በአገራችን እየተመዘገበ ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት ዘለቄታ ለማረጋገጥ በትምህርትና ሥልጠና፣ በምርምር ተቋማትና በኢንዱስትሪ መካከል የሚፈጠረው ትስስር ወሳኝ ሚና እንዳለው ይታመናል፡፡ ይህ ደግሞ የልማት ፕሮግራሞችንና የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን ከማረጋገጥ አንፃር ያደጉ አገሮችን ቴክኖሎጂዎች በማፈላለግ፣ በመምረጥ፣ በመጠቀም፣ በማላመድና በተመሳሳይ ሒደቶች የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት ለኢንዱስትሪዎች የማማከር ድጋፍ እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
እንዲሁም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና መምህራን፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ተቋማት ሠልጣኞችንና አሠልጣኞችን በኢንዱስትሪዎች ውስጥ የተግባር ሥልጠና እንዲያገኙ ከማድረጉም በላይ በተቋማቱ መካከልም የሚፈጠረው ትስስር የመተባበር ባህል ለመፍጠር በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥነት ያለው አደረጃጀት፣ የአመራርና የክትትል ሥርዓት ሊዘረጋለት እንደሚገባም ታምኖበታል፡፡
ይሁንና ቀደም ባሉ ዓመታት ኢንዱስትሪዎች ምሩቃንን ከዩኒቨርሲቲዎች ከመቀበልና ከመቅጠር ባለፈ በትብብርና በትስስር ለመሥራት የጎላ ተሳትፎ አልነበራቸውም፡፡ ለዚህም እንደ መግለጫ የተቀመጡት ነጥቦች በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ተማሪዎችን ተቀብለው ለማስተናገድ ያላቸው ፍላጎት አናሳ መሆን፣ አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች የነባር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ብቻ መቀበል፣ ተማሪዎችን ከተቀበሉም በኋላ ምንም ዓይነት ማሽን እንዳይነኩ መከልከልና ቴክኒካል ሰነዶችን እንዳያዩ አለመፍቀድ ጥቂቶቹ ችግሮች ነበሩ፡፡
ዩኒቨርሲቲዎችም ከኢንዱስትሪዎች ራሳቸውን አግልለው በንድፈ ሐሳብ ትምህርት ላይ ብቻ በመጠመድ የቆዩበት ጊዜ እንደነበርም ይታወቃል፡፡ በዚህም ከከፍተኛ ትምህር ተቋማት የሚወጡ ተማሪዎች ወደ ኢንዱስትሪው ሲቀላቀሉ እንግድነት ይሰማቸው እንደነበር ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም ምሩቃኑ በሥራ ቦታቸው ለልምምድ ጊዜ በመውሰዳቸው ኢንዱስትሪውም ሆነ አገር ከኢንዱስትሪው ማግኘት የነበረባትን ጥቅም በጊዜው ማግኘት ያልቻለችበት ወቅት እንደነበር የምጣኔ ሀብት ልሂቃን ይስማሙበታል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በኢንተርንሺፕ አማካይነት የዩኒቨርሲቲዎችና የኢንዱስትሪዎች ግንኙነት አዲስ ቅርጽ እየያዘ የመጣ ቢሆንም፣ አሁንም ችግሮችን ከመሠረቱ ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመቀራረብና አብሮ በመሥራት የኢንዱስትሪዎችና የዩኒቨርስቲዎችን ትስስር እውን ማድረግ እንደሚገባ ብዙዎችን ባለጉዳዮች እያስማማ መጥቷል፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም ተደጋጋፊና ተመጋጋቢ በመሆናቸው ለያይቶ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡
በመሆኑም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢፌድሪ አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 691/2003 አንቀፅ 22(6) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በመንግሥትና በግል የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማትና በኢንዱስትሪው ዘርፍ መካከል ለምርምርና ቴክኖሎጂ ልማት እንቅስቃሴ የሚያግዝ ምቹ የእርስ በርስ ትስስርና ቅንጅታዊ አሠራር እንዲፈጠር ለማመቻቸት መመርያ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡
በመመርያውም መሠረት ትስስሩ ሁለት የአደረጃጀት እርከኖች ያሉት ሲሆን፣ እነዚህም በብሔራዊ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ምክር ቤት ሥር የሚደራጅ ብሔራዊ የትስስር ፎረምና የልማት ኮሪደሮችን መሠረት አድርጎ የሚደራጅ ቀጣናዊ የትስስር ፎረም በመባል ይታወቃሉ፡፡
