ሰውየውን አላውቀውም፡፡ እሱም አያውቀኝም፡፡ ድንገት ፊቴ ተገትሮ፣ ‹‹ለጥቂት ሳተኝ!›› ሲል ደነገጥኩ፡፡ ምናልባት የአዕምሮ ሁከት ይኖርበት ይሆን? ወይስ ከድንገተኛ አደጋ አምልጦ ነው የመጣው? ጥቁር ሙሉ ልብስ ከነጭ ሸሚዝ ጋር ለብሷል፡፡ አንገቱም ላይ ከረቫት አስሯል፡፡ ንፁህ ጥቁር ጫማም ተጫምቷል፡፡ ፊቱ ከሳ ከማለቱ በስተቀር ሁለመናው ደህና ነው፡፡ ‹‹ለጥቂት ሳተኝ!›› ሲለኝ ምን ይሆን የሳተው በማለት ዓይኖቼን ከእሱ ላይ አንስቼ አካባቢያችንን ቃኘሁት፡፡ ከታክሲ ወያላዎች ሁከትና ከተላላፊዎች በስተቀር ከወትሮ ምንም የተለየ ነገር የለም፡፡ ምናልባት ተሳስቶ ይሆን የሚያናግረኝ በማለት ዝም ብዬ ሳየው፣ ፈገግ ብሎ እያየኝ መልሴን ይጠብቅ ጀመር፡፡
ቅዳሜ ጥቅምት 19 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀኑ ሰባት ሰዓት ፒያሳ ከመኮንን ሆቴል (ባቅላባ ቤት) ከፍ ብሎ ካለው አፍሪካ ካፌ በራፍ ላይ ነው የተገናኘነው፡፡ እሱ የካፌው ታዛ ሥር ሆኖ እኔ ደግሞ ወደ ካፌው ልገባ ስል፡፡ በተፈጥሮዬ ትዕግሥተኛ ስለሆንኩ፣ ‹‹ወንድም ምንድነው የሳተህ?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ ሰውየው ፈገግ እንዳለ፣ ‹‹ውስጥ ገብተን ቡና እየጠጣን ብነግርህስ??›› ሲለኝ ተስማምቼ ተያይዘን እንደ ጓደኛ ዘለቅን፡፡ በሰዎች የሞላው ሰፊው ካፌ ውስጥ ጥግ ላይ ቦታ አግኝተን ወንበር ከያዝን በኋላ አስተናጋጇ በፍጥነት መጥታ ትዕዛዛችንን ተቀበለች፡፡ እሱ ጥቁር ቡና፣ እኔ ደግሞ ማኪያቶ ይዘን ወሬ ጀመርን፡፡
በግምት በሃምሳዎቹ አጋማሽ ላይ የሚገኘው ድንገተኛው ወዳጄ ቡናውን በቀስታ ፉት እያለ፣ ‹‹የት ነው የተወለድከው? ያደግከውስ? የት ተማርክ?. . .›› እያለ ጥያቄዎቹን ድንገት ሲደረድርብኝ መናደድ ይሁን ወይም መገረም በፈጠረብኝ ስሜት ውስጥ ሆኜ ፍጥጥ ብዬ አየሁት፡፡ ‹‹ምነው ጥያቄዬ አልተመቸህም?›› ሲለኝ፣ ‹‹የእኔ ማንነት ምን ያደርግልሃል?›› ብዬ መለስኩለት፡፡ ‹‹ወንድም ፕሊስ አትከፋ፡፡ በአጭሩ የአዱ ገነት ልጅ ነህ? ወይስ. . .›› ሲለኝ፣ ‹‹የስድስት ኪሎ ልጅ ነኝ፤›› ብዬ ፍርጥም አልኩኝ፡፡ ‹‹ኦ! ስድስት ኪሎ? አንበሶቹ ሠፈር? ምሁራኑ ጎራ?. . .›› እያለ ሲስቅ ከወፈፌ ጋር መገናኘቴ ታወቀኝ፡፡ ሰውየው የቀረበለትን ቡና እያጣጣመ ውስጤን በሚሰረስር ዓይነት አስተያየት ሲመለከተኝ ከአማኑኤል የወጣ ነው የመሰለኝ፡፡
ሰውየው፣ ‹‹እኔ እንኳን ላናድድህ፣ ወይም ጊዜህን ያላግባብ ልሻማብህ፣ ወይም በማይረባ ጉዳይ ቅዳሜህን ላበላሽብህ ሳይሆን፣ አንድ የሚገርም ነገር ገጥሞኝ ለማን ልናገር ስል ነው በአጋጣሚ የተገናኘነው. . .›› ሲለኝ ጆሮዬን ቀና አደረግኩ፡፡ ‹‹የሳተኝ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?›› ሲለኝ፣ ‹‹ንገረኛ?›› ብዬ አፈጠጥኩበት፡፡ ‹‹ዛሬ በጠዋት ከቤቴ ወጥቼ ቀጨኔ መድኃኔዓለም አካባቢ ለቅሶ ልደርስ ሄድኩ፡፡ የመሥሪያ ቤቴ የጥበቃ ሠራተኛ ባለቤታቸው ሞተው ሐዘን ስለተቀመጡ ነበር ልደርሳቸው የሄድኩት፡፡ እሳቸውን አስተዛዝኜ ከተሰናበትኩ በኋላ ታክሲ መያዣው ጋ ስደርስ ዓይኔ ጉድ አየ. . .›› ብሎ ከትከት እያለ ሳቀ፡፡
