የኢትዮጵያ ሪኢንሹራንስ (ኢትዮ ሪ) ኩባንያ ሥራ በጀመረ የመጀመሪያው ዓመት ከ59 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ አስመዘገበ፡፡
በሰባት ባንኮች፣ 17 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ 80 ግለሰቦችና አንድ የሠራተኛ ማኅበር ይዞ እ.ኢ.አ. ጁላይ 2016 ሥራ የጀመረው ኢትዮ ሪ በሒሳብ ዓመቱ 519.5 ሚሊዮን ብር አረቦን እንደሰበሰበ አስታውቋል፡፡
ከዚህም ውስጥ 37 በመቶ ከአስገዳጅ ጠለፋ መድን ውል ኢንዲሁም 62 በመቶ ከአስገዳጅ ቀጥታ መድን የሰበሰበ ሲሆን፣ ቀሪውን አንድ በመቶ ደግሞ ለግዙፍ አደጋ ሥጋት ከሚሰጥ ጠለፋ መድን የሰበሰበው ነው፡፡
ኩንያው በሒሳብ ዓመቱ 82.2 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ሲፈጽም፣ የኩባንያው አጠቃላይ የጉዳት ካሳ መጠባበቂያ 71.9 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ሪፖርት የተደረገው አጠቃላይ የሕይወት ዘርፍ የጉዳት ካሳ መጠን 3.7 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡
ኩባንያው ከካሳ ክፍያ ወጪዎች በተጨማሪ 12.8 ሚሊዮን ብር አስተዳደራዊ ወጪ በበጀት ዓመቱ አስመዝግቧል፡፡
ዛሬ ኅዳር 10 ቀን 2010 ዓ.ም. በተደረገው የኩባንያው ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ኩባንያው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመሰከረ የጠለፋ ዋስትና ሰጪ ለመሆን ያስችለው ዘንድ ራዕይ 2027 ሰንቆ ለመጓዝ ማቀዱን ይፋ አድርጓል፡፡