በመሆኑም በብሔራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን ምክር ቤት ሥር የተቋቋመው ብሔራዊ የኢንዱስትሪ ዩኒቨርስቲ ትስስር ፎረም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሰብሳቢነትና በትምህርት ሚኒስቴር ጸሐፊነት የሚመራ ነው፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥት ለኢንዱስትሪ-ዩኒቨርስቲ ትስስር የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያመላክት ነው፡፡
ቀጣናዊ የዩኒቨርስቲ ኢንዱስትሪ ፎረምን መነሻ በማድረግም ለየዘርፎቹ ተስማሚ የሆኑ ትስስሮች እንዲካሄዱ የተፈቀደ ሲሆን፣ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በበላይነት የሚያስተባብረው የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ልማት የኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ ትስስር ፎረምም ግንቦት 26ቀን 2006 ዓ.ም. የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተመሥርቷል፡፡
የፎረሙ አባላትም በኢንጂነሪግ ዘርፍ ትምህርት የሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የዘርፉ ኢንዱስትሪዎችና የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ተቋማት ሲሆኑ ዋነኛ ትኩረቱም በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ መስክ የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታና ሽግግር ሆኖ የጋራ ምርምር፣ ማማከር፣ ኢንተርንሺፕ፣ የግብይት ክህሎትን መፍጠርና የመሳሰሉትን እንደሚያካትት ተጠቁሟል፡፡
መንግሥት ለመሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ልዩ ስትራቴጂያዊ ትኩረት መስጠቱን ተከትሎ የዘርፉን ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ያስችላል፡፡
በተመሳሳይም የዘርፉን ሁለንተናዊ ልማት ለመደገፍ በሠለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት፣ በምርጥ ተሞክሮ ትግበራ፣ በምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በቴክኒክና ምክር አገልግሎትና በፋሲሊቴሽን ሥራዎች አፈጻጸም መልካም ጅምሮች ቢኖሩም ከሚፈለገው ፈጣንና ቀጣይ ዕድገት አንፃር በሁሉም መስኮች ብዙ ለመሥራት መንገድ ይከፍታል፡፡
መንግሥትም በዘርፉ የሚታየውን የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለማስወገድና የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ለማፋጠን እንዲቻልም የብረታ ብረት ዘርፍ የልማት ቀጣና ተብለው በተለዩ አምስት የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ወይም ኢንስቲትዩት እንዲከፈትና የዘርፉ የሰው ኃይል ልማት፣ የምርምርና ሥርጸት ሥራዎችና የኢንዱስትሪ ዩኒቨርስቲ ትስስር ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በማድረግ አገሪቷ ከዘርፉ የምትጠብቀውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ማረጋገጥ እየሠራ ይገኛል፡፡
በዚህ መሠረት የሰው ኃይል ልማት፣ ምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የዩኒቨርስቲ ኢንዱስትሪ ትስስርና በሌሎች የዘርፉ የልማት ፖሊሲ የተለዩ ወሳኝ ጉዳዮች በተቀናጀ መልኩ ወደ መሬት በማውረድ የተሳለጠ ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ ያስችል ዘንድ በተለዩት የኢንዱስትሪ ልማት ኮሪደሮች ላይ ያተኮሩ ንዑስ የቀጣና ዩንቨርስቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ፎረሞች ማቋቋም ወሳኝ በመሆኑ ዘርፉን እንዲያስተባብር ሥልጣን በተሰጠው የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በዘርፉ በተለዩ ስድስት ንዑስ የልማት ቀጣናዎች አደረጃጀቱን ተግባራዊ በማድረግ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡
በእነዚህ ሁለት ዓመታት የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ስድስት ቀጣናዎችን በመለየት፣ በአካባቢው የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማትን ከኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰርና ስምምነት እንዲፈጥሩ የጋራ የመግባቢያ ሰነድ በማፈራረም፣ በምህንድስና ዕጩ ምሩቃንንና የቴክኒክና ትምህርት ሥልጠና ተቋም ተማሪዎችን በኢንዱስትሪዎች ኢንተርንሽፕ እንዲወጡ በማግባባት፣ በክልሎች የሚገኙ ኢንዱስትሪ ቢሮዎች ትስስሩን እንዲመሩት በማድረግና የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርጉ በማድረግ መልካም የሚባሉ እንቅስቃሴዎች ታይተዋል፡፡
ለአብነት በትግራይ ክልል የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ልማት ዘርፍ ዩኒቨርስቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ፎረም የሚገኙ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲና ፖሊ ቴክኒክ የትምህርት ተቋማት 117 ለሚሆኑ ከተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ለመጡ ባለሙያዎች በማስተርስ፣ በዲግሪና ዲፕሎማ እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በመቀሌ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተምረው በተለያዩ ተማት በተለያዩ የትምህርት ዘርፍ አፓረንትሺፕ የወጡ ተማሪዎች ቁጥር 262 ሲሆን ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ በመስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ በመካኒካልና ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ አፓረንትሺፕ የወጡ ተማሪዎች ብዛት 59 እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በኢንዱስትሪያል፣ በኤሌክትሪካልና ኮሚፒውተር ኢንጂነሪንግ የተመረቁ 324 ተማሪዎች ደግሞ ትስስሩ በፈጠረው የጋራ መግባባት በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ተመድበው እንዲሠሩ መደረጉም የትብብሩን ውጤታማነት ማሳያ ነው፡፡ በመሆኑም ትስስሩ የአንዱ ለአንዱ ተጠቃሚነትን በማሳደግ ድምር ውጤቱ አገራዊ ልማት የሚያሳድግ በመሆኑ ከዚህ በበለጠ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ይታመናል፡፡
ጉዞው ግን አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ በትምህርት ተቋማትም ሆነ በኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ድጋፍ የሚያደርጉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚፈለገውን ውጤት እንዳይመጣ አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡ እንደ ችግር ከተጠቀሱት መካከልም ኢንዱስትሪውን ይደግፋሉ ተብለው የተሙ የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎች ገና ሥራው ላይ በጥልቀት አለመግባታቸው፣ መግባቢያ የስምምነት ሰነድ ላይ የኢንዱስትሪ ቢሮ ሚና አለመካተቱ፣ በትስስሩ በባለድርሻ አካላት የተሠሩ ሥራዎች በወቅቱ ሪፖርት አለመደረጉና በተሠሩ ሥራዎች ላይ ክትትል ማነስ፣ የትምህርት ተቋማት ለኢንዱስትሪው ችግር ፈጣን ምላሽ አለመስጠት፣ በትምህርት ተቋማት የኢንዱስትሪውን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ጥናቶች አለመከናወናቸው የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ሆነው ተጠቅሰዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች በመቅረፍና በትስስሩ አገሪቱ ማግኘት የምትፈልገውን ውጤት ለማስመዝገብ እንዲቻል ታዲያ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የዩኒቨርስቲና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ምሁራንንና የኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጆችን ጥቅምት 2009 በግቢው በመጋበዝ የ2008 በጀት ዓመት አፈጻጸምና በ2009 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ትውውቅ ተደርጓል፡፡
በዕቅድ ትውውቁ ወቅት በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ልማት ዘርፍ የትምህርት፣ ሥልጠናና የምርምር ሥራ የሚሠሩ ዩኒቨርስቲዎች፣ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና፣ የምርምር ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች መካከል የሚፈጠር ትስስር ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲተገበር አጠቃላይ አንቅስቃሴውን መምራት፣ ማስተባበር፣ መከታተልና መደገፍ የዕቅዱ ዓላማ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የዘርፉን የትስስር ሒደት እንዲያቀናጅ ኃላፊነት የተሰጠው የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና በስድስቱ ንዑስ ቀጣናዎች የተደራጁ የትስስሩ ተዋንያን ሥራውን የመደበኛ ዕቅዳቸው አካል በማድረግ በተመሳሳይ የማስፈጸም አቅምና ደረጃ ላይ እንደሚደርሱ ዕቅዱ ታሳቢ አድርጓል፡፡ ከፍተኛ ውሳኔ የሚፈልጉ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ሲኖሩ ደግሞ በብሔራዊ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ምክር ቤት በኩል ለመንግሥት የውሳኔ ሐሳብ እንዲቀርብ እንደሚደረግ በዕቅድ ትውውቁ ወቅት ተገልጧል፡፡
ትስስሩ የሚከናወነው በስትራቴጂካዊ ጥናት በተለዩ የኢንዱስትሪ ልማት ኮሪደሮች ላይ በማተኮር ሲሆን ለዚህም የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ልማት ዘርፍ የኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ትስስር ፎረሞች ስድስት ንዑሳን ቀጣናዎች አደራጅቷል፡፡
ስድስቱ ንዑሳን ቀጣናዎችም የአዲስ አበባ ቁጥር 1 እና ቁጥር 2 የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ልማት ዘርፍ ዩኒቨርስቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ፎረም፣ በኦሮሚያ ክልል ቁጥር 1 የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ልማት ዘርፍ ዩኒቨርስቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ፎረም፣ በትግራይ ክልል የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ልማት ዘርፍ ዩኒቨርስቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ፎረም፣ በአማራ ክልል የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ልማት ዘርፍ ዩኒቨርስቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ፎረምና በድሬዳዋ አስተዳደር የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ልማት ዘርፍ ዩኒቨርስቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ፎረም መሆናቸው ታውቋል፡፡
እነዚህ ንዑሳን ቀጣናዎች በአካባቢያቸው ያሉትን ዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ተቋማት ያቀፉ ሲሆን ተቋማቱም ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ጋር የተሳሰሩ ናቸው፡፡
በትስስሩ ሒደት የትስስሩ ተዋንያን ትስስሩን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ወጥ የሆነ ተቋማዊ መዋቅር፣ የሰው ኃይል፣ ፋሲሊቲና በጀት እንደሚመድቡ ታሳቢ የተደረገ ሲሆን በትስስሩ ማዕቀፍ የሚሠሩ የጋራ ምርምር ሥራዎች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ካውንስል አማካይነት የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ በውድድር አሸንፈው የፋይናንስ ድጋፍ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
በመሆኑም ኢንዱስትሪ፣ ዩኒቨርሲቲና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ትስስሩ ከፍተኛ የመንግሥት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን ለኢንዱስትሪዎች የማማከርና የምርምር እንዲሁም ባለሙያዎችን የማስተማር ተግባርን ሲፈጽሙ፣ የዩኒቨርሲቲም ሆነ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ተቋማት ተማሪዎች ደግሞ በኢንተርንሺፕ ከኢንዱስትሪዎች የሙያና የክህሎት ሥልጠና እንዲሁም በሥራ ምደባን ሲያገኙ፣ የኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ ትስስሩ የተጠናከረና ተመጋጋቢ ከመሆኑም በላይ አገሪቱ የምትፈልገውን በዕውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት የዳበረ የሰው ኃይል ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ አገሪቱም አሁን ያለውን የልማት እንቅስቃሴ የሚያፋጥንላት አስተማማኝ ኃይል ታገኛለች፡፡
(ዳዊት ወልደ ኢየሱስ፣ ከአዲስ አበባ)