ወይ አንዳንድ ቀን? ከምኑ ጋር ነው የተገጣጠምኩት ይሆን? ‹‹ምን እንዳየሁ ታውቃለህ?›› በማለት መልሴን መጠበቅ ሲጀምር፣ ‹‹ራስህ ንገረኝ እንጂ ምን አውቃለሁ?›› ብዬ የሚለውን ለመስማት ተመቻቸሁ፡፡ ‹‹እኛ ፈጣሪን እያስቀየምነው ነው እንጂ እሱ እኮ ተዓምር ያሳየናል. . .›› እያለ ወደ ጣሪያው አንጋጠጠ፡፡ ለአንድ ደቂቃ ያህል ፀሎት መሰል ነገር ካጉተመተመ በኋላ፣ ‹‹በ1969 ዓ.ም. የቀበሌያችን የአብዮት ጥበቃ ሊቀመንበር የነበረ የቀይ ሽብር ነፍሰ ገዳይ አሥር የሠፈራችንን ልጆች ገድሎ፣ ብዙዎችን እስር ቤት አጉሮ በቶርቸር አሰቃይቶ፣ እህቶቻችንን ደፍሮ እያናፋ እንደ ልቡ ሲኖር ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ከገባ በኋላ ሰባት ዓመት ብቻ ታስሮ ወጥቶ እየሳቀብን አንጀታችንን ሲያሳርር የኖረን ነፍሰ ገዳይን አየሁት፡፡ በሕይወት ካለነው በታች ከሞቱት በላይ ሆኖ ሳየው የአምላክ ተዓምር አስገረመኝ፤›› ብሎ ሳቀ፡፡ ሳቁ ግን ንዴት አለበት፡፡
‹‹ምን ሆኖ ነው ያየኸው ታዲያ? ስለው፣ ‹‹አንድ እጁ ክንዱ ላይ ተቆርጧል፡፡ ሁለት እግሮቹ ከጭኖቹ በታች የሉም፡፡ አንድ ዓይኑ ጠፍቷል፡፡ አንዱም በጭላንጭል ካልሆነ አያይም፡፡ ለአካባቢው ሰዎች እንግዳ ቢሆንም ዊልቸሩን እየገፋች ለልመና የምታንቀሳቅሰው ምስኪን ልጅ በመኪና አደጋ እንዲህ መሆኑን ነገረችኝ፡፡ እነዚያን የጨፈጨፋቸውን ወንድሞቼንና እህቶቼን እያሰብኩ እንዲህ ሆኖ ሳየው በጣም ገረመኝ፡፡ እሱ ለሠራው ግፍ በሕግ ትክክለኛውን ፍርድ ባያገኝም፣ ፈጣሪ ግን መምጪያው አይታወቅምና እንዲህ አድርጎት አረፈው፡፡ ለእሱ ይኼ ሳይሆን የሚገባው ስቅላት ነበር፡፡ ነገር ግን በፈጣሪ ሥራ ጣልቃ ባልገባም አይሆኑ ሆኖ አየሁት. . .›› ሲለኝ፣ ‹‹ታዲያ የሳተህ ምኑ ነው?›› አልኩት፡፡ ‹‹ያ እያነጣጠረ እየተኮሰ ወንድሞቼን የገደለው ዓይኑ ሊያውቀኝ አልቻለም፣ የቀረውን አውሬ ዓይኑን በመከራ ቢበለጥጠውም አላወቀኝም. . .›› እያለ ሲስቅ ተናድጄ፣ ‹‹ይኼን ያህል ያስፈነጥዛል? ወይስ ሌላ ጉዳይ አለ?›› ስለው እሱ ደግሞ፣ ‹‹አልገባህም ለካ? ፈንጥዤ መሰለህ እንዴ? ለ40 ዓመታት የማልረሳው ያ ክፉ ዓይኑ ሊለየኝ አለመቻሉ አናዶኝ ወፈፍ እንዳደረገኝ እኮ ነው የተገናኘነው. . .›› ብሎኝ ሳይሰናበተኝ በንዴት ውስጥ ሆኖ ጥሎኝ ሄደ፡፡ በዚህ ንዴቱ እንኳንም በጥፊ አላላሰኝ እንጂ ምን ይደረግ ነበር?
(መስፍን ጌታሁን፣ ከስድስት ኪሎ)