሮች ብቻ እንዲከናወኑ በግልጽ የተቀመጠው መመርያ እየተተገበረ አለመሆኑ እየታወቀ ቁጥጥርና ዕርምጃ ሲወሰድ አልታየም፡፡

ለግንባታ የተመረጠው ብሎኬት፣ ብረትና የመሳሰለው ግብዓት ማረጋገጫ ሊሰጣቸው እንደሚገባ የተቀመጠው መመርያስ መቼ ነው ተፈጻሚ የሚሆነው? ከግንባታ ፈቃድ ጋር ራሳቸውን ለገንዘብ ይሸጣሉ የተባሉት ‹‹ጭቃ ሹሞች›› በእርግጥ አሉ ወይ ይህንንስ የሚመለከተው አካል ያውቀዋል ወይ የሚለውም ሊፈተሽ ይገባል፡፡

አስገራሚው ነገር ግን ከመወጣጫ ጋር በተያያዘ ክፍተት አለበት የተባለው የአዋጁ ክፍል መታየቱ ትክክል ቢሆንም፣ ይህ ክፍተት የታወቀው ከአምስት ዓመታት በኋላ መሆኑ ግን አዋጁን ለማስተግበር የተሠራ ሥራ የሌለ አስመስሎታል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ይህንን ክፍተት አይቶ ፈጣን ማስተካከያ ማድረግ ሳይቻል በመቅረቱ ስንቱ ሠራተኛ ለአደጋ መጋለጡ አይታወቅ ይሆን? አሁንም ከግንባታ ሥራዎች ጋር በተጎዳኘ የሚታየው ዘርፈ ብዙ ችግር አፍጥጦ እየታየ ከዓመታት በፊት የወጣውን የአዋጅ ማስፈጸሚያ አንድ አንቀጽ ብቻ አሻሽሎ ችግሩ ሁሉ ይፈታል ብሎ መነሳት ተገቢ ስላልሆነ በደንብ ይፈተሽ፡፡ አዋጁን በአግባቡ የማስተግበሩ ጉዳይም ጊዜ የሚሰጠው አይደለም፡፡

ይሻሻላል የተባለው አንቀጽ የቱንም ያህል አንገብጋቢ ቢሆን፣ ትልቁ ችግር ግን አጠቃላይ አዋጁን ለመተግበር ያለው የተነሳሽነትና የተግባር እንቅስቃሴ ችግር እንደሆነ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ይሻሻላል የተባለው አንቀጽም ቢሆን ይሻሻላል ተባለ እንጂ ይህንን አንቀጽ አሻሽሎ የሕንፃ መወጣጫዎች በብረት እንዲሆኑ ለማድረግ ሌላ አምስት ዓመት ስላለመፍጀቱስ ምን ዋስትና አለን?

በጠራራ ፀሐይ በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች ሕንፃዎች ሲደረመሱ አይተናል፡፡ የተገነቡና በግንባታ ላይ የነበሩ የሕንፃ ክፍሎች ወደ ፍርስራሽነት የተቀየሩት በድማሚት አልነበረም፡፡ በጥራት ጉድለት እንጂ፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ወጥ እንቅስቃሴ ማድረግ እንጂ አንዱን ሰበዝ እየመዘዙ መፍትሔ እሰጣለሁ ብሎ መነሳት የማይመስል ሥራ እንዳሆን ይታሰብበት፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት